በአንዳርጋቸው አሰግድ
የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች አምርረው የሚመላለሱበት አንድ ጥያቄ ስለታሪክ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጥያቄዎችን ለታሪክ ባለሙያዎች ትተን ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ለመሻገር የተቸገርነው አንድም፣ ታሪክ ቢወደድም ቢጠላም ፖለቲካዊ ስለሆነም ነው። ስለሆነም ነበር የኢትዮጵያ ነገሥታት ሊቃናትንና መነኮሳትን እያስመጡ መዋዕለ ዜናቸውን ሲያጽፉ የኖሩት። ሊቃናቱና መነኮሳቱም፣ የተረኛውን ነጋሢ አንጋሽና አወዳሽ ዝክር ሲጽፉ የኖሩት። ስለነበረም ነው የብሔር እንቅስቃሴዎች ወደ ፖለቲካው መድረክ ከመጡበት ከ1960ዎቹ ወዲህ የፖለቲካ ግባቸውን ለማራምድ የየራሳቸውን ትርክት ወደ ማሳወቅ የተሻገሩት። ስለዚህም ደግሞ እንኳን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የተመሠረተችው ኢትዮጵያ ያቀፈቻቸው የመላ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ቀርቶ፣ የቅድመ አፄ ምኒልክ የስድስትም ይሁን የአምስት ወይም የሦስት ሺሕ ዘመን ትርክት የሚያነታርከው።
ፖለቲካዊው ትርክት በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በተካሄደው የአፄ ምኒልክ መስፋፋት ዝክር ላይ ያተኮረ የነበረውን ያህል፣ ምልልሱ ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በመጋቢት 13 በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔርተኞች›› ባሏቸውና ‹‹የብሔር ብሔርተኞች›› ባሏቸው ክፍሎች መካከል እየሆነ ሄደ። በምልልሱ አንዱ ክፍል ምኒልክን ላያስነካ ገትሮ እንደሞገተ ስድሳ ዓመታት ተቆጠሩ። ሌላው ክፍል ተገቢ የመብት ጥያቄዎችን ይዞ የተነሳ ቢሆንም ቅሉ፣ የአፄ ምኒልክ መስፋፋት ባደረሰው በደልና ሰቆቃ ታሪክ ላይ ተወስኖ እንደሞገተ ስድሳ ዓመታት ተቆጠሩ። ውይይቱ/ክርክሩ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ተከንችሮ የቆመውንም ያህል፣ ‹‹ትምክህተኛ›› እና ‹‹ጠባብ››፣ ‹‹የአንድነት›› እና የ‹‹ገንጣይ/አስገንጣይ›› ኃይል እየተባባሉ ተካረሩ። ስለጋራ ወደፊት ለመወያየት መቀራረብና መደራደር አቀበት ሆነ።
በሁለቱም በኩል የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው እስከዚህም የደረሱትን በደሎችና ሰቆቃዎች አንዱ በማሳነስና ሌላው በማጉላት መሟገታቸው አይደለም። ይልቁንም ለፖለቲካ ግባቸውና ተከታይን ለማበራከት ሲሉ የታሪክንና የማኅበራዊ ክንዋኔን ትንተናን ለማፋለስ እስከ መድፈር ጭምር መሄዳቸው ነው። ከዚህም በባሰ ደግሞ የዛሬው ታሪክ ሠሪዎች እነሱው ቢሆኑምና ትኩረታቸውን የሚጠይቁ በርካታ አጣዳፊ ጉዳዮች ከፊታቸው ያሉ ቢሆንም ቅሉ፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአፄ ምኒልክ ኢትዮጵያ ላይ ሲመላለሱና ሲወነቻቸፉ የሚያባክኑት ጊዜና ጉልበት ነው። የባሰውን የሚያሳስበውና የሚያስደምመው ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተገኙት መሠረታዊ ለውጦች ላይ ቆመው፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ መሐንዲሶች ለመሆን በጋራ አለመትጋታቸው ነው።
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የ2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ሰው ቢሆኑ ኖሮ፣ ከ100 ዓመት በፊት ከጻፉት ሐተታ አንድም ቃል ሳይለውጡ ጽሑፋቸውን ለድጋሚ ዕትም ይሰጡት ነበር። በንባቡ የበረታ የ2011 ዓ.ም. አንባቢ ከጽሑፋቸው የሚከተለውን ሲያገኝ ደግሞ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን በእውነት 21ኛው ክፍለ ዘመን ገብተናል ወይስ አልገባንም በማለት ራሱን አምርሮ ይጠይቅ ነበር። የሚከተለው ነው፡፡
‹‹የእኛ የኢትዮጵያዊያን ያለፈው ታሪክ እጅግ ያሳዝናል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍፁም የሆነ ሰላም አግኝተን አናውቅም። የተወደደች አገራችን ዘወትር በጠላቶች ተከባ ስትኖር ነበረች፣ ትኖራለችም። ነገር ግን የውጭ ጠላት ከዚህ በፊት አላዋረደንም። አንድነትም ስንሆን ምንም የሚደፍረን እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል። ዘወትርም በስምምና በፍቅር አድረን ብንሆን እስከ ዛሬ ድረስ ብዙውን ትልልቅ ነገር መፈጸም እንችል እንደነበር ጥርጥር የለውም። እግዚአብሔር ብዙ በረከት ሰጥቶናልና። ትምህርትን በቶሎ መቀበል የሚችል ልቦናና የጦረኛን ባህሪ ማለፊያና ሀብታም አገርንም። ካለመስማማታችን የተነሳ ግን … ወደ ኋላ ቀረን …።
‹‹የድሮውም የአሁኑንም ኑሯችን እጅግ ያሳዝናል። በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ፣ አዕምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን። እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም። ሕዝቦቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው በአንድነት ሆነው ሲደክሙ፣ እኛ አንድ ዘርና ወንድማማች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም። እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል። ስለዚህም እግዚአብሔር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ ባለቤቶቹ ሰነፍን። ሌሎቹም ነገሥታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል፡፡ ይንቁናልም፤›› (ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ፣ 1902)።
ነጋድራስ ከመቶ ዓመታት በፊት ‹‹እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም›› ያሉት ባህሪይ፣ ከፖለቲካዊ ትርጉሙ አንፃር የኢትዮጵያን ሕዝቦች በማመልከት አይደለም። ይልቁኑ ገዥዎቿንና ልሂቃኑን በማመልከት ነው። ለዛሬው ሁኔታ ብናውለው ዶ/ር ነጋሶ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔረተኞች›› እና ‹‹የብሔር ብሔርተኞች›› ያሏቸውን ክፍሎች ማለት ይሆናል። የትናንቷና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፣ ተዋናዮችና ምሁራን ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ገና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሰጡትን ‹‹(በፖለቲካ) ስምምና (በሕግ የበላይነት) ፍቅር አድረን ብንሆን….›› ኖሮ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሜዳ በኢትዮጵያ የፖለቲካ በሬ አሳምረው ለማረስ የበቁና የሚበቁ በሆኑ ነበር።
ለቡድን መብት የሚታገለው ክፍል ‹‹የኢትዮጵያ ብሔርተኛ›› የተባለውን ክፍል ‹‹የቀድሞውን የብሔር ጭቆና መልሰህ ልታመጣ!›› እያለ ይጠረጥረዋል። ለዜግነት መብት የሚታገለው ክፍል ‹‹የብሔር ብሔርተኛ›› የተባለውን ክፍል ‹‹አገር ልትከፋፍል!›› እያለ ይጠረጥረዋል። አተኩረን ብንመለከት ግን ሁለቱ ወገኖች ለመተማመን በመቸገራቸው እንጂ፣ ልዩነትን እያገዘፉ ጥያቄውን የተከታዮች ማበራከቻ መሣሪያ ስላደረጉት እንጂ፣ እንዲያም ሲል የሥልጣን መወጣጫ መሰላል ስላደረጉት እንጂ፣ የዜግነትና የቡድን መብቶች የማይነጣጥሉ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። በዴሞክራሲያዊ ሕግና ሥርዓት መንገዶች የሚታረቁ መብቶች ናቸው።
አሀዳዊ ወይስ ፌዴራላዊ አስተዳደር በሚለው ላይ የሚካሄደውም ምልልስ ለተከታዮች ማበራከቻ እየዋለ ተወሳሰበ እንጂ፣ የ2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ‹‹ልዩነት›› ሆኖ ሊያመላልስና እርስ በርስ ሊያጠራጥር ባልተገባው ነበር። አሀዳዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ ምድር ላይመለስ ታሪክ ሆኖ አልፏል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በልበ ሙሉነትና ሽንጡን ገትሮ ለአሀዳዊ አስተዳደር የሚሞግት ወገን ሥፍራ የለውም። የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ተግባርና ኃላፊነት ይልቁንም ኢሕአዴግ ተግባራዊ ያላደረገውን ፌዴራሊዝም በሰጥቶ መቀበልና በወደፊት ተመልካች ውይይትና ድርድር በተግባር ፌዴራላዊ ማድረግ ነው። የኢትዮጵያ የሆነን የቆንጆ ፌዴራሊዝም መሥራች አባቶች ለመሆን የመሥራትና የመብቃት ነው።
ወደ ርዕሱ ለመመለስ ነጋድራስን የቀደሙ የዴሞክራሲ መብት አስተማሪዎችም ነበሩን። ለዚህም የአውሮፓዊያን ዘመነ አብርሆት (Period of Enlightment) መሥራቾች ተብለው ከሚታወቁት ዴሰካር፣ ሎክ፣ ካንትና ቮልቴር በፊት ስለሰብዓዊ መብትና የፆታ እኩልነት በተሻለ የተመራመሩትና ያስተማሩት የእኛው የ17ኛው ክፍለ ዘመን የጎንደሩ እንፍራዝ ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ (ወርቄ) እና ተማሪያቸው ወልደ ሕይወት ናቸው። እነሱ ነበሩ፣ ‹‹ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው››፣ ‹‹ፆታዎች እኩል ናቸው›› የሚሉትን የሰብዓዊ መብት መርህና አቋም ‘ሐተታ’ በተሰኘው ድርሰታቸው ውስጥ ያወጁት (Dag Herbjørnsrud the African Enlightenment፣ 2016)። ወደየብሔሩ ቤት ገብተን ብንጠይቅ ተመሳሳይ አመለካከቶች ይገኛሉ።
ዳግ ሄርብዮርንስሩድ ቀጥሎ እንደሚለው፣ ‹‹የአውሮፓውያኑ ዘመነ አብርሆት ወደ ፖለቲካ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አደገ። ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለተደረገው ትግል ፈር ቀደደ። የእነ ዘርዓ ያዕቆብ ግን ወደ ፖለቲካ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ለማደግ ሳይታደል ቀረ››፡፡ ስለዚህ ግን እነ ዘርዓ ያዕቆብ ገና ከ300 ዓመት በፊት የተሟገቱለትን የሰው ልጆች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ የእኩልነት መብት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊያን በዚህና በዚያ ምክንያቶች (ሰበቦች) ለግለሰብ ዜጋ ይሁን፣ ለብሔር የማያውቁበትና የሚገድቡበት ምክንያት የለም። ከ300 ዓመታት በኋላም ቢሆን ተግባራቸውና ኃላፊነታቸው ይልቁንም የኢትዮጵያን ዘመነ አብርሆት ጎህ ማብራት ነው።
ታሪክ ከየት እንደመጣን የሚገልጽልን የትናንት ሥረ መሠረት ነው። የዛሬውን ለመረዳት የሚያግዘን የትምህርት ገበታ ነው። መደገም የሌለባቸውን የታሪክ ሰቆቃዎችና ግድፈቶች ዘርዝሮ የሚያቀርብልን መስተዋት ነው። አኩሪ የታሪካችን ገጾችም እንደዚሁ፣ የዛሬውን ለመረዳት የሚያግዙን የትምህርት ገበታዎች ናቸው። የዛሬውና የወደፊቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በሚጠይቁት ልክ እንድንደጋግማቸው የሚያነሳሱን የታሪክ ቅርሶቻችንና እሴቶቻችን ናቸው። ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው አሁንም በጥሩ እንዳስተማሩት፡፡
‹‹ታሪክን መማር ለሁሉ ይበጃል። የታሪክ ትምህርት የሚጠቅም፣ ግን የእውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው። እውነተኛ ታሪክን መጻፍ ግን ቀላል አይደለም። ሦስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልጉናልና። እነዚህም ተመልካች ልቦና፣ የተደረገውን ለማስተዋል የማያዳላ አዕምሮ፣ በተደረገው ለመፍረድ የጠራ የቋንቋ አገባብ፣ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ። የአገራችን የታሪክ ጸሐፊዎች ግን በእነዚህ ነገሮች ላይ ኃጢያት ይሠራሉ። በትልቁ ነገር ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ። ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልኦ ልባቸውን ያጠባሉ። አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ለአንባቢ አይገባም፤›› ይላሉ፡፡
በሌላ አገላለጽ ታሪክ ሙያውን በተካኑና በነጋድራስ ቃል ‹‹የማያዳላ አዕምሮ›› ባላቸው ምሁራንና ልሂቃን በየዘመኑ ውስጥ በአግባቡ እየተካተተና በማስረጃ ተመሳክሮ ሲተረክ ነው የጎደለው የሚሟላው። የተዛነፈው የሚቃናው። የተጣረሰው የሚታረመው። ድክመቶች የሚለቀሙት። ጥንካሬዎች የሚነቀሱት። ልዩነትና ተመሳሳይነት የሚጎሉት። በየጊዜው የተከሰቱት ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች የሚተነተኑት። መስተጋብሮች የሚገለጹት። ተወራራሽነቶች የሚንፀባረቁት። የጋራ እሴቶችና ፀጋዎች የሚደሩት። የትምህርት መቅሰሚያ ገበታነቱ የሚደምቀው። የጋራ ሥረ መሠረት የሚጠናከረው። ከታሪክ ጋራ መታረቅና ብሔራዊ/አገራዊ ወደፊት ተመልካችነት የሚዳብረው። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችና ብሔሮች የጋራ ወደፊትና ለብሔረ መንግሥት (Nation State) መገንባትና መደርጀት የሚያስተሳስረው። የሚያስተባብረው። የጋራ ወደፊትን የሚያፀናው።
ታሪክ ከላይ እንደተመለከተው ቢወደድም ቢጠላም ፖለቲካዊ ነው። በኢትዮጵያ ግን አክርሮና ተካሮ በአሁኑ ወቅት ተቃርኖና ተፃርኖ የሌለበት አንድም የታሪካችን ገጽ የለም። አቶ ኢብሳ ጉተማ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት ‹‹ኢትዮጵያዊው ማነው?›› ብሎ በግጥም ያቀረበው ጥያቄ የዛሬም ጥያቄ ሆኖ ያመላልሳል። እንዲያውም ለማለት ይቻላል፡፡ በዛሬው ወቅት አንዳንድ ጽንፈኞች የሚሄዱበት መንገድ ወስዶ ወስዶ መቋጠሪያው ከሚያጥር ሁኔታ ውስጥ እንዳይቀረቅር ያሠጋል። በሌላው በኩል ዛሬ አፍጠውና አግጠው ያሉት በርካታ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጥያቄዎች አስቸኳይ የጋራ መልሶችን ይፈልጋሉ። የዛሬው የፖለቲካ መሪዎች ስለዚህም በአስቸኳይ ሰብሰብ ብለው በአንድ በኩል በጽንፈኞች እየተጠለፈ ያለውን የፖለቲካ ድባብ በአስቸኳይ መግታት አለባቸው። በሌላው በኩል ለአንዳንድ አስቸኳይ የፖለቲካ ማኅበራዊ ጥያቄዎች አስቸኳይ መልሶችን መስጠትና በተግባር ማሳየት አለባቸው።
በእኔ ዕይታ ለዛሬው ሁኔታ የሚበጀው ምናልባት ለአዎንታዊ ለውጥና ለጋራ ወደፊት የቆመው ክፍል የታሪክን ጉዳይ፣ ከዛሬው የፖለቲካ ምዕራፍ ምልልስ ውስጥ ለማስወጣት ቢስማማ ነው። በዚህ ስምምነት መሠረትም በአንድ በኩል በዛሬው አጣዳፊ የፖለቲካ ማኅበራዊ ጥያቄዎች ላይ አትኩረው ሊሠሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል የጋራ ወደፊት ግንባታ መሪነትና አስተማሪነት ሚናቸውን በጋራና በአግባቡ ለመጫወትና ለመወጣት ይችላሉ።
የመሪ አስተማሪነት ሚናቸው በሦስት ዓብይ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ቢፈጸም ጠቀሜታው ከፍተኛ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። አንደኛ በታሪክ ጠባሳዎች ሥፍራ ላይ፣ ሁለተኛ በክፉና በጎ የጋራ ትውስታዎች ሥፍራ ላይ፣ ሦስተኛ በጋራ ወደፊት ሥፍራ ላይ። በሚከተሉት ክፍሎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አተኩሬ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማቅረብ እሞክራልሁ።
የታሪክ ጠባሳ ያልታተመበት አንድም ኅብረተሰብ የለም
ክሎድ ሌቪ ስትራውስ በጥሩ መንገድ እንዳሉት፣ ‹‹ከዝቅተኛው ማኅበረሰብ አንስቶ የታሪክ ሁነቶች ጠባሳ ያልታተመበት አንድም ኅብረተሰብ የለም›› (“There is no society, however primitive, which does not bear the ‘scar of events”, Claude Levi Strauss, Structural Anthropology, 1968)። ታሪካችንን በዚህ መነጽር ብንመለከተው፣ ከኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ ሺሕ የታሪክ ጠባሳዎችን ለመደርደር ይቻላል። ሺሕ የሕዝቦቻችንን ሰቆቃዎች ለመደርደር ይቻላል።
ከቅድመ አክሱማያዊንና አክሱማያዊን ወታደራዊ ዘመቻዎች እስከ ዮዲት፣ ከሦስት ክፍለ ዘመኑ የክርስቲያንና የእስላም ኢትዮጵያ ጦርነቶች እስከ የኦሮሞዎች የሰሜን፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጉዞ፣ ከዘመነ መሳፍንት የመቶ ዓመት ግጭቶች እስከ ቴዎድሮስ ፀረ ካህናት ድርጊቶች፣ ከቴዎድሮስ፣ ከዮሐንስና ከአሉላ የብሔራዊ ነፃነት ትግል፣ ከቴዎድሮስ ፀረ ካህናት ድርጊቶች እስከ ዮሐንስ ፀረ እስላም ድርጊቶች፣ በአፄ ምኒልክ የደቡብ ዘመቻ ወቅት ከተፈጸመው ሰቆቃ እስከ ዓድዋ፣ ከሰገሌ ጦርነት የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት እስካሰፈነው የባለ መሬቶች አገዛዝ፣ ከነዋይ ወንድማማቾች የ1953 ዓ.ም. የቤተ መንግሥት ርሸና እስከ የደርግ የ1960ዎቹ ርሸና፣ ከነጭ ሽብር እስከ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቀይ ሽብርና እስከ ‹‹አንድ ሰውና አንድ ጠብመንጃ እስኪቀር ድረስ›› የነበሩትን ሰቆቃዎችና ጠባሳዎች ሁሉ ለመቁጠር ይቻላል። ዛሬም የሚሊዮኖች መፈናቀል ያተማቸውን ጠባሳዎች ለማከል ይቻላል….።
ሌቪ ስትራውስ ‹‹የሁነቶች ጠባሳ ያልታተመበት አንድም ኅብረተሰብ የለም›› ሲሉ፣ ስለዚህም የታሪክ ጠባሳ ነገር አይነሳ ማለታቸው አይደለም። የታሪክ ጠባሳዎች በተገቢ የሚነሱ ቢሆንም ቅሉ፣ ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፌርናን ብሮዴል አስከትለው እንዳሉት፣ ‹‹የአጭር ጊዜ ሁነቶችን (History of Short Events) ከዘመን ተሻጋሪ ክንዋኔዎች (Long Lasting Movements) ሳይታክቱ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ማለት ነው (At each moment, one has to distinguish between long-lasting movements and short bursts”, Fernand Braudel፣ On History 1982)።
በሌላ አገላለጽ የፖለቲካ ተዋናዮች በታሪክ ዓይንና ሚዛን የአጭር ጊዜ የሆኑትን ሁነቶች ለፖለቲካ ግብ ማራመጃ ሲጠቀሙባቸው፣ ታሪክ ከታሪክነት ይልቅ ፍርድ ቤት ይሆናል። የደጋፊ ማበራከቻና የሥልጣን መጨበጫ መሣሪያ ይሆናል ማለታቸው ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክ የአጭር ጊዜ ሁነቶች የተውትን የታሪክ ጠባሳዎች ከሚደርደርና ቁርሾ ከሚያቋጥር አተራረክ ተላቆ፣ የሕዝቦቿን ዘመን ተሻጋሪ የጋራ ትውስታዎች (Shared Memories) የሚተርክ ቢሆን፣ የሕዝቦቿን የጋራ ወደፊት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በብዙ ክንድ ለማቀራረብና ለማቅለል ይቻላል ማለት ነው። የዛሬዎቹ የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ከታሪክ ጠባሳዎች ይልቅ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ክፉና በጎ የጋራ ትውስታዎች አጉልተው የሚያስተምሩ ቢሆኑ፣ የሕዝቦቿን የጋራ ወደፊት መሠረት ያደላደሉ መሪዎች የመሆን ዕድል አላቸው።
በየነገሥታቱ መዋዕለ ዜና ጠባቂዎች ይጻፉ የነበሩት የየነገሥታቱ ታሪክ በነጋድራስ ገብረ ሕይወት ግሩም አባባል፣ ‹‹የንጉሡን እንጂ የሕዝቡን ጥቅምና ጉዳት አይቆጥሩም›› ነበር። ስለዚህም ስለነገሥታቱና ስለመሳፍንቶቹ እንጂ፣ ስለሕዝቡ ታሪክ (Peoples History) የተላለፈልን ወይም የተጠናውና በጽሑፍ የቀረው ትንሽ በጣም ትንሽ ነው። የጀርመኑ ገጣሚና ድራማቶግ ቤርቶልት ብሬሽት ‹‹ሄር ካ›› በተባለው ስብስቡ ውስጥ ‹‹(እገሌ) ይኼንና ያንን ጦርነት አሸነፈ›› ይባላል። ፈረሱን ውኃ ያጠጣለት ሰውም አልነበረም ወይ? መጫሚያውን የወለወለ ሰውም አልነበረም ወይ? ምግብ ያበሰለለትም ሰውም አልነበረም ወይ?›› እያለና የታወቁ ነገሥታቶችንና ጄኔራሎችን ዝክር እያስታወሰ ብዙ ይጠይቃል።
የስድስትም ይሁን የአምስት ወይም የሦስት ሺሕ ዘመን ጦርነቶችንና የሕዝቦች ንቅናቄዎችን የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ አንጥረኞች፣ ፋቂዎች፣ ሕፃናት፣ ጎልማሶች፣ ሽማግሌዎች፣ እናቶች… እንዴት ኖሩት? እንዴት አለፉት? ብሎ የጠየቀ የታሪክ ድርሰት የለንም። የታሪካችን ትርክት ይብዛም/ይነስም አንድ የጋራ ትርክት ለመሆን የሚበቃው፣ የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ አካቶና ተንትኖ የተጻፈ ታሪክ ሲኖረን ነው። የዛሬውና የመጪው ትውልድ የጋራ ወደፊቱ የሚበራው በነገሥታቶች፣ በኤሚሮች፣ በአባ ዱላዎች፣ በአባ ሞጢዎች፣ በጄኔራሎችና በድርጅቶች መሪዎች… ገድል ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝቦቿ በተጨባጭ በኖሩት ታሪክ ትርክት የደረጀ ሲሆን ነው። አቶ ታምሩ ፈይሳ ገና በ1950ዎቹ ‹‹ድሃው ይናገር›› በሚለው ግሩም ግጥሙ፣
‹‹አንድ ጭብጥ ቆሎዬን ክርሽም አደርግና
አንድ ጣሳ ውኃዬን ግጥም አደርግና
ተመስገን እላለሁ ኑሮ ተገኘና››
ያሰኘው አትዮጵያዊ ታሪክ ሲጻፍና ስንስተማረው ነው። የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ተራሮች ያላነሰ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እውነተኛ ታሪክ ሥራ ከፊታቸው አለ። ያን ጊዜ ነው የኢትዮጵያን ሕዝቦች የስድስትም ይሁን የአምስት ወይም የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ በእውነት የምናውቀው። ያን ጊዜም ነው ዘመናትን የተሻገሩ የጋራ ትውስታዎቻችን ባለቤቶች መሆናችን የሚበራልን። የጋራ ወደፊታችንን በጋራ ለማየት የምንችለው።
ዘመናትን የተሻገሩ የጋራ ትውስታዎች ባለቤቶች ነን
በረዥሙ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ላይ ዘመን ተሻጋሪ ማኅተማቸውን ያተሙት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ዓበይት ክንዋኔዎች ክሎድ ሌቪ ስትራውስ እንዳሉት፣ ‹‹(እነዚያ) የአጭር ጊዜ ሺሕ ፍንዳታዎች የተዋቸው ሺሕ የታሪክ ሰቆቃዎቻችንና ጠባሳዎቻችን›› አይደሉም። ይልቁንም ኢትዮጵያ የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶችን መቀበሏና ሕዝቦቿ ሃይማኖቶቹን የየራሳቸው ማድረጋቸው፣ ከሦስት ክፍለ ዘመን የክርስቲያንና የእስላም ኢትዮጵያ ጦርነቶች በኋላ፣ የሃይማኖቶቹ ተከታዮች በራሳቸው ጥበብ ያደረጁት ተከባብሮና ተደጋግፎ አብሮ መኖር፣ የኢትዮጵያን አገራዊ ጠረፍ በዓለም አቀፍ ካርታ ላይ ለማተምና ለማሳወቅ የተደረጉት የጋራ ትግሎችና በተለይም የዓድዋው የጋራ ድል፣ ብሔራዊ ነፃነትንና ሉዓላዊነትን ለማስከበር የተካሄደው የአምስት ዓመቱ የአርበኞቻችን የጋራ ትግልና ድል፣ ስለዚህም በቅኝ አገዛዝ ሥር ያልወደቅን አንድ ሕዝብ መሆናችን፣ የአፄ ምኒልክ የደቡብ ዘመቻዎችና የፊውዳላዊ ሥልተ ምርት ግንኙነት መደርጀት፣ ለዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትና ወደ ካፒታላዊ ሥልተ ምርት ለመሻገር የተደረጉትና የሚደረጉት ጥረቶች፣ የአፍሪካን ኅብረት ለመገንባት የተደረጉት ጥረቶች፣ ለፊውዳላዊ ሥልተ ምርት መወገድ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት የተደረጉት የጋራ ትግሎች፣ የሰለሞናዊውን አፄያዊ ሥርዓት በሪፐብሊካዊ ሥርዓት ለመተካት የተደረጉት የጋራ ትግሎች ናቸው። ኢትዮጵያ የተበጀችው በእነዚህ ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ ክንዋኔዎች ድምር ነው። በእነዚህ በሕዝቦቿ ሁሉ ድርሻ ለሺሕ ዓመታት በተከናወኑትና ሕዝቦቿ ሁሉ አሻራቸውን ባሳረፉበት ተቀጣጣይ፣ ተከታታይና ተያያዥ የጋራ ታሪክ ክንዋኔዎችና ጉዞ ነው።
የኢትዮጵያ የታሪክ ልሂቃንና ምሁራን በዚህ ረገድ የትናንቱ በዛሬው ላይ ያሳረፈውን፣ የዛሬው በነገው ላይ የሚያሳርፈውን ዘመናት ተሻጋሪ የታሪክ ማኅተም አበጥሮ የማውጣትና የማስተማር ግዴታ አለባቸው። ቢያንስ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ወዲህ ያለውን የታሪካችንን ክንዋኔና ሒደት ተቀጣጣይነት፣ ተከታታይነትና ተያያዥነት በሚያሳይና የሁሉንም ድርሻና አሻራ በሚያጎላ መንገድ ፈትፍተው ሊያቀርቡልን ይገባል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና የማኅበራዊ ሳይንስ ልሂቃንና ምሁራንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሺሕ ዘመን ሺሕ የፖለቲካና የማኅበራዊ መስተጋብሮች ያተሟቸውን የጋራ ትውስታዎች ፈልፍለውና አቀናብረው ሊያቀርቡን ይገባል። ይህ ቢፈጸም የብሔራዊ ማንነታችን መሠረት ፈርጥሞ ይደለድላል። የጋራ ወደፊታችን ግንባታ ማገር ጠንክሮ ይቆማል። ኢትዮጵያዊነት ሥጋ ለብሶ ይፈካል፣ ይደራል። የኢትዮጵያን ሕዝቦች የጋራ ማንነት ካበጁት ከሺሕ ዘመን ሺሕ መስተጋብሮችና የጋራ ትውስታዎች መካከል አንዳንዶቹን ማነሳሳት ተገቢ ነው፡፡
ከሃዳር የሰው አፅም እስከ የመልካ ቁንጥሬ ሰውና የድንጋይ መሣሪያዎች፣ በከሊጋኡዳና የሻቤ ዋሻዎች ካሉት የእንስሳት ሥዕላት እስከ የሸዋ፣ የአሩሲ፣ የሐረር፣ የሲዳሞ ትክል ድንጋያትና እስከ ዳወሮ ግንብ፣ የቅድመ አክሱምና የአክሱማዊያን ሰፊ የንግድ መሰተጋብሮች፣ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ለነብዩ መሐመድ ተከታዮች የተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ፣ ከአክሱም እስከ ላሊበላና ጎንደር፣ ሐረርና ጅማ ያሉት ጥንታዊ ሕንፃዎች፣ የሙሐመድ ነጋሽና የሼኽ ኑር ሁሴን መካነ መቃብራት፣ በኢትዮጵያ ምድር የደረጁት በርካታ አፄያዊ፣ ንጉሣዊ፣ ኤምራዊ፣ ሡልጣናዊና ሞጣዊ መንግሥታት፣ ከሰሜን እስከ ባሌ ተራሮች የቆሙት ጥንታዊ አብያተ ክርስትያናት፣ ገዳማትና መስጊዶች፣ የደጋና ቆላ ሥልተ ምርት ዘይቤዎች ያደረጇቸው የሽማግሌ፣ የገዳ፣ የሴራና የሄር ኢሳ ማኅበራዊ አስተዳደር፣ የሰሜኑ ወገኖች ከመተማ እስከ ሞያሌና ቀብሪ ደሀር ዘልቀው የመሠረቱት የብዙ መቶ ዓመታት ኑሮ፣ የኦሮሞ ወገኖች ከባሌ እስከ ጎንደር ቤተ መንግሥት ያደረጉት ጉዞ ሁሉ የሺሕ ዘመን የጋራ መስተጋብሮችና የኢትዮጵያዊ ማንነታችን የጋራ ትውስታዎች ናቸው። እስከ ዛሬም ያልተዘመረላቸው ሺሕ የኢትዮጵያ ሴቶች ጀግኖች፣ ሺሕ የኢትዮጵያ ብሔሮች ጀግኖች፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ወዝ/ላብ አደር ያካሄዷቸው ማኅበራዊ ትግሎች፣ በኤርትራ፣ በኦጋዴንና ባድመ የወደቁት የመላ ኢትዮጵያ ልጆች፣ ሲኮሩበትና ሲንቁት የማይወደው የአንድ ሕዝብ ሥነ ልቦናዊ ባህሪያችን የቀረፁት የታሪክ ሁነቶች ሁሉ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ብሔራዊ መስተጋብሮችና የኢትዮጵያዊ ማንነታችን የጋራ ትውስታዎች ናቸው።
የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ትምህርትን ለማስፋፋት፣ ለፀረ ቅኝ አገዛዝና ለፀረ አፓርታይድ ትግልና ለአፍሪካ ኅብረት ድርጅት መመሥረት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች እስከ ነዋይ ወንድማማቾች ለሪፐብሊካዊት ኢትዮጵያ የተደረገው ትግል፣ በተደጋጋሚ የተከሰቱት የድርቅ ዓመታት ያስከተሉት ዕልቂትና መፈናቀል፣ ጥላሁን ገሠሠ በድርቅ ላለቁት ወገኖች ‹‹ዋይ! ዋይ! …›› እያለ ባዜመው ስንኝ ከዳር እዳር ያለቀሰው፣ የተማሪው እንቅስቃሴና በ60ኛው ዓመት የፈለቁት ኅብረ ብሔር ድርጅቶች ለባለ ርስት/ጭሰኛ የምርት ግንኙነቶች መሰረዝና ለብሔር/ብሔረሰቦች መብት መታወቅና መከበር ያደረጉት የጋራ ትግል፣ ከጄኔራል ታደሰ ብሩ እስከ ዋቆ ጉቱ፣ ከዋቆ ጉቱ እስከ ወልደ አማኑኤል ዱባለ ለብሔሮች መብት መታወቅና መከበር የተካሄዱት ትግሎች፣ ከደደቢትና ከአርማጭሆ እስከ የግንቦት 1981 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ሙከራና እስከ አዲስ አበባና ዳር ድንበር ድረስ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ኢሠፓ አገዛዝ ለመገርሰስ የተደረጉት የጋራ ትግሎች፣ በመንግሥት ሽብር (State Terror) ከዳር ዳር የተፈጸመው ፍጅት… ሁሉ የጋራ ብሔራዊ መስተጋብሮቻችንና የኢትዮጵያዊ ማንነታችን የጋራ ትውስታዎች ናቸው።
እነዚህና ብዙ ያላነሳኋቸው የሺሕ ዘመናት የታሪክና የማኅበራዊ መስተጋብሮች፣ ኢትዮጵያዊያንን አጥብቀው ያስተሳሰሩና የጋራ ማንነታችንና ምንነታችንን የገነቡና ያደረጁ ብሔራዊ ትውስታዎች ናቸው። የጋራ ብሔራዊ ንብረቶቻችንና እሴቶቻችን ናቸው። ብሔራዊ ማንነታችን ናቸው። እንዲያም ሲል ቆንጆ ፌዴራላዊ ሥርዓትንና የጋራ ወደፊታችን ለመገንባት የሚያስችሉን የጋራ ጡቦች ናቸው።
የጋራ ወደፊት
አተኩረን ብንመለክት አሜሪካኖች፣ ስፓኒሾች፣ ቬትናሞች፣ ቺሊያኖች፣ ሩዋንዳዊያን፣ ሴራሊዮናዊያን፣ ላይቤሪያዊያን፣ ደቡብ አፍሪካዊያን…. እንቋጠር ካሉ ብዙ የሚቋጠሩት አላቸው። ይሁንና የጋራ ወደፊታቸውን አስቀድመው (Pursuing a Shared Vision of their Future) የጋራ ቤታቸውን (ብሔረ መንግሥታቸውን) በመገንባት ተጉ። እኛ ግን ከሦስት ሺሕም ይሁን ከመቶ ዓመታት በኋላ ራሱን የኢትዮጵያን መኖር/አለመኖር መጠየቅ ገባን። አሁንም አተኩረን ብንመለከት ግን በአፄ ምኒልክ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ/ኢሠፓ ዘመናት የነበሩት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማኅበራዊ ዓብይ ቅራኔዎችና የታሪክ ጠባሳዎች በኢትየጵያ ሕዝቦች የጋራ ትግሎች በአብዛኛው ተሽረዋል። ሁለት ትውልድ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍሏል። በሌላ አገላለጽ ዓብይ ቅራኔ ይባሉ የነበሩት የባለ መሬት/ጭሰኛና የብሔር ቅራኔዎች በአብዛኛው ከተሻሩና ከተለወጡ ግማሽ ክፍለ ዘመን ተጠግቷል። ከአፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ የተተከለው የባለመሬት/ጭሰኛ የምርት ግንኙነት ተሽሯል። የኢትዮጵያ ብሔሮች ባህላቸውን ማዳበር፣ በቋንቋቸው ማስተማርና መፍረድ፣ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ከጀመሩ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ ሆኗል።
ይህንን ማለት ግን የተሻሩት ሥርዓቶች ቅራኔዎች ቅሪቶችና ርዝራዦች በነዋል፣ ጠፍተዋል፣ በዛሬው ሁኔታ ላይ ተፅዕኖና ጫና የላቸውም ማለት አይደለም። የተለወጡ ሥርዓቶች፣ ቅራኔዎች፣ ቅሪቶችና ርዝራዦች እንኳን ትናንትና በተለወጠችው ኢትዮጵያ ቀርቶ አብዮታቸውን ከዛሬ መቶና ሁለት መቶ ዓመታት በፊት ባካሄዱት አገሮች ውስጥም አሉ። በእንግሊዝ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሞናሪኪስቶችና በሪፐብሊካኖች መካከል የሚካሄደው ትግል እስከ ዛሬ ይካሄዳል። የፈረንሣይና የሩሲያ ሞናሪኪስቶችም እስከ ዛሬም አለን እንዳሉ ናቸው። የአሜሪካ የ18ኛው ክፍለ ዘመን አብዮት ከተካሄደ 250 ዓመታት ቢያልፉም፣ የነጮች የበላይነት አቀንቃኝ ክፍሎች ቅሪት እስከ ዛሬም አልተወገደም። ይሁን እንጂ የዛሬው የየአገሮቹ ዓብይ ቅራኔዎች ምንጭ፣ የዛሬው የየአገሮቹና የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እንጂ፣ የትናንትናዎቹ ቅራኔዎች፣ ቅሪቶችና ርዝራዦች አይደሉም። የትናንትናዎቹ የታሪክ ጠባሳዎች አይደሉም። ይህ ቢሆን ጀርመንና እስራኤሎች፣ አሜሪካና ቬትናሞች፣ የደቡብ አፍሪካ ነጮችና ጥቁሮች… በአንድ ጠረጴዛ የሚቀመጡበት ምክንያት የለም። ኢትዮጵያዊያንም በጭስ ጋዝ ከፈጇቸው ጣሊያኖች ጋራ የሚቀመጡበት ምክንያት የለም።
የ1960ዎቹ ትውልድ ከእነ ድክመቱና ስህተቶቹም ቢሆን፣ የባለ ርስት/ጭሰኛ የምርት ግንኙነትን ታሪክ አድርጎ አልፏል። የብሔሮች መብት እንዲታወቅና እንዲከበር ባደረገው ትግል፣ የኢትዮጵያን ብሔሮች ጥያቄ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ አጀንዳ ላይ አስቀምጦ አልፏል። ከእነ ድክመቱና ስህተቶቹም ቢሆን፣ በጋራ ለመኖር የሚያስችል ፌዴራላዊ አስተዳደር ቆሟል። የዛሬው የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ስለዚህም ለዛሬና ለነገ በበጎ የሚተርፍን ታሪክ በመሥራት እንጂ፣ ትናንት በተሻሩት የትናንትና ታሪክ ቅራኔዎችና ጠባሳዎች ቆፈን ቆፍድደው ቅርሾ በመቋጠር፣ በመቃቃር፣ በመናቆርና በመጋጨት የዛሬውን ትወልድ ጊዜና ሐሳብ የሚያባክኑበት ምክንያት የለም። ተግባርና ኃላፊነታቸው ይልቁኑ በተገኙት አዎንታዊ ድሎች ላይ ቆመው የጋራውን ወደፊት በጋራ መገንባት ነው። ጉድለቶችን አርመው የጋራውን ወደፊት ማቆንጀት ነው። በሌላ አነጋገር ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ ነው። ተግባርና ኃላፊነታቸው፣ ስለዚህም የቀረውን ግማሽ የመሙላት ነው። ቆመው የሚገኙት ሊያባክኑት ከማይገባቸው የታሪክ አጋጣሚ ፊት ነው። በአንዱ ወይም በሌላው ፅንፈኛ ከተረቱ፣ እንኳን ለልጅ ለጆቻቸው ለእነሱም የሚተርፍ ምድርና ጎጆ ባለቤት አይሆኑም።
ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጥር አንድ ለአንድ ስብሰባ ባሰሙት ንግግርም፣ ‹‹ዕውቀት ሲንሸዋረር ገነትንም እንድንጠላው ያደርጋል›› ብለው ነበር፣ እውነት አላቸው። መምህራን፣ ምሁራን፣ ልሂቃን፣ ጋዜጠኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ወላጆች፣ የእምነት አባቶች፣ የብሔር መብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ ተዋናዮች፣ . . . ሁሉ የብሔራዊ መግባባት አጎልባቾችና የጋራ ወደፊት ገንቢዎች እንጂ፣ ‹‹የዕውቀት አንሸዋራሪዎች›› መሆን የለባቸውም ማለታቸው ይመስለኛል። ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ብርጭቆው ግማሽ ጎደሎ ነው እያሉ የሚያጨልሙ፣ የሚያናቁሩና የሚያጋጩ የፖለቲካ ተዋናዮችን አይደለም። ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ ነው እያሉ የጎደለውን ለመሙላት የሚጥሩ የለውጥ አርበኞችን ነው። የትናንቱን ጠባሳዎች አክመውና አጠግገው የነገይቱን አዲሲትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አብርተው የሚመሩ መሪዎችን ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡