Tuesday, May 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አኃዛዊ ስሌቱ ምላሽ ያላገኘውና ያሽቆለቆለው የቱሪዝም ገቢ ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተመዝግቦበታል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የስምንትና የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቀረቡ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይገኝበታል፡፡ ሚኒስቴሩ በዘጠኝ ወራት ስላከናወናቸው ተግባራት ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሪፖርት አሰምተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በቱሪዝም መስክ 505,769 የውጭ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ከ2.56 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ምንም እንኳ ሚኒስትሯ የቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ቢሉም፣ ካቻምና ከተመዘገበውም ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረው የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር ከ686 ሺሕ በላይ እንደነበር ሚኒስቴሩ በወቅቱ ይፋ ያደረገው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በገቢ ደረጃም ቢሆንም በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ፣ ካቻምና ከተገኘው የ2.6 ቢሊዮን ዶላር አኳያም ያነሰ ሆኗል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በቱሪዝም ዘርፍ ስለተከናወኑ ጉዳዮች በተለይም ስለጎብኝዎችና ስለተገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን በአንድ አንቀጽ ብቻ ተወስኖ መታየቱ ሳያስገርም አይቀርም፡፡ የዚህ አባባል ምክንያቱ ደግሞ በውጭ ቱሪስቶች ቁጥርና በሚመዘገበው ገቢ መጠን ላይ ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎች ናቸው፡፡

ሚኒስቴሩ በሚከተለው ስሌት መሠረት አንድ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጣበት ወቅት በአማካይ የ16 ቀናት ቆይታ በማድረግ በትንሹ በቀን 234 ዶላር ወጭ እንደሚያደርግ ይታሰባል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት እንዲሁም ወደ አንድ ሚሊዮን ቱሪስት (ለትራንዚት የሚመጣውን ጨምሮ፣ ለስብሰባና ለመዝናናት የሚመጡትን ያካትታል) ሊመጣ እንደሚችል የታቀደው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ይገኛል የተባለው የገቢ መጠንም ከ3.7 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ነበር፡፡ በውጤቱ ወደ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ስለመገኘቱ ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አኃዝ ከሚገባው በላይ የተጋነነና ስሌቱም በተባበሩት መንግሥታት ሥር የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ከሚያወጣቸውም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ አኃዞች ጋር የማይገናኝ ነው የሚሉ ትችቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡

በየዓመቱ የሚወጣው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪነት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ዝቅተኛ ደረጃ ካላቸው አገሮች ተርታ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ሪፖርት በምታደርገው የቱሪዝም ዘርፉ ገቢና የቱሪስቶች ቆይታ እንዲሁም በቆይታቸው ወቅት በሚያጠፉት የገንዘብ መጠን ግምት ላይ በመንግሥት አኃዞችና በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መካከል ሰፊ ልዩነት ታይቷል፡፡

ይህ ይባል እንጂ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ባቀረቡት ግን ‹‹ከአሁን ቀደም የነበረው የቱሪስት ስታትስቲክስ ሥርዓት ውስንነት የነበረው በመሆኑ ሥርዓቱን በማዘመንና ጠቃሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ የጠራና ትክክለኛ መረጃ ለማሰባሰብና ለማደራጀት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ወደ አገራችን የሚገቡ ቱሪስቶችን ቁጥር፣ የተገኘውን ገቢ መጠንና የቱሪስቶች ፕሮፋይል ከቀድሞው በተሻለ መልኩ ለማደራጀት ተችሏል፤›› በማለት ይናገሩ እንጂ፣ ከዚህ ቀደም የሚኒስቴሩን ኃላፊዎችንና ባለሙያዎች ጨምሮ በበርካታ የዘርፉ ተዋንያን ዘንድ በመንግሥት እንዲተገበር ሲወተወት የነበረውን ‹‹ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት›› የተሰኘውንና የዓለም ቱሪዝም ድርጅት አገሮች እንዲተገብሩት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ያስተዋወቀውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ኢትዮጵያ መተግበር ስለመጀመሯ፣ ሚኒስትሯ በግልጽ በሪፖርታቸው አላመላከቱም፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም ቢሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ ክትትል በማድረግ ስላደረጓቸው ጫናዎች ብዙም የተባለ ጉዳይ የለም፡፡

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከቱሪዝም ዘርፍ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በጥቂቱ ከፍ ያለ ገቢ ተገኝቶ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገኝ ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም ሀብት አኳያ የሚገባትን ያህል ባትጠቀምበትም፣ በአፍሪካ በ17ኛ ደረጃ የሚያሠልፋትን የቱሪስት ብዛት እንደምታስተናግድ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከ850 ሺሕ ያላነሰ ቱሪስት ኢትዮጵያ እንደጎበኙ የባህልና ቱሪዝም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ካቻምና ከ934 ሺሕ በላይ ቱሪስት ተመዝግቦ ነበር፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች