የዓለም ሕዝቦችን ቀልብ ከሚስቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እግር ኳስ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ያለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ እዚህ ግባ ባይባልም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በየክልል ከተሞች በርካታ ተመልካች መታደም ጀምሯል፡፡ በዚያው ልክ በድጋፍና በክለብ አለኝታነት ሽፋን ቅጥ ባጣና አገር በሚያናውጥ ‹‹ብሔርተኝነት›› የተለከፉ፣ ክፉ አድራጊ ግለሰቦችና ወጣቶች የሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥ ለዜጎች ማኅበራዊና ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ ስታዲየሞችም የነውጥ ቀጣና እየሆኑ መጥተዋል፡፡
ይህ በሁሉም ማዘውተሪያዎች የሚስተዋለው የሥነ ምግባር መጓደል አበው ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በችግሩ መንስዔና መፍትሔው ላይ በማተኮር ሚያዝያ 14 እና 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ውይይት አድርገዋል፡፡ በመድረኩ ለችግሩ መንስዔ የሚባሉ ነጥቦች ያላንዳች ሥጋትና መሸማቀቅ ተነስተዋል፡፡
ውይይቱን በንግግር ያስጀመሩት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) እና የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን፣ ለስፖርቱ ሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት በሁለት መለዮ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት ማለትም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ የክልል ስፖርት አመራሮች፣ የክለብ መሪዎች፣ አሠልጣኞች፣ ተጨዋቾች፣ ተመልካቾች፣ የስፖርት ሚዲያውና የፀጥታ አካላትና ሌሎችም መሪ ተዋንያን መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሮቹ ከሆነ፣ ‹‹እግር ኳሱን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ዓይነቶች አሉ፡፡ እግር ኳስ ከተቀሩት ስፖርቶች ብዙ ተመልካችና ተከታታይ አለው፣ ይሁንና ኅብረተሰባችን እንደሚጠብቀው ወደፊት መጓዝ አልቻለም፡፡ ይህ ቀረሽ የማይባል ማኅበራዊ ቀውስ ማስከተሉ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ግን ውሎ አድሯል፡፡ ችግሩን በምኞት ብቻ ሳይሆን በተግባር ሠርተን እግር ኳሱ ከገባበት ማኅበራዊ ቀውስና ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ማጥራት ይጠበቅብናል፣›› ብለው በተለይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ችግሩ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ መንግሥት የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት ስላለበት ለመዝጋት ይገደዳል ሲሉ የችግሩን መጠንና ዓይነት ጭምር በማመላከት አስጠንቅቀዋል፡፡
የሥነ ምግባር መጓደልና ሥርዓት አልበኝነት እግር ኳሱን ከመጉዳት አልፎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጎሳ፣ በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ላይ ያተኮሩ ልዩነቶችና መቆራቆዞች እዚህም እዚያም እየተበራከተ መምጣቱን የተናገሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረ መስቀል፣ ‹‹ስፖርቱ ከፍ ያለ የሞራል ልዕልናን የሚጠይቀውን ያህል፣ በተቃራኒው ነውጠኝነትና ሥርዓት አልበኝነት ነግሧል፤›› ብለዋል፡፡
ስፖርት አቅምን ለማዳበር፣ አካልና መንፈስን ለማደስና ለአገር ሰላም ትልቅ አቅም እንዳለው ያከሉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ፣ ‹‹እግር ኳስ ፍቅርና ሰላም ብቻ ሳይሆን የታመመን ፖለቲካ ለመፈወስ አስፈላጊ ነው፡፡ በአገራችን ግን ከዚህ በተቃራኒው የረብሻ፣ የሁከትና ብጥብጥ መድረክ ሆኗል፤›› በማለትም ችግሩን ወደ ራስ ተመልክቶ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ፣ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ነገሩን አስቸጋሪና የከፋ ያደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሁለቱ ቀን የውይይት መድረክ የተለያዩ ሙያተኞች የችግሩ መንስዔ አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ የአብዛኛው የትኩረት ማጠንጠኛ አሁን ላይ እግር ኳሳዊ ያልሆኑ፣ ከስፖርቱ መርህ ያፈነገጡ ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች ሲከሰቱ መመልከት የዕለት ተዕለት ትዕይንት እየሆነ መምጣቱ ላይ ነው፡፡ በዋናነትም ሙሰኝነት፣ የሕግ የበላይነት ጥሰት፣ ብሔርተኝነት፣ የፖለቲከኞች ፍላጎት ማስፈጸሚያ በመሆን አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫያ እየወሰደ ስለመሆኑ ጭምር ተነግሯል፡፡
እንደ ብዙዎቹ ተናጋሪዎች እምነት የችግሩ መነሻ እግር ኳሳዊ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም መንግሥትና የሚመለከታቸው ተቋማት ለጉዳዩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ ክለቦች በስተቀር ብዙዎቹ ክለቦች አሁን ላይ የመኖርና ያለመኖር ህልውናቸው የሚወሰነው ከጀርባቸው ብሔርንና ዘርን መሠረት ባደረጉ ፖለቲከኞችና ተመልካቾች እንደሆነም ያምናሉ፡፡
‹‹በፊፋም ሆነ በካፍ የማይፈቀዱ በስታዲዮሞች ውስጥ ዘርና ብሔርን መነሻ ያደረጉ ስያሜዎች፣ ባነሮች፣ መፈክሮችና ተያያዥ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ ይህን የመቆጣጠርና የማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥርስ አልባ ሆኗል፡፡ የክልል ክለብ አመራሮች ከፌዴሬሽኑ ሥልጣንና አቅም በላይ ናቸው፡፡ ፖለቲካውና ፖለቲከኛው የሚፈነጭበት መደበቂያ ሆኗል፤›› የሚሉት ታዳሚዎችና ጥናት አቅራቢዎች እግር ኳሱ በአጠቃላይ የብሔርና የዘር ማንነት መለኪያ ሆኖ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ለሕይወትና ለንብረት ውድመት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
‹‹እግር ኳስ ጨዋታ ወደ ጦርነት ተለውጧል፣ ዘርና ፖለቲካ ገብቶበታል፣ ከሁሉም በላይ መንግሥት ለዘርፉ የሚበጅተው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ሙስና ተንሰራፍቷል፡፡ በእግር ኳሳዊ መድረኮች የሚደመጡ አስተያየቶችና ትችቶች በሙሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፤›› በማለት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያስረዱት አንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮች ላይ በርካታ ጥናቶችና ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ልዩነቱ አሁን ላይ የችግሩ ስፋትና መጠን ይለያል፡፡ ይህን ያረጋገጠው ደግሞ የሸራተን መድረክ ነው፡፡ ከሦስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች በታደሙበት በዚህ መድረክ ስፖርቱ ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆኑ እስካልቀረ ድረስ፣ መሬት ላይ ባለው ተጨባጭ እውነታ እግር ኳሱ አይደለም፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ወደ ቤታቸው ለመመለስ ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌላቸው ነው ሲናገሩ የተደመጡት፡፡
የሕግ የበላይነት ሊኖር እንደሚገባ፣ ከክልል ካቢኔ ጀምሮ ፖለቲከኞች ከስፖርቱ እጃቸውን ማንሳት እንዳለባቸው፣ ከዘርና ከሃይማኖት የፀዳ የክለብ ስያሜና አደረጃጀት፣ እንዲሁም ለእግር ኳሱ ወጪና ገቢው የሚታወቅ የፋይናንስ ሥርዓት ማስፈን፣ በዋናነት ደግሞ ለስፖርት አፈጻጸም የሕግ ማዕቀፍና ተያያዥ ተግዳሮቶችን የተመለከቱ ነጥቦች ከተለያዩ ተቋማት በመድረኩ የታደሙ አካላት የተሰነዘሩ አስተያየቶች ናቸው፡፡
በመጨረሻም መድረኩ የሁለት ቀን ውሎውን ያጠቃለለው የመፍትሔ ሐሳቦችን በአቋም መግለጫ በማውጣት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ የዘር ልዩነት እንዲጠፋ የኦሊምፒክና የዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ደንብና መመርያዎች እንዲከበሩ ማድረግ፣ ዘርና ብሔርን መሠረት አድርገው የሚቋቋሙ ክለቦች ስማቸውን እንዲቀይሩ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ሌሎችም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አስተዳዳሪዎቻቸውን ሲመርጡ በችሎታና ብቃት ላይ ተመሥርተው እንዲሆን፣ ስፖርት በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲስፋፋ ትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት፣ የስፖርት ተቋማት የፋይናንስ ሥርዓቶች በፖሊስና በፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩ፣ የስፖርት ተቋማት መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ከፊፋና ከካፍ ቋንቋዎች ቢያንስ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ መሆን እንዳለባቸው፣ ውድድሮች ሲኖሩ የፀጥታ አካላት ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግ፣ ስታዲዮሞች ተገቢው የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የሕክምናና የአምቡላንስ አገልግሎትና በቂ የመፀዳጃ ሥፍራዎች እንዲኖራቸውና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የመንግሥት ቁርጠኝነትና ውሳኔ እንዲኖር ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡