ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው ከ40 በላይ የሚሆኑ አገሮች መሪዎች በሚታደሙበት የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቻይና ገቡ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎችን ያቀፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የልዑካን ቡድን፣ በቻይና ቆይታው የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘምን ጨምሮ የተለያዩ ስምምነቶችን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ከቻይና የተበደረችው ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ሲኖርባት፣ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና- አፍሪካ ትብብር ፎረም ለመሳተፍ ሄደው፣ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የወጣበትን የአዲስ አበባ – ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት የዕዳ ክፍያ ከአሥር ዓመት ወደ ሰላሳ ዓመት እንዲራዘም መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ በቻይና የሚካሄደው የአሁኑ ጉባዔ ‹‹የጋራ የሆነውን ብሩህ መጪ ጊዜ መሥራት›› የሚል መሪ ቃል ሲኖረው፣ ካሁን ቀደም እ.ኤ.አ. በ2017 በተካሄደው ጉባዔ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተሳትፈው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. በ2013 በቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የተጠነሰሰው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ እስካሁን ድረስ የትብብር ማዕቀፉን ሰነድ በመቀበል፣ 124 አገሮችና 29 ዓለም አቀፍ ተቋማት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከፈራሚ አገሮች ተርታ መሠለፍ በአፍሪካ ከቀዳሚ ፈራሚዎች አንዷ ናት፡፡
እ.ኤ.አ. የ2019 ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን በማስመልከት መግለጫ የሰጡት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን፣ ጉባዔው የወሬ ስብስብ ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ ሥራ ላይ የሚተኮርበት ነው ብለዋል፡፡
‹‹የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ ከኢትዮጵያ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ይጣጣማል፡፡ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣትና አገራዊ ራዕይ ለማሳካት በሚደረገው ጉዞ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማቀላጠፍ ያግዛል፤›› ሲሉ አምባሳደሩ አክለዋል፡፡
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሥልጣን ዘመን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በፅኑ እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና ለኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ብድር መስጠት ማቆሟና ከዚህ በፊት ለሰጠቻቸው ብድሮች ክፍያ እንዲፈጸምላት ጥያቄ ማቅረቧ ሲነገር ቆይቷል፡፡ የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጉብኝት በዚህ ጉዳይ ላይ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ድርድር በማድረግ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚረዳ ይጠበቃል፡፡