በ13ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ላይ ለእይታ ከሚበቁ ፊልሞች በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከተሠሩት ዘጋቢ ፊልሞች ውስጥ “My Name is Gennet” ይገኝበታል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ ከባህር ማዶ ዘጋቢ ፊልሞች ደግሞ “One Day in Aleppo”, “City Of Ghost”, “13th”, “When the War Comes”, “Thank you For the Rain” ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከሚታዩ ፊልሞች ይጠቀሳሉ፡፡
በኢንሺየቲቭ አፍሪካ አዘጋጅነት የተጀመረው አዲስ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ከሚያዝያ 22 ቀን ጀምሮ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ በማኅበራዊ ፍትሕ፣ በማንነትና በባህል ብዝኃነት ላይ ያተኮሩ ከ60 በላይ የሚሆኑ ምርጥ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ፊልሞች በአሊያንስ ኢትዮፍራንዜስ፣ በቫምዳስ ኢንተርቴይመንት፣ በሀገር ፍቅር ቴአትርና በጣሊያን ባህል ማዕከል ይቀርቡበታል፡፡
የፌስቲቫሉ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬከተር አቶ ክቡር ገና ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ «የዚህ ፌስቲቫል አንዱ ዓላማ ሕዝብን ከፊልሞች ጋር ማገናኛት ብቻ ሳይሆን፣ ባለሙያዎችን ማስተዋወቅና ፌስቲቫሉ ከታየ በኋላ ፊልሞቻቸው ወደ ሌላ ፌስቲቫል ቀርበው በዛ ደግሞ የተለየ ሽልማትና ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ነው።»
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመታወቅ የበቃው አዲስ ኢንተርናሽናል ዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተመረጡና የተለያዩ ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተራኪ ፊልሞች በማሳየት ታሪኮቹ ቀልብ እንዲስቡና ተመልካቾች ወደ ለውጥ ተግባር የሚገፋፉ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
እንደ አቶ ክቡር አገላለጽ፣ በ13ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ለሰው ልጅ ህልውና አስጊ በሆኑት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ኢፍትሐዊነትን ተከትለው በሚከሰቱ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ምርጥ ዘጋቢ ፌልሞች ይቀርባሉ፡፡ ለዚህ ፌስቲቫል ከመላው ዓለም ከተላኩ ከ450 በላይ ፊልሞች መካከል ሊያነጋግሩ የሚችሉ 60 ፊልሞች የተመረጡ ሲሆን ይዘታቸውም በማኅበራዊ ፍትሕ፣ በማንነትንና በባህል ብዝኃነት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአብዛኛው ይታዩ የነበሩት ፊልሞች ከሰብዓዊ መብት ጋር ብቻ የተያያዙ ሳይሆን ከሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ጋር የተጣመሩ ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ከሚቀርቡት 80 በመቶ የሚሆኑ ፊልሞች ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ናቸው ሲሉ አቶ ክቡር አውስተዋል፡፡
ዘጋቢና አጫጭር ፊልሞችን ለተመልካች ከማቅረብ በተጨማሪ በየዓመቱ በዘርፉ በታላላቅ መድረኮች ተሸላሚ የሆኑና ዓለም አቀፋዊ ዝናን ያተረፉ የዘጋቢ ፊልም ዳይሬክተሮችን በመጋበዝም የኢትዮጵያ ጀማሪ ፊልም ሠሪዎች ልምድ እንዲቀስሙ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
እንዳለፉት ዓመታት በዘንድሮ ፌስቲቫል ላይ ከተጋበዙትና ልምዳቸውን ከሚያካፍሉት አሥር ዳይሬክተሮች ውስጥ ሮቢን (Bias)፣ ኒክ ዘ ቹኪ (DEMLA)፣ ጁሊያ ዳሂር (Pane a Vite)፣ ሚካኤል ሮበርት (Peer Gynt) እና ሳሚር አቡጃማራ (The Desert of The Desert) ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የፌስቲቫሉ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬከተር አቶ ክቡር ገና እንደተናገሩት፣ የፊልም ፌስቲቫሉ በአፍሪካ ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ የአዲስ ፊልም ፌስቲቫል የ13 ዓመታት ያልተቋረጠ ጉዞና በየሒደቱ የሚያሳየው ውጤት ቀዳሚ አድርጎታል።
በ1999 ዓ.ም በጣሊያን የባህል ማዕከል 11 ፊልሞችን በማሳየት የተጀመረው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በዓመት ዓመት እየተሻሻለ በመምጣቱ በየዓመቱ ከ60 በላይ ዘጋቢና አጭጫር ፊልሞች የሚታዩበት መድረክ ለመሆን በቅቷል፡፡ የታዳሚዎችን ቁጥር ለማሳደግም ፌስቲቫሉ በዋና ዋና የክልል ከተሞች እንዲካሄድ በማድረግ እስከ 30,000 የሚደርስ ተመልካች ማግኘት መቻሉ ተገልጿል፡፡
በተመስገን ተጋፋው