Tuesday, July 23, 2024

ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ራሳቸውን ይፈትሹ!

ይህንን ርዕሰ ጉዳይ የምናነሳው፣ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የቀድሞውን የኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) እንደ ምሳሌ በማውሳት ነው፡፡ እሳቸው በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት ውስጥ በተከሰተው መሰንጠቅ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት፣ ኃላፊነታቸውን ካስረከቡ በኋላ የደረሰባቸው ፈተና አይዘነጋም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አደገኛ የሚባለው ጥላቻና ቂም በቀል ሰለባ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መሀል አንዱ፣ እሳቸው ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ለተተኪው ከለቀቁ በኋላ፣ ሊያገኙዋቸው ይገቡ የነበሩ ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ እንዲሻሩባቸው ተደርገው ከባዱን የመከራ ገፈት ቀምሰዋል፡፡ ለሚያምኑበት ዓላማ በፅናት በመቆማቸው ምክንያት የታላቅ ሰብዕና ባለቤት በመሆን የሕዝብ ፍቅር አግኝተዋል፡፡

ያንን ሁሉ መከራ በፅናት ተሻግረው ያተረፉት ትልቅ ነገር ቢኖር የሕዝብ ክብርና ፍቅር ነበር፡፡ ከግል ጥቅምና ሥልጣን በላይ ለአገር በማሰብ ለህሊናቸው ያደሩ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ በጣም ትሁት፣ ቅን፣ ታማኝና ለእውነት የቆሙ ሰው ስለነበሩ እንደተከበሩ አልፈዋል፡፡ አብረዋቸው የሠሩም ይመሰክሩላቸዋል፡፡ እንደ ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ለህሊና የተገዛ ሰብዕና ተላብሶ ማለፍን የሚያህል መታደል ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እሳቸው ላመኑበት ዓላማ ሲሉ ሥልጣንን፣ ክብርን፣ ዝናንና ጥቅማ ጥቅምን ንቀው አልፈዋል፡፡ እሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም፣ ታሪካቸውና ሥራቸው ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ይታወሳሉ፡፡ ላመኑበት ዓለማ በፅናት የቆሙ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ስለነበሩም ዝንተ ዓለም ይመሠገናሉ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ የገዘፈ የሰብዕና ባለቤት የሆኑ ልጆቿን በተለያዩ ዘመናት ዓይታለች፡፡ በጦር ሜዳ ሕይወታቸውን ከገበሩላት፣ ደማቸውን ካፈሰሱላትና አጥንታቸውን ከከሰከሱላት በተጨማሪ፣ በተለያዩ መስኮች ስሟን ያስጠሩ ጀግኖች ልጆች ነበሯት፡፡ ዛሬም እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ከልጆቿ ብዙ ነገሮች ትፈልጋለች፡፡ አስተማማኝ ሰላም፣ በሕግ የበላይነት ሥር የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ፍትሐዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን መሻቶች ዕውን ለማድረግ ግን በተለይ ፖለቲከኞችና ለመብት እንሟገታለን የሚሉ ወገኖች ሰከን ማለት አለባቸው፡፡ ይህ ስክነት የሚያስፈልገው አገርን ወደ ቀውስ ከሚያንደረድሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ለመታቀብ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎና ይሁንታ ሰላሟና ደኅንነቷ አስተማማኝ የሆነ አገር ለመገንባት ጭምር ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ አገርን የማያስቀድም የፖለቲካ ዓላማም ሆነ አጀንዳ እንዳይኖር የሚታገሉ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ያስፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀቀኝነት፣ ቅንነትና ንፅህና ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን ሳያሟሉ በሕዝብ ስም መነገድ ቁማርተኝነት ነው፡፡ 

ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ወገኖች ለአገር የሚጠቅም ሥራ ካላከናወኑ፣ የዓላማ ሰው ሆነው ሰብዕናቸውን መገንባት ካልቻሉና የሚወክሉትን ማኅበረሰብም ሆነ የመላውን ሕዝብ አመኔታና ክብር ካላገኙ አደባባይ በኩራት ለመውጣት ይቸግራቸዋል፡፡ ለትውልድ የሚተላለፍ አርዓያነት መገንባት ሲገባቸው፣ ሕዝቡ ውስጥ ግጭት እየቀሰቀሱ የአገርን ህልውና የሚፈታተኑ ከሆነ ትውልድና ታሪክ ይጠይቋቸዋል፡፡ ለጥፋት ብቻ የሚዘረጉ እጆች አገርን የሚጎዱ ቢሆንም፣ ለጊዜው ነው እንጂ በሕዝብ ዘንድ ጥላቻን ነው የሚያተርፉት፡፡ ለአገሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ያለው አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር የሚሰጠው፣ ለዓላማ ኖረው የሚያስከብሩትን ብቻ ነው፡፡ ለግልና ለቡድን ጥቅም እየተስገበገቡ ራሳቸውንና አገርን የሚያዋርዱትን ይፀየፋቸዋል፡፡ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጓቾች በዚህ ደረጃ ራሳቸውን ካልፈተሹ የሚያልሙት ሁሉ የእምቧይ ካብ ከመሆን አያልፍም፡፡

አገር ከትናንት የተሻለ ሥርዓት ገንብታ ለዜጎቿ በሙሉ የምትመች መሆን የምትችለው፣ መጀመርያ በህልውናዋ ላይ መቆመር ሲያበቃ ነው፡፡ በመቀጠል ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት፣ በሕግ የበላይነት የሚያምንና ተግባራዊ የሚያደርግ መንግሥታዊ ሥርዓት መመሥረት ሲቻል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች መልክ እየያዙ መጠናከር ሲቻል፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንፀባራቂ አገር መሆን ትችላለች፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ከራስ በፊት ለአገር የሚሉ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ወገኖች መኖር አለባቸው፡፡ በአደባባይ ሰላምን እየደሰኮሩ ውስጥ ውስጡን ሴራ መጎንጎን ለአገር ጥፋት እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ በዚህ ዓይነት ድርጊት የተካኑ እኩዮች በሚፈጥሩት ችግር ከሦስት ሚሊዮን በላይ ወገኖች መፈናቀላቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን መገደላቸው ከቶውንም ሊረሳ አይገባም፡፡ በግጭት ነጋዴዎች አማካይነት እየደረሰ ያለው ፈተና የአገርን ካስማና ማገር እየነቃቀለ መሆኑን መዘንጋትም ተገቢ አይደለም፡፡ በእኩይ መንፈስ የተሞሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለአገራቸው የሚለፉ ትጉሃን ወገኖችን ማደናቀፍና ተስፋ ማስቆረጥ የዘወትር ተግባራቸው እንደሆነ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የተሰገሰጉትን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ዕኩይ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ ኃይሎች ራሳቸውን ቢፈትሹ ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም ድርጊታቸው ያሳፍራልና፡፡

ለአሁኑ ወጣት ትውልድም ሆነ ለመጪው ትውልድ አርዓያ ለመሆን የሚያስችል ሰብዕና ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሰብዕና ከትምህርት፣ ከልምድና ከክህሎት በተጨማሪ ትህትናን፣ ቅንነትንና ታማኝነትን ማካተት ይኖርበታል፡፡ በሥነ ምግባር የዳበረ ኅብረተሰብ የክፋት ድርጊቶችን የሚፀየፍ በመሆኑ ለሴራ፣ ለጥላቻና ለቂም በቀል ፖለቲካ አይንበረከክም፡፡ ላመኑበት ዓላማ በፅናት የሚቆሙ ጀግኖችን የሚያፈራ ከመሆኑም በላይ፣ ማናቸውንም ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ሥነ ልቦና ይኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በዚህ አይታማም፡፡ ጥሩ መሪ ካገኘ አስደማሚ ገድሎችን እንደሚያከናውን ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ታላቅ ምሳሌ ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ጥቁር ሕዝብ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ የተጎናፀፈው ይህ ድንቅና ታላቅ ድል፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደር የለሽ የአገር ፍቅር ስሜት አመላካች ነው፡፡ ይህንን ጨዋ፣ ምሥጉን፣ ታታሪና አስተዋይ ሕዝብ በአግባቡ መርቶ ታላቅነትን መጎናፀፍ እየተቻለ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ መገኘት አስነዋሪ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ይህንን መርህ ጥሰው ያልተገባ ድርጊት ውስጥ ሲገኙ፣ የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን ሲሰብኩ ሊበቃችሁ ይገባል መባል አለበት፡፡ በአገር ህልውና ቀልድ ስለሌለ ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...