Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከተስፋ በላይ ትዝታ ምን ይፈይዳል?

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ወደ ሳሪስ፡፡ ተጓዥ ቋጠሮውን ይዞ ለማይሞላ ቋት ይራኮታል። ተስፋ በመከራ ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ ሥጋ ለባሹን እያቁለጨለጨ ያባላዋል። ጠገብኩ ባይ የለም። በቃኝ ባይ ለቁጥር ጠፍቷል። ዓይን ፈጦ አጥንት ገጧል። ሻጭና ሸማች በዋጋ ይጣላል። ተስፋ ነጋችንን እየቀረፀው መንገድ አይሰለቸንም። ሁኔታዎችን አሥልቶ፣ ከጊዜ ጋር አብሮ፣ የአረማመድ፣ የአኗኗርና የአስተሳሰብ ሥልት የሚያበጅልን የአብዛኞቻችን ጎዳና አንድ ነው። ሥሌቱን የማንደርስበት፣ ክፍልፋዩን ቆጥረን የማንጨርሰው አሻራው ከባድ የሆነ የሰው ልጆች የውጣ ውረድ መድረክ ይኼው ጎዳና ነው። እግረኛው፣ ባለአውቶሞቢሉን፣ አውቶብስና ታክሲ ተጠቃሚውን እያጣደፈው በወጣችለት ፀሐይ በበራለት የንጋት ብርሃን ነግዶ ለማትረፍና ዘርቶ ለማጨድ ይጓዛል። ጉዞው ቀልብ አያውቅም፡፡ ስንክሳሩ ተራኪን ያደክማል። የግርግሩ መናኸሪያ ትዝብት መለያው ነው። እያንዳንዱ በገዛ ራሱ የሕይወት መስመር ታቅዶ የሚጠብቀው፣ ተጀምሮ ያላለቀ አጀንዳ ባለቤት ነው።

እጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ አቅጣጫ ይዞ እየሄደ አቅጣጫው የጠፋበት  ብዛቱ ነው። ይኼን ለሚያይ ቅስም ይሰብራል። የሚጠሉትን እንደሚያፈቅሩት አምነው፣ የሚሹትን እንደሚንቁት ቆጥረው የግፊያውን ሠልፍ ያደመቁት ነፍሶች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከቶ ምን ቃል ይኼን ቅስም የሚሰብር ትዕይንት ይገልጻል? ጥቂት ከፈት ብለው ፈገግታቸው በሚታይ ጥርሶች ጀርባ የጨፈገገ እህህ ይንበለበላል። የሆነውን ከመሆን አልፎ ሕዝበ አዳም ራስን ፈልጎ ማግኘትና ማስተዋል ፍፁም ርቆታል። ይህን መሰል አብረክራኪ እውነት ጎዳናው ላይ ያፏጫል። ቀና ብለው በሚራመዱ ሰዎች ውስጥ የጎበጠ ማንነት ድንቅር እያለ ዕይታን ያጭበረብራል። በተነፉ ደረቶች ውስጥ የተነፈሱ ህልሞች ይዋኛሉ። ‹‹ምድሪቷ ቂሟ ከማን ጋር እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፤›› ይላል አንዱ አልፎ ሂያጅ። ስብራት የሚጠግን ሥርዓት ሰፍኖ መንፈስ የሚያድስ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር፣ የሕዝብ የበላይነት ያልናፈቀው የለም፡፡ ደመኝነትን ታሪክ የሚያደርግ ተግባር ያልናፈቀው ማግኘት ያዳግታል፡፡ ከመጋቢው መንገድ፡፡

 ወያላው በሠልፍ ላይ ሠልፍ ይደርባል። ‹‹ማንም ሳይፈተሽ አይገባም፤›› ይላል ሾፌራችን። ‹‹ደግሞ ምን መጣ? ብላችሁ ብላችሁ በዚህ አሮጌ ታክሲ ጭራሽ ፍተሻ?›› ተቆጣች አንዷ። ‹‹ከፈነዳ በኋላ ከመጠራጠር አሁን መበራበር አይሻልም?›› ወያላው ተለሳልሶ ተጠጋት። “እውነት ነው ታጣቂው በስቷል። ወዳጅና ጠላት መለየት ከብዶናል፡፡ ደግሞ ሚሊሻ ተማምነን ወጥተን እንቅር? ፈትሽ ወንድሜ. . .፤›› ትላለች አንዲት ወይዘሮ። ‹‹የተማረ ይግደለኝ!›› ወያላው ያመሠግናታል። ‹‹የተማረ ነው የተሾመ? ተምታቷል እኮ፤›› ይላል ከወይዘሮዋ ጀርባ ሽብረክ ብሎ የቆመ ሠልፈኛ፡፡ ቁጣ ቁጣ ያላት ለግላጋ ተራዋን፣ ‹‹ጫፌን እንዳትነካኝ ሰውዬ። ወንድም ሴትም በጅምላ ሲፈትሽ ዝም ትላላችሁ? ምንድነው ጉዱ?›› ብላ ከመስመሯ አፈንግጣ ወጣች።

ይኼኔ አንዱን ትተው ሌላ ሲያሲዙት ዘራፍ ማለት የለመደው ሁሉ፣ ‹‹ለካ እሱም አለ?›› እያለ ወያላውን ገፍትሮ ገባ። ሾፌሩ የሚያደርገውን አሳጣው። ‹‹ሰውዬ ፖሊስ ነው የምንጠራው። አርፈህ ሥራህን ሥራ። ይኼ በልጅ አመካኝቶ አንክቶ መብላት ድሮ ቀረ፤›› ስትል እንዳልነበር ያቺ ወይዘሮ፣ ‹‹ምን በልጅ ብቻ? በሕዝብ ድምፅ፣ በሥልጣንና በልማት አሳቦ መበስበስም ቀርቷል። ዘመኑ የለውጥ ነው፤›› ይላል ቀድሞን ዘሎ ገብቶ መጨረሻ ወንበር ላይ ጥጉን የያዘ ዓይነ ድፍርስ። ይኼኔ ወያላው እኩያው መሆኑን አሥልቶ፣ ‹‹እስኪ መጀመርያ የዞረ ድምሩ ይልቀቅህ። ከዚያ ትፖተልካለህ፤›› አለው። ያ ዘሎ ተነሳ። ካልተጋደልን አሉ። ቋንቋም እንደ መጠጥ ተሳክሮ ማሳከሩ ሳያንስ ጭራሽ ያደረ ነገርና ስካር ሲደረብበት ጎዳናው በአንድ እግሩ ቆመ። ዳሩ ልብ እንደ ዋዛ ቀጥ አይልምና እግር ምን ጊዜም ወደፊት መራመዱን አያቆምም!

ጉዟችን ከተጀመረ ቆይቷል። ዘመኑ የአዳኝና የታዳኝ ሆነብኝ. . .›› ሲል የቆየ አንድ ተሳፈሪ፣ ‹‹ቆይ ባናድግስ? ጥንቅር ብሎ ቀርቶ እንደ ነበርነው ብንኖር?›› ብሎ በምሬት ሲጠይቅ ብዙዎች አጉረመረሙበት። ‹‹ተው! ተው! ተቀምጦ ከመኖር እየሄዱ መሞት ምንኛ መታደል ነው። እንዴ ምን ነካው? የድህነት አሸዋ ላይ ተቁሞ መኖር አይቻልም አላሉም እንዴ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር?›› ብላ ከቀይዋ ቆንጆ ወጣት ተሳፋሪ ጋር አብራ የተቀመጠች ወይዘሪት መለሰችለት። በማያቋርጥ እንቅስቃሴ የተሞላችው ሕይወት ወደፊት መራመዷን እየቀጠለች ዕድገት ይቅር? ይቀጥል? ክርክርና ውይይት እየከረረና ተሳፋሪውን በስሜት እያገነፈለ ጦዘ። ጥቂቶቻችን በአድማጭነታችን ስንፀና አላስችል ብሏቸው አብዛኞቹ መደነቋቆሩን ሥራዬ ብለው ያዙት።

ይኼኔ ወያላው፣ “አቦ አትነጅሱና?” ሲል የተሳፋሪዎችን ቀልብ ገፈፈው። ጫቱን እየቀነጣጠበ እጅግ የተበሳጨ ፊቱን እያሳየ። ‹‹መወያየት እኮ ዴሞክራሲያዊ መብታችን ነው!›› ቢለው ጎልማሳው፣ ‹‹ታዲያ እንዲህ ያለ ውይይት ነው? ያውም በወሳኙ በቂማ ሰዓት?›› ብሎ መለሰለት። ‹‹የተሻለ ሐሳብ ስንናገር የለውጥ አደናቃፊ መባልንስ ለመድነዋል። የቃሚ አደናቃፊ መባል ግን መቼ ተጀመረ?›› ይላል አንዱ ተሳፋሪ በሹክሹክታ። ወዲያው ቅጠልና ቅጠላውያን ሰሞኑን አትክልት ነክ የምግብ ዓይነቶችን በተመለከተ እየተሰጠ ስላለው ማብራሪያ ማውራት ሲጀምሩ አጠገቤ የተቀመጠው፣ ‹‹አዳሜ በቃ ያለ ቀጭ ቀጭ አይንቀሳቀስም ማለት ነው?›› ይለኛል በሹክሹክታ። ሹክሹክታ ግን እስከ መቼ?

መጨረሻ ወንበር አካባቢ ደግሞ ሌላ ወሬ እንሰማለን። ወያላችን ጫቱ ላይ ነው። ‹‹እኔ ምለው ከመቼ ወዲህ ነው አዲስ አበባ እንዲህ ሰው የበዛው?››ይላል አንድ ‘ዳያስፖራ’ ተሳፋሪ ሲኮላተፍ የተለየ ስሜት በሚያጭሩ ቃላት። ‹‹አልሰሜን ግባ በለው አሉ! እኔ እኮ መንግሥት አልሰማን አለ ብለን የምንጮኸው ዝም ብለን ነው፡፡ መጀመርያ መቼ እርስ በርሳችን ችግራችንን አወቅነው ስል ማን ሰምቶኝ? ግን ይኼው. . .›› ብላ አንዲት ነገር ነገር የሚላት አጠገቡ እንደ ተቀመጠች ተንበለበለች። ‹‹ይቅርታ! እኔ እኮ እዚህ አገር ስላልነበርኩና ከሦስት ቀን በፊት የመጣሁ በመሆኔ ነው የጠየቅኩት?›› ሲላት ይባስህ ብላ፣ ‹‹ጭራሽ እናንተ አይደላችሁ እንዴ እኛ እናውቅላችኋለን እያላችሁ በየኢንተርኔቱ ጓዳ ስለአገሬና ሕዝቧ ብሎም መንግሥቷ የምትወሸክቱት? እኔ ምለው ለመሆኑ ወደፊት በሚካሄደው የአዲስ አበባ ምርጫ ልትሳተፉ አላሰባችሁም?›› ስትለው ደንግጦና ግራ ገብቶት ሁሉንም ተሳፋሪዎች ይቃኝ ጀመር።

ብዙም ሳይቆይ እየተንቀሳቀሰች የነበረችውን ታክሲ አስቁሞ፣ ‹‹እባክህ ቦታ ቀይረኝ?›› አለ ወያላውን። ሊወርድ አስቦ የሠልፉ ነገር ሐሳቡን እንዳስቀየረው ያስታውቅበታል። አንድ ፈቃደኛ ወጣት ከኋላ መቀመጫ ተነስቶ ከቀየረው በኋላ ጉዟችን ቀጠለ። ‹‹አይ ታክሲ ስንቱን ያሳየናል?›› ይላል ከሾፌሩ ጀርባ ያለ ጎልማሳ። ሕይወት በጋራ ቋንቋ በሰላምና ባለመግባባት ብዙ እያሳየችን የኖርነው፣ ቢያንስ ግማሹ ታክሲ ውስጥ መሆን አለበት። ቀለበት መንገዱን ይዘን መምዘግዘግ እንደ ጀመርን፣ ‹‹ይኼ ቀለበት መንገድ የስንቱን ቀለበት አስወለቀ?›› አለ የማይናገር የሚመስለው ወያላ መንገዱ መሀል እየዘለለ የሚሻገር ትልቅ ሰው እያየ። “እንዴት?” ሲሉት፣ ‹‹ድልድይ ፈልጎ መሻገር አላስችል ብሎት ስንቱ ነው ያለቀው?›› ከማለቱ በቅጡ ያላስተዋልናቸው አዛውንት፣ ‹‹‘ጊዜ ጠብቀህ ተናገር፣ ውኃ ሲጎድል ተሻገር’ ነዋ ከጥንትም ብሂሉ። የዘንድሮ ሰው ምክር ጠላ እንጂ!›› ብለው እጃቸውን አመናጨቁ! ‘መጥኔ!’ ዓይነት።

 መዳረሻችን እየተቃረበ መጥቷል። ሳሪስ ደርሰን መውረዳችን ነው። ከላይ ታች ግርግሩ አይሏል። ሩጫውና ግፊያው ተደምሮ አካባቢው በወከባ ደምቋል። ‹‹ይህች ኑሮ የምትባል ላትሞላ ነገር በከንቱ ታደክመናለችም አይደል?›› አሉ አዛውንቱ። ‹‹ያያሉ አይደል አባት? እንዲያው በእናንተ ጊዜ እንዴት ነበር?›› አላቸው አጠገባቸው ያለ ወጣት። ‹‹መቼም እኔ በዚህ በእናንተ ዘመን የሚያስከፋኝ ነገር እንዳለ ሁሉ የምቀናበት ነገር አለ። እኛ እኮ እውነት ለመናገር እንደ እናንተ ሩጫ አናውቅም። በዋዛ ፈዛዛ ስንቱን ጊዜ ሸኘነው መሰላችሁ? ያ ባይሆንማ እማማ ኢትዮጵያ እንዲህ ሆና ባልጠበቀቻችሁ ነበር. . .›› ብለው፣ ‹‹እናንተ በጣም ታስቀናላችሁ። ችኩልነታችሁና ከላይ ከላይ መዋለላችሁ ብቻ ቅር ያሰኛል እንጂ ላባችሁ ችፍፍ እያለ ወዲያ ወዲህ ስትሉ እቀናለሁ አከብራችኋለሁ። አይዟችሁ እስኪ በርቱና ለዚህች አገር ድረሱላት። ታዲያ የአገር ጉዳይ እናንተንም ይመለከታል። ከዳር ቆሞ መንሾካሾክ አቁሙ። የአሉባልታ ዘመን አልፏል። መረጃ እንደሆነ ለእናንተ ቅርብ ነው። በመረጃና በዕውቀት ጠጋ ጠጋ በሉ። ታክሲ ውስጥ ብቻ ተሸጋሽጋችሁ እስከ መቼ? መጪው ዘመን እኮ የእናንተ ነው። ያለ ዕውቀት የሚደናቆሩትን በዕውቀትና በመረጃ ጠጋ ብላችሁ አግዙዋቸው፤›› ሲሉ ወጣት ጠቅላላ ያድርግልን ብሎ ጮኸ፡፡ ወያላው “መጨረሻ” ሲል አጠገቤ የነበረችው ቆንጆ ‹‹ነገሩስ መልካም ነበር፡፡ ግን የአዳኝና የታዳኝ ጊዜ. . .›› እያለች ስትናገር፣ ‹‹አይምሰልሽ! ሁሉም ያልፋል፣ እስኪያልፍ ግን ያለፋል ቢባልም ከእኛ ትዝታ በላይ የተሻለ ተስፋ አለ፤›› ሲሉ አዛውንቱ፣ በትንሳዔ በዓል መዳረሻ ላይ መሆናችን እየታሰበኝ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ተስፋ እያለ ትዝታ ምን ሊረባ! መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት