Monday, July 15, 2024

ለአገር የማይፈይድ ዕውቀት ዕርባና የለውም!

በድህነትና በጉስቁልና የሚሰቃዩ የሚሊዮኖች እናት ኢትዮጵያ፣ ከወደቀችበት አንስተው የሚታደጓት የቁርጥ ቀን ልጆቿን እየፈለገች ነው፡፡ ዳር ድንበሯን በሕይወት መስዋዕትነት ከሚጠበቁ ልጆቿ በተጨማሪ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው ከአስፈሪውና ከአንገት አስደፊው ድህነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚገላግሏት ልጆቿንም ትሻለች፡፡ ይህንን መሻቷን ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ በተለይ ምሁራንና ልሂቃን ልጆቿ በእጅጉ ያስፈልጓታል፡፡ ነገር ግን ለአገራቸው ሌት ተቀን ከሚደክሙ ትጉሃን ይልቅ፣ አላስፈላጊ ድርጊቶች ውስጥ የተሰማሩ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ ሚሊዮኖች በረሃብ እየተሰቃዩ፣ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የሰቆቃ ኑሮ መከራ እያዩ፣ በመጠለያ ችግር እየተቆራመዱ፣ በሕክምና ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች እየሞቱ፣ በኋላቀር ግብርና ምክንያት ምርታማ መሆን አቅቷቸው ለዕርዳታ እየተጋለጡ፣ ለሥልጣኔ ባዕድ ሆነው፣ ወዘተ. የአገሪቱ ምሁራንና ልሂቃን ሊደርሱላቸው አልቻሉም፡፡ ሐኪሙ፣ መሐንዲሱ፣ የግብርና ባለሙያው፣ መምህሩ፣ ቴክኖሎጂስቱ፣ ወዘተ. ለአገርና ለሕዝብ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋጽኦ ዘንግተው፣ መፍትሔ አልባና የሰለቸ የፖለቲካ ዲስኩር ላይ ተጥደዋል፡፡ ከትምህርት ማዕድ የተቋደሱት ዕውቀት ለአገር ፋይዳ ከሌለው፣ የምሁርነት ካባ ደርቦ መንጎማለል ምን ያደርጋል?  ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ማስወገድ ያልቻሉ ምሁራን ከንቱ ወሬ ምን ይፈይዳል?

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ቻይና አቅንተው፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ያለባትን ብድር ወለድ ማሰረዛቸው ተሰምቷል፡፡ ከቻይና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ተብለው የተወሰዱ ብድሮች ወለድ መጠኑ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከቻይና በተጨማሪ የተለያዩ አገሮችና ዓለም አቀፍ በአበዳሪዎች ብድር መጠንም እንዲሁ ከባድ ነው፡፡ የዕዳ አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀች አገርን መታደግ የሚቻለው በሥራ እንጂ፣ ለአገር ፋይዳ በሌለው እንቶ ፈንቶ አይደለም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ መማር ዕርግማን እስኪመስል ድረስ፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች አኳኋን ግራ እያጋባ ነው፡፡ የገበዩት ዕውቀት እየባከነ አገር እየተጎዳች ነው፡፡ ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነትና በጉስቁልና መኖሩ አልበቃ ብሎ የዕዳ ተራራ አናቱ ላይ ተቆልሎ፣ ምሁራኑና ልሂቃኑ ሊታደጉት አልቻሉም፡፡ አገርን ወደ አንድ ዕርከን ፈቀቅ የሚያደርግ ሙያዊ ኃላፊነትን መወጣት ሲገባ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ነጋ ጠባ ቅራኔ እየዘሩ ግጭት መቀስቀስ አሳሳቢ ልማድ ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የግጭት ነጋዴዎች እንጂ እንዴት ምሁራን ወይም ልሂቃን ይባላሉ? አገርን ከዕዳ ማጥ ውስጥ አውጥቶ ሕዝብ መታደግ የማይችል ዕውቀት ከባዶ ገረወይና ተለይቶ አይታይም፡፡

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት አብረው ያኖሩትን የተከበሩ የጋራ እሴቶቹን በመናድ፣ በጥላቻና በቂም በቀል በተሞሉ ታሪክ መሰል ተረቶች መከፋፈልና ማጋጨት የእነዚህ የግጭት ነጋዴዎች መለያ ነው፡፡ የግለሰብና የቡድን መብቶችን በማጣጣም የጋራ የሆነች አገርን ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ መሆን ሲቻል፣ በተለይ ስመ ምሁራንና ልሂቃን የፖለቲካ ነጋዴዎች አገር ለማፍረስ የተማማሉ ይመስላሉ፡፡ በነጋ በጠባ ነገር መሸረብ፣ ማሴር፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ጥርጣሬና አለመተማመን መፍጠር፣ ሥጋት የሚያባብሱ ሐሰተኛ ወሬዎችን መንዛትና የመሳሰሉት መደበኛ ሥራቸው ነው፡፡ ሕዝቡን በዘር፣ በእምነት፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰሉት ልዩነቱን በመለጠጥ ለማፋጀትና አገርን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ ለመክተት ይሯሯጣሉ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድም አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው ሊያፈርሷት ግን እንቅልፍ ያጣሉ፡፡ ይህንን ምስኪን፣ ደሃና ጎስቋላ ሕዝብ እጅግ መሪር ከሚባል ኑሮ ውስጥ በማውጣት የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው ከመትጋት ይልቅ፣ ለእነሱ በጣም ቀላሉ ሥራ ቀውስ ፈጥሮ በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ ሥልጣኑን የሚፈልጉት ለክብር፣ ለዝና ወይም ለጥቅም ብቻ ሳይሆን ለድብቅ ዓላማቸው ጭምር ነው፡፡ ይህ ድብቅ ዓላማ ደግሞ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ ያነገበ ነው፡፡ ለአገር ህልውና ደንታ የሌላቸው ምሁራን ተብዬዎች ምን ይፈይዳሉ?

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሠልጥነናል የሚሉ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች ደሃ አገር ውስጥ መኖራቸውን እስኪረሱ ድረስ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ መሽገው ለአገር የማይጠቅም ነገር ሲያቦኩ ውለው ያድራሉ፡፡ የሚረጩት መርዝ በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ስሜታውያንን በጭፍን በመንዳት ግጭት እየቀሰቀሱ ለንፁኃን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በተማሩት ሙያ አገር ማሳደግና በሕግ የበላይነት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዕገዛ ማድረግ ሲጠበቅባቸው፣ እነሱ ግን ጎራ ለይተው ምስኪኑን ሕዝብ በዘርና በሃይማኖት ጭምር ለማፋጀት አቅላቸውን ስተዋል፡፡ በኃይለኞች አፈና ምክንያት ድምፃቸው ጠፍቶ የነበሩት ሳይቀሩ፣ የነፃነትን ዋጋ በአግባቡ መረዳት አቅቷቸዋል፡፡ ነፃነትን ለአምባገነንነት ገጸ በረከት የሚያቀርቡ ድርጊቶች ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ከንቱ ፉከራ ውስጥ ሆነው መደማመጥን አጥፍተዋል፡፡ በተለይ ወጣቶችን በአልባሌ ቅስቀሳዎች በስሜት በማነሳሳት ሥርዓተ አልበኝነት እንዲነግሥ ተግተው እየሠሩ ነው፡፡ እነዚህ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች የዴሞክራሲን መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች እየተጋፉ፣ አገሪቱን ለአምባገነንነት ወይም ለመፈረካከስ እያመቻቹ ነው፡፡ እነዚህ ፋይዳ ቢሶች በዚህ ከቀጠሉ የአገር ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡

ለሐሳብና ለንግግር ነፃነት ድምፃቸው እስኪሰልል ድረስ ሲጮሁ ከነበሩት መካከል፣ የዜጎችን ነፃነት ለማፈንና የአንድ ጎራ የበላይነት ለማንገሥ አደገኛ ባህሪ የተላበሱ አሉ፡፡ የሌሎችን መብት በመደፍጠጥ ተረኛ ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን ታጥቀው ተነስተዋል፡፡ የአደባባይ ሰዎችን በማሸማቀቅ ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ማድረግ፣ ሰዎች ሲሳሳቱ እንኳ ምን ያህል መሳሳት እንደሚችሉ ሆን ብሎ ማወቅ አለመፈለግ፣ ተቃራኒ ሐሳብ ወይም አስተያየት ያላቸውን የለየላቸው ጠላቶች አድርጎ መፈረጅ፣ ከኋላ ያዘጋጁትን ኃይል ማስፈራሪያ ማድረግና ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረግን ጉዞ ማጨናገፍ የተለመዱ ድርጊቶቻቸው ናቸው፡፡ መማር ዕርግማን እስኪመስል ድረስ ብዙዎች አንገት እየደፉ ነው፡፡ ይህችን አገር ትናንት ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር በተደረገው ትግል በግንባር ቀደምትነት የሞት ሽረት ትግል ያደረጉ፣ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጠው በተግባር ያረጋገጡ ዜጎችን፣ አሁን ለምን የራስህ የተለየ አቋም ይኖርሃል እየተባሉ ዘመቻ የሚከፈትባቸው በእነዚህ እኩዮች ቅስቀሳ ነው፡፡ አንድ ሰው ተሳስቷል ቢባል እንኳ መብቱ የት ድረስ ሊሆን እንደሚችል ችላ ማለት፣ ለአገር አጥፊ እንጂ አልሚ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ አገርን በሚያጠፉ ከንቱ ድርጊቶች ውስጥ የተሰማሩ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች ዕውቀታቸው ለጥፋት እየዋለ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ለአገር ፋይዳ የሌለው ዕውቀት ደግሞ ዕርባና ቢስ መሆኑን ይረዱ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...

በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ አጠቃላይ ገበያው እንዳይታመም ትኩረት ይደረግ!

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...