Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትመንግሥትና ሃይማኖት ድንበራቸው የት ነው?

መንግሥትና ሃይማኖት ድንበራቸው የት ነው?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኝነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት የትኛውም ዓይነት ሃይማኖት ፖለቲካ ሆኖ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት (ስቴት) ላይ ሊወጣና መንበረ መንግሥቱን የእምነቱ መሣሪያ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሃይማኖት ፓርቲ ሊሆን፣ ፓርቲም የሃይማኖት አቀንቃኝ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል በሽግግሩ ወቅት ከብሔርተኝነት ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ቡድን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ በሕግ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዚያን ዓይነቱን ቀዳዳ ደፍኖታል፡፡ ያ ቀዳዳ ክፍት ሆኖ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት ገለልተኝነት የሚፈርስበት ዕድልም አብሮ ይኖር ነበር፡፡ በተጨማሪም በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ውስጥም፣ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብ እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡

መንበረ መንግሥትን ከሃይማኖት ወገናዊነት የማራቅ መነሻና መድረሻ ሃይማኖቶችን መግፋት ሳይሆን፣ የትኛዎቹም ሃይማኖቶች በየትኛውም ሃይማኖት የበላይነት (ጫና) ሥር እንዳይወድቁ፣ እኩል ተከባሪነትና የህልውና መብት እንዲያገኙ መጠበቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የቆነጠጠ፣ እምነትን በኃይልም ሆነ በማስገደድ መገደብንም ሆነ ማስቀየርን የሚከለክልና መሠረታዊ የሲቪል መብቶችን በማይሽር ሁኔታ፣ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ የጋብቻ ምሥረታና ዳኝነት ሥርዓቶች ቦታ የሰጠ ሕገ መንግሥት ሊያዋቅር መቻሉ ሁነኛ ጥንካሬ ነው፡፡ እናም ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን ወይም መንግሥት  ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ አንዱ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

- Advertisement -

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትኛውም ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት ነፃነት ሳይጋፋ እምነቱን የማራመድ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የቆሙለትን እምነት በተመለከተ ትክክለኛ አተረጓጎሙና አያያዙ ይህ ነው ብሎ መስበክ፣ የምዕመናንን ግንዛቤና የእምነት አተገባበር በማስተማር ማበልፀግ መብት ነው፡፡ በግድ መጫን ግን መብት መድፈር ነው፡፡ መስበክ መብት እንደሆነ ሁሉ መሰበክም የማይገድቡት መብት ነው፡፡ የተሰበኩትን (የተቀበሉትን) እምነት ጠበቅ አድርጎ መያዝ፣ ላላ አድርጎ መያዝ፣ ወይም መቀየርና አለመቀየር የግለሰቡ መብት ነው፡፡ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ልጆቻቸውን በእምነታቸው ማነፅ መብታቸው ነው፡፡ የወላጅን እምነት ይዞ ለመቆየት ግን ተወላጅ አይገደድም፡፡ እነዚህን መብቶች ለመጣስ ማንም አልተፈቀደለትም፡፡ ማንኛውም ቤተ እምነት ነባር አማኞቹን ይዞ ከመቆየት ባሻገር፣ አዲስ ተከታዮችን ለማፍራት የማስተማር ሥራ ማካሄድን ትርጉም የሚሰጡትም እነዚህ የግል መብቶች መኖራቸውና መረጋገጣቸው ነው፡፡

እናም የእምነት ቡድናዊና የግል መብቶች እንዳይረገጡ መንከባከብ፣ ሌላው ቀርቶ በሌላው ላይ ሲጓደሉ ሲያዩ እንኳ ነገ በእኔ ብሎ መቆርቆር የራስን የእምነት ተቋምና የምዕመናንን መብት የማስጠበቅም ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን መሰሎቹን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ከማስከበር ውጪ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር መወገን የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ወይም ያንን የፖለቲካ ፓርቲ ደግፉ/ተቃወሙ/አውግዙ ብሎ ለምዕመናኖቻቸው መስበክ የሃይማኖት ተቋማትን አይመለከታቸውም፡፡ ምዕመናኖቻቸው የተለያየ የፖለቲካ እምነትና ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በአንድ እምነት ውስጥ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የየቤተ እምነት መሪዎች ኃላፊነታቸው ከፖለቲካ ውገና ገለልተኛ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮቻቸውን ያለ አድልኦ ማገልገል ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት መወጋገን ከጀመሩ ለመንግሥታዊ ሃይማኖት መንገድ ይከፈትለታል፡፡ ፓርቲው ሥልጣን ቢይዝ ድጋፍ የሰጠው ሃይማኖትም ባለ ልዩ መብት ልሁን ባይ ይሆናል፡፡ ወደ ሥልጣን የሚያመራ ወይም ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ ለፖለቲካ ድጋፍ የሃይማኖት መድረክን ከመጠቀም መራቁና ይህም ቀጣይነት ማግኘቱ ሃይማኖት ፖለቲካን እንዳይፈተፍት ይከላከላል፡፡

ይህ ማለት ግን ፖለቲካና ሃይማኖት ጭርሱኑ አይደራረሱ ማለት አይደለም፣ ቢባልም የማይቻል ነው፡፡ ከእምነት ነፃናትና እኩልነት ጋር የተያያዙ መሠረታዊ መብቶች ተደፍረው ይኼንን በማውገዝ መንገድ ላይ የፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ የሆነ ፖለቲካ ፓርቲ አጥፊ ቅስቀሳ አድርጎ ሃይማኖታዊ አምባጓሮ ቢከሰት አነሳሹ ፓርቲ ተወጋዥ ከመሆን አያመልጥም፡፡

መንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትንም የሚያገናኟቸው ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተቋማትን ወደ መንግሥት አካላት ሊወስዷቸው ይችላሉ፡፡ የሃይማኖቶች ሰላም ጉዳይ ሃይማኖቶችንና መንግሥትን ያገናኛሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚኖራቸው የበጎ ሥራና የልማት ዕቅድ ከመንግሥት  የልማት ዕቅድ ጋር ተጋጭቶ ብክነት እንዳይሆንባቸው፣ የልማት ዕቅዳቸውን ከመንግሥት ጋር ቢያገናዝቡ አስተዋይነት ነው፡፡ መንግሥት ከሚያካሂዳቸው (ከሚደግፋቸው) የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥም የሃይማኖት ጉዳይ ተደርገው ሊምታቱ የሚችሉ (የሃይማኖት መሪዎችን ማብራሪያና የቅርብ ድጋፍና መተማመኛ ጭምር የሚሹ) ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በተመለከተም አብሮ መሥራት መጠንቀቅ ይኖራል፡፡

ከዚህ ያለፈ መጠጋጋት ግን ለመንግሥትም ሆነ ለሃይማኖት ተቋማት ጠቃሚ አይደለም፡፡ ወሰንን አልፎ በማያገባ ለመግባትም ያጋልጣል፡፡ በደርግ ዕድሜ ማብቂያ ላይ እነ ሕወሓት በሃይማኖት መሪዎች ‹‹ወንበዴ፣ የአገር ጠላት›› ተብለው እንዲኮነኑ የተደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚያ ዓይነት ጥፋት ዛሬ ላይደገም የሚችለው በሥልጣን ላይ ያለ ገዥ ቡድን/ፓርቲ ለፖለቲካ ዓላማ የሃይማኖት ተቋማትን መገልገያ ከማድረግ ሲፆም፣ የሃይማኖት ተቋማትም መንግሥት የወደደውን መውደድ፣ የጠላውን መጥላት ይገባኛል/ይጠቅመኛል ከሚል የአስተሳሰብ ቅጥር ግቢ ሲወጡ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ወጣቶችና ሕዝቦች ትግል ከኢሕአዴግ ከራሱ ውስጥ በግድ ፈልቅቆ ያወጣው ለውጥና አመራር ድል ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ‹‹በዕርቅ እንተቃቀፍ›› የዓብይ አህመድ መፈክርና ፕሮጀክት ሃይማኖትንም በግንባር ቀደምትነት ያካተተ በመሆኑ ነው፡፡ የለውጡ አመራር፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከቋንቋ ጀምሮ፣ ቋንቋን ጨምሮ፣ ያታከቱ ጠምዛዛ አባባሎችን እርግፍ አድርጎ ጥሎ፣ በሥዕላዊና ሕዝብ አንጀት ውስጥ መጎዝጎዝ በሚችል አያያዝና አይረሴ አገላለጽ ከሕዝብ ጋር መነጋገር ባወቀ አመለካከት በዕርቅ እንተቃቀፍ ብሎ ተዓምር ሊባል የሚችል ጀብዱ የፈጸመው፣ መንግሥትና ሃይማኖትን በማስታረቅ ብቻ አይደለም፡፡ በኦርቶዶክስ ክርስትናም፣ በኢትዮጵያ ሙስሊሞችም ውስጥ የተፈጠረውን፣ ይልቁንም የገዛ ራሱ ፓርቲ ገዥው ፓርቲ በማናለብኝነትና ይሁነኝ ብሎ የፈጠረውን የጥላቻና የክፍፍል ጎራ በመናድም ጭምር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን (ሕዝብና መሪ ሳይለይ) ባስደመመ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት፣ (በእግዚአብሔር፣ በሲኖዶስ ሕግ፣ በቁርዓን በሸርዓ ቢባል እንቢ ያለውን) የክርስቲያኑን፣ የሙስሊሙን፣ የአገር ውስጡን፣ የውጭ አገሩን ሰው ሁሉ የውስጥ ፀብ ያፈረሰ ዕርቅና አንድነት አመጣ፡፡ ይህም እግረ መንገዱን ጭምር በየቦታውና በየዘርፉ የመነጋገሪያ መድረኩን፣ የንግግር፣ የእምነት የመሰብሰብ የመደራጀት ነፃነቱን አሰፋ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና ከሃይማኖት ከእምነት ጋር የተያያዙ ሌሎች ያልተሞከሩ፣ ያልተፈተሹ፣ ያልታሰሱ፣ የነፃነትና የመብት ጥያቄዎችንና አጠቃቀማቸውን ጠራ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥም የከዚህ ቀደሙ የኢሕአዴግ የእኔ ብቻ ልክ አገዛዝ፣ እኔ ብቻ ካልገዛሁ የአገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ዘዬ ያስከተለው የሃይማኖት የመንግሥት አያያዝ ብዙ ጭቃ ወጣ፡፡ ብዙዎቹ ተበዳዮችም፣ ከሁለቱም ወገኖች ቂም በቀልን ተሻግረው፣ ቁርሾን ትተው፣ በጋራ የአገር ዴሞክራሲ ንጣፍና መደላድል ላይ ተጋባዥ እንግዳ ሆነው ሳይሆን ያገባናል ብለው በንቁ ተሳታፊነት ይታያሉ፡፡

የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደ ዜጋ ለአገር ጉዳይ ጎልተው ከሚታዩበት ንቁ ተሳትፎ ግንባር ቀደም ሚና በተጨማሪም፣ ያለፈው ክፉና የመከራ መንግሥታዊ አያያዝ በማንኛቸውም ሁኔታ እንዳይደገም መከላከል የሚችል በልዩ ልዩ የሪፎርም ሥራዎች ውስጥ በየፊናቸው ተሰማርተዋል፡፡

አንድ ዓመት የሞላው ለውጥ በሒደት ውስጥ በተለይም ከሕዝብ ድጋፍ አኳያ አሳሳቢ ውጣ ውረዶች ቢያጋጥመውም፣ ለሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት የተፈነጠቀው ዕድልና የተከፈተው በር በጭራሽ እንዳይቀለበስ ዴሞክራቶችም፣ አማኞችም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኃላፊነታችንን የመወጣት ተግባርም አርቆ አስተዋይነትን፣ ንቁነትን፣ የሕዝብን የማትመምና ድጋፉን የመቀዳጀት ተግባርን፣ ለዚህምና ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መረማመድን ይጠይቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተደጋግሞና በሰፊ እንደተገለጸው የመንግሥትንና የሃይማኖትን መለያየት ይደነግጋል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም፡፡ አይኖርም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ይላል፡፡ የዚህን አንደምታና ትርጉም ከላይ ተመልክተናል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 የእኩልነት መብትን (የሃይማኖቶችን እኩልነት ጭምር) ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 27 ደግሞ የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ድንጋጌን ከተጠቀሱት የመብት (የእኩልነት፣ የሃይማኖትና የእምነት መብትና ነፃነት) ድንጋጌዎች የሚለየው አንቀጽ 12 (የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ድንጋጌ) በተለየ ምዕራፍ በሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች ምዕራፍ ስለሚገኝ ነው፡፡

ይህን ያህል የመሠረታዊ መብትና ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥታዊ መዋቅርና ሥርዓት ጋር ግንኙነት ያለው በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል የተበጀ አጥር ሲበዛ መከበር፣ በጥንቃቄና በስስት መታየት አለበት፡፡ የሃይማኖቶች እኩልነትና ነፃነት የሚረጋገጠው፣ ሃይማኖቶችም የመንግሥት ፖለቲካ መሣሪያ ከመሆን የሚመከቱት በሃይማኖትና በመንግሥት መካከል ያለው ‹‹አጥር የከለለው›› ግንኙነት የማይደፈር ከሆነ ብቻ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እውነቱን ለመናገር ‹‹የሰማይ መላዕክት፣ የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊያውቁት ይቻላቸው›› ያልነበረ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለሲኖዶስም ለሸሪዓ ሕግም አልገዛም፣ ከእሱ በታች አልሆንም ያለውን ግትርነትና ፀበኝነት እንዲሟሽሽ አድርገዋል፡፡ የመንግሥትንም (የገዛ ራሳቸውን ፓርቲ) የሕገ አስከባሪነት ገመና አጋልጠዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ጋር መነጋገርንም ያወቀ አንደበተ ርቱዕነታቸውና አያያዛቸውም፣ የሕዝብን ልብ የመርታት ማንም አግኝቶት የማያውቅ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ሲናገሩ፣ መልዕክት ሲልኩ (በጽሑፍም በቃልም) ከሁኔታው፣ ከአጋጣሚው፣ ከተደራሹ ጋር የተያያዘና የሚገጥም በ‹‹ዕውቅ የተሰፋ›› ንግግር ማድረግ ችለውበታል፡፡

ምናልባትም በንግግር፣ በመልዕክት ጸሐፊዎቻቸው (Speech Writers) የሚታገዘው ይህ ችሎታና አፈጻጸም ግን እስካሁን በዝርዝር ከተነጋገርንበት አንቀጽ 11 ጋር የሚጣላ መንሸራተት እንዳያጋጥም መሥጋት በከፉ መታየት የለበትም፡፡

የዶ/ር ዓብይን ብዙዎቹን ምናልባትም ሁሉንም አደባባይ የወጡ ንግግሮች ሰምቻለሁ፡፡ በፓርላማ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት ሲቀበሉ ያደረጉት ንግግር፣ ከያዘውና አሁን እየተለመደ የመጣው ‹‹ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ›› ጀምሮ የመጋቢቱ ለውጥ አንድ ዓመት አከባበር ላይ ‹‹በመጀመርያ ዘለዓለም እንደ አሁን የሆነለት፣ ትናንት ዛሬና ነገን አስተሳስሮ ለዚህች ድንቅ መዓልት ያበቃን ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን›› ንግግራቸውን የከፈቱበት መንደርደሪያ በተለይም ከኢትዮጵያ ባህል፣ ያለፉት 45 ዓመታት፣ የመጨረሻዎቹ 27 ጭምር ካቋቋሙት ልምድ ጋር እየተገናዘቡ ቢታዩና ያልተፈለገ አፀፋዊ ምላሽ እንዳያመጡ ብርቱ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡

አሜሪካኖች ያንን በመሰለ ከ200 ዓመት በላይ በዘለቀ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ገንዘባቸው ላይ In God We Trustss ቢሉ፣ ፓርላmaው በሚሰማው ንግግርና በሚያስፈጽመው መሀላ God Bless America, So Help Me God ቢሉ አፀፋዊ አደጋ የማያስከትል ሆኖ በመቋቋሙ ነው፡፡ አገራችን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያላቸውን ‹‹መሃላ››ዎች እንኳን መሃላም ቃል ኪዳንም አትላቸውም፡፡ ‹በቃል እገባለሁ› ተዳፍነው ቀርተዋል፡፡ መለኪያችን ከዚህ በፊት የተጓዝንበትና የደረስንበት እንኳን ‹‹ደረሳችሁ›› ዓይነት ‹‹ማስመሰል›› ባይሆንም፣ ተመሳሳይ ነገር ግን ተቃራኒ ነገር ውስጥ ላለመግባት ግን ከወዲሁ ማሰብ ጠንቃቃነት ነው፡፡ የደረጃ መለኪያችን ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ነው፡፡ በተለይም ሃይማኖታዊ በዓል በመጣ ቁጥር መንግሥት የሚያስተላልፈው ስፋት ያለው የመልካም ምኞትና የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ፣ ሁሉንም ‹‹እኩል የማስደሰት›› የማዳረስ ጣጣና ፈተና ውስጥ መግባት የለበትም፡፡

ሌሎችም ሲነገሩ እንዲሁ፡፡ የሃይማኖት በዓላትን መሠረት አድርገው መንፈሳዊ መሪዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ በእግረ መንገድ ‹‹አገራችንን ይባርክልን፣ ሰላማችንን፣ ፍቅራችንን፣ ዕድገታችንንና ልማታችንን ያብዛልን›› የሚሉ ዓይነት መልካም ምኞቶችን ከመግለጽ ወጣ ያሉ፣ ‹‹የዴሞክራሲ ግንባታን፣ የልማት መስመርን የማስቀጠል›› ወይም በመጪው ምርጫ በንቃት የመሳተፍ ጥሪዎች ሲሰነዘሩ ያጋጥማል፡፡ የዚህ ዓይነት ወጋዊ ጥሪዎች መንግሥትንም ሆነ መርሐ ግብሮቹን ከሚበጁት ይበልጥ ለሐሜት የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የዚህ ዓይነት ጥሪዎች በውስጠ ታዋቂ የሚያመላክቱት ተቃራኒ መልዕክትም አለ፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ምዕመናን በንቃት እንዲሳተፉ እናሳስባለን ባይነት በራሱ፣ ነገ ደግሞ በምርጫው አትሳተፉ ብሎ ለሚል ጥሪ ፈቃድ የሚሰጥ ነው፡፡

የመንግሥት አካላትንም ሆነ የሃይማኖት ሰዎችን ሊያሟልጭ የሚችል ሌላ እውነታም አለ፡፡ ዛሬ ያለው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ካርታ ከበፊቱ (በደርግ ዜና ከዚያ በፊት ከነበረው) በጣም የተለየ ገጽታ አለው፡፡ ከአካባቢ ባለ የመንግሥት ሥልጣን ውስጥ የየአካባቢው ብሔረሰባዊ ዓብይ ጥንቅር እንደሚንፀባረቅ ሁሉ፣ የዋናዎቹ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች የክምችት ገጽታም ተንፀባርቆ ይታያል፡፡ በክልላዊ የሉዓላዊ ባለቤትነት እሳቤ ውስጥ ንዑሳንን/መጤ ማኅበረሰቦችን የመዘንጋት ወይም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ባለመብትና ባይተዋር የማየት ችግር እንዳለ ሁሉ፣ በሃይማኖትም መሰል ችግር ያጋጥማል፡፡ በተለይ ውጥንቅጥነት በሚሳሳባቸው ሥፍራዎች ዘንድ ባለ ማኅበረሰባዊ ይዞታና የመንግሥት አካላት ውስጥ የአንድ ዓይነት ሃይማኖት ሰዎች ደምቀው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በዚያ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ የገለልተኝነትን ኃላፊነት የመዘንጋት ድጥ አስተዳዳሪዎችን ሊፈታተናቸው፣ ጭራሽ ሳይታወቃቸው ኃላፊነታቸው ሊያጠፋባቸውም የሚችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ በአካባቢው ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ተከታዮችም የራሳቸውን ሃይማኖት የአካባቢው ባለቤትና ዋና ባለመብት አድርገው ቆጥረው፣ ከዚያ ውጪ ያሉ እምነቶች መብት በእነሱ እጅና ችሮታ ውስጥ ያለ አድርገው የሚያስቡበት ስህተት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

የዚህ ዓይነቱ የበላይነት ስሜት የእብሪትም መፍለቂያ ነው፡፡ ላሽቆጥቁጥ፣ በማነስህ ልክ መብትህ አንሶ ይሠፈርልህ የሚል አፈናና መተናኮል ሊያፈልቅ ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ጽንፈኞች ይወዱታል፡፡ በአንድ ወቅት በጅማና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባባቢዎች፣ በመንግሥት መረጃ መሠረት ሃዋርጃ የተባለ ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድን የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ግፍ ለመፈጸም የደፈረው፣ የዚህ ዓይነት አካባቢያዊ የባለቤትነት ትምክህትን መንደርደሪያ አድርጎ ነበር፡፡

የሌላውን የእምነት ነፃነት ሳይታናኮሉ እምነት በግልም ሆነ በቡድን የማራመድ፣ የማምለክ፣ የመማርና የማስተማር መብት በቁጥር የማይገደብ (የማይሸረፍ) እኩል መብት መሆኑ ሲዘነጋ፣ የሃይማኖት ሰላምም ዋና ውሉን ሳተ ማለት ነው፡፡ የእምነት እኩልነትን የማስከበርና የመብት ጥሰቶችን የሚከለክል ጤናማ (ኃይጅናዊ) አመለካከት፣ ጨዋ የሃይማኖቶች ግንኙነትና የእምነት አተገባበር የማዳበር ሥራዎች መሬት መንካት ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ እንዲሁም በየትኛውም ደረጃ ያለ የአስተዳደር እርከን ሕዝብን ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ ለሚደርስ ጥፋት ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡

ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና በኩል የሚመጣ ጽንፈኝነት ነገረኝነት የሚጀምረው ከአመለካከቱ ነው፡፡ ሌሎች እምነቶች ከእሱ አጠገብ እኩል የመኖር መብት፣ እኩል ክብር ያላቸው ሆነው አይታዩትም፡፡ በራሱ ሃይማኖት ውስጥ ሳይቀር ለዘብተኛ አማኝ ወይ ሌላ ስንጣሪ መኖር ብሎ ነገር አይቀበልም፡፡፡ “ትክክልና የተቀደሰ” ከሚለው እምነት ውጪ ያለ ሁሉ የክህደት/የርኩሰት ወይም የሰይጣን ዓለም ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት አያኗኑርም፡፡ ‹‹የገሃነም/የሳይጣን›› ዓለምና ‹‹የቅድስና›› ዓለም እንዴት ይኗኗራል? ከሰይጣን ማደሪያ ጋር መነካካት፣ መርከስ ወይም ከገሃነም ጋር መነካካት ይሆናል፡፡ ይህን የእርኩሰትና የዘለዓለም ሞት ሠፈር የማስወገድ፣ የማፅዳትና በቅድስና የመተካት ኃላፊነትና ተግባር ከሰማይ የተሰጠው ደግሞ ለእሱ (ለጽንፈኛው) ነው፡፡ ሲሰብክ እንኳ ድርጊቱ ሆኖ የሚታየው ማስተማር ሳይሆን፣ ከዘለዓለም እሳት/ሞት የማትረፍ ሥራ ነው፡፡ ቅድስና እኔ ዘንድ ብቻ ያለ (ሌላው ሁሉ የእርኩሰት ጎዳና) ብሎ የሚል እምነት ንዑስ እንኳ ቢሆን ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ ተሰቅዘውለት እሱ ለመናኘት፣ የሥርዓተ ትምህርት ሰፋሪና የትምህርት ቤቶች ቃኚ ለመሆን ዕድሉን ቢያገኝ አያቅማማም፡፡ የዚህ ዓይነት ጽንፈኛ ፍላጎቶች በኦርቶዶክስ ክርስትና፣ በፕሮቴስታንት ክርስትና ፍልቃቂ እምነቶች ሆነ በእስልምና ውስጥ ያጋጥማሉ፡፡

ለማዊ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት በሃይማኖት እንዲቃኝ፣ ፀሎትና ስግደት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲገባ መፈለግ የሃይማኖት ጭቆናን፣ የመንግሥትና የሃይማኖት ዝምድናን መልሶ መጥራት ነው፡፡ እንደ አካባቢው ሁኔታ ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ትምህርት ቤት ውስጥ ይግባ ቢባል በዚያ አካባቢ ያሉ ንዑስ ሃይማኖቶች ተጨቋኝ ይሆናሉ፡፡ አንዱ ጋ ዋና የሆነ ሃይማኖት ሌላ ቦታ ላይ ንዑስ ሆኖ ይገኛልና ጭቆናው ለራሱም መድረሱ አይቀርም፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች በየበኩላቸው የሚሰማሩባቸው የየብቻ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሯቸው ማሰብ፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ሊሟላ የማይችል ቅዠት ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ የትምህርት ቤት ልዩነት ሳይኖር ለየትኛውም እምነት ተከታዮች የፀሎት፣ የስግደትና የእምነት ክበብ መብት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተፈቀደ ይሁን ማለትም የትምህርት ሥራ ይመሳቀል፣ የትምህርት ቤቶች ሰላም በእምነት ንቁሪያና መሸራደድ ይበጥበጥ ብሎ መልቀቅ ነው፡፡

ጭንቀታችን ጽንፈኛ ፍላጎት ቦታ አግኝቶ እንዲረካና እንዲያድብ ከሆነ ጽንፈኝነት አልገባንም ማለት ነው፡፡ ለጽንፈኝነት የሚታየው መብትና የመብት መጣስ ብሎ ነገር ሳይሆን ገሃነምና ገነት ነው፡፡ ጽንፈኝነት መብት አክብሮና ተቻችሎ ኗሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ገሃነም የመግባት መብትን ከማክበር ይልቅ፣ በግድ ገነት ማስገባት ይበልጥበታል፡፡ ሃይማኖት ለወጥክ ብሎ ከዝምድና ማግለልና ካልገደልኩ ባይነት የሚከሰተው ለውጡን መብት አድርጎ ከማየት ይልቅ፣ ወደ ቅስፈት (እርኩሰት) መግባት አድርጎ ከመቁጠር ነው፡፡ ለምሳሌ እስላማዊ ተብሎ የሚጠራው ጽንፈኝነት ባለጉልበት በሆነበት አካባቢ፣ እምነትን በግድ ማስቀየርና ማባረር ሲከፋም ግድያ የሚያካሂደው ለዚህ ነው፡፡ በየትኛውም ሌላ ሃይማኖት ውስጥ ያለ ከሌላው ሃይማኖት ጋር ጎን ለጎን ተከባብሮ ከመኖር ይልቅ፣ ሃይማኖታዊ አብዮት መሳይ አጥለቅላቂ ለውጥ ማምጣት የሚታየው፣ የአንዱ ወይ የሌለው እምነት ተከታይ መሆንን ከመብት የማይቆጥር፣ ከእሱ ውጪ ያለውን ሁሉ የክህደትና የቅስፈት መናኸሪያ አድርጎ የሚመለከትና አትቀላቀሉ አትነካኩ ብሎ የሚቀሰቅስም አደገኛ የጽንፈኛት ዝንባሌ ነው፡፡ በሰይፍ ከሚቀጡትና እምነት ከሚያስቀይሩት የሚለየውም በደረጃ ብቻ ነው፡፡

በትምህርት ቤቶች ውስጥ እምነቶችን የማራመድ ነገር ያሳሰበን ለመብት ማሰብ ከሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ መብቱን ማስከበሪያ መንገዶች መቼ ጠፉና? ሞልተዋል፡፡ መኖሪያ ቤት፣ ቤተ አምልኮ፣ የሃይማኖት ትምህርት ቤት፣ የሃይማኖት ጋዜጣና መጽሔት፣ ወዘተ ሁሉ አሉ፡፡ ተማሪዎቻችንን (ልጆቻችንን) በሃይማኖታዊ ግብረ ግብነት ለማነፅ አማራጮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዓለማዊ ትምህርትም ከሥነ ምግባር ጋር አይቃረንምና ትምህርት ቤቶች ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር መጣበቅ ሳያስፈልጋቸው፣ ተማሪዎቻቸውን በመልካም ምግባር ማነፅ ይችላሉ፣ በደንብ ከተሰናዱ፡፡

ከትምህርት ቤቶች ባሻገር፣ ሃይማኖታዊ ያልሆነ የሥራ ገበታን ለእምነት ማሠራጫነት መጠቀም አደገኛ የምግባር ጉድለት ነው፡፡ የገበያና የመጓጓዣ ሠልፎችን፣ አውቶቡሶችን የስብከት መድረክ አድርጎ መጠቀም፣ ወደ ሥራ የሚበር ሰውን ‹‹አንዴ ላናግርህ›› ብሎ ወይም ቤት አንኳኩቶ ልስበክህ ማለት ከትንኮሳ ይቆጠራል፡፡ በእነዚህ ዓይነቶቹ ሰብከቶች ውስጥ አልፈናል፡፡ ስድድብ፣ ንጭንጭ፣ የድብደብ ክስቶችም ያጋጥማሉ፡፡ አግባብ ባልሆነ ቦታ ልስበክ ከመባሉ ይብስ አሰባበኩም ይበልጥ ‹‹ወረራ›› ነው፡፡ እምነትና ፅድቅን ከቶ ከዚህ በፊት ሰምቶ ለማያውቅ ከኃጢያትና ከዘለዓለም ሞት እኔ ላድናችሁ፣ ሌላ መዳኛ የላችሁም የሚል የዚህ ዓይነት አተያይ ‹‹እኛን ያልዳንን አድርጎ መዳቢ አንተን ማን አደረገህ?! እኛ ሃይማኖት የለንም?!” የሚል ቱግታን ይቆሰቁሳል፡፡ መንገድ ላይ እምነትን ማሠራጨት ቢያስፈልግ እንኳ፣ የሚሻ እንዲወስድ ጽሑፎችን በመደቀን ብቻ መቆጠብ ጨዋነትን የተላበሰ ነው፡፡

አግባብ ባለው ሥፍራና የመገናኛ ዘዴ እምነትን በመስበክ ረገድም፣ የሌላውን እምነት በመንቀፍ ላይ መመሥረት በእኛ ሁኔታና የሥልጣኔ ደረጃ ጤናማ አይደለም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የትኛውንም ሃይማኖት ከመተቸትም ባለፈ ማሽሟጠጥም የንግግር ነፃነት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሃይማኖት ስላልተቸንና ስላላሽሟጠጥን የሚጎድልብን የለም፡፡ ነቀፋና ሽሙጡን እንሞክር ብንል ሃይማኖትን በሃይማኖት ላይ እስከ ማስነሳት የሚሄድ ጣጣ ልንጎትት እንችላለን፡፡ ምዕራባውያኑም ከሌሎች ጋር ተደማምሮ አሽሟጠውና ተሳልቀው ጽንፈኛ አሸባሪነት ጥርስና ጥቃት ውስጥ ከመግባት በቀር ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ከፋይዳ ቢስ ሽሙጥ ፈንታ፣ ዴሞክራሲና የሐሳብ ነፃነታችን ለምን በጽንፈኛ አሸባሪነት ተጠመደ? ከወጥመዱስ እንዴት መውጣት ይቻላል? በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ላይ ቢያናጣጥሩ ፍሬው ለሌላውም የሚፈይድ ውጤት ባመጡ ነበር፡፡

የሃይማኖት መተቻቸት ፀብ ያማዝዛል ብሎ መጠንቀቅና ትችትን በዱላና በጥይት መቅጣትን ተገቢ ብሎ መፈጸም በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ መምታታት የለባቸውም፡፡ ነቀፋና ዘለፋ፣ አምባጓሮ የመጀመር ወይም በቱግታና በጋጋታ የመቅጣት መብትን አያጎናፅፉም፡፡ የዚህ ዓይነት ዕርምጃ (በአንድ ሰው ተፈጸመ፣ በሺሕ ሰው) መብት የሚረግጥ ወንጀል ነው፡፡ እምነቴ ወይም ብሔረሰቤ ተነካ ብሎ በጋጋታና በግንፍልነት የኃይል ዕርምጃ መውሰድን ተገቢ መብት አድርጎ ማሰብ እጅግ አደገኛ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ተሠራጨ ማለት ወደ ሕግ መሄድን የጋጋታና የቱግታ ዕርምጃ እየተካ በየአሉባልታው ሁሉ ዘራፍ እንዲል መሠረት አገኘ ማለት ነው፡፡ የጋጋታ ዕርምጃ አዙሪት ውስጥ ከተገባ በሕግ የተፈቀደ መብት እስኪመስል ድረስ ሊያምስ ይችላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...