በንጉሥ ወዳጅነው
ዓለም በተለያዩ ጊዜያት ከሚያጋጥሟት ፈተናዎች ዋነኛው የሰው ልጅ የሚያካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ነው፡፡ አገሮች በተናጠል ወይም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች እርስ በርስ የሚያደርጉት አለመግባባትና ጥላቻ የሚቀሰቅሰው ጦርነት፣ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሕዝቦችን አፋጅቷል፡፡ ከዚያም በላይ የዓለም አገሮች ጎራ ለይተው የተጠዛጠዙባቸው እንደ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ያሉ ክስተቶች በአውዳሚነታቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለእነዚህ ጦርነቶች መቀስቀስ በርካታ ምክንያቶች በየታሪክ ድርሳናቱ ቢጠቀሱም በአብዛኛው ከመሪዎች አምባገነናዊ፣ ዘረኛና ዘራፊ አስተሳሳብ የሚመነጨው የተሳሳተ አመለካካት ከፍ ያለውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለይ ሕዝቦችን በማይገባ የጥላቻና የቂም መንገድ በመንዳት በትንንሽ ምክንያቶች (በዘረኝነት፣ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ፣ እንዲሁም በድንበር፣ በጋራ ሀብት፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም . . .) ሰበብ የሚለኮስ እሳት በቀላሉ ሳይበርድ፣ እስከ ትውልድ የሚደርስ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡
ይህ ችግር በሠለጠነው ዓለም ጉዳት ካደረሰ በኋላ በይቅርታና ወቅቱ በሚጠይቀው ጠንካራ አገረ መንግሥት ግንባታ እሳቤ እየተቀረፈ ነው፡፡ በሦስተኛው ዓለም በተለይ በአፍሪካ ግን ቅኝ ገዥዎችና የተዛባ አስተሳሳበ አራማጆች በቀደዱት ቦይ በመፍሰስ፣ እስካሁንም ድረስ ጥላቻ፣ ቂመኝነት፣ ግጭትና መለያየት ተባብሶ የቀጠለባቸው አገሮች ትንሽ አይደሉም፡፡
የአገራችን ሁኔታም ከዚህ እውነታ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ እንደ ብዙ ሰፋፊ አገሮች ኢትዮጵያም ብዝኃነት የሞላባት፣ የተፈጥሮ ባለፀጋና የታሪክ ምሰሶ ብትሆነም በውስጥም ሆነ በውጭ ኃይል የግጭትና የጦርነት ሰለባ ሆና ነው የቆየችው፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ የእነዚያ ዘመናት ቅሪት አስተሳሳቦች በአሁኑ ትውልድ አዕምሮ ውስጥም እንዲመላላሱ እየተደረጉ፣ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትና መነጣጣል እያንዣበበ መሄዱ ነው፡፡ አገራችን ምንም እንኳን በሕዝቦቿ ጥንካሬና በፈጣሪም ረዳትነት ሳትጠፋ እዚህ ብትደርስም፣ በየዘመናቱ ያለቀባት ምሁርና አምራች ኃይል ግን ለኋላቀርነትና ድህነት መባባስ የራሱ ድርሻ እንደነበረው ይኼ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡
ካለፉት የታሪክ ዝንፈቶችና የተሳሳቱ የጥላቻ መንገዶች ዓለም እየወጣ ወደ ሥልጣኔና ትብብር ቢመጣም፣ በዛሬዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ለምን የመራራቅና የመገፋፋት እሳቤ ተጠናከረ ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል፡፡ የተቃርኖ አስተሳሳብስ እስከ የት ድረስ ሊወስደን ይችላል ብሎ ማውጠንጠንም ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች የዚህ ሁሉ መዘዝ መነሻ የጎሳ ፌዴራሊዝም መከተላችን፣ ጠንሳሹም ሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ የፖለቲካ ኃይል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
እሱ ብቻ ሳይሆን ግን የ1960ዎች ፖለቲካ አብዛኛው ተዋናይ በማንነትና በዘር ላይ የተመሠረተን የፖለቲካ ትግል እንደ ጠቃሚ አማራጭ ወስዶ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ በተለይ የፊውዳሉን አገዛዝ ለመገንደስ በአንድ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና መሰል ሁነቶች ላይ ያነጣጣረ የሚመስል ሕዝብን ያለየ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ የብሔርና የማንነት መብትና ጥቅምን ለማስከበር ከሚዛኑ ያለፈ ትኩረት መስጠትም ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ይህን አስተሳሳብ በአዲሱ ትውልድ ላይ ለማስረፅ ሐሰተኛና የተጋነነ ትርክትን በተራ የፖለቲካ ቀለም እየቀቡ ጥላቻን መዝራት ዛሬ ለደረስንበት አብሮነት መዳከምና የቂም በቀል ፖለቲካ ዳርጎን ይገኛል፡፡
እንግዲህ ይህ ለምንና እንዴት ሆነ ከማለት ይልቅ ከጥላቻና ከዘረኛ አስተሳሳብና የፖለቲካ ቅኝት እየወጣን ወደ አገራዊ አንድነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የሕዝቦች አንድነት ልንመለስ እንችላለን ብሎ ማብሰልሰል ተገቢና አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ፋሽስታዊ ባህሪ የነበራቸውና በዘረኝነት ብቻ ለከፋ ግጭትና መለያያት የተዳረጉ የዓለም አገሮች አካሄድም ተሞክሮ ሊሆነን ይችላል፡፡
ለአብነት ለመጠቃቀስ ያህል ጀርመንን በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የናዚ ፓርቲው አምባገነን መሪ አዶልፍ ሒትለር ጀርመኖችን ከዓለም የሚነጥል ፋሽስት ብቻ ሳይሆን፣ የውስጥ አንድነታቸውንም የሚሸረሽር ዘረኛና ከፋፋይ አዘቅት ውስጥ ከትቷቸው ነበር፡፡ የዚያ አስተሳሳብ ጥንስስ በርዕዮተ ዓለምና በፖለቲካ አስተሳሳብም ታግዞ በርሊንን ከሁለት የከፈለ ግንብ እስከ መገንባት ያደረሰ ነበር፡፡ ጀርመናዊያንም ምሥራቅና ምዕራብ በመባባል ተከፋፍለው ለዓመታት ቆይተዋል፡፡
በኋላ ግን የጀርመን ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ አብዛኞቹ ምሁራንና የፖለቲካ ኃይል ግልጽ ምክክርና ኅብረት ፈጥረው ሕዝቡንም በማንቃት ዘመን ተሻጋሪ ጠንካራ አገራዊ አንድነት አረጋግጠዋል፡፡ ዛሬ በቆዳ ስፋቷ ከእኛ ኦሮሚያ ክልል ያነሰችው ጀርመን፣ በሥልጣኔም ሆነ በዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋ ግንባር ቀደም የምድራችን ተጠቃሽ አገር የሆነችው ከአገራዊና ከኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚመነጭ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞዋ ነው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ ማጠናከሪያ በሁለተኛነት ሩሲያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያቺ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችና በሶሻሊዝም ርዕዮት ቀዳሚ መሞከሪያነት የምትታወቅ ምድር፣ በታሪኳ በተመሳሳይ በጠባብነትና በዘረኝነት ከፍተኛ ፈተና አስተናግዳለች፡፡ ከሩሲያ አብዮት በኋላ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት ግራ ዘመም (Center Left) በመሆኑና በኒዮሊብራሊዝም ኃይል የቀዝቃዛው ጦርነት ተፅዕኖ ሶቮዬት ኅብረት ወደ 15 ብጥስጥስ አገሮች ልትበተን ችላለች፡፡ ዛሬም ድረስ የእነ ስታሊን ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፈለግ የኪሳራ ምልክት ሆኖ እየተጠቀሰም ይገኛል፡፡
ይሁንና አሁንም የተባባሩት ሩሲያ ፓርቲ ሀልዮትን በማግኘቱ (በተለይ ከቭላድሚር ፑቲን መምጣት በኋላ) በአንድ በኩል በዕድገትና ሥልጣኔ ቀዳሚ የምትባል አገር፣ በሌላ በኩል ያለውን ሕዝብ የሚያስተሳሳርና የተበተነውንም የሚመልስ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ እዚህም ላይ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አገራዊ አንድነት ማቆጥቆጡ ድርሻው ከፍተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡
የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት አገሮች አንዷ የሆነችው ቻይናንም ብንመለከት (ፀረ ዴሞክራሲያዊነቱም ቢኖር በሁሉም ሕዝቦች ላይ እንጂ ነጣጥሎ የሚፈጸም አይደለምና)፣ በሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ረገድ የማይናወጥ ሐውልት በመገንባት ከትውልድ ትውልድ የምትሸጋገር ምድር ነች፡፡ ይህም በተባባረና በሚደማማጥ የሕዝብ አቅም ዓለምን ጉድ ያሰኘ ዕድገትና ሥልጣኔ እንድታረጋጋጥ አስችሎታል፡፡
በመሠረቱ ፌዴራላዊ አስተዳዳርን ባትከተልም 1.3 ቢሊዮን ከሚሆነው የቻይና ሕዝብ ውስጥ 93 በመቶ የሚሆነው “ሀን” በሚባለው ብሔር የሚታቀፍ ነው፡፡ ቀሪው ስድስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብም የ56 አናሳ ብሔሮች አባል እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ግን በኮሙዩኒስት ፓርቲውም ሆነ በአገረ መንግሥቱ እንደ መጠናቸው የሚወከሉበት አግባብ ሳላለ፣ በአገረ ቻይና በእኩልነት መንፈስ የሚጠቀሙበት ዕርምጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ስለመጣ፣ ምንም ቢሆን እንደ ሕዝብ በአንድነታቸውና በቻይና ሉዓላዊነት ሊደራደሩ አይችሉም፡፡ መነጣጣልና የቂም በቀል ፖለቲካም በዞረበት አይታዩም፡፡
ከላይ ከጠቃቀስናቸው አገሮች በተጨማሪ በተለይ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚያራምዱ እንደ ህንድ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና መሰል አገሮችንም ስንመለከት፣ በቀለም (አልፎ አልፎ የሚታይ ችግር ቢኖርም) በዘርና በጎሳ ተሰባስቦ ከመታገልም ሆነ አንዱ ሌላውን ከማሳደድ ልክፍት ከተላቀቁ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አረረም መረርም በአገራቸው አንድነትና በሉዓላዊ አንድነታቸው ላይ መደናገርና መወዛገብ ውስጥም ሊገቡ አይችሉም፡፡
ብዙዎቹ እንደሌላው ዓለም ሁሉ በታሪካቸው ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ አስከፊ ጦርነቶችና አገዛዞችን ማሰለፋቸው ቢታወቅም የዛሬው ትውልድ በሥልጣኔና በዕድገት የራሱን ታሪክ እንዲጽፍ ከማንቃት ባሻገር፣ በማይበጀው ትርክትና ጥላቻ ላይ እንዲጠመድ አይፈልጉም፡፡ የዜግነት ፖለቲካ ሥር በሰደደበት መስተጋብር ውስጥ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለእኩልነትና ለአንድነት በመጠቀምም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንግዲህ እነዚህና ሌሎች በርካታ አገሮች አብነቶችን ስንፈትሽ የአገራችንስ ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ሊሆን ይገባዋል የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲ፣ መንግሥትንም ሆነ መላውን የፖለቲካ ልሂቃን እባካችሁ ከዘር፣ ከጎሳና ከጥላቻ ፖለቲካ ወጥተን በአንድ አገር በእኩልነትና በመተሳሳብ እንደሚኖሩ ሕዝቦች ተደማምጠን፣ በሠለጠነ መንገድ እንጓዝ ማለት መቻል አለብን፡፡
በመሠረቱ ከላይ እንደ ተጠቆመው የአገራችን አንዱ ትውልድ በጎሳ ፌዴራሊዝምና አክራሪ ብሔርተኝነት ሲነጉድ በመቆየቱ፣ ሁላችንንም ጎሰኛና መንደርተኛ እያደረገን መጥቷል፡፡ ነገር ግን በዚህ አካሄድ ከቀጠልን የጋራ ቤትና በታሪክ “የእኛ” ስንላት የኖርናትን አገር ለልጆቻችን ስለማስተላላፋችን ዋስትና ሊኖረን አይችልም፡፡ ልማት፣ ሰላምና ብልፅግናንም ማሰብ ከንቱ ምኞት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡
አገራችን ባለፉት 28 የኢሕአዴግ አገዛዝ ዓመታት የቆየችው ከመደብ ይልቅ፣ በብሔር የመብት ጥያቄ ላይ የሚነታረክ ትውልድ እንደያዘች ነበር፡፡ ይህ ሁነትም በልዩነት መዘውርና በነጣጣይ ፖለቲካ ተረግዞ የወለደልን አክራሪ ብሔርተኝነትን፣ የፖለቲካ ጥላቻንና መገፋፋትን ነው፡፡ እንደ አገር የምንከተለው በጎሳና በማንነት ላይ የሚያተኩረው ፌዴራሊዝም ቢሆን በልማት፣ በብሔረሰብ መብትና ታሪክ በማስተዋወቅ ረገድ ያመጣው ለውጥ እንዳለ ባይካድም፣ በአብዛኛው የሕዝቡንና የአገርን አብሮነትና መስተጋብር በተቃርኖ ፖለቲካ በማናጋት የአገረ መንግሥቱን አንድነት ክፉኛ አድክሞታል ቢባል ግነት የለውም፡፡
እንዲያው ከላይ ያነሳናቸውን አገሮች የኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የአገረ መንግሥት ጥንካሬ ትተን፣ አሁን ማን ይሙት የብሔር ፌዴራሊዝም አዋጭና ዘላቂ የአገር አንድነት የሚያስከብር ቢሆን ዛሬ በዚህ ደረጃ መገኘት ነበረብን? እንደ አገር “ተለወጥን!” እያልንስ ይህን ያህል አገራዊ ትርምስ (ተዟዙሮ የመሥራት፣ በየአካባቢው ተረጋጋቶ የመኖር፣ የማልማትና የመጠቀም ሥጋት ተባብሶ) ይታይ ነበር?
እስኪ ነገሩን በጥሞና እናጢነው፡፡ ችግሩ የተዘራው በ27 ዓመታቱ በኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ቢሆንም፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ምን ያህል ግጭት፣ ሥርዓት አልበኝትና መፈናቀል እንደተከሰተ ብሎም የሕዝብ አለመተማማንና የአገር ገጽታ እንዳሽቆለቆለ መመዘን የሚከብድ አይሆንም፡፡ በተለይ በማንነት ላይ የተመሠረቱት አብዛኞቹ ክልሎች ከፌዴራሉ መንግሥት ያፈነገጠ አካሄድ ለመከተል በመሞከር፣ የአገሪቱን ጉዳይም “አያገባኝም“ ወደሚል ጠርዝ በመግፋት ፀያፍ ድርጊቶች ሲያሳዩ ተመልክተናል፡፡
እንደሚታወቀው በሌላው አገር እምብዛም በማይታወቅ ሁኔታ የሥርዓቱ አካሄድ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትና የፈጠራ ተረክ የሞላበት ነበር፡፡ ይህ ጉዞ የዘር ፖለቲካን በመውለድ በሁሉም አካባቢ መካረርና የመስገብገብ ፍላጎት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሠረቱ በጎሳ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ትግል በየትኛውም አገር ቢሆን በዚህ ዘመን የሌለ ሲሆን፣ በነበረበት ጊዜም አገሮቹን ለኪሳራ የዳረገና ያዋረደ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡
በእኛ አገርም ሦስት አሥርት ዓመታትን ቆይቶ አዛውንቶቹ ኦነግና ሕወሓትን የመሳሰሉትን ኃይሎች ካለማክሰሙ ባሻገር፣ የዘመኑ አክራሪ ብሔርተኛ የፖለቲካ ኃይሎችም በአሁኑ ትውልድ በፈረጠመ ድጋፍ ተወልደዋል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ በሕጋዊነት ከተመዘገቡት ከ100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች 75 በመቶ የሚሆኑት የብሔር ፓርቲዎች እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ወጣቱም በመደብ፣ በዕድሜ ወይም በአቅጣጫና በአማራጭ ሐሳብ ከመሰባሰብ ይልቅ በማንነቱ (ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣. . .) እየተዋቀረ አስፈሪ መልክ ወደ መያዝ እያዘነበለ ነው፡፡
በመሠረቱ በአገሪቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት መተግበሩ በራሱ ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ ትልቁ ፈተና ግን ክልሎች በዋናነት በብሔር ንፍቀ ክበብ በመካለላቸው፣ በዘር የተደራጁ ሚዲያ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይል የመሳሳሉትን በአቅማቸው ልክ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳሻቸው በመገንባታቸውና በማዘዛቸው አጉል ፉክክር እንዲጀምሩ ይጋብዛል፡፡ ከክልል ወርዶ ዞኖችም በብሔር የተቋቋሙት የራሳቸውን የብሔርተኛ መንገድ እየተከተሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ የፌዴራሉ መንግሥት ደከም ያለ ሲመስል መፋጠጥ ላለመምጣቱ ዋስትና አይኖርም፡፡
እንግዲህ ዛሬ እንደ አገር ለውጥ ለማስቀጠልም ሆነ አገር ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን ጠብቃ እንድትሄድ ለማድረግ በምንፋለምበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ በዚያው ልክ አገርን ወደ ኋላ የሚመልሱና የተጠረቃቀሙ ተግዳሮቶችም አላላውስ እንዳሉን በግልጽ መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የሌሎች አገሮች ተሞክሮን ጭምር በማጣቀስ፣ እንደ ዜጋ የመፍትሔ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈልገውም የችግሮቹ ሁሉ ሰንኮፍ ከዘር ፖለቲካ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ ይህን ለመሻገር ደግሞ የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት በግልጽ የሚያረጋጋጥ መፍትሔ ያለ ይሉኝታ ማምጣት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለዚህም በሁሉም በኩል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግልን ማጠናከር ግድ የሚል ነው፡፡
በአጠቃላይ “የአገራችን ሕዝቦች ጨዋ፣ አንድነትና መከባበርን የሚያውቁ፣ ለዘመናት በመቻቻልና በመደማማጥ የዘለቁ፣ አንዳንዱ ሕዝብም በባህላዊ ተወፊቶቹ ዴሞክራሲያዊነትንና ዕርቅን የተለማማደ . . . ” እያልን ምንም ያህል ብንዘምር፣ ከአክራሪ ብሔርተኛ ፖለቲካ ካልተወጣ አገራዊ አንድነትና እኩልነትን ማስፈን አዳጋች መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የዘር፣ የጎሳና የማንነት ፖለቲካ ኅብረ ብሔራዊ ሆነውን ሕዝብ እየገፋ፣ ያለ ጥርጥር ጠባብነትና ዘረኝነትን እያፋፋ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ሁሉም ነገር “የእኔ ነው፣ የእኔ ነው” የማለቱ ስግብግብነትም ይባባስ እንደሆን እንጂ ሊቀንስ የሚችልም አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የለውጥ ኃይልና ይህ ትውልድ ዓለም በኪሳራ እየተዋረደ ከተወው የዘር ፖለቲካና ከጎሳ ፌዴራሊዝም አገሪቱን በማውጣት፣ ሕዝብን ያሳተፈ መፍትሔ ሊፈልጉ ግድ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡