Wednesday, December 6, 2023

የዳኝነት ነፃነት ዕውን ለማድረግ የቀረበው ረቂቅ ሕግ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ የዳኝነት ሥልጣን በፌዴራልና በክልሎች የተከፋፈለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት የማቅረብና ፍርድ የማግኘት መብቱ በሕገ መንግሥቱ የተጠበቀ ነው፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ ስለዳኝነት ነፃነት በተጠቀሰው መሠረት ተግባራቸውን ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ተገማች የሆነ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዳኝነት የሚጠበቀውን አገልግሎት ለማግኘት ደግሞ የሕግ ማዕቀፎችን በመፈተሽ፣ ያሉባቸውን ክፍተቶች ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥም አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (1) ድንጋጌ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦና ፀድቆ ላለፉት 24 ዓመታት በሥራ ላይ የከረመውን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 ድንጋጌን በሌላ አዋጅ መተካት አስፈልጓል፡፡

አዋጁን ለአራት ጊዜያት ለማሻሻል ቢሞከርም፣ በአሁኑ ጊዜ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ችግሮች ለመፍታት ክፍተቶች ስላሉበትና የተቀናጀ መዋቅራዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማስፈን በቂ አለመሆኑንና የተሻለ የፍርድ ቤቶች አዋጅ ማስፈለጉን በመግለጽ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል፡፡

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በአገሪቱ የተዘረጋውን የፌዴራል ሥርዓት መሠረት በማድረግ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸውን የዳኝነት ሥልጣን የደነገገ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም ክፍተቶች ስላሉበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አዲስ አስፈጻሚ አመራር በተሾመለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር የተቋቋመውና 17 ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ጉባዔ በሦስት ንዑስ ኮሚቴ በመደራጀት፣ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ እንደተናገሩት አንደኛው ንዑስ ኮሚቴ ለ24 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 በተሻለ አዋጅ መቀየር እንዳለበት በመተማመን፣ ረቂቅ አዋጁን በማዘጋጀት ለውይይት እንዳቀረቡት ቅዳሜ ሚያዝያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በሳፋየር አዲስ ሆቴል በውይቱ ላይ ለታደሙት ዳኞች፣ ለዓቃቤያነ ሕግ፣ ለጠበቆች፣ ለሕግ ባለሙያዎችና ለባለድርሻ አካላት አስታውቀዋል፡፡

በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 25/88 እና ረቂቅ አዋጁን በማነፃፀር የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡ አቶ አብደላ ዓሊ የተባሉ የሕግ ባለሙያና የጥናት ቡድኑ አባል ሲሆኑ፣ የውይይት መነሻ ሐሳባቸውን በቀድሞ አዋጅ ባልተካተተውና ትርጉም ባልተሰጠው ‹‹መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት›› ከሚለው ጀምረዋል፡፡

አቶ አብደላ እንዳብራሩት፣ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለባቸው ተብሎ ከ1986 ዓ.ም. እስከ 1996 ዓ.ም. ድረስ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከቀረቡት 8,000 የፍትሐ ብሔር መዝገቦች ውስጥ፣ ‹‹ያስቀርባሉ›› የተባሉት 25 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2010 ድረስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከነበሩት 121,769 መዝገቦች በሰበር አጣሪና በሰበር ሰሚ ችሎቶች በቀጠሮ ላይ የነበሩ መዝገቦች ደግሞ 94,506 ናቸው፡፡ ይኼ ቁጥር (94,506) በመደበኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ችሎት ከነበራቸው 27,263 መዝገቦች ብዛት ጋር ሲነፃፀር፣ በሰበር ሰሚ ችሎት የነበረው መዝገብ ብዛት 77 በመቶ ብልጫ እንዳለው በመጠቆም፣ ‹‹መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት›› የሚለው በአዋጁ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአዋጅ 25/88 ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሚለው ትርጉም ስላልተሰጠው፣ በዳኛው ወይም በችሎቱ አረዳድ ‹‹ያስቀርባል›› እየተባለ፣ ችሎቱን በፋይል ብዛት ከመደበኛው ችሎት በላይ ማድረጉንም አክለዋል፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹መሠረታዊ የሕግ ስህተት›› ማለት ግልጽ የሆነ ሕግን ወይም የሕግ መርህን በመጣስ የተሰጠ ፍርድ፣ ጉዳዩን ዓይቶ የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን በሌለው ሲሰጥ፣ በአስተዳደር አካላት ከሥልጣን ውጪ የተሰጠን ውሳኔ ጨምሮ ዘጠኝ እውነታዎችን በረቂቁ በትርጉምነት አስቀምጠዋል፡፡

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ያልተካተተና በረቂቁ ተካቶ ለውይይት የቀረበው ሌላው ነጥብ፣ በተለይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮች ከሁሉም የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች እየመጡ በመሆናቸው፣ በማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ጉዳዮች ወደ ሰበር እንዳይቀርቡ በመመርያ ማገድ ተገቢ መሆኑ በረቂቁ ተጠቅሷል፡፡ በሰበር ሰሚ ችሎት የሚቀርቡ አቤቱታዎች በሦስት ዳኞች መጣራታቸው ቀርቶ በአምስት ዳኞች እንዲታዩና እንደሚያስቀርቡ እየታወቀ፣ ‹‹አያስቀርቡም›› በማለት የሚታለፈው መብት እንዲከበርም በረቂቁ ተካቷል፡፡ በአምስት ዳኞች የታየው መዝገብ መሠረታዊ ስህተት አለበት ከተባለ ለዘጠኝ ዳኞች ቀርቦ በፓናል ከመታየቱ በፊት፣ ‹‹መሠረታዊ የሕግ ስህተት›› በተሰጠው ትርጉምና በተዘረዘሩት ማስቀረቢያ ነጥቦች ላይ ሁለት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አስገዳጅ ውሳኔዎችን በማጣቀስ ክርክር ሲቀርብ፣ ችሎቱ በቀረበለት ጉዳይ ላይ መሠረታዊ የሆነ የትርጉም ልዩነት የተፈጠረበትን ሕግ የሚመለከት ክርክር ሲያጋጥም፣ ወይም በሕዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ሲታስብ ብቻ እንዲሆን በረቂቅ ሕጉ ተካቷል፡፡

ረቂቁን ያዘጋጀው ኮሚቴ ሌላው ነባሩን አዋጅ ያሻሻለው በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትና በከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር የዳኝነት ሥልጣንን በሚመለከት ነው፡፡ ባለው አዋጅ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማየት የሚችለው የፍትሐ ብሔር ጉዳይ እስከ 500 ሺሕ ብር ድረስ የነበረ ሲሆን፣ አዲስ በቀረበው ረቂቅ ግን እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ፣ እንዲሁም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ደግሞ ከዚያ በላይ እንዲሆን ነው፡፡ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት ተጠሪ ዳኞችና ሰብሳቢ ዳኞች፣ ከስም ባለፈ ለቦታው ሥልጣንና ኃላፊነት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በረቂቁ ተካቷል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ ስያሜን በሚመለከትም፣ ‹‹የፌዴራል ዳኞች ጉባዔ›› ቢባል የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በረቂቁ ሌላው የተካተተው ሐሳብ መሠረታዊ የሕግ ስህተት በ60 ቀናት ውስጥ እንዲታረም የሚለውና ስህተት የሠራው ችሎት፣ ስህተት መሆኑን ከተረዳ በኋላ ራሱ እንዲያርም ቢደረግ የሚሉ ናቸው፡፡ በአዋጅ 25/88 በ38 አንቀጾች ቀርበው የነበሩት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ድንጋጌዎች በረቂቁ ዝርዝር ሐሳቦችንና የተሻሉ አማራጮችን በማካተት በ44 አንቀጾች ድንጋጌዎቹን ከፍ በማድረግ ለውይይት ቀርቦ የመጀመርያ ዙር ውይይት ተደርጓል፡፡ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ የሆነበት ዋና ዋና ዓበይት ምክንያቶች ለሰበር የሚቀርቡ መዝገቦች (አቤቱታዎች) ተገማች አለመሆን፣ የጉዳዮቹ ፍሰት ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣትና በአጠቃላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና ለማቃለልም ጭምር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘውን አዋጅ 25/55 ለመተካት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በማንሳት የሕግ ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውንና ግብዓት ይሆናል ያሉት ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ዓሊ መሐመድ በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት፣ ይግባኝ በወንጀልም ሆነ ፍትሐ ብሔር ላይ የሚቀርብ መብት ነው፡፡ የተሳሳቱና የተዛቡ የሥር ፍትሕ ሰጪ ፍርድ ቤቶች የሰጧቸውን ውሳኔዎች ይጨምራል፡፡ በ(ICCPR) አንቀጽ 14 ላይ ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ በስህተት ወይም በተዛባ ሁኔታ የተሰጠን ፍርድ በይግባኝ እንዲታይ የመጠየቅ መብት መሆኑን መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የይግባኝ ሥርዓት ተከታይ ስትሆን ሌሎች አገሮች ግን ሪቪው ሥርዓት መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ዓሊ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ስህተት መሆኑ ከታወቀ ተበዳዩ ብቻ ሳይሆን ማንም በይግባኝ ሊያሳርመው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሪቪው ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች በማንኛውም መንገድ የተሰጠው ውሳኔ ስህተት መሆኑን ባወቁ ጊዜ፣ ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ሪቪው እንዲያደርገው ማንም ማቅረብ ይችላል፡፡ ይኼ የሚያሳው የተወሰነ ጊዜ (Period of Limitation) የሌለው መሆኑን ነው ያሉት አቶ ዓሊ፣ በኢትዮጵያም ለሰበር የሚቀርብ አቤቱታ የጊዜ ገደብ ሊቀመጥለት እንደማይገባ በመጠቆም፣ በረቂቅ አዋጁ 60 ቀናት የሚለው እንዲቀር ጠይቀዋል፡፡ መሻር ያለበትና ሊፈጸም የማይገባው ከፍተኛ የፍትሕ መጓደል ሆኖ ሲገኝ ሊታረም እንደሚገባው አክለዋል፡፡ ሌላው አቶ ዓሊ የተቃወሙት ሐሳብ በአምስት ዳኞች የተሰጠ ፍርድ በዘጠኝ ዳኞች በፓናል መታየት አለበት የሚለውን ነው፡፡ ፍርድ አንዱ ዘንድ ማብቃት ስላለበት ማብቃት አለበት ብለዋል፡፡ አሜሪካኖችም ያን ያህል የበቁ አይደሉም ያሉት አቶ ዓሊ፣ በአንድ ወቅት ‹‹ጥቁሮችና ነጮች እኩል መማር የለባቸውም›› ብለው በመፍረድ፣ ፍርድ አንድ ቦታ እንዲያልቅ ማድረጋቸውን በመጠቆም በዘጠኝ ዳኞች በፓናል ይታይ የሚለውን አልተስማሙበትም፡፡

የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጎችን በመጥቀስ ሆነ ብለው ክርክር የሚያጓትቱ እንዳሉ ጠቁመው፣ ወደ ይግባኝ ሲመጣ ውሳኔ ማጓተቻ በማይሆንበት መንገድ የሚታይበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚሻልም ጠቁመዋል፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሦስት ዳኞች ችሎት የማጣራት ሒደት እንዲቀር በረቂቁ የቀረበን ሐሳብ አቶ ዓሊ ተቃውመዋል፡፡ በአሜሪካም ጉዳዩን ያስቀርባል? ወይም አያስቀርብም? ለማለት አራት ለአምስት ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ጠቁመው፣ የጀርመኖችን የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አሠራር ለመከተል ከመሞከር፣ ችሎቶችን በማስፋት ጉዳዮችን እያጣሩ መሥራቱ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል የመጀመርያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የየራሳቸው ሥልጣን ስላላቸው አገሪቱ ከተቀበለቻቸውና የሕጓ አካል ካደረገቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንፃር ቢሠራ ጥሩ መሆኑን አሳስበው፣ የፍርድ ቤት ክርክሮች ሁሉ ከመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይጀምሩ ማለት ተገቢ እንዳልሆነና እንደ ሙስና፣ አሸባሪነትና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚጠይቁትን ልምድና ችሎታም እያሰቡ መሥራቱ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

ሌላው አቶ ታፈሰ የታባሉ ጠበቃ በሰጡት አስተያየት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 (2) ድንጋጌ መሠረት የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በሁሉም ክልሎች እንደሚቋቋሙ መደንገጉን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ላለፉት 28 ዓመታት ጥቂቶች ብቻ በውክልና ሲሠሩ ከመታየታቸው ውጪ፣ በየትኛውም ክልል ለምን እንዳልተቋቋሙና እንደማይቋቋም ጠይቀዋል፡፡ ውሳኔ መስጠቱን ያወቀ ፍርድ ቤት በራሱ ዕርማት ይሰጣል በሚል በረቂቁ የተካተተው መታረም እንዳለበት ጠቁመው፣ ያ የማይሆን ከሆነ ለብልሹ አሠራርና ለሙስና የተጋለጠ ከመሆኑም በተጨማሪ ሁሉም ይታረምልኝ በማለት ሌላ ጫና ሊያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ጠቁመዋል፡፡ መርህ ተጥሶ ሥራ ስለማይሠራ፣ አንድ መታረም ያለበትና የተሳሳተ ውሳኔ በሥነ ሥርዓት ሕጎቹ መሠረት ሊታረም እንደሚችልም አክለዋል፡፡

ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶችን መዝገቦ እያጨናነቋቸው የሚገኙ የይግባኝ መሥፈርቶች አለመኖራቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቀንዓ የተባሉ ዳኛ፣ ክርክሮች በየደረጃቸው የሚያልፉትን የክርክር ሒደት እንደ አዲስ ከመጀመር፣ ለይግባኝ ብቻ የሚያስፈልጉ ነጥቦችን ለይቶ ማቅረብና ማየት የሚቻልበት ድንጋጌ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡ ይግባኝ የሚባልባቸው ጉዳዮች ሥልጣን በተሰጠው የዳኝነት አካል የተፈጸሙ ጉዳዮች (የግልግል ዳኝነትን ጨምሮ) መሆን እንዳባቸውም ገልጸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 (1) ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፍትሕ ከገንዘብ ጋር መወዳደር ወይም ገንዘብን መሠረት ማድረግ እንደሌለበት፣ በዋናነት ከመብት አኳያ መታየት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡   

ከይግባኝ ጋር በተያያዘ በርካታ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹‹አያስቀርብም›› የሚል አጭር ፎርም ተዘጋጅቶ ያ እየተሞላ መሰጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ አቤት ባይ ለምን እንደማያስቀርብ እንኳን ማብራሪያ ባልተሰጠበት ሁኔታ ፍርድ ቤቶችን ገለልተኛ ናቸው ለማለት እንደማያስደፍርም ጠቁመዋል፡፡ በሦስት ዳኞች ‹‹ያስቀርባል›› የተባለን ጉዳይ፣ አምስት ዳኞች ያስቀርባል ከተባለበት ጭብጥ ወጥተው የሚሰጡትን ውሳኔ በተመለከተ፣ ሦስት ዳኞች አያስቀርብም በማለት ከእነ ነፍሱ የሚቀብሩት ጉዳይ ምን ያህል እንደሆነ መገመት እንደማያዳግት በመጠቆም፣ የማጣራት ሥራው በአምስት ዳኞች እንዲሆን ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡  

ሕግ በባህሪው ውስብስብ ስለሆነ ሦስት ዳኞች ሲሰየሙ ሦስት መዝገብ ቢዘጋጅላቸውና በየግል መርምረው በውይይት አንድ የጋራ ውሳኔ ላይ ቢደርሱ የተሻለ ፍትሕ ስለሚሰጥ፣ ከመጀመርያ ደረጃ ጀምሮ ጉዳዮች በሦስት ዳኞች እንዲታዩ ሐሳብ ያቀረቡም ነበሩ፡፡

በዳኞች ላይ መሥራት የተሻለ ፍትሕ ለማግኘት ዓይነተኛ አማራጭ መሆኑንም የሕግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 25/88 በአዲስ አዋጅ መተካቱ አግባብ መሆኑን በመደገፍ አስተያየት የሰጡት ደግሞ የሕግ ባለሙያው አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁ ናቸው፡፡ አቶ ታምሩ እንደተናገሩት፣ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አካሄድን የሚከተል መሆኑን አልወደዱትም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሰበር ሰሚ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የተጀመረው ከ1900 ዓ.ም. በፊት በኢትዮጵያ መሆኑ ነው፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ የፍርድ ቤቶች አወቃቀር መሠረቱ አሜሪካ መሆኑን ያወሱት አቶ ታምሩ፣ የፍርድ ቤቶቹን አወቃቀር እንደ ኢትዮጵያ የገለበጠ ማንም እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ የአሜሪካን መመሳሰል በማየት ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ መገልበጥ ተገቢ ባለመሆኑ መጠንቀቅም አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡

ነገር ግን የአሜሪካኖቹን እንውሰድ ከተባለ መወሰድ የሚገባው አንድ ትልቅ ቁም ነገር፣ እነሱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚቀጥሯቸው የሕግ ኤክስፐርቶች ዓይነት ለኢትዮጵያ ዳኞችም ሊመደቡላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳኞች የሚመረምሩት፣ ፍርዱን የሚጽፉት፣ ሁሉንም ነገር የሚያደርጉት ራሳቸው በመሆናቸው በዕውቀትና በልምድ ከእነሱ ያላነሰ ቋሚ ተመራማሪ ሊመደብላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ዝም ተብሎ የሕግ ረቂቁን ብቻ እንደ አሜሪካ አድርጎ አሠራሩን ሌላ ማድረግ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችልም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ‹ሲቪል ሎው› ሥርዓት ተከታይ ብትሆንም፣ የዳኝነት አፈጻጸሙ ወይም ትርጉምን በተመለከተ የ‹ኮመን ሎው› ሥርዓትን የሚጋራ ሥርዓት እንደሆነ አቶ ታምሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ቀድሞ የተፈጸመ ክስተት ውሳኔ (Precedent) እንደ ምሳሌ የምንወስድ ስለነበርን፣ ወደ ሰበር የሚመጣን ጉዳይ የሚገድብ መሠረት መፍጠር አልቻልንም፤›› ብለዋል፡፡

መሠረታዊ የሕግ ስህተት ለሚለው በረቂቁ የተሰጠው ትርጉም ከሕገ መንግሥቱ አንፃር ስላልተቃኘ እንደሚጋጭ አስተያየታቸውን የሰጡት ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመጡ ባለሙያ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሚለው በረቂቅ ደረጃ ላይ ባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ውስጥ የተካተተ በመሆኑ ከዚያ አንፃርም ቢታይ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ በመመርያው ወደ ሰበር ይግባኝ እንዳይገቡ መታገድ ስላለባቸው ጉዳዮች በረቂቁ መቀመጡን ባለሙያው ገልጸው፣ በሕገ መንግሥቱ ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ድንጋጌ የሚጣረስ ስለሚሆን ቢታረም ጥሩ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሰበር የሚሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ክልሎችም እንደሚገዙበት መደንገጉ ተገቢ አለመሆኑን፣ በተለይ ፍትሐ ብሔርን በሚመለከት ክልሎች ሕግ ያወጣሉ ተብሎ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ስለሚጣረስ እንዲታሰብበት አስተያየታቸውን አካፍለዋል፡፡

አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም የተባሉ ጠበቃ በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት፣ ከ1988 ዓ.ም. በፊት አዲስ አበባ በ25 ከፍተኛ የተከፋፈለች ነበረች፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ የራሱ ፍርድ ቤት ነበረው፡፡ የዳኞችም ሥልጣን በቦታ የተከፋፈለና የተሳለጠ ነበር፡፡ ከ1988 ዓ.ም. ወዲህ ግን ፍርድ ቤቶች በአራት መከፈላቸውን፣ ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ዳኞች ተባረው የዳኛ እጥረት በመፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዳኛን ስትሾመው የቦታውን ሥልጣንና ወሰን ለይተህ ስጠው›› የሚለውን አባባል መከተል የሚጠቅም ቢሆንም፣ ከመጨናነቁ አንፃር ለብልሹ አሠራር በር ስለሚከፍት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ አደረጃጀትን ተከትሎ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች መቋቋም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ሌላው አቶ ታምራት ያነሱት ለሰበር ችሎት ስለሚከፈል ዳኝነት ነው፡፡ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ማረም ሲገባ ያለ ሕግ በቢሮ ውስጥ መመርያ ክፍያ ማስከፈል ተገቢ ባለመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ፍርዱ የሕግ ስህተት ባይኖረው እንኳን ተከራካሪው በጠበቃ የመወከል መብቱ ከታለፈ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት በመሆኑ ይኼንን ማረም በክፍያ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡ ወደ ቀጣይ የሕግ አካል ቢኬድ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አገርን ሊያስቀጣ እንደሚችልም አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በርካታ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን በጥልቀትና በስፋት ሰጥተው፣ ለቀጣይ ሁለተኛ ዙር ውይይት ቀጠሮ በመያዝ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -