የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የሚያዋስኑ ድንበሮች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን በተመለከተ ዝምታን መርጧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ሐሙስ ሚያዝያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን ተቋማዊ መልክ ለማስያዝ እየተሠራ እንደሆነ በመግለጽ፣ የድንበሩን መዘጋት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ፣ ተከፍተው የነበሩ የሁለቱ አገሮች ድንበሮች መዘጋት የጀመሩት በታኅሳስ ወር 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡
የመጀመርያ የድንበር መዝጋት ዕርምጃ የተወሰደው በኤትርትራ በኩል እንደሆነ በወቅቱ መታወቁ ይታወሳል፡፡ የቅርብ ጊዜውና የሁለቱ አገሮችን ድንበሮች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ ያደረገው የሚያዝያ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕርምጃ ከኤርትራ ወገን እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹በሁለቱ አገሮች መካከል ስምምነት ከተፈጸመ ጊዜ ጀምሮ የድንበሮችንና የሰዎችን ዝውውር፣ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችንና ግንኙነቶችን ተቋማዊ መልክ ለማስያዝ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በመልካም ሒደት ላይ ናቸው፤›› በማለት ያብራሩት አቶ ነብያት፣ በተጠየቁት የድንበሩ መዘጋት ምክንያት ላይ ግን አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡
‹‹እነዚህ ዝርዝር ሥራዎች ናቸው በቀጣይ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚኖረው ግንኙነት ተቋማዊ ቅርፅ የሚያስይዙትና በእያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምላሽ ማግኘት የሚቻለው፤›› ሲሉም ደምድመዋል፡፡
የሁለቱ አገሮች ድንበሮች ከተከፈተ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከሁለቱም በኩል ድንበር እያቋረጡ ሲያጠያይቁና ሲገበያዩ ቆይተዋል፡፡
የኤርትራ መንግሥት የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር የድንበሮቹን መከፈትም ሆነ መዘጋትን በሚመለከት እየቀረበበት ስላለው ትችትና ወቀሳ በድረ ገጹ ባስፈረው ጽሑፍ፣ ድንበሮቹ የተዘጉት ሕጋዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ተግባራትን ለመፈጸም እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ድንበሮቹ ሲከፈቱ ዜጎች እንዲኮበልሉ መንግሥት አመቻቸ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ የሕግ ጉዳዮችን ለማመቻቸት ሲባል ሲዘጉ ደግሞ መልሰው የሚጮሁ እንዳሉ በመግለጽ ተቺዎችን ሸንቁጧል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር በተቋቋመ ቡድን ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሕጋዊ ማዕቀፍ ለማበጀት እየተሠራና የሁለቱም አገሮች የቴክኒክ ቡድኖች እየተገናኙ እንደሚወያዩ ቢነገርም፣ እስካሁን የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ የደረሰበት ደረጃ አልተገለጸም፡፡