እ.ኤ.አ. በ2013 የቻይናው ፕሬዚዳንት ዥ ፒንግ “One Belt One Road” (አንድ የኢኮኖሚ መቀነትና አንድ መንገድ) የተሰኘ ግዙፍና አኅጉሮችን ተሻግሮ፣ አገሮችን የሚያስተሳስር ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ፕሮጀክት አኅጉሮችን አቋርጦ 65 አገሮችን በግዙፍና ውስብስብ መሠረተ ልማቶች የሚያስተሳስር የበርካታ ትሪሊዮን ዶላሮች ኢንቨስትመንት ነው፡፡
ይህ የቻይና መንግሥት ኢኒሼቲቭ እንደታሰበው የሚሳካ ከሆነ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ አኅጉሮች ከፍተኛ የንግድ ትስስርን በማሳለጥ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት መሳካት የዓለምን ጠቅላላ ኢኮኖሚ 30 በመቶ የሚወክሉ አገሮች ኢኮኖሚን አስተሳስሮ በአንድ እንደሚያቆም የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
አገሮቹ የሚወክሉት የኢኮኖሚ ድርሻ ብቻ ሳይሆን፣ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ሥር ተሳታፊ የሆኑት አገሮች የሕዝብ ብዛት አጠቃላይ የዓለም ሕዝብን 62 በመቶ እንደሚወክል የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም 75 በመቶ የሚሆነው የዓለም የኃይል ምንጭ በእነዚሁ አገሮች ውስጥ እንደሚገኝ የሚገልጸው የዓለም ባንክ መረጃ፣ የቻይና መንግሥት ኢኒሼቲቭ የሚሳካ ከሆነ ለዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይጠቁማል፡፡
ይህ የቻይና ኢኒሼቲቭ ቻይናን በየብስ ከመካከለኛው ደቡብ እስያ አገሮች በመሠረተ ልማት በማገናኘት ወደ አውሮፓ የሚያቀና ነው፡፡ ሌላኛው የኢኒሼቲቩ አካል ደግሞ ቻይናን በባህር መሠረተ ልማቶችና ትራንስፖርቶች ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በመቀጠልም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የገልፍ አገሮች፣ እንዲሁም ወደ ሰሜን አፍሪካ በማቅናት አገሮችን የሚያስተሳስር ነው፡፡ ይኸው ኢኒሼቲቭ በህንድ ውቅያኖስ ዙሪያ የሚገኙ አገሮችንም ጭምር የሚያስተሳስር ስለሆነ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ጂቡቲም በዚህ ፕሮጀክት ሥር የተካተቱ አገሮች ናቸው፡፡
ይህ የቻይና መንግሥት አኅጉር አቋራጭና ግዙፍ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ፕሮጀክት አዲስና የተሻሻለ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በመፍጠር ፈጣን የንግድ ግንኙነት በአገሮች መካከል እንዲከናወን የሚያስችል እንደሚሆን፣ የተሻለ የኢንቨስትመንት ዕድልን በመፍጠር ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንደሚፈጥር የዓለም ባንክ ያምናል፡፡
ይሁን እንጂ ይኼንን ኢኒሼቲቭ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ የፖሊሲና የኢኮኖሚ ፈተና እንደሚፈጥር ባንኩ ሥጋቱን ይገልጻል፡፡ ይኼንን ሥጋት መሠረት በማድረግ የዓለም ባንክ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ ላይ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም የቻይና ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ›› ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች መታየት ቢጀምሩም፣ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ቢሊዮን ዶላሮችን ከቻይና በብድር የወሰዱ የኢኒሼቲቩ አባል አገሮች በከፍተኛ የብድር ጫና ችግር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡
የቻይና መንግሥት ከስድስት ዓመታት በፊት ይፋ ያደረገውን አንድ የኢኮኖሚ መቀነትና አንድ መንገድ (ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ) አሉታዊ የኢኮኖሚ አንድምታውን አስመልክቶ ጥናታዊ ዳሰሳ ያደረገው ሴንተር ፎር ግሎባል ዴቨሎፕመንት የተሰኘ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ መንግሥታዊ ያልሆነ የጥናት ተቋም፣ በቻይና መንግሥት ይፋ የተደረገውና በትግበራ ላይ የሚገኘው ይህ ኢኒሼቲቭ በመጠነኛ ጉድለቶች በተሳካ ሁኔታ መፈጸም የሚችል ከሆነ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በተሳታፊ አገሮች ከማስገኘቱ ባለፈ፣ ተሻጋሪ ውጤቱ በዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ላይም እንደሚንፀባረቅ ያትታል፡፡
ነገር ግን ይህ ኢኒሼቲቭ ግዙፍና በተለያዩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ የሚገኙ አገሮችን በቻይና በሚገኝ የገንዘብ ብድር ለማስተሳሰር ያቀደ መሆኑ፣ ከኢኮኖሚ ፋይዳው ይልቅ ሊፈጥር የሚችለው የኢኮኖሚ ቀውስ ሊብስ እንደሚችል ያሳስባል፡፡
መሠረታዊ የሥጋቱ ምንጭም በቻይና ግንባር ቀደም መሪነትና ኢኒሼቲቩ የሚጠይቀውን ገንዘብ በቻይና ብድር አቅራቢነት ለመዘወር የታቀደ መሆኑ፣ ሌሎቹን ተሳታፊ አገሮች ከፍተኛ የውጭ ብድር ጫና ውስጥ በመክተት ድንበር ተሻጋሪ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚችል፣ እንደሆነና የዚህም ምልክቶች ከወዲሁ መታየት መጀመራቸውን አገሮችን በማጣቀስ ያቀርባል፡፡
በቻይና መንግሥት መሪነት የተጀመረው ይህ ኢኒሼቲቭ በእስያ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ አኅጉሮች የሚገኙ 68 አገሮችን በመንገድ፣ በትራንስፖርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና በቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረት ልማቶች ለማስተሳሰር የወጠነ ሲሆን፣ ይኼንን ለውጥ ለማድረግ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ውስጥ ስምንት ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የጥናት ተቋሙ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
የጥናት ተቋሙ ባደረገው ምርምር በዚህ ድንበር ዘለል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ኢኒሼቲቭ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት 68 አገሮች መካከል የ35 አገሮች ጫና መጠን መካከለኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ቀሪዎቹ 33 አገሮች ግን ገና ኢኒሼቲቩን ለማስፈጸም ከቻይና ብድር መውሰድ ሳይጀምሩ በከፍተኛ የውጭ ብድር ጫና ውስጥ እንደሚገኙ ያመለክታል፡፡
ከእነዚህ ከፍተኛ የብድር ጫና ውስጥ ከሚገኙ አገሮች ውስጥ ደግሞ ስምንቱ ማለትም ጂቡቲ፣ ኪግሪስታን፣ ላኦ፣ ማልዲቭስ፣ ሞንጎሊያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ፓኪስታንና ካጃኪስታን በከፍተኛ ደረጃ የብድር ጫና ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ኢኒሼቲቩን ለማስፈጸም በተጨማሪ ብድር የሚወስዱ ከሆነ እንደ አገር መውጣት ከማይችሉት የዕዳ ወጥመድ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ፣ ብድሩን እያቀረበ የሚገኘው የቻይና መንግሥትም ብድሩን ለማስመለስ የአገሮቹን ኢኮኖሚ በከፊል ወደ መቆጣጠር ዕርምጃ ውስጥ ሊገባ እንሚችል ያስረዳል፡፡
ቻይና ብድሯን ለማስመለሰ ልታደርግ የምትችላቸውንና በተወሰኑ አገሮች ላይም ከወዲሁ የጀመረቻቸውን ዕርምጃዎች በማሳያነት ጥናቱ ያቀርባል፡፡
ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2011 ታጃኪስታን በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ሥር ለተካተተ አንድ መሠረት ልማት ማስፈጸሚያ የወሰደችውን ብድር መልሳ መክፈል ባለመቻሏ፣ የቻይና መንግሥት ከታጃኪስታን ጋር ከሚወዛገብበት የድንበር ክፍል ውስጥ 1,152 ካሬ ኪሎ ሜትር ያህሉን አካባቢ ለመውሰድ በመስማማት የታጃኪስታንን ዕዳ መሰረዙን በዋቢነት ያስረዳል፡፡
በሌላ በኩል በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ውስጥ የተካተተውን ሐምባኖታ የተባለ የባህር ወደብ ለመገንባት ስምንት ቢሊዮን ዶላር ብድር በስድስት በመቶ የወለድ ምጣኔ የወሰደችው ሲሪላንካ ብድሩን ለመመለስ ወገቤን በማለቷ፣ ያለባትን የዕዳ መጠን ያህል አክሲዮን ከወደቡ ላይ የቻይና መንግሥት እንዲይዝና ወደቡንም ለ99 ዓመታት በሊዝ እንዲያስተዳድር እ.ኤ.አ. በ2017 ስምምነት ፈጽማለች፡፡
ሌላኛዋ ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማታል ተብላ የምትታሰበው የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ጂቡቲ ስትሆን፣ ወደብና የተለያዩ መሠረት ልማቶች ለመገንባት የአጠቃላይ ጂዲፒዋን (GDP) 75 በመቶ የሆነ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና ተበድራለች፡፡ ይኸው ጥናት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ብድር ከቻይና የምትወስድ ከሆነ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እንደምትወድቅ የገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የተዘረጋውን የባቡር መስመር ለመገንባት በከፍተኛ የወለድ ምጣኔ የወሰደችውን አራት ቢሊዮን ዶላር ዓይነት ተጨማሪ ብድር ውስጥ የምትገባ ከሆነ፣ የኢትዮጵያም ዕጣ ተመሳሳይ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡
ጥናቱ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ላይ ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ በሥጋት ደረጃ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለዚህና ለሌሎች የባቡር ፕሮጀክቶች ከቻይና በብድር የተገኙ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ሳይጠናቀቁ ወይም ኢኮኖሚያዊ ውጤት ማምጣት ሳይጀምሩ ብድርና ወለድ የመክፈያ ጊዜያቸው ከሁለት ዓመታት በፊት በመድረሱ፣ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን ሌላኛውን ገጽታ ከወዲሁ መቅመስ ጀምራለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን በያዙ ማግሥት ያደረጉት፣ የቻይና ብድሮችን ወቅታዊ ጉዳት ለጊዜው ማራቅ የሚቻልበትን ድርድር ከቻይና መንግሥት ጋር ማድረግ ነበር፡፡
ይህም ተሳክቶላቸው የብድርና ወለድ ክፍያው የተጀመረው የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ብድር መመለሻ ጊዜ ከ13 ዓመት ወደ 30 ዓመት እንዲገፋ፣ ባለፈው ሳምንት ከቻይና መንግሥታት ጋር ተፈራርመዋል፡፡
በተጨማሪም እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ድረስ መክፈል ከነበረባቸው የብድር ወለዶች ውስጥ ያልተከፈሉት ወለዶች እንዲሰረዙ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ይኼንን ይሁንታ ከቻይና ስታገኝ ምን መስዋዕት አድርጋ እንደሆነ በይፋ ባይታወቅም፣ አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ግን ኢትዮጵያ ይኼንን ለማግኘት ለቻይና መንግሥት በባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ልትሰጥ እንደምትችል ይናገራሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በቻይና በነበራቸው ቆይታ ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል፡፡ ከተለያዩ የቻይና ታላላቅ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ለኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ መስመር ዝርጋታ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት እንዲደረግ አስችለዋል፡፡ ሌሎች ስምምነቶችም ተፈርመዋል፡፡