Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የወልዲያ – ሃራ ገበያ – መቀሌ የባቡር ፕሮጀክትን ለማስቀጠል ፈታኝ የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የወልዲያ – ሃራ ገበያ – መቀሌ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ግንባታ ለመፈጸም መቸገሩን፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን፣ ማክሰኞ ሚያዚያ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።

በ2007 ዓ.ም. የተጀመረውን ይኼንን ፕሮጀክት ለማስቀጠል የሚያስፈልገው ከፍተኛ በጀት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ከውጭ መንግሥታት በብድር ይገኛል በሚል እሳቤ ቢጀመርም፣ የተባለው ገንዘብ ከውጭ ባለመገኘቱና ከመንግሥት ወጪ እንደሚደረግ የታሰበው ቀሪ ድርሻም በሚፈለገው መጠን ባለመገኘቱ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል አስቸጋሪ እንደነበረ ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የባቡር መስመሩን ግንባታ ሁለት በመቶ ያህል እንኳን ማከናወን እንዳልተቻለ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸምም ከ54 በመቶ ከፍ ማለት እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ መፍትሔ እንዲያገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ተጨማሪ በጀት ሊፈቅድ እንደሚገባ፣ ይኼንንም በተመለከተ ለሚኒስቴሩ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡

የወልዲያ – ሃራ ገበያ – መቀሌ የባቡር መስመር የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ አካል ሲሆን፣ የፕሮጀክቶቹ መሠረታዊ ዓላማ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አካባቢዎችን፣ እንዲሁም በመቀሌና በኮምቦልቻ የተገነቡትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከጅቡቲ ወደብ ጋር ለማገናኘት ነው።

በ2007 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የመቀሌ-ወልዲያ የባቡር መስመር ዝርጋታ 120 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ የሚሸፍን ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ወቅት ታሳቢ የተደረገው አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪ 1.54 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአዋሽ – ወልዲያ – ሃራ ገበያ መስመር ግንባታ አጠቃላይ ወጪ 1.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት በመገባደድ ላይ ነው።

ይህ ፕሮጀክት ገና ወደ ሥራ ባይገባም ግንባታውን ለማከናወን የተገኘው የውጭ ብድር መመለሻ ጊዜ በመድረሱ፣ መንግሥት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ብድር መክፈል ጀምራል።

በሌላ በኩል ከጥንስሱ አንስቶ የትራንስፖርት አገልግሎቱ አዋጭ እንዳልሆነ የሚታወቀውና ወደ ሥራ ከገባም በኋላ በየዓመቱ 1.5 ቢሊዮን ብር ገደማ ኪሳራ በማስመዝገቡ መንግሥት እንዲደጉመው የሚጠየቅበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 132 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ የነበረ ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን በ45 ሚሊዮን ብር ዝቅ ያለ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሪፖርት ያመለክታል።

በተመሳሳይም ከኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት የመንገደኞችና የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 648 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ መፈጸም የተቻለው ግን 75 በመቶ ያህሉን ብቻ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

መንግሥት ሥራ ለጀመሩት የባቡር ፕሮጀክቶች የተበደረውን አራት ቢሊዮን ዶላር ብድር መመለስ የጀመረ ሲሆን፣ ይኼንን ጫና ለመሸከም ፕሮጀክቶቹም ሆኑ ነባራዊው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያስችል ባለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለአዲስ አበባ ጂቡቲ መስመር የተገኘው ብድር የመመለሻ ጊዜ እንዲራዘም፣ ከአበዳሪው የቻይና መንግሥት ጋር በመደራደር ይሁንታ ማግኘታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች