Wednesday, July 24, 2024

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የፖለቲካ ተመራማሪ ጋር እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ባለሀብት ስልክ ይደውላሉ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንኳን አደረሰህ፡፡
 • ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • በዓል እየደረሰ አይደል እንዴ?
 • አሁን እኮ ምንም በዓል በዓል አይልም፡፡
 • እንዴ ለምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሉም ነገር ተቀዛቅዟል እኮ፡፡
 • እሱማ ፆሙ ሲፈታ ሁሉም ነገር ይሟሟቃል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከለውጡ በኋላ እኮ ፆምና ፍስኩ አይለይም፡፡
 • ምን?
 • በቃ ምንም እንቅስቃሴ ስለሌለ ፍስኩ ራሱ ፆም ነው የሚመስለው፡፡
 • ለነገሩ ሰምቼ ነበር፡፡
 • ምንድነው የሰሙት?
 • የለውጡ ደጋፊ ሳትሆን አደናቃፊ እንደሆንክ ነዋ፡፡
 • እኔማ የለውጡ ቀንደኛ ደጋፊ ነበርኩ፡፡
 • ብትሆንማ ኖሮ እንደዚህ አትልም፡፡
 • እንዲህ ያስባለኝ እውነታው ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በፊት ለበዓል ምን እንደምታደርግ ሰምቻለሁ፡፡
 • ምን አደርግ ነበር?
 • በዓል በደረሰ ቁጥር አይሱዙ ሙሉ በግ ነበር የምትገዛው አሉ፡፡
 • በደህናው ጊዜ ነበራ፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር እንዳሉት በፊት በዓል ሲደርስ ለሁሉም ሚኒስትሮች እኔ ነበርኩ ሙክት የምሰጣቸው፡፡
 • መቼም ከለውጡ በኋላ በሬ ነው የምታድለው ብዬ ልጠብቅ?
 • ወደው አይስቁ አሉ፡፡
 • እንዴት?
 • አሁንማ ለእኔ ራሱ የሚገዛልኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • አየህ ለዚህ ነው የለውጡ አደናቃፊ ነህ ያልኩህ፡፡
 • ምን አደረኩ?
 • ከለውጡ በፊት ለሚኒስትሮች በግል የምታድል ከነበረ አሁንማ በሬ ነበር ማደል የነበረብህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ኢኮኖሚው በወሬ ነው እንጂ የበሬ የሆነው፣ እውነታው ከበግም አንሶ የዶሮና የእንቁላል ላይ ደርሷል፡፡
 • አንተ እውነትም የለየለት ተቃዋሚ ሆነሃል፡፡
 • መቼም እውነት ሲነገራችሁ አትወዱም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዲህ ስላልከኝ ይተወኛል ብለህ አስበህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡
 • ምኑን ነው የሚተውኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • የበዓል ድርሻዬን ነዋ፡፡
 • የምን የበዓል ድርሻ?
 • ስማ እኔ ሕዝብ እያገለገልኩ እናንተ እኔን ካላገለገላችሁ መኖር አንችልም፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለበዓል ሙክት ላክልኝ፡፡
 • የባሰው መጣ፡፡
 • ምነው?
 • ጭራሽ አፍ አውጥተው ይጠይቃሉ?
 • ምን አለበት?
 • የበፊተኞቹ ቢያንስ አንቀሳቅሰውን ነበር የሚጠይቁት፡፡
 • እ. . .
 • ስለዚህ ሥራ ሳንሠራ ለእናንተ ስጦታ ከየት ይመጣል?
 • ሙክት አልክም እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ምን ነካዎት?
 • ምነው?
 • ባለፈው የአምስት ሚሊዮን ብር እራት ካልገባህ አሉኝ፡፡
 • ምን አለበት ታዲያ?
 • ክቡር ሚኒስትር አገር በልመና አይተዳደርም፡፡
 • እ. . .
 • አሁን ደግሞ ማስፈራራት ጀመራችሁ፡፡
 • ለማንኛውም እኔ የማደርገውን አውቃለሁ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • አስወርሰዋለሁ፡፡
 • ምኑን?
 • ድርጅትህን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ባለሀብት ስልክ ይደውልላቸዋል]

 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • አሞኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን እኮ ሁሉም ታሟል፡፡
 • አመመዎት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው አገር ታሟል ብዬ ነው፡፡
 • ለነገሩ አሁን ማን ጤነኛ አለ ብለው ነው?
 • ምን ሆንክ ግን?
 • ስኳርና ደም ግፊት ተባብረው ሊደፉኝ ነው፡፡
 • ሆስፒታል አልሄድክም ታዲያ?
 • መታከሚያ ከየት አምጥቼ ክቡር ሚኒስትር?
 • እየቀለድክ ነው?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁሉም ሰው ችግር ነው እንዴ የሚያወራው?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ትንሽ የሚታመን ወሬ ብታወራ ምናለበት?
 • ምን አወራሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተን የመሰለ ባለሀብት መታከሚያ አጣሁ ሲል ታዲያ እንዴት ይታመናል?
 • ክቡር ሚኒስትር ገንዘብ እኮ የለም፡፡
 • እንዴት ነው አንተ ገንዘብ የማይኖርህ?
 • መንግሥት ነው እንጂ የሌለው፡፡
 • ምን?
 • ዶላር የታለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አገር ውስጥ አትታከምም እንዴ?
 • እዚህ ታክሜ በራሴ ላይ ሌላ በሽታ ልጨምር፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር ሆዱን የታመመ ሰው ጉሮሮ የሚቀዱ ዶክተሮች ያሉበትን አገር እንዴት አምኜ ነው የምታከመው?
 • መድኃኒት እየወሰድክ ነው ግን?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን እኮ አገሪቱ ማሳከሚያ ዶላር ብቻ ሳይሆን መድኃኒት መግዣ እያጣች ነው፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • አሁንስ ሰለቸኝ፡፡
 • ምኑ?
 • ለዶላር ሠልፍ፡፡
 • እ. . .
 • ለነዳጅ ሠልፍ፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ለዳቦም ሠልፍ፡፡
 • እውነት ነው፡፡
 • ምግብ ቤት ሠልፍ፡፡
 • እዚያም አለ?
 • ለትራስፖርት ሠልፍ፡፡
 • ልክ ነህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሳይታወቃችሁ ሁሉንም ሕዝብ ምን እያደረጋችሁት እንደሆነ ታውቃላችሁ?
 • ምን እያደረግነው ነው?
 • ተቃዋሚ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ሰላም ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እናንተ እያላችሁ ሰላም ይኖራል ብለህ ነው፡፡
 • ከእኛ ወርዳችሁ አርፋችሁ ሥራችሁን ብትሠሩ አይሻልም?
 • እናንተ እያላችሁ መቼ ሥራ ይሠራል?
 • እ. . .
 • በየቦታው እሳት እየለኮሳችሁ ማጥፋት ሰለቸን፡፡
 • አሁን የፓርኩን እሳት እናንተ ለኮሳችሁት ልትሉ ይሆናል እኮ?
 • ኧረ አገሪቱ ውስጥ የሚነሳውን እሳት ሁሉ የምትለኩሱት እናንተ ናችሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ቀስ ብለው የቤቴንም ቡታጋዝ እናንተ ናችሁ የምትለኩሱት እንዳትሉን?
 • ቤቴንም ልታነዱ አስባችኋል?
 • ኧረ ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስነግርህ እናንተ እያላችሁ አገር ልትረጋጋ አትችልም፡፡
 • በዚሁ ከቀጠልን ግን አስጊ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እ…
 • አገሪቱ እኮ በዶላር ጠኔ እየተመታች ነው፡፡
 • ዶላሩን ሰብስባችሁ ይዛችሁ እንዴት አገር በጠኔ አትመታ?
 • ለዚህ ችግር በአፋጣኝ መፍትሔ ካልሰጣችሁት መዘዙ ብዙ ነው፡፡
 • መፍትሔው እኮ እናንተው ጋ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የደበቃችሁትን ዶላር አውጡት፡፡
 • አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ከመሸሽ የተረፈውን ዶላር ማለቴ ነው፡፡
 • ይልቁንስ ቀልዱን ትታችሁ ሥራችሁን ሥሩ፡፡
 • ምን እንሥራ?
 • የልማት ድርጅቶቹን ሽያጭ ማፋጠን አለባችሁ፡፡
 • እ…
 • እንደዚያ ካደረጋችሁ ቢያንስ አገሪቱን ከዶላር ጠኔ ልትታደጓት ትችላላችሁ፡፡
 • እሱ እንደዚህ ቀላል አይደለም፡፡
 • ምኑ ነው የከበዳችሁ?
 • የሕዝብ ሀብት ስለሆነ በጥንቃቄ ነው መደረግ ያለበት፡፡
 • ለማንኛውም እኛም አሰፍስፈን እየጠበቅን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑን?
 • የልማት ድርጅቶቹን ሽያጭ፡፡
 • ምን ለማድረግ?
 • ለመግዛት ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምትገዙት?
 • ሼር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የፖለቲካ ተመራማሪ ጋር እያወሩ ነው]

 • የታሪክ ተጠያቂ እንዳትሆኑ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ችግሩን እኮ አግኝታችሁታል፡፡
 • የምኑን?
 • የአገሪቱን ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ባለፈው የአገሪቱ የፀጥታ ሥጋት የብሔር ፖለቲካ ነው ብላችኋል፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ መርዘኛ ዘረኝነት ነው የአገሪቷን ችግር እያባባሰ ያለው፡፡
 • እሱ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
 • ምን እንደሚገርመኝ ያውቃሉ?
 • ምንድነው?
 • ዘረኞች እኮ ልክ እንደ እንስሳ ናቸው፡፡
 • ኧረ አትሳደብ፡፡
 • እንስሳ ስድብ መቼ ይገባዋል ብለው ነው?
 • ቆይ ተረጋጋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንስሳ ብቻ ነው የራሱን ዓይነት የሚፈልገው፡፡
 • እ…
 • ይኸው የእኛ አገር ፖለቲከኞች ከዚህ ዘር ውጪ አታግቡ፣ አትነግዱ እያሉ አገር እየበጠበጡ ነው፡፡
 • እሱስ እውነት ብለሃል፡፡
 • የሚገርምዎት ስለዘረኞች ሳስብ፣ ምናለ ቢያንስ ከበቅሎ ቢማሩ ያስብለኛል፡፡
 • እንዴት?
 • በቅሎ የሚወለደው ከእናቱ ፈረስና ከአባቱ አህያ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ታዲያ ዘረኞች ምናለ ከእነዚህ እንስሶች ቢማሩ፡፡
 • ጥሩ ምልከታ ነው፡፡
 • ለማንኛውም የአገራችንን ዘረኞች ለመፈወስ አንድ ማሠልጠኛ ተቋም ላቋቁም ነው፡፡
 • ምን የሚባል?
 • በቅሎ የዘረኞች ማሠልጠኛ ተቋም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ። ይህንን ደብዳቤ እየውና በጠየቁት መሠረት እንዲፈጸምላቸው አድርግ። ጉዳዩ ምንድነው? ከአንድ ክልል የቀረበ የትብብርና ድጋፍ ጥያቄ ነው። የምን ትብብር...

[ክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጃቸው ከሆነች አንድ ባለሀብት የተደወለላቸውን ስልክ አንስተው በኮሪደር ልማቱ ላይ የምታቀርበውን ቅሬታ እየሰሙ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እኔ የኮሪደር ልማቱ ላይ ተቃውሞም ሆነ ጥላቻ እንደሌለኝ የሚያውቁ ይመስለኛል? በዚህ እንኳን አትታሚም።  የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር። አውቃለሁ ስልሽ? ለኮሪደር ልማቱ አዋጡ ሲባልም ያለማመንታት አምስት ሚሊዮን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]

ለምንድነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው? ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም። መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስልዎህ ከሆነ ተሳስተሃል። አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር? ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ...