በቅርቡ የተዋወቀው የከተማ ውስጥ የውኃ መናፈሻ (River Park) ለከተማችን እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑ ምንም አጠያያቂ አይደለም፡፡ ላደጉ አገሮችም ቢሆን ከተማ ማስዋብና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ማዘመን ከባድ ሥራ ከመሆኑም በላይ፣ ይህን ለማከናወን ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እንደሚጠይቅ ዕሙን ነው፡፡
በመሆኑም እንደ አገራችን ላሉ ፈጣን ዕድገት ለማምጣትና ለዜጎቻቸው የተመቻቸ የመኖሪያና የመሥሪያ አካባቢ ለማደራጀት ጥረት ለሚያደርጉ አገሮች፣ ሁኔታው ከባድና ለዚህ ዓይነቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠትም አስቸጋሪ ስለሚሆንባቸው በዘመናዊ አደረጃጀት የተያዙ ከተሞች (ዋና ከተማዋን ጨምሮ) ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በሥራ ላይ ለማዋል ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ሁሉን አቀፍ አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የአዲስ አበባን ገጽታ ሊቀይር በሚችል መልኩ የውኃ አካላት ያሉት መናፈሻ እንዲሠራ መንግሥታቸው ማቀዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አብስረዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተዘረዘሩት በርካታ ጠቀሜታዎች አንድ ሁለቱን ብቻ በዚህ ጽሑፍ በማጉላት ሥራው ከምንም በላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት በፍጥነት ቢጀመር ተገቢ እንደሚሆን አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡
አንደኛ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር ይህ ፕሮጀክት ሲተዋወቅ በከተማዋ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር እያለ እንዴት ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ በጀት ይመደባል? የሚል አስተያየት እንዳለ ተጠቁሟል፡፡ ሐሳቡ ተገቢ ቢሆንም ይህ ፕሮጀክት ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ያውም አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው፣ እንዴት? ቢባል ፓርኩ ከአንደኛው የከተማ ጫፍ ተነስቶ ወደ ሌላው ጫፍ የሚዘልቅ በመሆኑ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል፡፡
በመሆኑም የመጀመርያው የፕሮጀክቱ ዲዛይን ሥራ በባለሙያ ከተጠናቀቀ አብዛኛው ሥራ ከፍተኛ ባለሙያ ባልሆኑ ነገር ግን ብዛት ያላቸው ሠራተኞችን የሚያሳትፍ ሲሆን በቀጣይም በአትክልት እንክብካቤ፣ በፅዳት፣ በጥበቃ ሥራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በቋሚነት ሊያሰማራ የሚችል አቅም አለው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት መጠለያና ምግብ አጥተው በየጎዳናው ሰውነታቸውን የሚያደነዝዙ፣ ጤናቸውን የሚያውኩ ነገሮችን እየተጠቀሙ በየድልድዩ ሥር የሚውሉ፣ የሚያድሩ በርካታ ወጣቶችን (ሴቶችም ወንዶችም) ወደዚህ ሥራ ብናሰማራ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቅነሳ ነው ማለት ነው፣ ማደሪያና መፀዳጃ የሆኑት ጎዳናዎች የከተማችንን ደረጃ የማይመጥኑ በመሆናቸው ይህን ችግር የፓርኩ መገንባት በእጅጉ የሚቀንስና የሚያስተካክል ነው፡፡ እንዲሁም በየኪሎ ሜትሩ በፓርኩ ዳርቻ ላይ መጠለያና መፀዳጃን ያሟላ ግንባታ ቢካሄድና ሥራውም በዚህ አግባብ ቢመቻች በጣም በቀላል ወጪ የጎዳና ተዳዳሪዎችንም ሆነ የሥራ አጡን ቁጥር ለመቀነስ ትርጉም ያለው ሥራ ሊከናወን ይችላል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ፓርኩ ሰፊ ቦታ የሚሸፍን እንደመሆኑ መጠን በዳር በዳር የእግር ጉዞ ማድረጊያ የብስክሌት ማሽከርከሪያ ቦታ እንደሚመቻች ስለሚታመን ለነዋሪው ምቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ በመሆን ጤናማ ዜጋ ለሥራ ዝግጁ የሆነ የተነቃቃ መንፈስ ያለው የሰው ኃይል መፍጠር ያስችላል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ፓርኩ ሰፊ ርቀት እንደመሸፈኑ በውስጡ የገንዘብ ተቋማት (ባንኮች) ዘመናዊ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖችን በማስቀመጥ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ሊያሳድጉበት ለውጭ ጎብኚዎችም ምቹ ሁኔታን ሊፈጥሩበትም ይችላሉ፡፡ የምግብና የመጠጥ አቅርቦት፣ የመዝናኛና የፊልም ማዕከላት፣ የላይብረሪና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ማዘጋጀት ስለሚቻል የእነዚህ አገልግሎቶች ኪራይ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ለዩኒቨርሲቲዎች የምርምርና የጥናት ማዕከላትን በማደራጀት በርካታ ጠቀሜታ ሊሰጥ የሚችል ግዙፍ ማዕከል ይወጣዋል፡፡
በሒደትም የተገነባበትን ወጪ ሸፍኖ ሌላ የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚደጉምም ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ከተማችን አረንጓዴ ዕፅዋት ለዓይን እየጠፋ እዚህም እዚያም ወጥነት በሌላቸው የሕንፃ ዲዛይን ግንባታ በመብዛቱ፣ እንዲሁም በሰውም የአጠቃቀም ልምድ የቆሻሻ አወጋገድና ባልተገባ ቦታ መፀዳዳት የከተማዋን ገፅታ በእጅጉ እያበላሸ የነዋሪውም ጤና እየታወከ ስለሆነ የዚህ ፓርክ መገንባት በጎላ መልኩ ይህን ገፅታ ያሻሽላል፡፡ እንደሚታሰበው ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስለሚሆን ለደረቅም ይሁን ለፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ በዘመናዊ መልክ ስለሚደራጅ እንደ ሞዴል ሆኖ ሌሎች አካባቢዎችም ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል፡፡
የአዲስ አበባ ተሞክሮም ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች (ከተሞች) እየተሸጋገረ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአየር ንብረት መሻሻል ዘመናዊና የተደራጀ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ስለሚሆን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አጀማመርዎ ፈጣን ባለጉዞ ይህንንም ጉዳይ ይበርቱበት፡፡ አንዴ ከተጀመረ የአዲስ አበባ ነዋሪውም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ በውጭም ያሉ ደጋፊዎችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡
(ውቢት ኢትዮጵያ፣ ከአዲስ አበባ)