Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ሥነ ፍጥረትጉማሬ እና የውኃ ላይ ኑሮው

ጉማሬ እና የውኃ ላይ ኑሮው

ቀን:

ጉማሬዎች በአንድ ወይፈን የሚመሩ ከአሥር እስከ 15 የሚደርስ አባላት ባሉት መንጋ የሚኖሩ ማኅበራዊ እንስሳት ናቸው። እስከ 150 የሚደርሱ አባላት ያሏቸው መንጋዎች የታዩባቸው ጊዜያትም አሉ። ጉማሬዎች በየብስም ሆነ በውኃ ውስጥ መኖር የሚችሉ ሲሆኑ፣ አብዛኛውን ጊዜ ማታ ማታ ከውኃ ወጣ ብለው በዳርቻው ላይ ያሉትን ዕፀዋት ይመገባሉ። ብዙውን ጊዜ ከሚኖሩበት ውኃ ርቀው መሄድ አይፈልጉም። ይሁን እንጂ በደረቅ ወራት አንዳንድ ጉማሬዎች እስከ አሥር ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ተጉዘው ምግባቸውን እንደሚቃርሙ ታውቋል።

ጉማሬዎች ድንበራቸውን እንዴት እንደሚከልሉ በግልጽ አይታወቅም። በሚያስገርም ሁኔታ ፋንድያቸውን በጅራታቸው የሚበትኑት እንስት ጉማሬዎችን ለመማረክ ወይም ወደ እረኞቻቸውን ለማስፈራራት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ። ጥቃት ሲሰነዘርባቸው እንደ ፈረስ ያሽካካሉ። በሚጣሉበት ጊዜ ደግሞ ያጓራሉ ወይም ይጮኻሉ። ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በሚጠልቁበት ጊዜ እንኳን የሚያስገመግም ድምፅ ይሰማል። አውራው ጉማሬ ሙህ ሙህ የሚል ድምፅ በማሰማት ማንነቱን ያሳውቃል።

ጉማሬ ሙሉውን ቀን የሚያሳልፈው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በውኃ ተሸፍኖ ነው። ግዙፍ የሆነው አካላቱ ይህን ለማድረግ ያመቸዋል። እንደ ሌሎቹ አራዊት ጥሩ ዋናተኛ ነው ባይባልም እስከ 15 ደቂቃ ውኃ ውስጥ ተቀብሮ ሊቆይ ይችላል። አፍንጫዎቹ፣ ዓይኖቹና ጆሮዎቹ በአንድ አካባቢ ያሉ በመሆናቸው የቀረውን የአካል ክፍል ውኃ ውስጥ ሊሰውር ይችላል። መዳራትንና ተራክቦን ጨምሮ አብዛኞቹ የጉማሬ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑት በውኃ ውስጥ ነው።

ከስምንት ወር የእርግዝና ጊዜ በኋላ ብዙ ጥልቀት በሌለው ውኃ ውስጥ አንድ ጥጃ ይወለዳል። ጥጃው መሬት ላይ ወይም ከቁርጭምጭሚት የማያልፍ ጥልቀት ባለው ውኃ ውስጥ ሆኖ ይጠባል። ጉማሬ በጣም ጠንካራ እንስሳ ይሁን እንጂ ልጅ የማሳደግ ኃላፊነቱን አቅልሎ አይመለከትም። እናቲቱ ልጅዋን በከፍተኛ ጥንቃቄ ትንከባከባለች። ልጇን በጀርባዋ ላይ አዝላ ውኃ ላይ የምትንሳፈፍ ጉማሬ ማየት በእርግጥም የሚያስደስት ትዕይንት ነው። ገራም የምትመስለው ይህች እንስሳ ልጇን ከጀርባዋ ለማውረድ የሚቃጣ ፍጡር ቢኖር አምርራ ትጣላለች።

ጉማሬ ብቻውን ሆኖ ሣር በሚግጥበት ጊዜ አንበሶች ሊያጠቁት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከሁሉ የሚከፋው የጉማሬ ጠላት የሰው ልጅ ይመስላል። ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ‹‹ሰዎች የጉማሬዎችን ቁጥርም ሆነ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ስፋት በእጅጉ ቀንሰዋል›› ይላል። ‹‹ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጉማሬዎች በአዳኞች ከመገደላቸውም በላይ በአንድ ወቅት የጉማሬዎች መኖሪያ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ የእርሻ ማሳዎች ሆነዋል።››

  • ንቁ! በጄደብሊው ዶትኦርግ (2003)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...