Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየበዓል ሕግጋትና የተጓደለው አፈጻጸማቸው

የበዓል ሕግጋትና የተጓደለው አፈጻጸማቸው

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ሰሞኑን ተደራራቢ ብሔራዊ በዓላት አሉ፡፡ ባለፈው ዓርብ ስቅለት፣ ዛሬ ደግሞ ትንሳኤ ነው፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ዓለም አቀፉ የወዛደሮች ቀን በመሆኑ በዓል ነው፡፡ ሚያዚያ ሃያ ሰባት ደግሞ የድል ቀን ነው፡፡ በአሥር ቀናት ውስጥ አራት ብሔራዊ በዓላት ይከበራሉ፡፡ ሁለቱ ሃይማኖታዊ፣ ሁለቱ ደግሞ ታሪካዊ በዓላት ናቸው፡፡ የብሔራዊ በዓልነት ደረጃ የያዙት በሕግ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የበዓል ሕግጋትና ዓላማቸውን እንዲሁም በአፈጻጸማቸው ላይ የተስተዋሉ ዝንፈቶችን መቃኘት የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡ የተዛነፉትን በማስተካከል በበዓላት መከበር አማካይነት እንዲሳኩ የሚፈለጉትን ግቦች እንዲሳኩ መስተካከል ያለባቸውን በእግረ መንገድ መጠቆም ነው፡፡

የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀንን በሚመለከት ወግና ሥርዓት የሚያስይዙ ሕግጋት አሉ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴም ዘመን አዋጅ ወጣላቸው፡፡ ኋላ በደርግ አገዛዝ ወቅት እንደ አዲስ ሕግ ወጣ፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜም ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው በ1967 ዓ.ም. የወጣው፣ የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ ቁጥር 16/1967 እና ይህንን ተከትሎ በዚሁ ዓመት የወጣው የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጅ ቁጥር 28/1967 እንዲሁም በ1985 ዓ.ም. የወጣው፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ ቀንና ሰዓት ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 43/1985 ናቸው፡፡

አዋጅ ቁጥር 16/1967 ሲወጣ የሚከተሉትን ዓላማዎች በመያዝ ነው፡፡ በዓላት የተለያዩ በጎ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ከግምት በማስገባት በመጀመሪያ የተገለጸው ዓላማ ‹‹የኢትዮጵያውያንን እኩልነትና አንድነት ለማስጠበቅ›› አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎም፣ ‹‹ሕዝቡ ጊዜውን በተለያዩ የተንዛዙ የዕረፍት ቀናት ሳያሳልፍ የሥራን ጠቃሚነት የበለጠ እንዲረዳና እንዲያምን›› አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል አሠራር ማስፈን በማስፈለጉ ነው፡፡ ሦስተኛው፣ ‹‹በታሪክም፣ በሃይማኖትም፣ በልማድም የሚከበሩ በዓላትን ሳይዘነጉ ማሰብና ማክበር›› አስፈላጊ በመሆኑም ጭምር እንደሆነ በአዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡

በዓላቱ መሠረታቸው ታሪክም፣ ሃይማኖትም ወይም ባህልም ቢሆን ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም ብሔራዊ በዓላት እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡ ብሔራዊ መሆናቸው በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀብትም፣ ማያያዣም፣ አንድነት መፍጠሪያም እንዲሆኑ በማሰብ ነው፡፡

በአዋጁ ላይ መስከረም አንድ በይፋ ‹‹የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ›› ስለሆነና ‹‹ኤርትራ ከእናት አገሯ ከኢትዮጵያ የተቀላቀለችበት›› በመሆኑ ድርብ በዓል ነበር፡፡ ይሁንና ይህ በዓል ኤርትራ ከእንደገና ከኢትዮጵያ ስትገነጠል (ደርግ መንግሥት ሲወደቅ) በሕግ ሳይሻር ባለማክበር በገቢር ቀሪ ሆኗል፡፡

መስከረም ሁለትም ‹‹የለውጥ ቀን›› ተብሎ ይከበር የነበረና በሕግም የታወቀ ቢሆንም ይህም በተግባር ቀርቷል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የዓለም ወዛደሮች ቀን (እ.ኤ.አ. ግንቦት 1/ሜይ 1)፣ የድል ቀን ታሪካዊ በዓላት ናቸው፡፡ መስቀል፣ ገና፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሳኤ (ፋሲካ)፣ ኢድ አድሃ፣ ኢድ አልፈጥርና መውሊድ ሃይማኖታዊ በዓላት ናቸው፡፡

መስከረም ሁለት በሕግም ባይሆን በተግባር ቀሪ እንደሆነው ሁሉ ግንቦት ሃያም እንዲሁ በሕግ ሳይሆን በገቢር በዓል ሆኗል፡፡ እነዚህ ብሔራዊ በዓላት ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ እሑድ ደግሞ ሳምንታዊ የዕረፍት ቀንነቱ በቀድሞው አዋጅ የነበረው በድጋሜ ጸንቷል፡፡

በእነዚህ የበዓል ቀናት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የግል ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች ሕዝባዊ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ይህ መርህ ነው፡፡ መርሁ እንደተጠበቀ፣ በርከት ያሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ግን ይኼው አዋጅ ዘርዝሯል፡፡ በተለይም ሆቴልና ሆቴል ነክ ድርጅቶች፣ የሕክምና የመድኃኒት መሸጫዎች፣ መዝናኛዎች፣ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዘክሮች፣ አስከሬን ሳጥንና የአበባ መሸጫ ሱቆች፣ የፖሊስና የሕዝባዊ ደኅንነት ጥበቃ፣ እሳት አደጋ፣ የመብራት፣ የውኃ፣ ስልክ፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅቶች፣ የማመላለሻና የነዳጅ ማደያ፣ የፀጉር ማስተካከያዎችና የንጽሕና መስጪያዎች በበዓላት ቀንም እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

እነዚህ በዓላት በመንግሥትና በሕዝብ ዘንድ በምን መልኩ መከበር እንዳለባቸው  ከዝርዝርነት ቆጠብ ያሉ መመርያዎችን የያዘ አዋጅ በዚሁ ዓመት ወጥቷል፡፡ እንደ አዋጁም፣ ታሪካዊ በዓላትን በዋናነት የመንግሥት ኃላፊዎችን ድርሻ ሲያስቀምጥ፣ ሃይማኖታዊ የሆኑትን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም የመስጊድ ኢማሞች  የየከተማው ከንቲባ ወይም የመዘጋጃ ቤት ሹም ጋር በመመካከር ፕሮግራም አውጥተው ያከብራሉ፡፡ ከንቲባ ወይም የማዘጋጃ ቤት ሹም በበዓሉ አከባበር ላይ ይገኛሉ፡፡

ታሪካዊና ባህላዊ የሆኑትን ዘመን መለዋጫ፣ የአድዋ ድል፣ የድል ቀንና የዓለም ወዛደሮች ቀንን በሚመለከት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዚዳንት) ወይም ርዕሰ መንግሥት (ጠቅላይ ሚኒስትር) እንዲሁም የዘመን መለወጫን በሚመለከት የባህል ሚኒስትር የሚኖራቸውን ሚናም ግዴታም ያስቀምጣል፡፡

የባህል ሚኒስትር በዘመን መለወጫ ዕለት በሬድዮና በቴሌቪዥን ስለነፃነት፣ ስለአንድነት ለሕዝብ መግለጫ መስጠት እንዳለበት አዋጁ ይደነግጋል፡፡ በቀሪዎቹ ታሪካዊ በዓላት ላይ ፕሬዚዳንቱ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓድዋ ድል ቀን አዲስ አበባ፣ ምኒልክ አደባባይ ከዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ጋር በመሔድ የትግሉንና ድሉን ታሪካዊነት በማስታወስ ንግግር ማድረግ፣ የሚያዚያ ሃያ ሰባቱን የድል ቀን ጊዜም እንዲሁ ከሁለት አንዳቸው ንግግር ማድረግ አለባቸው፡፡

የዓለም ወዛደሮች ቀን የፈረንጆቹን የቀን አቆጣጠር ተከትሎ እንዲከበር ነው የተወሰነው፡፡ ማለትም የፈረንጆች ግንቦት 1 ቀን ሚያዚያ 23 ወይም 24 ቢውልም እንዲሁ እየተቀያየረ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወዛደሩ ቀን አንድ እንዲሆን ተመርጧል፡፡ በተግባር ግን ይህ በዓል ሚያዚያ 23 ቀን ሆኗል፡፡ በዚህ በዓል ላይ የወዛደሩን አቋምና ዓላማ በሚመለከት ንግግር እንዲደረግ ሕጉ በመግለጽ በዚሁ ዕለት የሠራተኛው ማኅበር መሪም እንዲሁ ለሰፊው ንግግር እንደሚያደርግ ሕጉ ላይ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

በዘመነ ኢሕአዴግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 43/1985 ዓቢይ ትኩረቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ ሰዓት መወሰን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከሰኞ እስከ ሐሙስ ያሉትን በአንድ ጎራ በማድረግ ዓርብን ግን ከጧት ያለውን የሥራ ሰዓት አምስት ተኩል ላይ እንዲቆም ወስኗል፡፡ ይህ የእስልምና እምነት ተከታዮችን መብት ለማክበር ሲባል የወጣ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ሰዓትንም ትምህርት ሚኒስቴር በተለየ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር ከጧት ሁለት ሰዓት እንደሚጀምር የግል ትምህርት ቤቶች ግን በትምህርት ሚኒስትር መመርያን ተከትለው የራሳቸውን የትምህርት ሰዓት ሊወስኑ እንደሚችሉ ፈቅዷል፡፡

በሕግ፣ በዓላት እንዲሆኑና እንዲከበሩ የተወሰኑትን ማክበር ግዴታ ነው፡፡ ይህንን መተላለፍ በደንብ መተላለፍ ቅጣትን ያስከትላል፡፡ ደንብ ተላላፊነቱ የሚመነጨው በዓሉን ካለማክበር ነው፡፡ የበዓላት አከባበር ሥርዓቱን አለማክበር እንዲሁ ያስቀጣል፡፡ በመቀጮ ወይም እስከ ስምንት ቀን የሚደርስ እስራትን ያስከትላል፡፡ ይህ የደንብ መተላለፍ ተጠያቂነት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 817 ላይ ተደንግጓል፡፡ አስጠያቂነቱ በአሁኑ የወንጀል ሕግ ብቻ ሳይሆን በቀድሞውም ሕግ ላይ የነበረ ነው፡፡

የመንግሥት፣ የግልና የንግድ ተቋማት ሕዝባዊ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተብለው እያሉ ሲሰጡ ከተገኙ የደንብ መተላለፍ ይሆናል፡፡ ሕጉ ላይ የበዓላት አከባበር ሥርዓቱን ምን መምሰል እንዳለበት መወሰን ያለባቸውን አካላትን ተወስኗል፡፡ እነዚህ አካላት የሚያወጧቸውን ሥርዓት መጣስም እንዲሁ ደንብ ተላላፊነት ሊሆን ይችላል፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ቁምነገር ቢኖር የበዓላት አከባበርን መተላለፍ ለምን ቅጣት ሊያስከትል ቻለ? መንግሥት በዚህ ደረጃ መቅጣትንስ ለምን መረጠ? በሌላ አገላለጽ በዓልን ከማክበር መንግሥት ማሳካት የሚፈልግው ግብ ምንድን ነው? እንደማለት ነው፡፡ በቅድሚያ በአዋጅ ቁጥር 16/1967 መግቢያ ላይ የተጻፉትን በግብነት ዕውቅና የተሰጣቸውን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህን ግቦች ከላይ ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያውያን አንድነትና እኩልነት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ነው፡፡

በዓላትን ማክበር በሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር ያግዛል፡፡ በአድዋ ድል በዓል አከባበር በዕለቱ ስለአንድነት ስለአርበኝነት ስለኢትዮጵያዊነት ዜጎች የጋራ እሳቤና ዕውቀት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ሊያደርግ ስለሚችል ለአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት (Nation Building Process) ላይ ጉልህ ድርሻ መኖሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡ የድል በዓልንም በዚሁ መልኩ የሚኖረውን ሚና በምክንያትነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

ሃይማኖታዊ በዓላትም ቢሆኑ በአንድ በኩል በተለያዩ እምነቶችም አማኞችም መካከል እኩልነት እንዲኖር በሌላ በኩል ደግሞ አንዱ ስለሌላው ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖርና መገናዘብ እንዲያድግ የማድረግ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በመሆኑም አገራዊ አንድነትንም እኩልነትንም ለማሳደግ የሚሠሩ ሥራዎች በተቻለ መጠን ለማበረታትም፣ ከዚያ ባለፈ ደግሞ ቢያንስ አንድነትና እኩልነት ላይ የማደናቀፍ ተግባር እንዳይኖር የሕግ መሠረት ለመስጠት ነው፡፡

ከላይ ከቀረቡት ምክንያቶች በተጨማሪም ደግሞ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን በእነዚህ ዕለታት ዕረፍት ባለመስጠት የታሰበላቸውን ዓላማ እንዳያሳኩ እንቅፋት እንዳይፈጥሩም ጭምር ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ ሌሎች ምክንያቶችንም ማንሳት ይቻላል፡፡

ከበዓላት በተጨማሪ ሳምንታዊ የዕረፍት ቀን መኖር የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች አሉት፡፡ ዕረፍት ማግኘት በራሱ ሕገ መንግሥታዊ መብትም ነው፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነት ለማድረግም አብዘኃኛው ሰው በተመሳሳይ ዕለት ዕረፍት የሚያደርግበት ጊዜ መኖር የተለመደ ነው፡፡ ጋብቻ ለመፈጸም፣ ዘመድ ከዘመድ ጋር ለመጠያየቅ፣ ዕቁብ ለመጣል፣ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችን ለመፈጸም ወዘተ የጋራ የዕረፍት ቀን አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡

በበዓላትም ይሁን በሳምንታዊ የዕረፍት ቀናት ማረፍ ሲገባቸው በሥራው ባህርይ ምክንያት በሥራ የሚያሳልፉ ሠራተኞች ከመደበኛ ክፍያቸው በተጨማሪ እንዲከፈላቸው በአሠሪና ሠራተኛም በሲቪል ሰርቪስ አዋጆቹም ላይ በግልጽ ከነስሌቱ ተቀምጧል፡፡ ይህ እንግዲህ ከላይ በአዋጆቹ ላይ በበዓላትና በሳምንታዊ የዕረፍት ቀናት መዘጋት የሌለባቸውን ወይም እንዲዘጉ የማይገደዱት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን የሚመለከት ነው፡፡

ከላይ ያየናቸው ሕግጋት ተከባሪነታቸው ጉራማይሌ መሆኑ አንዱ ሕጸጻቸው ነው፡፡ በአዋጆቹ ላይ በበዓልነት ዕውቅና ሰጥቷቸው እያለ ሳይሻር በገቢር ቀሪ የተደረገ አለ፡፡ መስከረም ሁለት ቀን ይከበር የነበረው ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡

በሕግ በዓልነቱ ሳይደነገግ የሚከበር መኖሩም እንዲሁ ለሕግ የሚሰጠው ዋጋ እያሽቆለቆለ ከመሄዱ የመነጨ መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የግንቦት ሃያ በዓል ተጠቃሽ ነው፡፡

በዓላቱ በምን ሁኔታና ሥርዓት መከበር እንዳለባቸው በወጣው አዋጅ መሠረትም እየተከበሩ አለመሆናቸው እንዲሁ ሌላው ሕጸጽ ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓልን በሚመለከት የባህል ሚኒስቴር ማስተላፍ የሚገባውን መሥራት ያለበትን ሥራ ሕጉ በሚያዘው መሠረት እየተከናወነ አይደለም፡፡ በአድዋ ድል በዓልም ቢሆን በምኒልክ ርዕሰ ብሔሩ ወይንም ርዕሰ መንግሥቱ በቦታው በመገኘት ስለአገራዊ አንድነትና ስለአድዋ ታሪክ ንግግር ማድረግ እንደሚገባቸው በሕግ የተወሰነውም አይደለም ስለበዓሉ ትልቅነት በምኒልክ አደባባይ ተገኝቶ ንግግር ማድረግ ይቀርና በተቃራኒው ታሪኩንም ተዋናዮቹንም የማሳነስና የማኮሰስ ተግባር እንደ ሥራ ተቆጥሮ የቆየ መስሏል፡፡ ሚያዚያ ሃያ ሰባት የሚከበረውን የድል በዓልም ቢሆን ይኼው ዕጣ አልቀረለትም፡፡

ስለሆነም፣ የባህል ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እና/ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣት በእነዚህ ሕግጋት አማካይነት ማሳካት የተፈለገውን ግብ እንዳይሳካ የራሳቸው ድርሻ አለው ማለት ይቻላል፡፡

እንዲሁም በእነዚህ የበዓላት ቀናት ጥሰት ሲፈጸሙ ሕጉ ላይ በተቀመጠው መሠረት በደንብ መተላለፍ የማስጠየቅ ሒደት አለመስተዋሉም ሌላው ሕጸጽ ነው፡፡ በመሆኑም ሕግጋትን ባለማክበርም አዲስ ሕግ ባለማውጣትም ዓላማዎቹን ያለማሳካት ዝንፈት ተስተውሏል፡፡ ይህ ዝንፈት በአገራዊ አንድነት (ኢትዮጵያዊነት) መሻሻል ላይ ማበርከት ያለበትን ሚና ማበርከት ሳይችል ቀርቷል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...