Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየተዘነጋው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ማኅበር በአገር አቀፍ ደረጃ ማቋቋም የወቅቱ...

የተዘነጋው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ማኅበር በአገር አቀፍ ደረጃ ማቋቋም የወቅቱ አጀንዳ ቢሆን!

ቀን:

በክንፈኪሩቤል ተስፋ ሚካኤል

መጽሐፍ ቅዱሱ እንዲህ ይላል፣ ‹‹በደሃዎች እርሻ ብዙ ሲሳይ አለ ከፍርድ መጓደል ግን ይጠፋል›› (መጽ ምሳሌ 13›23)፣ ‹‹በጠቅላላው ግን የአገሩ ጥቅም እርሻን የሚወድ ንጉሥ ቢኖር ነው›› (መጽ መክብብ 5፡9) የዓለማችን እጅግ ብዙ አገሮች የየአገሮቻቸውን ሕዝብ የመመገብ ጉዳይ ከአሳሳቢነት ደረጃ ከወረደ ዘመናትን አሳልፏል፡፡ የእነርሱ ችግር የምግብ ማማረጥና የአመጋገብ ጉዳይ ሆኖ እናያለን፡፡ ሆኖም ግን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እስከ አለንበት ዘመን ድረስ የዘለቀ ራስን የመመገብ ጉዳይ ተግዳሮት ሆኖብናል፣ ስለሆነም በቀን ሦስቴ ሕዝባችንን የመመገብ ጉዳይ ታላቅ ፈተና ከመሆኑም ባሻገር ምን ማድረግ እንደሚገባን ግራ ተጋብተናል፡፡ ምክንያቱም የእርሻንና የአርሶ አደሩን ጉዳይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችላ ብለነዋልና፡፡

ኢትዮጵያ ስላሳለፈቻቸው የረሃብ ዘመናት በጥቂቱ እንይ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ትንሽ ከታሪክ ማኅደር ብናጣቅስ፣ በዘመነ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ የአገዛዝ ዘመን ማለት በ1965 ዓ.ም. የተከሰተውን የወሎ ረሃብ ለመሸፋፈን የዘውዳዊ የአገዛዝ መንግሥት በብዙ መንገድ ሞክሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ እንዲሁም የቢቢሲው ጆናታን ዲምቢልቢይ ተቀናጅተው ረሃቡ ለዓለም እንዲዘገብ ሪፖርት በማድረጋቸው የንጉሡን የአስተዳደር ሥርዓትና ገመና አጋልጠዋል፡፡ በዚህ በወሎ ረሃብ ወደ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እረግፏል፡፡ ከወሎ ረሃብ ከሁለት ዓመታት በኋላ የንጉሡ መንግሥት ተወገደ፡፡ የአንዱ ውድቀት ለሌላው መነሻ ይሆናልና ወታደራዊው ደርግ ሥልጣንን በመፈንቅለ መንግሥት ከመያዙ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በፕሮፓጋንዳ ዘመቻው የወሎን ረሃብ ለሕዝብ በቴሌቪዥን በማሳየት የሕዝብን ዕንባ ካራጨ በኋላ በእኔ አገዛዝ ይህ አይፈጸምም በማለት ማለ፡፡ የንጉሣዊው ሥርዓት ለሕዝብ ደንታ እንደሌለውና ግዴለሽ መሆኑን ኮነነ፡፡ ዳሩ ምን ይባላል ‹‹አትፍረድ፣ ይፈረድብሃል›› ተብሏልና በራሱ በደርግ የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያ ዳግም ታሪካዊውን የትግራይንና የወሎን ረሃብ በ1978 ዓ.ም. አስተናገደች፣ በዚህም የዓለም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በየ መስኮቶቻቸው ዘግናኙን ረሃብ በሰፊው ዘግበውታል፡፡ እናም ኢትዮጵያ የሚለው ስም እስከ ዛሬ ሲነሳ ረሃብተኛነትና ለማኝነት አብሮ ይነሳል፡፡ አይ አለመታደል! የኢሕአዴግ ጥምረት ወታደራዊውን አምባገነናዊ አገዛዝ አስወግዶ በሥልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታትም ቢሆን እንዳለፉት ዘመናት አሰቃቂው ረሃብ ተከስቶ ባይታይም ከስምንት ሚሊዮን ለማያንስ ሕዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ስንዴ በመለመን ኢትዮጵያ የታወቀች አገር ሆናለች፡፡ ‹‹የተደበቀ ረሃብ›› ብንለው ያስኬዳል፡፡ እጅግ የሚያስገርመው የኢሕአዴግ ጥምረት የቻይናን የዕድገትና ልማት ተምሳሌት እንከተላለን እያለ ቻይና ወደ 1.6 ቢሊዮን የሚጠጋውን ሕዝቧን ለመመገብ የቻለችበትን ጥበብ ተረድቶ ለመተግበር ያልቻለበት ምክንያቱ ምንድነው? ብንል ከልመና የሚገኝን ስንዴ ለመግዛት የሚለገሰውን ዶላር ለሚቀራመቱ ባለሥልጣኖች የስንዴ ግዥ ‹‹የማትነጥፍ ላም›› እንደሆነች በቅርቡ ዓቃቤ ሕጉ በይፋ ለሕዝብ የገለጹት ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለእርሻና ግብርና ሥራ እንዲሁም ለእንስሳት ዕርባታ ያልተመቸች አገር አድርገው ያመኑ የሕወሓት ኢሕአዴግ ጥምር ድርጅት ባለሥልጣናት በርካታ ቢሆኑ ነው እንጂ ታዲያ እንዴት አገራቸው ለ27 ዓመታት ስንዴ ስትለምን አላሳፈራቸውም! ፍፁም በረሃማዎቹ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ አልጄሪያ፣ ወዘተ. ወንዝ አልባ ሆነው እንኳን ያውም ነዳጅ ዘይት ሳያገኙ ስለረሃብ ታሪካቸው ሰምተንም አናውቅም፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ለእርሻም የተመቸች በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች የተለየች አገር ናት፡፡ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ሲታይ ከባህር ጠለል በታች ካለው ከአፋር ምድር፣ እስከ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ፣ እስከ ራስ ዳሽን የሰማይ ጥግ ተራሮች እስከ ለጥ ያሉት የሶማሌ፣ የአርሲ፣ ባሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ሜዳዎችን፣ የምዕራብ ኢትዮጵያን ወጣ ገባ ጋራዎችና ሜዳዎችን ወዘተ. ያካትታል፡፡ የአፈሯ ለምነት የማያበቅለው ዕፅዋት የለም፡፡ ጂኦሎጂስት እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ ገጸ ምድር ከቮልካኒክ፣ ከሜታሞርፊክና ሴዲሜንታሪ የዓለት ዓይነቶች የተዋቀረንና  በማዕድናት የበለፀገ በመሆኑ የአፈሩ ለምነት የታወቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንሳቲስቶች በጥናታቸው ማስረጃነት የአፈሩን ለምነት አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ‹‹የባዕዳኑ ማዳበሪያ አምራቾችና ሻጮቾች ስግብግብነት፤››  ታክሎበት የማዳበሪያ ምርታቸውን በምድራችን ለማራገፍ ያደረጉት ‹‹ሴራ›› ተሳክቶላቸው ምድራችን ብዙው በኬሚካል ተበክላለች፣ ዛሬ ያለማዳበሪያ ማምረት ተቸግረናል፣ ምርጥ ዘር ከእኛው ተወስዶ ዳግም ዘር እንዳይሰጥ አምክነው እየላኩልን አይደል፡፡ የአገራችንን ተመራማሪዎች ማን ይስማቸው፣ ልክ እንደ ስንዴው የማዳበሪያው ግዥ ሌላው ‹‹የማትነጥፍ ላም›› ስለሆነች ድራማው ቀጥሏል፡፡ የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ተብሎ ስለተገነባው ፋብሪካና ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ወደ ድንጋይነት ስለተለወጠው ማዳበሪያ ጉዳይ በእኛው ኢቲቪ ያየነው አሳዛኝ የዘመነ ሕወሓት ኢሕአዴግ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ለመሆኑ ተጠያቂነት የሌለበት አገር ሆኖ እስከ መቼ ይቀጥላል?

የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ስንመለከት እንደ ምድሪቷ አቀማመጥ ለእርሻም የተመቸች አገር ናት ቆላማ፣ አለያም ወይና ደጋማ ወይም ደጋማ ነው፡፡ የሙቀትና የቅዝቃዜው ሁኔታ እንደ ምድሩ አቀማመጥ መለያየቱ ጠቀሜታው ታላቅ ሲሆን፣ ይህንን ተመርኩዞ እንደ መልክዓ ምድሩ አቀማመጥ መሠረት የአገዳ እህሎች፣ ልዩ ልዩ አዝዕርቶች፣ አትክልቶችና ፍራ ፍሬዎች፣ በርካታ ዛፎችና ዕፅዋቶች ይበቅላሉ፡፡ ድሩሲላ ዱንጂ ሂውስተን በ1926 ዓ.ም. በጻፈችው “Wonderful Ethiopians of the Ancient Cushite Empire” በሚለው መጽሐፏ (ፒራሚድ ገንቢዎቹ ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን) በሚል በአጭር በተተረጎመው መጽሐፍ) ኢትዮጵያ ለዓለም ሕዝብ ያበረከተችው እጅግ ብዙ ነገር እንዳለ ራሳቸው የምዕራቡ ዓለም ታላላቅ የምርምር ሰዎች ያረጋገጡትን ጽፋለች፡፡ ዛሬ ዓለም የሚመገባቸው አዝዕርት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ወዘተ. ምንጫቸው ከኢትዮጵያ ለመሆኑ በብዙ ማስረጃ አቅርባለች፡፡ ዛሬማ ጭራሹን በዓለም በብቸኝነት ጤፍን በማምረት የምትታወቀው አገራችን የአዝዕርቱ የባለቤትነት መብቷ በአንድ የአውሮፓ አገር ግለ ሰብ ተነጥቆ መብት ለማስመለስ ፍርድ ቤት መቆሟ ታላቅ ውርደት አይደለም እንዴ? አገራችን ምን ነካት ብንል በየ መሥሪያ ቤቶቻችን ያሉት ኃላፊዎች በዕውቀታቸው ሳይሆን፣ በፖለቲካ ታማኝነታቸው የተቀመጡ ስለሆነ በሙያው የሕግ ዕውቀት ያለውን ሰው ስለማይጠቀሙ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እንደዋዛ አሳልፈው የሰጡ ብዙ ስምምነቶች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም፣ ጊዜ ይግለጸው ብለን እንጠብቅ፡፡

የኢትዮጵያን የውኃ ሀብት በተመለከተ በገጸ ምድርም ሆነ በከርሰ ምድር ሀብቶቿ ሃይቆቻችንን ሳንጨምር ከፍተኛ የውኃ ሀብት ካላቸው ጥቂት አገሮች ተርታ ትመደባለች በዚህም ለመስኖ እርሻ የተመቸች አገር ናት፡፡ ታላቁ ዓባይ ከ27 የማያንሱ ገባር ወንዞችን ውኃ ተቀብሎ ሱዳንንና ግብፅን ያጠጣል፣ ያረካል፣ ሕይወታቸውም በአንድ ዓባይ ላይ ተመሥርቷል፡፡

እኛ ብዙ ተጨማሪ ታላላቆች ወንዞች አሉን በከንቱ የሚፈሱ ዋቤ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ኦሞ፣ ባሮ፣ ዳቡስ፣ ጊቤ፣ አዋሽ ወዘተ. ብለን መዘርዘር ነው፡፡ ፈጣሪ እንደሥራችን ሳይሆን እንደ ቸርነቱ የሚለግሰንን የበልግና የክረምት ወራቶችን ዝናብ ጨምረን ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ፀጋ በፈጣሪ የተሰጣት አገር ሕዝብ ለምን ይራባል? ለምንስ ውኃችንን በአግባቡ አንጠቀምበትም ብለን ብንጠይቅ መልሱ ያው የፖለቲካው ችግር ያስከተለው መሆኑን ማወቅ ምርምር አያስፈልገውም፡፡ የመስኖም ይሁን የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከመገንባታችን በፊት እስኪ የትኛው ነው በዕውቀት በጥንቃቄና ጥራት ባለው ሁኔታ በቂ የጂኦሎጂ፣ ኃይድሮሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ፣ የአፈር ጥናት፣ የሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ ኃይድሮሊክስ፣ ስትራክቸራልና ጂኦፊዚካል ጥናቶች፣ ወዘተ. የተካሄዱባቸው ብለን ብንጠይቅና የተከሰቱትን ችግሮች ለምንድነው ብለን ብንመረምር ዘገባው የሚያበረታታ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡

በትግራይ የመከኑ ብዙ ግድቦች አሉ፣ የተከዜ ግድብ ሙሉ ኃይል ለማመንጨት አልቻለም፣ በጊቤ ሁለት የዋሻ ሥራ የነበረበት ጂኦሎጂካል ገጠመኝ በቂ የጂኦፊዚካል ጥናት እንዳልነበረ ያመለክታል፡፡ በአማራ ክልል የተገነቡ በርካታ የመስኖ ግድቦች በችግር የተከበቡ ናቸው፡፡ በአዋሽ አካባቢ የመስኖ ግድብ ግንባታ ያጋጠመው ችግር በእኛው ቲቪ ተመልክተናል እንዲህ እያልን ብንዘረዝር፣ የባከነው ጊዜ ጉልበትና የናረው ባጀት አገሪቷን ከፍተኛ ዕዳ እያስከፈላት መሆኑን እየታዘብን ነው ማለት ይቻላል፡፡ የዓባይ ግድባችንን በናፍቆት ከመጠበቅ ሌላ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ወንዞች ብዛትና ግድቦቻችን እንኳን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ሊጨመርብን ቀርቶ በነፃ በተሰጠን ነበር፡፡  እንዲያው በስመ አገር በቀል እየተባለ በቂ ዕውቀት ክህሎት፣ ልምድና ችሎታ ለሌላቸውና በጥንካሬ ላልቆሙ በርካታ በአገር በቀል ለሚባሉ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ግንባታዎቹ መሰጠታቸው ያው የተለመደው ‹‹የማትነጥፍን ላም›› የማለብ ጉዳይ ሆኖ አየነው፡፡ ጊዜ ወስዶ በቂ ክህሎት ዕውቀት ልምድና ችሎታ መገንባት ተገቢ አይደለም አላልኩም፡፡ ይህ ሁሉ የጥቂቶች ስግብግብነት ያመጣው ውድቀት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ በቁጥሩ በአፍሪካ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መድረሱ ይነገራል፡፡ ከዛሬ 50 ዓመታት ገደማ በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 25 ሚሊዮን ይጠጋ እንደነበር መረጃዎች አሉ፡፡ ይህ ቁጥር በወታደራዊው ደርግ ዘመን ወደ 50 ሚሊዮን እንደጨመረና በዘመነ ኢሕአዴግ ወደ 100 ሚሊዮን እንዳሻቀበ እየሰማን ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የወጣቱ ቁጥር ከአገሪቱ ሕዝብ 70 በመቶ መድረሱ በመልካም ጎኑ ቢታይም የተከሰተው የሥራ አጥነት ችግርና እያስከተለ ያለውን የአገሪቱን አለመረጋጋት ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ይህ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እንደ ዋዛ የሚታይ ጉዳይ መሆን የሌለበት ሲሆን፣ ይህንን ከፍተኛ የሕዝብ ብዛትና የወጣት ሥራ አጥነት ወደ አምራች ዜጋ ለመቀየር የአገሪቱን የእርሻና ግብርና ምርታማነት በማሳደግ ምድሪቷም የበረከት ምድር ማድረግ ምን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብሎ መጠየቅና ተቀዳሚውን ተግባር መለየት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሚና ፈፅሞ ተረስቷል፡፡ ለምሳሌ ስለእርሻ ካነሳን በጋምቤላ ክልል ዘመናዊ እርሻ እንዲያካሂዱ ወደ ሦስት መቶ ለሚጠጉ ግለሰቦች የልማት ባንክ ወደ ስምንት ቢሊዮን ብር (ወደ 275 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) ያበደረውና አሁን ግለሰቦቹ ገንዘቡን የት እንዳስገቡት የማይታወቀው ብድር ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ማደራጃነትና ምርታማነት ለማሻሻል ታቅዶ ቢሠራበት ኖሮ ዛሬ ላይ ስንት ሥራ አጥ ወጣት ይጠቀምበት ነበር? ስንት የዶሮ ዕርባታዎች፣ የወተት ላም እርባታዎች፣ እርድ እንስሳዎች ማደለቢያዎች፣ የዓሳ ዕርባታዎች የንብ ማነቦች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዎች፣ ስንት ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች፣ ዘመናዊ ጎተራዎች፣ የውኃ ፓምፖች፣ እህል ማጓጓዣ መኪናዎች፣ የሸማች ማኅበራትና የንግድ ትስስር የመሳሰሉትን የአገራችን ገበሬዎች ይኖራቸው ነበር፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴግ ለዚህ ምን መልስ አለው? መንግሥት ከታክስ ከፋዩ ሕዝብ የስበሰበውንና ዱካው የጠፋውን ስምንት ቢሊዮን ብር የማስመለስ ግዴታ አለበት፡፡ ግለሰቦቹ ከምድራችን ውጪ ወደ ሌላ ፕላኔት እንዳልወጡ መላ ምት አያስፈልገውም፡፡ ይህን የተረጋገጠ እኩይ ድርጊት የሚመስሉ ብዙ ዘረፋዎች ከሕዝብ ዓይን የተሰውሩ አይደሉም፣ ታዲያ ለአገራችን  ገበሬዎች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ማን ይቁምላቸው? ድርጅት ያላቸው! ስለሆነም መደራጀታቸው የግድ ይላል፡፡

ወደ እርሻው ትርክት ስንመለስ ኢሕአዴግ ራሱ ላዘጋጀው የእርሻ መር ኢንዱስትሪያዊ ልማት ስትራቴጂ መሳካት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሚናና ተሳትፎ ታላቅ ይሆን እንደነበርመረዳትና ማመን ይገባው ነበር፤ ሆኖም ግን አርሶ አደሩን ለማደራጀት ከመሥራት ይልቅ ለጥቂት ‹‹ምርጦቹ››  ብድር ከማመቻቸትና ከማዘረፍ ውጪ የሠራው ምን ነገር አለ? በእርሻውና በግብርና መስክ እንደ ለውጥ ከታየ ጥቂት ታታሪ ገበሬዎችን ሚሊየነሮች አደረግኩ እያለ ኢሕአዴግ ሲሸልም አይተናል፡፡ እነርሱም በጥናታቸው እንጂ ምን ተደረገላቸው? ብዙኃኑ ገበሬ ግን ያው እንደ ቀድሞው ነው፡፡ ገበሬው ምርታማ አድጎ ቢሆን ኖሮ የሸማቹም ኅብረተሰብ እሮሮ እያሻቀበ ባልመጣ ነበር፣ ለዕለት ተዕለት ምግቡ ከገቢው ከ40 እስከ 50 በመቶ እያወጣ ለሚኖረው ዝቅተኛ ገቢ ላለውና ለደሃው ሸማች ኑሮ እንዴት ይገፋል? ከቲማቲም፣ ቃሪያና ሰላጣ ውድነት የተነሳ ቢያንስ ጥሬውን በዳቦ ለመብላት ለብዙኃኑ ዳገት ሆኗል፡፡ ሽሮ ድሮ የደሃው ምግብ ነበር፣ ዛሬ ለሀብታሙ ተትቷል፡፡ ብዙ ሕዝብ የለመደው ጤፍና እንጀራ ስለተወደደ፣ ሰብዓዊነት ከውስጣቸው ተሟጦ የጠፋ ስግብግቦች ሰጋቱራ፣ ጀሶና ጥቂት ‹‹የጤፍ›› ዱቄት ቀላቅለው እየጋገሩ የከተማውን በላተኛ ለጤና ችግር ዳርገውታል፡፡ በሌላው ዓለም የመጨረሻ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው አንድ እንቁላል፣ ወተት፣ ዳቦ፣ ለአኛ ብርቅ እየሆነብን ነው፡፡ ተማሪዎች ያለ ቁርስ ትምህርት ቤት እየመጡ በረሃብ እየወደቁ ስለመሆናቸው መንግሥት ራሱ አምኖ በየ ትምህርት ቤቱ ደሃ ተማሪዎችን ለመመገብ ተገዷል፡፡ ታዲያ በተፈጥሮ ፀጋ ለታደለች እንደ ኢትዮጵያ ላለች አገር ታዲያ ይህ አሳዛኝም አሳፋሪም አይደለም? በገጠሩም አርሶ አደሩ ተርቧል፡፡

ኢሕአዴግ መንግሥት ብዙ የተናገረለት የእርሻ መር ስትራቴጂው ተሳክቶለት ቢሆንማ ኖሮ ላለፉት በርካታ ዓመታት ቢያንስ ስንዴ፣ ጥጥ፣ ዘይት፣ ስኳር ወዘተ. በዶላር አናስመጣም ነበር፣ የኢንዱስትሪ ግብዓትም እንዲህ ማነቆ አይሆን ነበር፣ ብዙኃኑ ደሃው ኅብረተሰብም ምሬት ውስጥ አይገባል ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ጥምር ድርጅቶች ስለልማትና፣ ስለአፈጻጸም ችግር፣ ስለሙስና ወዘተ. በማያቋርጠው ግምገማቸው የፈየዱት አንዳችም ነገር አልነበረም፣ ዶ/ር ዓብይ እስከ መጣበት ዘመን ድረስ ምንም ፋይዳ አላመጡም፡፡ በእርሻው መስክ ምርታማነትን ለማምጣት ኢሕአዴግ አጋሬ ነው ብሎ የሚጠራውን የኢትዮጵያ አርሶ አደርና አርብቶ አደር በአገር አቀፍ  ደረጃ በማኀበር ለማደራጀት ባለመፈለጉ፣ ቢያንስ ደርግ የሞከረውን አርሶ አደሩን የማደራጀት ሥራ ችላ በማለቱ ታላቅ ዋጋ እየከፈለበት ይገኛል ይህን በቶሎ ካላደረገ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ይቀጥላል፡፡ ኢሕአዴግ መሠረቴ ነው ያለውን አርሶ አደር ለማደራጀት የፈራበት ምክንያት የተደራጀ ሕዝብ ለመብቱ መታገሉ ስለማይቀር ለሥልጣኑ መቀጠል በመሥጋት ይሆናል፡፡ አርሶ አደሮች በዚህም በዘመነ ኢሕአዴግ የተረፋቸው ነገር አንድ ለአምሰት አደረጃጀትና በካድሬዎች ቁጥጥር ሥር መዋል ሲሆን የደረሰባቸውን መከራና ችግሮች ለእነርሱ መተው ይሻላል፡፡

የሚገርመው ጉዳይ ኢሕአዴግ አጋሬ ነው ከሚለው አርሶ አደር ይልቅ ለአገሪቱ  የኢኮኖሚ አንዳች ለውጥ ለማያመጡ ከ60 በላይ ለሚሆኑ ተቃዋሚ ተብየው ፓርቲዎች (ዛሬማ 108 ደርሰዋል) ከማደራጀትና የገንዘብና ሌላም ወዘተ. ድጋፍ ከማድረግ፣ በቴሌቪዥን መስኮቶች እያቀረበ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ ተጨባጭ የኢኮኖሚያዊ ለውጥ በማምጣት የወጣቱን ሥራ አጥነት ችግር በእጅጉ ሊፈታ የሚችለውን አርሶ አደሩን ማደራጀት ነበረበት፡፡ ይህንን ችላ ማለቱ ያውም ለአብዮታዊ ዴሞክራቲክ መንግሥት አሳፋሪ ነው፡፡ የዶክተር ዓብይ መንግሥትም ሆነ በምርጫ ሥልጣን እይዛለሁ የሚል ድርጅትም ለአገሪቱ የኢኮኖሚው ዕድገት የሚተጋ ከሆነ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ካላደራጀ አሳሳቢውን የወጣት ሥራ አጥነት አይፈታም፣ ዕቅዱም ሁሉ እንደማይሳካ ዕሙን ነው፡፡

ኢትዮጵያ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን (ኢአአማ) ማደራጀት ለምን ያስፈልጋል?

አገራችን ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በታላቅ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስና ፈተና ውስጥ ወድቃለች፡ መሠረቱ ከአርሶ አደሮችና አርብቶ አደር የሚሆን 70 በመቶ ለሚጠጋ የተማረም፣ እየተማረም ያለ፣ ያልተማረም ወጣት ሥራ ማጣቱ ያስከተለው ችግር ለራሱ ለኢሕዴግ መሰነጣጠቅና መዳከም፣ እንዲሁም ጥቅማቸው ለተነካባቸው የየክልል ዘራፊዎች የትርምስ አጀንዳ ይዞ ለመነሳት ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆን ዝርዝሩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ መተው ሻላል፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ከአገሪቱ ሕዝብ በቁጥር ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን በመቀበል አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ለኢኮኖሚያችን ዕድገት ማደራጀት በመልካም ጎኑ ማየት ብንችል በብዙ ረገድ ጠቃሚ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

ምክንያቱም የእነርሱ መደራጀት ዛሬ የምናየውን ጽንፈኝነት ወደ መሀል ያመጣል፣ ስለኢትዮጵያዊነትና ብሔርተኝነት ብዙ እንናገራለን፣ ኢትዮጵያዊነትና ብሔራዊነት ያለው ግን በኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ልብ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በዘመናት ሒደት በቋንቋ፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በወሰን፣ ወዘተ. ሳይለያይ በአብሮነት፣ በኅብረት፣ በአንድነት በመከራና በደስታ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ የተሳሰረና የተጋመደ ሕዝብ ነውና፣ ስለሆነም 

  • ያለ ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት አርሶ አደሩ በነፃነት በአገር አቀፍ ደረጃ ከተደራጀና መዋቅሩን እስከ ቀበሌ ከዘረጋ የወጣቶቻችንን ሥራ አጥነት ለመፍታት ያስችላል፡፡ 70 በመቶው ወጣት መሠረቱ ከዚህ ክፍል የወጣ ነውና
  • አርሶ አደሩን በማደራጀት የእርሻንና ግብርናን ምርታማነት ማሳድግ ይቻላል፣ የኢንዱስተሪ ግብዓትን ለማሳደግ ያስችላል፣ ኋላ ቀር የእርሻና የግብርና ሥራዎችን ያሻሽላል፣
  • 80 በመቶ የሚደርሰው የአገራችን አርሶ አደርና አርብቶ ሲደራጅ እርሻንና ግብርናን ለማዘመን፣ ምርታማነትን ለማሻሻል፣ አዳዲስ ቴክኖሎጆችን ለማስተዋወቅና ለመጠቀም፣ የምርጥ ዘርንና የማዳበሪያን አጠቃቀም ለማሳለጥ፣ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ያስችላል፣
  • በብሔር ፖለቲካ፣ በጎሳ ወዘተ. ምክንያት ለሚነሱ ግጭቶ ተጎጂው ራሱ በመሆኑ በመደራጀቱ ችግሩን በቀላሉ ለመፍታት ያስችለዋል፣ 
  • አርሶ አደሮችን የሚያፈናቅሉ ሴረኞችን በድርጅቱ አማካኝነት በተባበረ ኃይል ያስቆማል፣ ይታገላል፣ ያጋልጣል፣
  • በአገሪቱ ጉዳዮች ለመምከር ለመወያየት ድርጅቱን እንደ መድረክ ይጠቀምበታል፣ የመሬት ሥሪቱን ለማሻሻል የሐሳብ ግብዓት ይሰጣል፣
  • የተዛቡ መረጃዎችን የሚያሠራጩ ሐሰተኛ ወገኖችን ለመከላከል ያስችለዋል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት በእውነት የምንፈልግ ከሆነ በመንግሥት ድጋፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ያለ ገዥ ፓርቲ ጣልቃገብነት፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በነፃነት አገር አቀፍ ማኀበራቸውን እንዲያቋቁሙና መዋቅራቸውም እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲያደራጁ መሥራት የማንኛውም የአገሪቱ መንግሥት ኃላፊነትና ግዴታም ስለሆነ ሊታሰብበት የሚገባ ወቅታዊ አጀንዳ ነው፡፡ አገራችንን ለማረጋጋት የሚችሉት እነዚህ ታታሪና ሕግ አክባሪ ሕዝቦች ናቸው፡፡

የ1960 እስከ 70ዎቹ ፖለቲከኞች እባካችሁ አገራችን እንዳትረጋጋ ከማድረግ እጃችሁ ይሰብሰብ፡፡ ላለፉት ስህተቶቻችሁና የጥፋት ድርጊቶቻችሁ ሕዝባችሁን ይቅርታ መጠየቅ ሲገባችሁ፣ ይባስ ብላችሁ ለሥልጣን ጥማታችሁ ሕዝባችሁን ወደ ከፋ ብጥብጥና ዕልቂት አትግፉት፡፡ ይህ ካልሆነ ለሰላማዊ ሽግግር በቅርቡ የፈረማችሁትን ሰነድ መጣስ ስለሚሆን መንግሥት ወደ ሕግ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ መብትና ግዴታ ተነጣጥለው አይታዩምና፡፡ በሌላ ርዕስ ይቀጥላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...