Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክና ፓርላማው የማያውቋቸው የውጭ ምንዛሪ ቋቶች?

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ መነጋገሪያ ሆነው የሰነበቱበትን ንግግር አሰምተው ነበር። ገዥው አገሪቱ ከመድኃኒትና ከነዳጅ በቀር ለሌላ ሸቀጥ ግዥ ሊውል የሚችል በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንደሌላትና ያለውም ቢሆን አሳሳቢ እንደሆነ አመላክተዋል።

ገዥው ይህንን በተናገሩ ጥቂት ቀናት ውስጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ብቻ 13 ቢሊዮን ዶላር ‹‹አግኝታለች›› አሉ። እርግጥ ይህ አኃዝ ሾላ በድፍኑ ቢሆንም አብዛኛው በብድርና በዕርዳታ ሊሰጥ ቃል የተገባውን ጨምሮ፣ ከውጭ ሐዋላ (የግልና የመንግሥት)፣ እጅጉን ከተዳከመው ወጪ ንግድ፣ ከአገልግሎት ወጪ ንግድ (በተለይም ከአየር ትራንስፖርት)፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ከመሳሰሉት ምንጮች የተገኘና ቃል የተገባ ገንዘብ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከ2.6 ወር በላይ የገቢ ንግድ መጠንን ለመድፈን እንደማይበቃ የብሔራዊ ባንክ ገዥው በመጋቢት ወር መጨረሻ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የስምንት ወራት ሪፖርት አመላክተዋል፡፡ በሪፖርታቸውም የአገሪቱ የምንዛሪ መጠን የሚገኝበትን ደረጃ ጠቅሰዋል፡፡ ምንም እንኳ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለሁለት ወራት ተኩል የገቢ ሸቀጦችን ለመግዛት የሚያበቃ እንደሆነ ቢጠቅሱም፣ በወራት ልዩነት ውስጥ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያስተጋቡት የተምታታ መልዕክት የምንዛሪ ገበያው ላይ ጡዘት እንደፈጠረ ነጋዴዎችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዶላር የባንክ ለባንክ ምንዛሪ ከ28 ብር በታች ቢሆንም፣ በጥቁር ገበያው ግን ከ40 ብር በላይ ደርሶ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማሳሰቢያ በተለይም ኢትዮጵያውያን የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በውጭ ያስቀመጡትን የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ቤት እንዲመልሱ አሳስበው ነበር፡፡ በዱባይና በቻይና ያስመጡችሁትን ዶላር አምጡ ለአገር እንሥራበት ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እንደውም በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ባለሥልጣናት፣ ኢትዮጵያ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ደካማ ከሚባሉ አገሮች ተርታ በመመደብ፣ በባንክ ማጭበርበር፣ በሳይበር ወንጀሎችና በስወራና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በኩል ‹‹ከፍተኛ ተጋላጭ›› ከሆኑ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያን እንዲያወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ኅብረቱ እንዲህ ያለው ተጋላጭነት ለድንበር ዘለል የሽብር ወንጀሎች መስፋፋት ጭምር አደጋ እንደሆነ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ደካማ በሆነችባቸው የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርና መሰል ችግሮች ሳቢያ ሪፖርት ቢያቀርብባትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ መንግሥታቸው እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና የወሰዳቸው ዕርምጃዎችም ፍሬ እያሳዩ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ለሽብር ተግባር ሊውል የሚችል ገንዘብ ከሚዘዋወርባቸው አገሮች ተርታ ስሟ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

 ለአብነትም የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እየሠሩበት እንደሚገኙ፣ መንግሥትም አጠራጣሪ የገንዘብ ምልልሶችና ልውውጦች ሲከናወኑም ይህንኑ ሪፖርት የሚያደርግበትን አቅም እየገነባና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር እያሳወቀ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣውን ሪፖርትና ኢትዮጵያን በሥጋት ከሚፈረጁ አገሮች ስም ዝርዝር ውስጥ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ በየቀኑ በፍተሻ ኬላው በተለያየ ዘዴ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ገንዘብና ከዚህ መካከል ተደርሶበት በቁጥጥር ሥር የሚውለው መጠን ሲታይ፣ ኢትዮጵያ በመንግሥት ከሚነገርላት ይልቅ የከበደ ጉድ ተሸክማ እንደምትገኝ ያሳያል፡፡ 

መንግሥት በሕገወጥ መንገድ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመከላከል ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ከመናገር ባሻገር፣ ኢትዮጵያውያን መንግሥትን እንዲያግዙ አገራቸውን እንዲያለሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው ጥሪዎች ሳቢያ፣ በጥቁር ገበያና በባንኮች የሚደረገው የዶላር ምንዛሪ ከብር አኳያ መሳ ለመሳ ለመመንዘር የሚደርስበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ፍንጮች ታይተው ነበር፡፡ እንደውም ብዙ ዶላር ከውጭ እየገባ ስለሆነ፣ በእጃችሁ ዶላር አከማችታችሁ የያዛችሁ ወደ ባንክ አስገቡ የሚል መመርያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰጥተው ነበር፡፡ እንደውም ባንኮች ያለ ሕጋዊ ጥያቄ ማንኛውም ሰው ወደ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሲያመጣ እንዲቀበሉ በማለታቸው ጭምር በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ ስለመግባቱ ሲዘገብ ሰንብቶ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል በጥቁር ገበያው በኩል ወደ ሰማይ ተወንጭፎ የከረመው የምንዛሪ ዋጋ በሚገርም ፍጥነት አሽቆልቁሎ አንድ ዶላር በ30 ብር ድረስ የተመነዘረበት ወቅት ተከስቶ ነበር፡፡ ግን ብዙም ሳይዘልቅ በወረት ቀረ፡፡ ይባስ ብሎ አሁን ላይ አጣዳፊና አሳሳቢ ለሚባሉት ሸቀጦች ግዥ ካልሆነበ በቀር ዶላር የለም የሚለው የመንግሥት መርዶ መደመጡ ግራ አጋብቷል፡፡

ከዓመት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ አብዛኞቹ የግል ባንኮች ለደንበኞቻቸው የውጭ ጉዞና የሕክምና ወጪዎችን መሸፈኛ የሚውል የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በቂም ባይሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚታየው በተሻለ ደረጃ ያስተናግዱ ነበር፡፡ ይህም ማለት ቅድሚያ ይሰጣቸው ተብለው በመንግሥት ከተለዩት የመድኃኒት፣ የማኑፋክቸሪንግና መሰል ዘርፎች ባሻገር ያለውን ጥያቄ በሚያስተናግዱበት አግባብ የሚታየው ነው፡፡

ለአብነት ተራ የንግድ ባንክ ደንበኞች ለውጭ ጉዞ የሚጠየቁትን ሰነድ አሟልተው በቀረቡ ጊዜ ከ500 ዶላር ያላነሰ ግዥ መፈጸም ይችሉ ነበር፡፡ ይህ መጠን ግን በአሁኑ ወቅት ወደ 200 ዶላር ዝቅ ተደርጓል፡፡ አስመጪዎች የሆኑ እንደሆነ ግን ከብሔራዊ ባንክ የሚጠበቅባቸውን መስፈርትና ግዴታ አሟልተው በመቅረብ ጭምር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መስኮች ውጭ ለሆኑ ገቢ ዕቃዎች መግዣ የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በኮታና በወረፋ እየተስተናገደ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ እርግጥ በአንድ ወቅት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በፈጠረላቸው አጋጣሚ ሳቢያ በርካታ ባንኮች ውስጥ የተንሰራፋው ማጭበርበርና የውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎችን የመጠበቂያ ቅደም ተከተል በማባዛትና አንዱን ዶላር እስከ ስምንት ብር በመሸጥ ሲፈጥሩ የነበረው ትርምስ የቅርብ ጊዜ ትውስት ነው፡፡ አሁንም ድረስ ግን ይህ አድራጎት ሙሉ ለሙሉ ስለመቀረፉ አስረጅ ማግኘት አይቻልም፡፡

ዜጎቿ ለሕክምናም ሆነ አስፈላጊ ለሆናቸው ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የማይወጡት አቀበት በሆነባት፣ በህቡ ከፍተኛ የምንዛሪ ሥራ የሚሠሩና ከፍተኛ የዶላር ክምችት ያላቸው ጥቂቶች የሚዘውሩት መስክ እየሆነ እንደመጣ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉ የሚገልጹት ነው፡፡ እንደውም በዚህ ሰንሰለት ውስጥ እጃቸውን ያረዘሙት ጥቂት አስመጪ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ ጠቀም ያሉ ባለሥልጣናት ጭምር እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ለዚህ ማስረጃቸው ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ምንጮቿ ከሆኑት ከውጭ ብድርና ዕርዳታ፣ ከወጪ ንግድ፣ ከሐዋላ እንዲሁም ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትና ከመሳሰሉት የምታሰባስበው የውጭ ምንዛሪ በሰፊው ግዥ ሲፈጸምበት የሚታየው ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ፣ ለመድኃኒትና ለሌላው ቢሆንም፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ መጠን ግን ወደ ውጭ እየወጣ ያለው ወይም ወጥቷል ተብሎ እየተገለጸ የሚገኘው ገንዘብ ለግዥ ከሚውለው በላይ መሆኑን በማመላከት መንግሥት ተገቢውን ሥራ እንዲሠራና ሕዝብም እውነታውን እንዲያውቀው እንዲያደርግ አስተያየት ሰጪዎቹ ይጠይቃሉ፡፡

እንደ ብሔራዊ ባንክ ገዥው ሪፖርት፣ በዚህ ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ለገቢ ሸቀጦች ግዥ ያዋለችው የውጭ ምንዛሪ መጠን 10.5 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡  ከዚህ ውስጥ ለነዳጅ የዋለው ግዥ በምሳሌነት በባንኩ ገዥ ተጠቅሷል፡፡ 1.73 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የነዳጅ ግዥ ዓመታዊ የወጪ ዕድገቱ ከ20 በመቶ በላይ መጨመሩም ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በስምንት ወራት ውስጥ ለነዳጅ ግዥ የወጣውን ጨምሮ፣ ለማዳበሪያና ለመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ለሚውሉ ዕቃዎችን ለመግዛት 3.2 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንክ በኩል እንደተሰጠ በሪፖርት ቀርቧል፡፡ 

በስምንት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 1.64 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ከግል ሐዋላ (ከግለሰቦችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች) የተሰበሰበው የተጣራ ገቢም 3.82 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር በሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከተጣራ መንግሥታዊ የውጭ ሐዋላ 837 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተሰብስቧል፡፡ በጠቅላላው በሸቀጦች ወጪ ንግድና ገቢ ንግድ መካከል በስምንት ወራት ውስጥ የታየው የንግድ ሚዛን ጉድለት 8.9 ቢሊዮን ዶላር እንዳስመዘገበ፣ ዓምና ከነበረው 8.6 ቢሊዮን ዶላር አንፃርም የዘንድሮው ጉድለት ከፍ ማለቱን ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ገልጸው፣ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ያባባሰው ደካማው የወጪ ንግድ ገቢ ሊሸፍን የቻለው 15.6 በመቶውን የገቢ ንግድ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡ በመሆኑም ቀሪውን የገቢ ንግድ ለመሸፈን የአገልግሎት ገቢ፣ የሐዋላ፣ የውጭ ዕርዳታ ብድር፣ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የገቢ ምንጮች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባደረጉት ንግግር፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት 15 ዓመታትም ላይበቃ እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱን የወጪ ንግድ በማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች በማገዝ በቂ ገቢ ያስገኛሉ የተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በየአካባቢው እየተገነቡና ሥራ እየጀመሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ውስብስብ ያልሆነ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማዕከል ለማድረግ ያስችላሉ የተባሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በእስካሁኑ ቆይታቸው ያስገኙት ገቢ ግን የወደፊታቸውንም በሥጋት ለመመልከት የሚያስገድድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቦሌ ለሚን ጨምሮ፣ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ መቐለና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎችም ሥራ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ቀዳሚዎቹ ቦሌ ለሚና ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክንና ጠቅላላ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከቆዳና ከቆዳ ውጤቶች የወጪ ንግድ ጋር ተዳምረው ያስገኙት የውጭ ምንዛሪ ከ300 ሚሊዮን ዶላር አልበለጠም፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ከዘርፎቹ ሲገኝ ከነበረውም ያነሰ በመሆኑ ዘርፉንና የዘርፉን ተዋንያን ምን እየሠሩ ነው የሚያሰኙ ጥያቄዎችን ከወዲሁ ማጫሩ አልቀረም፡፡

በቴሌቪዥን መስኮቶችና በየጋዜጣው የሚወጡ የነጋዴዎችና የምሁራን ድምጾች መንግሥትን ጥያቄ ውስጥ ጥለዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው የተባሉ ነጋዴ፣ የብሔራዊ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለመድኃኒትና ለነዳጅ ብሎም ዋና ዋና ለሚባሉ ሸቀጦች ግዥ የሚውል መጠን ካልሆነ በቀር የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት አሳሳቢ እንደሆነ መናገራቸው፣ ይብሱን የጎነውን የጥቁር ገበያ ዋጋ እንዳባባሰው ከናሁ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ጠቅሰዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ግራ ቀኞች የታዩበትና የምንዛሪ መዋዠቅ የታየበት የአዲሱ መንግሥት አዲሱ ዓመት፣ በዓለም ባንክም ሆነ በዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዕይታም ቢሆን ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሕመሞቹ ያልጠገጉለት፣ ከቁስለት ያልሻረ ኢኮኖሚ ሆኖ እንዳገኙት በሪፖርቶቻቸው አመላክተዋል፡፡  

መንግሥት የውጭ ምንዛሪው እጥረት እንዲቀንስ ለማስቻልና የወጪ ንግድ እንዲበረታታ ለማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት የብርን የመግዛት አቅም ከዶላር አኳያ በ15 በመቶ ዝቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህንን የጠቀሰው የዓለም ባንክ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ማሳያ ሪፖርት፣ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ብሔራዊ ባንኩ የብር የመግዛት አቅም ከኢኮኖሚው መቀዛቀዝ አኳያም ጭምር እስከ ሦስት በመቶ ገደማ እንዲቀንስ (ዲፕሪሺዬት) ፈቅዷል፡፡ በመሆኑም የብር የመግዛት አቅም በኢኮኖሚው መዳከምና በመንግሥት ጣልቃ መግባት ሳቢያ የመግዛት አቅሙ በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ በድምሩ በ18 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም የተፈለገው የውጭ ምንዛሪ መጠን እየገባ አይደለም፡፡ ገብቶም ከሆነ ደግሞ አወጣጡ በብዙ አሻሚና አጠራጣሪ መንገዶች በሕጋዊም በሕገወጥ መንገድም ባህር እየተሻገረ እንደሚገኝ የብዙኃኑ ምልከታና የመንግሥትም ሐሳብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር በተለይም በሕገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚካሄድበትና በጥቁር ገበያው እንዳሻው ሲያሻቅብ፣ የውጭ ምንዛሪው ተዋንያን ጥቂቶች እንደሆኑ፣ የአገሪቱ የዶላር ባንክ ሒሳብ፣ የዳያስፖራ ሒሳብ ወይም አካውንት ያላቸው ጥቂቶች የሚጫወቱትን ቁማር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት አያውቁም ማለቱ የማይመስል አመክንዮ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች