Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአያት ሪል ስቴት ለሁለት የተለያዩ ግለሰቦች የሸጠው አንድ መኖሪያ ቤት ውዝግብ አስነሳ

አያት ሪል ስቴት ለሁለት የተለያዩ ግለሰቦች የሸጠው አንድ መኖሪያ ቤት ውዝግብ አስነሳ

ቀን:

በግልግል ዳኝነት የተሰጠን ውሳኔ ፍርድ ቤት አግዶታል

በሪል ስቴት ልማት ቀዳሚ የሆነው አያት ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር፣ ለሁለት የተለያዩ ግለሰቦች የሸጠው አንድ መኖሪያ ቤት ውዝግብ አስነሳ፡፡

አያት ሪል ስቴት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አሥር ውስጥ የገነባውን ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት፣ በ1997 ዓ.ም. አቶ ኪዳኔ ዮሐንስ ለሚባሉ ግለሰብ በጠቅላላ ዋጋ 984,605 ብር መሸጡን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ይኼንኑ ሕንፃ አያት በ2004 ዓ.ም. ኑሯቸውን አሜሪካ ላደረጉ ወ/ሮ ትርሲት ቶሎሳ ለሚባሉ ግለሰብ በ2.6 ሚሊዮን ብር መሸጡን የተፈራረሙባቸውና ክፍያ የተቀባበሉባቸው ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡

ውዝግቡ የተፈጠረው በ2004 ዓ.ም. ቤቱን በ2.6 ሚሊዮን ብር ሙሉ ክፍያ በመክፈል ከአያት አክሲዮን ማኅበር ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. አቶ ሰዒድ መሐመድ ከሚባሉ የአያት ተወካይ በሰነድ ከተረካከቡ በኋላ፣ ለማፅዳት ሲንቀሳቀሱበት መሆኑንም ማወቅ ተችሏል፡፡

አያት ቤቱን አቶ ኪዳኔ ለሚባሉ ግለሰብ በ1997 ዓ.ም. ሲሸጥ ክፍያውን እንዴት ማጠናቀቅ እንዳለባቸው በውል የተስማሙ ቢሆንም፣ ገዥው መጀመርያ ከከፈሉት 353,000 ብር ውጪ ቀሪውን በውላቸው መሠረት ሊከፍሉ ባለመቻላቸው፣ ለሦስት ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፎ ውሉን እንደሰረዘ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ቤቱን አዲስ ገዥ ሆነው ለቀረቡ ወ/ሮ ትርሲት ከፍ ባለ ዋጋ 2.6 ሚሊዮን ብር መሸጡንም በሰነዶች ላይ ገልጿል፡፡ መኖሪያቸው እንግሊዝ እንደሆነ የተገለጸው የመጀመርያው ገዥ አቶ ኪዳኔ፣ በውላቸው መሠረት አያት ቤቱን በ18 ወራት ሊያስረክባቸው እንዳልቻለና የሚፈልገውን ነገር ሁሉ በውላቸው ላይ ባሠፈሩት አድራሻ የሚያሳውቃቸው መስሏቸው ሲጠብቁ ቢቆዩም ምንም ሊደርሳቸው ባለመቻሉ፣ ወደ አገር ቤት መምጣታቸውንና ቤታቸውን እንዲያስረክባቸው ሲጠይቁ ባለመፈጸሙ  ወደ ግልግል ዳኝነት መሄዳቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

በግልግል ዳኝነት ለተመረጡት አቶ ሐጎስ ደበሱ፣ ዘካሪያ ቀንዓ (ፕሮፌሰር)፣ አቶ ኪሩቤል ኃይለ ማርያም፣ አቶ ዘነበ ጥላሁንና ያሬድ ለገሠ (ዶ/ር)፣ አቶ ኪዳኔ ዮሐንስና ወ/ሮ እምሯ አሰፋ አያት አክሲዮን ማኅበርን ከሰው ሲቀርቡ፣ አያት ቤቱን ለሌላ ሰው ስለመሸጡ ምንም ሳይል በቀጥታ ወደ ክርክር መግባቱን ሰነዶቹ ያሳያሉ፡፡ የግልግል ዳኞችም የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች ክርክር ከሰሙ በኋላ፣ አያት አክሲዮን ማኅበር ቤቱን ለአቶ ኪዳኔ እንዲያስረክብና አቶ ኪዳኔም የቀረባቸውን ሒሳብ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ቤቱን በ2.6 ሚሊዮን ብር የገዙት ወ/ሮ ትርሲት የግልግል ዳኝነትን ውሳኔ በመቃወም ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ቢጠይቁም ተቀባይነት በማጣታቸው፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማመልከት የግልግል ዳኝነት ውሳኔን አሳግደዋል፡፡ ወደ ክርክሩም እንዲገቡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አያት አክሲዮን ማኅበር ቤቱን ለወ/ሮ ትርሲት 2.6 ሚሊዮን ብር መሸጡን አረጋግጦ የአቶ ኪዳኔን በውሉ መሠረት የግዥ ውሉን ማቋረጡን ቢገልጽም፣ አቶ ኪዳኔ ቤቱን እንደተረከቡና አፈጻጸም እንዳወጡ በማሳወቅ ቤቱ የእሳቸው እንደሆነ እየተናገሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

ሁለተኛዋ ገዥ ወ/ሮ ትርሲትም ቤቱን መረከባቸውንና ለማፅዳት እየተንቀሳቀሱ ባለበት ወቅት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ባልደረባና ፖሊስ ሊያሠሯቸው እንዳልቻሉ በመግለጽ፣ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰዳቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አያት አክሲዮን ማኅበር አንድን መኖሪያ ቤት ለምን ለሁለት የተለያዩ ግለሰቦች እንደሸጠና በግልግል ዳኝነት ክርክር ሲጀመር ሁለተኛዋ ገዥ ለምን ጣልቃ እንዲገቡ እንዳላደረገ የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎችን ለማነጋገር ተሞክሮ፣ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ውዝግቡ ግን ቀጥሏል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...