ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ደረቅ ቼክ የሰጡ ተከሳሾችን የዳኝነት ኃላፊነታቸውን በመጠቀም በሙያዊ ግዴታቸው ላይ ከባድ የዲሲፕሊን ጥሰት በመፈጸማቸው ከዳኝነት እንዲሰናበቱ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ የተመለከተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ የጉባኤውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ በማድረግ ዳኛው ፈጸሙት የተባለው የዲሲፕሊን ጥፋት የዳኛውን የመደመጥ ባከበረ መልኩ በድጋሚ እንዲታይ ወሰነ።
የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጥፋት ፈጽመዋል በማለት ከዳኝነት እንዲሰናበቱ የሚያሳልፈውን ውሳኔ፣ ሹመቱን የሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አግባብነቱን ተመልክቶ ውሳኔውን የማፅናት ወይም ያለመቀበል ሕጋዊ ሥልጣን አለው። በዚህ አግባብም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቶ አየለ ዱቦ የተባሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የዲስፕሊን ጥፋት በመፈጸማቸው ከዳኝነት እንዲሰናበቱ በመወሰን ለፓርላማው ያቀረበው ጥያቄ፣ በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. በፓርላማው የመጀመርያ ውይይት ተደርጎበት በዝርዝር እንዲታይ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር።
ቋሚ ኮሚቴው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ፣ የጉባዔውን አባላትና በወቅቱ ኃላፊነት ላይ ያልነበሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የከፍተኛና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና እንዲሰናበቱ የተጠየቀባቸውን ዳኛ በመጥራት ላለፋት ወራት ጉዳዩን ከመረመረ በኃላ የደረሰበትን ውሳኔ፣ ማክሰኞ ሚያዚያ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፓርላማው አቅርቧል።
እነ አማኑኤል አዲሱና ሌሎች ሦስት ሰዎች በተከሰሱበት የተለያዩ ደረቅ ቼኮችን የመስጠት ወንጀል ጉዳያቸው በአራዳ ምድብ ችሎት በመታየት ላይ ሳለ፣ አንደኛ ተከሳሽ በጠበቃቸው አማካይነት የተከሰሱበት መዝገብ ቀድሞ በአቃቂ ምድብ ችሎት ከተመሠረተባቸው ተመሳሳይ ክስ ጋር ተጣምሮ እንዲታይላቸው አመልክተው ውድቅ እንደተደረገ፣ ይኸው አቤቱታ በይግባኝ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጥቶበት ሳለ ዳኛ አየለ ዱቦ አቻና የበላይ ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በአራዳ ምድብ ችሎት በመታየት ላይ የነበረውን መዝገብ እሳቸው ወደሚያስችሉበት አቃቂ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በማስመጣትና መዝገቡን ከሌላ ተመሳሳይ የክስ መዝገብ ጋር በማጣመር እንዲታይ አድርገዋል የሚለው፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የለየው የመጀመርያ ጥፋት ነው።
በሌላ በኩል ዳኛው መዝገቡን አጣምረው መመርመር ሲጀምሩ በተከሳሾቹ ላይ የተመሠረተውን ዋስትና የሚያስከለክል ከባድ የወንጀል ድርጊት ወደ ቸልተኝነት በመቀየር፣ በኋላም ተከሳሾቹ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ እንዲከራከሩ ሲጠይቁ ዋስትና በመፍቀዳቸውን ይኼንን ተከትሎ ተከሳሾቹ መጥፋታቸውን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በዳኛው ላይ የተመለከተው ተጨማሪ የዲስፕሊን ጥፋት መሆኑን ለፓርላማ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል። በተጨማሪም ዳኛው መዝገቡን አጣምረው ሲመለከቱ ክሱን መሥርቶ ጉዳዩን የሚከታተለውን ዓቃቤ ሕግ ዳኛው አለመጥራታቸው በሌላ ጥፋት በመለየት ከዳኝነት እንዲሰናብቱ በአብላጫ ድምፅ ወስኖ ፓርላማው ውሳኔውን እንዲያፀድቅ ጠይቆ ነበር።
የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተወሰነባቸውን ዳኛ ጠርቶ እንዳነጋገረና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጉዳዩን ሲመረምር ዳኛውን በአካል መልስ እንዲሰጡ አለማድረጉን፣ ይህም የመሰማት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የጣሰ ስለመሆኑ መረዳቱን፣ እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንስፔክሽን ጽሕፈት ቤት በዳኛው ላይ ያቀረበው የምርመራ ውጤት ከዲሲፕሊን ክስ ውጪ እንደነበር፣ ነገር ግን ጉባዔው የምርመራ ውጤቱ ፍሬ ነገር ባልሆነ ጉዳይ ላይ መሠረት አድርጎ መወሰኑን ዳኛው እንደማይቀበሉት መገንዘቡን የቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ይገልጻል።
በሌላ በኩል ዳኛው በተጠቀሱት አንደኛ ተከሳሽ ላይ የእስርና የ10 ሺሕ ብር ቅጣት መወሰናቸውን፣ ይህ ሆኖ ሳለ በእስር ላይ ካለ ግለሰብ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት መባሉን እንደማይቀበሉትና ተከሳሾቹ እንዲጠፉ አድርገዋል መባሉም ያልተረጋገጠ፣ ምናልባትም ከግምት የማያልፍ በመሆኑ የተወሰነባቸውን የጥፋተኝነት ውሳኔ እንደማይቀበሉት ስለመከራከራቸው የቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ያስረዳል።
ቋሚ ኮሚቴው ያነጋገራቸው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት ዳኛው በጽሑፍ መልስ እንዲሰጡ በወቅቱ መደረጉንና የሰጡት መልስ ግልጽና ለውሳኔ እንደማያስቸግር በመታመኑ፣ በአካል መልስ እንዲሰጡ አለመደረጉን እንደተናገሩና የጉባዔው የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብም ጉዳዮችን የሚመለከታቸው በሌሉበት ማየትን በአስገዳጅነት እንደማያስቀምጥ ማስረዳታቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ጉዳዩ እሳቸው ከመሾማቸው በፊት የተፈጸመ በመሆኑና ከአሠራርም አንፃር ምቹ ስለማይሆን ምክር ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንዲሰጥበት ማለታቸውን ሪፖርቱ ይጠቅሳል።
ከላይ የተገለጹትን መሠረታዊ ጭብጦች የገመገመው ቋሚ ኮሚቴ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ዳኛ አየለ ዴቦ ያላቸውን የመደመጥ ህገ መንግስታዊ መብት ሳያከብር ከዳኝነት እንዲሰናበቱ ያቀረበውን ውሳኔ ቋሚ ኮሚቴው ውድቅ በማድረግ የዳኛውን የመደመጥ መብት ባከበረ መንገድ ጉዳዩን የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በድጋሚ እንዲመለከተው ወስኗል። ይህ የቋሚ ኮሚቴው ውሳኔ የሚጸናው በፓርላማው ሲጸድቅ ነው።