Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ የተንቀሳቀሰበት የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ገንዘብ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታዩት ችግሮችና የአገልግሎት አማራጮች ውሱንነት ለዓመታት ሲነገርለት ቆይቷል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችም ይህን የሚተቹና የሚሞግቱ አስተያየቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለማሻሻል፣ ተደራሽነቱንም ለማስፋት የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች ቢኖሩም፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቆይተዋል፡፡

 የኅብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት አለመቻል ብቻም ሳይሆን፣ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ማበርከት የሚችለውን አስተዋጽኦ እንደገደበውም ምሁራኑ ያምናሉ፡፡ ኢንዱስትሪውን የሚመራው አካልም፣ ዘርፉን ይበልጥ የሚያሳድጉ አሠራሮች እንዲተገበሩ በሚያስችለው ደረጃ አለመደራጀቱም ተፅዕኖ ነበረው፡፡

በኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ ቀደም ብለው ሊተገበሩ ይችሉ እንደነበሩ ከሚታመኑ አገልግሎቶች ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ይጠቀሳል፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥ በተለያየ መጠሪያ የያዘው ይህ ዘርፍ፣ በአብዛኛው እስላማዊ የባንክ አገልግሎት ‹‹ኢስላሚክ ባንኪንግ›› በሚለው መጠሪያው በስፋት ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሚል ስያሜ አገልግሎቱ በባንኮች በመስኮት ደረጃ እየቀረበ ይገኛል፡፡

ይህ አገልግሎት በኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ በፊት መጀመር ነበረበት የሚሉ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ በሃይማኖታቸው ምክንያት መደበኛውን የባንክ አገልግሎት መጠቀም ያልቻሉ ዜጎችን ለማገልገል ያስችላል ከሚል መነሻ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አማራጭ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወደ ባንክ ባለመምጣቱ ሳቢያ፣ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል ሰፊ የገንዘብ ሀብት በየሰው ቤት እንዲቀመጥ አስገድዷል፡፡

የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ተንተርሶ እሑድ፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ዳሸን ባንክ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሊያበረክት የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ጠቀም ያለ መሆኑ ነው፡፡

ዳሸን ባንክ ወለድ አልባ አገልግሎትን በአግባቡ ለማቅረብ ይቻለው ዘንድ ያዋቀረው የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኡዝታዝ መሐሙድ ሐሰን  እንደሚገልጹት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እስካሁን ከተተገበረበት ጊዜ ቀደም ብሎ ቢተገበር ኖሮ ጠቀሜታው ሰፊ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ‹‹የፖለቲካ ሰዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አግላይ ሥራ በመሥራታቸው በርካታ ሙስሊሞች ገንዘባቸውን ቤታቸው እንዲያስቀምጡ አስገድዷቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

እምነቱ ወይም ሃይማኖቱ በሚፈቅዳቸው ሕግጋት መሠረት አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ስላልነበር ሕዝበ ሙስሊሙ ገንዘቡን በባንክ ማስቀመጥ አልቻለም፡፡ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት የማይጠቀሙት ከወለድ ጋር ላለመነካካት ሲሉ እንደሆነ የጠቀሱት ኡዝታዝ መሐሙድ፣ ሙስሊሞች ገንዘባቸውን ወደ ባንክ ይዘው አለምጣታቸው ደግሞ አገሪቷንም ይጎዳል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ አገልግሎት መጀመሩ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የወለድ አልባ አገልግሎት ሃይማኖታዊ መርሆ ቢኖረውም፣ የየትኛውም እምነት ተከታይ የሚጠቀምበት እንደ አንድ የባንክ አገልግሎት በአማራጭነት በመቅረብ ሕጋዊ የገንዘብ እንቅስቃሴን የሚደግፍ አቅም እንዳለው ይታመንበታል፡፡

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማስጀመር ከዓመታት በፊት የተጀመረው እንቅስቃሴ ውዝግብ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ለአገልግሎቱ ራሱን የቻለ አማራጭ ባንክ ለማቋቋም የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ ዘምዘም በሚል መጠሪያ ሊቋቋም የነበረው ባንክ ባይቋቋምም፣ ባንኮች አገልግሎቱን እንዲሰጡ የሚያስችላቸው ሕግ ወጥቶላቸዋል፡፡ ይህንኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድንጋጌን ተከትሎም በአሁኑ ወቅት 14 ባንኮች ወልድ አልባ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡  ባንኮቹ አገልግሎቱን መጀመራቸው እያሰገኘ ያለውንና ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ በመገንዘብም አንዱ መወዳደሪያቸው አድርገውታል፡፡  

መረጃዎች እንደሚጠቅሱት በወለድ አልባ አገልግሎት ሳቢያ ባንኮች 30 ቢሊዮን ብር ያህል ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ ከጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ በወለድ አልባ አገልግሎት ማሰባሰብ የቻለው ከሦስት በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አገልግሎቱን የሚሰጡ ባንኮች መበራከታቸውን ተከትሎ፣ በዚህ ዘርፍ የሚሰበሰበው ገንዘብ እያደገ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ በማግኘት አሥረኛው ዳሸን ባንክ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባስመዘገበው ውጤት ሳቢያ አገልግሎቱን ለማስፋፋት እንቅስቃሴዎች ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለያዩ  የክልል ከተሞች፣ ሰሞኑንም በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል የተዘጋጀው መድረክም አገልግሎቱን ይበልጥ የማስፋት ዕቅዱን ያሳየበት ነበር፡፡

ዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን ለመጀመር ቢዘገይም ምክንያት እንደነበረው ገልጿል፡፡ የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት፣ ባንኩ አገልግሎቱን ከማስጀመር የዘገየው፣ አሠራሩ እንደሌሎቹ የባንክ አገልግሎቶች የንግድ ግብይትን ብቻ ሳይሆን፣ የሸሪዓ መርሆዎችን፣ ዕሴቶችንና ሕግጋትን ከመጠበቅ አኳያ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ወለድ አልባ አገልግሎቱ የሸሪዓ ዕሴቶችን ሳያጓድል እየተከናወነ ስለመሆኑ የሚከታተል፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት፣ ዕውቅናና አመኔታን ያተረፉ፣ በዘርፉ በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ሥራ እንደገባ  በውይይት መድረኩ ተብራርቷል፡፡ በመድረኩ የሸሪዓ ኮሚቴ አባላቱ ከሕዝቡ ጋር ደርሷል፡፡

ስለአገልግሎቱ አቶ አስፋው እንደጠቀሱትም በአንድ ዓመት ወስጥ ብቻ 54 ሺሕ ተጠቃሚዎች ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ሒሳብ ከፍተው የቁጠባ ገንዘብ ማስቀመጥ የቻሉ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ የተሰበሰበው ገንዘብ አንድ ቢሊዮን ብር እንደደረሰም አስታውሰዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ባንኩ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በተጠቃሚዎች ዘንድ ተዓማኒነትን ለማግኘትና አሠራሩም የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ እንዲሄድ ለማስቻል ከባንኩ ውጪ ያለ አደረጃጀት በመዘርጋት እየሠራበት ይገኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከባንኩ ቦርድ እኩል ሥልጣን ያለው የሸሪዓ ኮሚቴ አቋቁሞ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱም በኮሚቴው አባላት እንዲመራና ውሳኔ እንዲሰጥበት እያደረገ እንደሚገኝ ለዋቢነት ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ የሚያመረቃ ውጤት እንዳስመዘገበ አስታውቋል፡፡ ለመላው የንግድ ማኅበረሰብ የሥራ ማስኬጃና የኢንቨስትመንት የፋይናንስ ጥያቄዎችን የማስተናገድ ሥራዎችንም ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ለማስኬድ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የባንኩ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በዳሸን ባንክ፣ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ቺፍ ኦፊሰር አቶ መስፍን በዙ ይማም፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ፋይናንስ ለማድረግ፣ ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጥ፣ የትኛው ይስተናገድ የሚለውን የመለየት ሥራ በማጠናቀቅ ፋይናንስ ማቅረብ ይጀመራል ብለዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ወለድ መክፈልም ሆነ መቀበል የማይፈልጉ ደንበኞችንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ አማራጭ አገልግሎቶችንም አካቷል፡፡ በተወሰኑ አገልግሎቶች ላይ የሚተገበረው ይህ ሥርዓት፣ ወደፊት ሌሎች ከዘርፉ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ አገልግሎቶችም ያካትታል ተብሏል፡፡

አገልግሎቱ በሸሪዓ አግባብ በተፈቀዱና ሀላል የንግድ ሥራ ዘርፎች ላይ ብቻ የሚተገበር በመሆኑ፣ ከመደበኛው የባንክ አሠራር ጋር ያልተቀየጠ፣ የራሱን የአሠራር ሥርዓት እንደሚከተል ተገልጿል፡፡ በወለድ አልባ አገልግሎት የሚንቀሳቀስ ገንዘብ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ጋር አይቀየጥም፡፡ አገልግሎቱ ተለይተው በተዘጋጁ መስኮቶች እንደሚሰጥ ከቀረቡ ማብራሪያዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ ገንዘቡ የሚንቀሳቀስበት መንገድም ብድር ከማቅረብ ጋር የተለየ ነው፡፡ ኡዝታዝ መሐመድ እንዳመለከቱት፣ በዚህ አገልግሎት አማካይነት ገንዘብ በባንክ ሲቀመጥና የተሰበሰበው ገንዘብም ሥራ ላይ እንዲውል በብድር ሲሰጥ፣ የሥራ ዘርፎቹ ተመርጠውና ተመርምረው ነው፡፡ ለምሳሌ የመጠጥ ፋብሪካ በዚህ ተቀማጭ ገንዘብ አማካይነት ልክፈት ቢባል አይፈቀድም፡፡ ለአሳማ ንግድ ሥራም አይፈቀድም፡፡ መጠጥ የሚሸጡ ሆቴሎችም ከዚህ አገልግሎት ፋይናንስ አያገኙም፡፡ ገንዘብ ሲቀመጥም ሆነ ለብድር ሲውል ከዚህ የፀዳ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡

ኡዝታዝ መሐመድ እንደገለጹት፣ በመስኮት ብቻ እየተሰጠ ያለው ወለድ አልባ አገልግሎት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለውጥ እያሳየ መጥቷል፡፡ ንግድ ባንክ ብቻውን ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስጠት 20 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ኡዝታዝ መሐመድ፣ ይህም የሚያመክተው አገልግሎቱ ወደፊት በመስኮት ብቻ እንደማይወሰን ነው፡፡ ወደ አማራጭ ባንክነት ደረጃ ለመሸጋገር ወደሚያስችለው ዕድገት እያመራ ነው ብለዋል፡፡ አገላለጹ ብድር ሳይሆን፣ ባንኩ ለሚያምናቸውና ትክክለኛውን አካሄድ ለሚከተሉ ባለሀብቶችና ኢንቨስትመንቶች ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በማቅረብ ከትርፉ የሚገኘውን ትርፍ መስጠት ነው፡፡

‹‹በእስላማዊ ባንክ መሠረት፣ ባንኮች ብድር የሚሰጡበት አሠራር የለም፡፡ ባንኩ ለሚሰበስበው ገንዘብ ብዙ ወጪ አለበት፡፡ የግድ ማትረፍ ስላለበት፣ ፕሮጀክትን አጥንተን ስናመጣ ባንኩ ዓይቶ እንደሚያዋጣው ሲያምንበት ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ገዝቶ ይሸጣል እንጂ ገንዘብ በብድር አይሰጥበትም፤›› ብለዋል፡፡

እርግጥ ባንኩ ለታማኝ ደንበኞቹ ገንዘብ ሊሰጥ የሚችልበት ክፍል ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፣ እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነ ደንበኛ ለወጪ ንግድ የሚያውለው ገንዘብ ቢፈልግ ባንኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚመልሰው ገንዘብ ሊሰጠው ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ይህንን ሲያደርግ ግን ወደ ውጭ ልከህ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ወደ እኔ ባንክ መግባት አለበት ካለውም ተቀባይነት የለውም፡፡ ወደ ውጭ የሚልከው አካል ብሩን እሰጥሃለሁ፣ ወለድ ግን አልፈልግም፡፡ የውጭ ምንዛሪውን ግን ትሰጠኛለህ ካለውም አይሆንም፡፡ ነገር ግን  ደንበኛው ከወጪ ንግድ የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለእናንተ ባንክ ሰጥቻለሁ ካለ ግን መብቱ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ኢስላሚክ ባንክ ይቅርና መደበኛው ባንክ ሥርዓትም ደካማ ነው፤›› ያሉት ኡዝታዝ መሐመድ፣ አንድ አገር በባንክ የሚመራ የፋይናንስ ሥርዓት ከሌለው የፈለገውን ያህል ገንዘብ ቢያገኝና ነዳጅ ቢወጣ ዋጋ የለውም ይላሉ፡፡ ‹‹ምክንያቱም ገንዘባችን የሚገባው ቀዳዳ በርሜል ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡››

ኢስላሚክ ባንኪንግ ለምን አስፈለገ በሚለው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡም፣ እስላማዊ የባንክ አገልግሎት በሀብታምና በድሃው መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ጭምር ስለሚረዳ ነው፡፡ ቢያንስ ልዩነቱ ከፍተኛ እንዳይሆን በማድረግ በኩል ጠቃሚ እንደሆነ አብራርተው፣ ማኅበራዊ ፍትሕን በማስፈን ረገድም ዓይነተኛ ሚና ስለሚጫወት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ይህ እንዲህ እንዳለ ዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ ሒሳብ ያላቸው ደንበኞቹን በሸሪዓ መርህ መሠረት በተለየ ለማገልገል እንዲያስችለው ያቀረባቸውን የሸሪክ፣ የአን ኒሳአ (የሴቶች) እና የሂባ (የስጦታ)፣ የኤሌክትሮኒክ ካርዶችንም አስመርቋል፡፡ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ፋይናንስ እንዲሁም በሸሪዓ መርሆዎች ዙሪያ በዘርፉ ምሁራን ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፣ ወለድ ሐራም ወይም ክልክል መሆኑን በተመለከተም ኡዝታዝ ሙስጠፋ ሐሚድ ያቀረቡት ጽሑፍም ተጠቃሽ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች