ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ ሁለተኛውን የትንሳዔ በዓል ልናከብር ነው፡፡ በዘንድሮው የትንሳዔ በዓል በዋዜማ ሰሞን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቻይና ተጉዘው በቆይታቸው ስለተገኙ መልካም ነገሮች የሚዘግቡ ዜናዎች እየተደመጡ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በቻይና ቆይታቸው ወቅት ተስፋ የሚሰጡ ዜናዎችን እንድናደምጥ ካደረጉ ክዋኔያቸው መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው፣ ዋነኛዋና ትልቋ አበዳሪያችን፣ የዕዳ ሸክማችንን በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ መስማማቷ ነው፡፡ ከዘገባው መረዳት እንደሚቻለው ቻይና ለኢትዮጵያ ለሰጠቻቸው ብድሮች እስከ 2018 ያለውን ወለድ ብቻ ሙሉ ለሙሉ ሰርዛለች፡፡ በዕዳ ጫና ለጎበጠችው አገራችን ይህ ትልቅ የምሥራች ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ይህ እንዲሆን ያደረጉት ጥረት ምን ያህል ውጤት እንዳለው አሳይቶናል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከዚህ ቀደም የፈጸሟቸው ተግባራትም ኢትዮጵያን ዕዳዋን በወቅቱ መክፈል የተሳናት ተብላ ከመፈረጅ የታደጓት ስለመሆናቸው ማስታወስ ግድ ይለናል፡፡ ከዚሁ ዘገባ ጎን ለጎን የ1.8 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ከቻይና መገኘቱን መስማታችንም የቻይና ጉዟቸው በውጤት የታጀበ ስለመሆኑ ያሳየ ነው ማለት ይችላል፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ ከተለያዩ ምንጮች በልመና ጭምር የተገኘው የውጭ ምንዛሪና ዕዳችንን ለማቃለል የተደረጉት ውጤታማ ሥራዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ትገባ ነበር? የሚል ጥያቄ እንድናቀርብ ያስገድደናል፡፡
እንደ አገር አምርተን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ካገኘነው ገቢ በላይ በልመናና በዕርዳታ የተገኘው ገንዘብ ብልጫ ያለው መሆኑ እንደ አገር ተጋርጦብን የነበረውን ችግር በጊዜያዊነትም ቢሆን ፈትቶ ለመራመድ አስችሎናል፣ ይህም ግነት አይደለም፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ወራት በፊት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በለውጡ የመጀመርያ ሰሞን አገሪቷ አጋጥሟት የነበረው አደገኛ የሚባል የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተፈታው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እንደነበር በይፋ ገልጸው ነበር፡፡
አሁንም ችግሩ የበረታ በመሆኑና የወጪ ንግዳችን አሁንም ከድጡ ወደ ማጡ በሆነበት ወቅት የውጭ ምንዛሪ ችግሩ እንዴት ሊቃለል ይችላል? ለሚል መጠይቅም አሁንም አንዱ አማራጭ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርገዋቸው እንደነበሩ ዓይነት ጥረቶች አሁንም መደረግ አለበት የሚል አንደምታ ያለው ምላሻቸው አስገርሞ ነበር፡፡ ስለዚህ ከሰሞኑ ከቻይና የተሰጠው የብድር ወለድ ስረዛና ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና የወጣ መሆኑ ሲሰማ የዚህ አገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትከሻ ላይ መውደቁ ብቻ ሳይሆን ልመናቸው መሳካቱን ያሳያል፡፡ ለችግሮቻችን ግን እንዲህ ባለው ጥረት ብቻ መዝለቅ እንደማይቻል ማሰቡም ተገቢ ነው፡፡
ነገር ግን አሁን ባለው የወጪ ንግድ ገቢ አንፃር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንን ለማሟላት የግድ በርካታ አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችሉ አመራሮችን መተግበር ጊዜ የማይሰጠው ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን ለማሳደግ ደግሞ በተወሰኑ አካላት የሚደረግ ጥረት ብቻ የትም የማያደርስ በመሆኑ አሁንም የወጪ ንግዱ ጉዳይ ከገባበት ደካማ አፈጻጸም በማውጣት የተሻለ ውጤት እንዲፈጸም ለሚያስችል አሠራር ካልተዘረጋ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰሞኑንም የተለያዩ መረጃዎች የሚነግሩን የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እየቀነሰ መቀጠሉን ነው፡፡ አገሪቷ ዘንድሮ በዘጠኝ ወር ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከቀደሙት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ ያሽቆለቆለ ነው፡፡ ይህ አኃዛዊ መረጃ አሁንም የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች አለመሠራታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም የአገርን የወጪ ንግድ ከፍ ለማድረግ እየሠሩ ያሉት ሥራ የሚያመረቃ ያለመሆኑን ነው ለአገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲህ መቀጠሉ አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ከሚባልባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ አገሪቱ በሬሚታንስ የምታገኘው ገቢ እያደገ ያለውን አበርክቶ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል ስላለ ነው፡፡
ዛሬም አገሪቷ ከምታገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ሁለትና ሦስት እጅ ብልጫ ያለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እየተገኘ ያለው ከሬሚታንስ ነውና የወጪ ንግዱ እስካልተስተካከለ በሬሚታንስ ለማሳደግ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማመቻቸትና መሥራቱ ይጠቅማል፡፡ ዛሬ ዶላር ካጣን የሚል ሁሉ በልመና በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ እየተጠቀመ የረባ ሥራ ካልሠራና የዶላር ግኝታችን ከልመና ለማላቀቅ በቀጥታ ካልተሠራ ችግሩ አሁንም ይቀጥላል፡፡