Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከግብር ጋር የተያያዙ 14 አዳዲስና ነባር መመርያዎች ተሻሽለው ፀደቁ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ገቢዎች ሚኒስቴርና ገንዘብ ሚኒስቴር ከግብር ጋር የተያያዙ 14 አዳዲስና ነባር መመርያዎችን አሻሽለው በማፅደቅ ወደ ሥራ እንዲገቡ መወሰናቸው ተገለጸ፡፡

  ሁለቱ ሚኒስቴሮች በየመሥሪያ ቤቶቻቸው የኃላፊነት ደረጃ ያወጡዋቸው መመርያዎች፣ ባለፈው ዓመት በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው ከነበሩት ከ20 በላይ መመርያዎች ውስጥ ተካትተው የነበሩ ናቸው፡፡

  በሁለቱ ሚኒስትሮች ተፈርመው ከወጡት መመርያዎች ውስጥ ስምንቱ በገቢዎች ሚኒስቴር የወጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ስድስቱ ደግሞ በገንዘብ ሚኒስቴር የወጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በገቢዎች ሚኒስቴር ከወጡት መመርያዎች ውስጥ፣ ከተከፋይ ሒሳብ የንግድ ትርፍ ግብር ቀንሰው እንዲያስቀሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ታክስ ከፋዮችን ለመወሰን የወጣው መመርያ አንዱ ነው፡፡

  የንግድ ሥራ ከተቋረጠ በኋላ በተገኘ ገቢ ላይ ግብር ስለሚከፈልበት ሁኔታ በገቢዎች ሚኒስቴር መመርያ የወጣ ሲሆን፣ የታክስ ክፍያ ጊዜ ማራዘምን የተመለከተው ሚኒስቴሩ ካወጣቸው መመርያዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

  በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከወጡት ስድስት መመርያዎች ውስጥ የቅድመ ግብር ክፍያ ሥርዓት አፈጻጸም፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ስለሚሆንበት መመርያና የታክስ ከፋዩን ሀብት ስለመያዝና ስለመሸጥ የወጣ መመርያ ይገኙበታል፡፡

  በተለይ የገቢዎች ሚኒስቴር ከወጡት መመርያዎች ውስጥ፣ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ የንግድ ትርፍ ግብርን ቀንሰው እንዲያስቀሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰብ የታክስ ከፋዮችን ለመወሰን የወጣው መመርያ አዳዲስ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡

  ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ሁለት በመቶ የንግድ ትርፍ ግብር ቀንሰው እንዲያስቀሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ፣ ሰፊ የአገር ውስጥ ግብይት ላላቸው ግለሰብ ግብር ከፋዮች ኃላፊነቱን በመስጠት የሚሠራበት ይሆናል፡፡ የታክስ ባለሥልጣን የመረጃ ምንጭ ማስፋት በማስፈለጉ የወጣ መሆኑን የሚጠቁመው መመርያው፣ የወጣበት ምክንያት በመግቢያው ላይ ተመልክቷል፡፡ በተመረጡ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ግለሰብ ግብር ከፋዮች ከተከፋይ ሒሳብ ላይ የንግድ ትርፍ ግብር ቀንሰው እንዲያስቀሩ ኃላፊነት በመስጠት፣ የንግድ ውድድሩን ፍትሐዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

  በግለሰብ ግብር ከፋዮች ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ተቀንሶ የሚከፈለውን የንግድ ትርፍ ግብር በሚመለከት ተፈጻሚ የሚሆነውን አሠራር መወሰን ጭምር የሚያመለክተው ይህ መመርያ፣ ከተከፋዩ ሒሳብ ላይ የንግድ ትርፍ ግብር ቀንሰው ገቢ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው የደረጃ ‹‹ሀ›› ግለሰብ ግብር ከፋዮች ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በአማካይ አሥር ሚሊዮንና ከዚያ በላይ ጠቅላላ ገቢ ያስመዘገቡ ግለሰብ ግብር ከፋዮች እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

  በእነዚህ ከተጠቀሱት ከደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ሌላ በንግድ ሥራ የተሰማሩ የደረጃ ‹‹ሀ›› ግለሰብ ግብር ከፋይ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከግምት ውስጥ ሳይገባ፣ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሰው የማስቀረት ግዴታ እንዳለባቸውም ይኼው መመርያ ያመለክታል፡፡

  በዚህ መመርያ ግዴታ የተጣለባቸው ተብሎ በዝርዝር የቀረበ አለ፡፡ እዚህ ውስጥ ማንኛውም ባለ ኮከብ ሆቴል ወይም ማንኛውም ሪዞርት፣ ከአንድ እስከ አራት ደረጃ ያላቸው ሥራ ተቋራጮች፣ ማንኛውም የሪል ስቴት አልሚና የምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኙበታል፡፡ መመርያው ተፈጻሚ የሆነበት ውል ተብለው ከተለዩት ውስጥ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግዥ የሚፈጽም ማንኛውም ግለሰብ ግብር ከፋይ፣ በምርት ገበያው በኩል ላደረገው ግብይት ብቻ ሁለት በመቶ መቀነስ አለበት፡፡ ሆስፒታሎችና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥፈርት መሠረት ከፍተኛና ከዚያ በላይ ደረጃ ያላቸው ክሊኒኮች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች፣ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት በመረከብ የሚያከፋፍል ማንኛውም ግለሰብ ግብር ከፋይ፣ በዚህ መመርያ የተገለጹትን መፈጸም እንደሚኖርባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ይህንን መመርያ በተጠቀሰው መንገድ ለማስፈጸም የታክስ ባለሥልጣኑ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሰው ገቢ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸውን ግለሰብ ግብር ከፋዮች በመመዝገብ፣ የምዝገባ ምስክር ወረቀት እንደሚሰጥም አመልክቷል፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት ከተከፋይ ሒሳቦች ላይ ግብር ቀንሰው ገቢ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግለሰብ ግብር ከፋዮች፣ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሰው የማስቀረት ግዴታቸውን መወጣት የሚጀምሩት በታክስ ባለሥልጣኑ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው ቀን ጀምሮ እንደሚሆንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ከተከፋይ ሒሳብ ላይ የንግድ ትርፍ ግብር በመቀነስ ለታክስ ባለሥልጣን ገቢ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግለሰብ ግብር ከፋዮች፣ የምዝገባ ምስክር ወረቀት የሚወስዱት ግብር ከሚከፍሉበት ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር የታክስ ባለሥልጣን እንደሚሆንም በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

  ከተከፋይ ሒሳብ ላይ መቀነስ ያለበት የንግድ ትርፍና አፈጻጸሙን በተመለከተ እንደተጠቀሰው፣ በዚህ መመርያ መሠረት ከተከፋይ ሒሳብ ላይ የንግድ ትርፍ ግብር ቀንሶ እንዲያስቀር ኃላፊነት የተሰጠው ግለሰብ ግብር ከፋይ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት ከሚያከናውነው ግብይት ላይ ተቀናሽ መደረግ ያለበትን ግብር ቀንሶ በማስቀረት፣ ለታክስ ባለሥልጣን ገቢ ማድረግ እንዳለበትም ይደነግጋል፡፡

  ይህንን መመርያ ለማስፈጸም ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሰው ገቢ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰብ ግብር ከፋዮች፣ ከታክስ ባለሥልጣን ፈቃድ በመውሰድ ደረሰኝ አሳትመው መጠቀም እንዳለባቸውም የገቢዎች ሚኒስቴር መመርያ ያመለክታል፡፡

  የገቢ ሒሳብ አመዘጋገብና ተያያዥ ጉዳችን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ሌላው ጉዳይ፣ ግብር ከፋዩ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ቀንሶ ገቢ ያደረገውን ግብር ገቢ የተደረገላቸው የክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የታክስ ባለሥልጣን የየራሳቸውን ድርሻ በማስቀረት፣ የሌሎችን ክልሎች ወይም ከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም የፌዴራል ድርሻ በመለየት አግባብነት ባለው የሒሳብ ኮድ በመመዝገብ ከዝርዝር መረጃው ጋር በወቅቱ ያስተላልፋሉ፡፡

  ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሶ ለሚመለከተው የታክስ ባለሥልጣን ገቢ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት ግለሰብ ግብር ከፋይ፣ በገቢ ግብር አዋጁ መሠረት ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብርን ቀንሰው እንዲያስገቡ ኃላፊነት ለተጣለባቸው ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶች የተደነገጉ ግዴታዎች አሉበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በታክስ አስተዳደር አዋጁም በእነዚሁ ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶች ላይ የተጣሉ አስተዳደራዊ ቅጣቶችና የወንጀል ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ይገልጻል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች