Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የውሸት ዘመን ወጎች!

በፋሲካ በዓል ማግሥት መንገድ እነሆ። ከቦሌ ወደ ሜክሲኮ የሚያቀናው ታክሲ ወያላ ይጠራል። ‹‹ይኼም ኑሮ ተብሎ ያመላልሰናል ከአሁን እስከ ድሮ›› በማለት ‹‹ስለ ገብሬል?›› ብሎ እጆቹን ይዘረጋል ለማኙ። መንገዱ በሚያስደንቅ ትርምስ ውስጥ ገብቷል። ‹‹እውነት ቋንቋ ሁሉን መግለጽ ቢችል ኖሮ ማየት ባላስፈለገ ነበር። ተመልከተው አሁን ይኼን የመሰለ ሙሉ ጤነኛ ውለዱ ሲለን፤›› ሲል የምንሰማው የማናውቀውና የማያውቀን መንገደኛ ነው። እዚያ የሞላላቸውና ሐሳባቸው የሰከነ ማኪያቶ እየጠጡ ወግ ሲጠርቁ ይታያሉ። እዚህ ደግሞ ያልሞላላቸውና ተስፋቸውን ነገ ላይ የጣሉት ነገን ለመያዝ ይጣደፋሉ። ይገርማል፣ ያስደንቃል። እርጋታና ቀልብ ማጣት የማይግባቡ ወንድማማቾች መስለው ጎዳናው ላይ ፈሰዋል። ሕይወት በአስደማሚ ጎኗ ነፀብራቋ የሚወጋን ይኼኔ ነው። ‹‹አቦ በሩን ለቀቅ አድርገው በበዓል ማግሥት ሰው ጠፍቶ አልሞላልኝ ብሏል፣ ጭራሽ ይኼ. . .›› ሲል የሚሰማው ወያላው ነው። ‹‹ምንድነው ሰሞኑን?›› ይለዋል እሱም ተራውን ለመጥራት ተራ እየጠበቀ ያለ ወያላ። ‹‹እንጃ! ምናልባት የበዓል ጠላና አረቄ እያዳከሙት ከቤት መውጣት ትቶ ይሆናላ፤›› ብሎ ይመልስለታል። ታክሲዋን እየታከኩ ተፈራራቂ የልመና እጆች ይታዩናል፣ ድምፆች ይሰሙናል፡፡ 

እዚያ የሚያማምሩ ሕንፃዎችን እያየን የሀብትን ውበት እናደንቃለን። እዚህ የነዳያን ጩኸት የሕንፃዎቹን ዕይታችንን እያቋረጠ ድህነትን ያስታውሰናል። ከወያላችን ጋር የስላቅ ወግ የከፈተው ሌላ ወያላ፣ ‹‹አንተ ደግሞ የቤት ኪራይ በየወሩ እየጨመረ ‹ዲሽ› የመግዛት አቅምህን ስላዳከመው ‹ኢቲቪ› የነገረህን አምነህ ነው እንጂ፣ ስታስበው እነማን ጠግበው በልተው ነው በጠላና ጠጅ የሚዳከሙት? ተው የዘመኑ ሰው እንዴት ‹ነቄ› እንደሆነ ወይ አልገባህም ወይ እንዲገባህ አትፈልግም። መንግሥት ለቤት ወረፋ ተሠለፉ ከሚለን በምግብ ራስን ለመቻል ቢያሠልፈን ከልባችን እንዴት በወደድነው?›› ብሎ፣ ‹‹አቤቱ መንግሥታችን ሆይ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ጋግርልን፤›› ሲል ቀልዱን ቀጠለ። ‹‹ግባ ያራዳ ልጅ!››፣ ‹‹የእኔ አፍ ቁርጥ ይበልልህ!›› የሚሉ ወዳጆቹ ከበቡት። ይኼኔ እኮ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በዚህ ይሰፈር ይሆናል፡፡

‹‹ሜክሲኮ! ሜክሲኮ!›› ይጠራል ወያላው። በጎን ጥቃቅን ጨዋታዎችን እንደቀጠሉ ነው። ‹‹ሜክሲኮ! ሜክሲኮ! ሜክሲኮ ነህ? አስገባው. . . አምስት ብር ነው ታዲያ እ?›› ብሎ ተሳፋሪውን በማማተር ቀጠለ። ‹‹ስማ! አንተን እኮ ነው የምለው? ከመቼ ወዲህ ነው አምስት ብር?›› ተቆጣ ሽበታሙ ጎልማሳ። ወያላው አልመልስልህ አለው። ‹‹ሾፌር ከዚህ ሜክሲኮ ሦስት ብር አይደለም? ምንድነው የሚለው ይኼ?›› ድምፁ ውስጥ ያለው ንዴት እንደ እሳት ወላፈን ይጋረፋል። ወያላው፣ ‹‹ገና አሁን ነው እንዴ ከአውሮፕላን የወረድከው? የመቼውን ነው የምታወራው? በቃ ከተሳፈርክ አምስት ብር ትከፍላለህ! ትከፍላልህ! ካልሆነ ውረድ! የሚከፍል ይሄድበታል፤›› ብሎት ጀርባውን ሊሰጠው ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹እኔ ከአሜሪካም ከአውሮፓም ስላልመጣሁ አልወርድም፣ አልከፍልም። አልበዛም እንዴ?›› ሲል ነገሩ ተካረረ። ታክሲዋ ሞልታለች። መንቀሳቀስ ግን አልተቻለም። ሁሉም ድምፁን አጥፍቶ ተቀምጧል። ጎልማሳው ለራሱ ብቻ የሚከራከር ይመስል በነገሩ ጣልቃ የገባ ተሳፋሪ የለም። ወያላው ጎልማሳውን ይባስ ብሎ ሲያበሳጨው፣ ‹‹ከሌለህ የለኝም በል ችግር የለም። ይኼ ሁሉ ሰው በታሪፉ ተስማምቶ አንተ ከሰው ትለያለህ?›› ብሎ ተናገረው። ጎልማሳው የሚናገረው ጠፍቶት ይቁነጠነጣል።

‹‹ምን አልክ? እኔ በየቀኑ 12 ሰዓት እየለፋሁ የማገኘው ገንዘብ እኮ ነው። እንደ ማንም ከእነ ማንም በጉልበትና በሥልጣን የምሸመጥጠው ገንዘብ መሰለህ? ላቤን ጠብ አድርጌ የማመጣውን ገንዘብ በወጉ እጠቀምበታለሁ እንጂ አዳሜ መብትና ግዴታውን ሳያውቅ ዝም አለ ብዬ ዝም ብዬ አላልፍህም። አልከፍልህም አልወርድም. . .›› ከማለቱ ጉምጉምታ ይሰማ ጀመር። ወዲያው ሁሉም ተሳፋሪዎች ወያላው ላይ ወረዱበት። የመብት ማስከበር ሳይሆን ‹አሰደብከን› ዓይነት። ‹‹ይገርማል እኮ እዚህ አገር ራስን ችሎ መኖር መክበዱ እያስገረመኝ፣ ራስን ችሎ መናገርም ጭንቅ ሆነ?›› ይላል ከጎኔ የተቀመጠ ተለቅ ያለ ሰው። ‹የጋጋሪ ቆስቋሽ› ማለት ይኼኔ አይደል ታዲያ!?

ታክሲያችን ተንቀሳቀሰች። የወያላውና የጎልማሳው ግጭት በውስጠ ታዋቂነት በስምምነት የተቋጨ መስሏል። ይህን ያስተዋለች አንዲት ወጣት፣ ‹‹እዚህ አገር እኮ ከተጻፈው ሕግ ይልቅ የሚሠራው ያልተጻፈው ሕግ ነው። ምን ዋጋ አለው ደግ ደጉን እየተውን ክፉ ክፉውን ጠበቅ አደረግነው እንጂ፤›› ትላለች። ‹‹እንዴት?›› ትላታለች ወዳጇ። ‹‹ፈረንጆች ‹አን ሪትን ሎው› ይሉታል። አለ አይደል ደካሞችን እንደ ማገዝ፣ ትልቅ ሰውን ማክበር ዓይነት ያለውን፤›› ስትላት፣ ‹‹አሁን ይኼንን ወያላ ተባብረን ስለጮኽንበት ነው እንጂ እኛን አክብሮ አልያም ይሉኝታ ይዞት ዝም ያለው?›› አለቻት። ቆየት ብላ ደግሞ፣ ‹‹እውነት እንዳልሽው ካልተጻፉ የኅብረተሰብ ሕጎች የተገነቡ እሴቶች ቢኖሩን ኖሮ፣ ከማንም በላይ መንግሥት ነበር ሕዝብን ማክበር የሚባለውን ነገር አውቆ መገኘት የነበረበት፤›› ስትላት የሁላችንም ጆሮ ወደ እሷ ተሳበ።

‹‹አቤት! ታክሲ ላይ ሲሳፈሩ መቦጥለቅ ሲወዱ፤›› ይለኛል ከጎኔ የተቀመጠው። ‹‹ደግሞ መንግሥትን እዚህ ምን ዶለው?›› ስትላት ወዳጇ፣ ‹‹እንዴት አይዶለው? አገር በሌብነት ስትታገት፣ ሕዝብ በኑሮ ውድነት አበሳ በልቶ ማደር ጭንቅ ሲለው፣ ራዕይ አጥቶ በዘር ሲናጭ እያየ ዝም አይደል ያለው? የራሱ ራዕይ የሌለው ‹የአገራችንን ራዕይ እናስፈጽማለን› ይለናል፤›› ብላ ሳትጨርስ ከኋላ የተቀመጠ ወጣት አቋርጧት መናገር ጀመረ። ‹‹ልማቱና ግንባታው ቀጥሏል፣ በዘር በመደራጀት ሽለላው ቀጥሏል፣ የድል አጥቢያው አርበኛ ፉከራው አይሏል። ሕዝብ የሚፈልገውን ማስቀደም አልተቻለም። ተመልከቱ በየቴሌቪዥን ጣቢያው ሰላማዊ ሆኖ ቀርቦ በፌስቡክ ጦርነት የሚያውጀውን፡፡ አሁን እንዲህ ላለው የኅበረተሰብ ወኪል ነኝ ባይ ጭንቅላት መገንባት ወይስ መንገድ መገንባት መቅደም ይገባዋል?›› ብሎ ዝም አለ። እንዲህ ያሉ ቆንጠጥ የሚያደርጉ ንግግሮች በታክሲያችን ያልተጻፈ ሕግ መሠረት በስንት ጊዜ አንዴ የሚገኙ ሳይሆን፣ የዕለት ተዕለት ልማድ ስለሆኑ ለምደነዋል። ዳሩ ወያላው፣ ‹‹ለሥራ ብቃትም ሆነ ትጋት የሌለው ታታሪውን ያማል!›› የሚል ጥቅስ ለጥፎ ገና ማውራት ሳንጀምር አዲስ አጀንዳ ይሰጠናል፡፡

ታክሲያችን መፈትለኳን ቀጥላለች። የሕይወት አስታማሚዎች በሽንቁር ተስፋ መሀል ይፍጨረጨራሉ። ወራጅና ወጪ ስለተፈራረቁ የአቀማመጡ ‹ፎርሜሽን› ተለዋውጧል። ከሾፌሩ ኋላ ሁለት ቆነጃጅት ተቀምጠዋል። አስተውለን ስናያቸው ደግሞ ታዳጊዎች መሆናቸውን ታዝበናል። አለባበሳቸው ወጣቶቹን ሳይቀር ‹ወይ ስምንተኛው ሺሕ! ያስብላቸው ጀምሯል። ከእነሱ ኋላ ሁለት አዛውንት ባልና ሚስት አሉ። ሚስት በዓሉን በማስመልከት የሰሞኑን የዋጋ ግሽበት ያነበንባሉ። የቀረነው እንደነበርነው ነን። ‹‹ኧረ ጎበዝ ምንድነው እንዲህ ዝምታው?›› ብሎ ጀመረ ሽበታሙ ጎልማሳ። እኛ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱን ወሬ እየሰማ የሚያወራ ስለመሰለን ትከሻችን ሰብቀን ዝም አልን። ዝምታችን ሳይከነክነው አልቀረም። ንግግሩን ቀጥሏል። ‹‹በዚህ ከቀጠልን እኮ ዋጋ የለንም። እንዴ! መውለድ እንዲህ አሳፋሪና አስፈሪ እስኪሆን ድረስ ዝም ብሎ ማየት ደግ ነው?›› ሲል ስለምንና ስለእነማን እንደሚያወራ ገባን።

ስለዘመኑ ታዳጊዎች ልቅ የሆነ አዋዋልና አመሻሽ ነው ሊያወራ የፈለገው። ‹‹እኔምለው ምነው ወላጆች ሁሉንም ነገር መንግሥት ጫንቃ ላይ ጥለው ልጆቻቸውን ረሱዋቸው? ቢያንስ በ‹አነስተኛና ጥቃቅን› ደረጃ በየአካባቢው የወላጆች ማኅበር ለማቋቋም የሚያስቡ ይጥፉ?›› ሲል አሁንም ዝም አልን። አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹እህም! ልፋ ያለው አሉ። ‹ፋየር ኤጅ› አያውቅም እንዴ ሰውዬው?›› ይላል። አዟውንቷ ቀስ ብለው ያው የገበያ ውሏቸውንና የዋጋውን ንረት እየደጋገሙ ለባላቸው እያወሩላቸው ቀጠሉ። ሁላችንም ወዲያው ጠረጠርን፡፡ ምናልባት የወላጆች ግድ አለመስጠት አልያም ቸል ያሉ መምሰል ምክንያት የኑሮ ቋጠሮ ይሆን እንደሆነስ? ማን ያውቃል በየቤቱ ያለውን ትግል?

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ስፖርትና ኑሮ ተዛምደው የውይይት አጀንዳውን በተራቸው ተቆጣጥረውታል። በሰሞኑ የቻምፒዮንስ ሊግ መነሻ ጨዋታው መልኩን ቀየረ። ‹‹ቡድናችን በውጤት አልተቻለም እ?›› ይላል ከኋላ ከተቀመጥነው አራት ወጣቶች አንደኛው። ‹‹እንዴ! ምን ነካህ? ኑሮ ራሱ ትግል በሆነበት አገር እኛ ራሳችን ብንወዳደር አናሸነፍም?›› ይለዋል በእኔና በእሱ መሀል ላይ የተቀመጠው ወጣት። ወዲያው ደግሞ በበዓል ሰሞን ሆነባቸው መሰል ስለምግቡና መጠጡ ወሬ ተቀየረ፡፡ ይኼን ጊዜ የሚስታቸውን የገበያ ዝርዝር በመስማት ታክተው የነበሩት አባወራ አዛውንት ሐሳባቸውን ሰነዘሩ። ‹‹ምግብና መጠጥ ብርቅ ነው እንዴ? ወይስ ኑሮ ስለተወደደ ነው?›› አሉ በድንገት። የታክሲ ተሳፋሪዎች ግራ በመጋባት ተያዩ። አዛውንቱ ቀጠሉ፣ ‹‹እኛ አገር ማስቆም ያቃተን ስንትና ስንት አገር የሚያፈርስ እኩይ ድርጊት ሞልቶ እያለ መብላትና መጠጣት ምን ያስደንቃል? በአሁኑ ጊዜ ሌብነት የሚባል ቦምብ፣ ዘረኝነት የሚባል ቦምብ፣ የኢፍትሐዊነት ቦምብ፣ የቂመኝነት ቦምብ፣ የኑሮ ውድነት ቦምብ፣ ምኑ ቅጡ? የቱ ተጠርቶ የቱ ሊወራ? በየቀኑ ከፍንዳታቸው ብናመልጥ ከፍንጣሪያቸው የማንደበቅ ማነቆዎቻችን ቦምብ ቢባሉ ምን ያንሳቸዋል?›› ሲሉ የነገር አዛምዶአቸው ተመቸን።

ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን በስተቀኝ በኩል ከአጠገቤ ተቀምጦ የነበረ ተሳፋሪ፣ ‹‹እውነት የጊዜያችን ቦምቦች ተቆጥረው ያልቃሉ?›› በማለት ጠየቀኝ። አብራን የነበረች ኮረዳ፣ ‹‹ፍሬንድ ተረጋጋ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም የባሰው የውሸት ቦምብ ነው፡፡ በየሄድክበት ውሸት በዝቷል፡፡ በሬዲዮ፣ በቲቪና በፌስቡክ ወዘተ. . .›› አለችን፡፡ ‹‹በዩቲዩብማ ተውት፡፡ ከአሜሪካ እስከ አዲስ አበባ መቀደድ ሆኗል፡፡ ለካ ዘፋኞቹ እየተቀባበሉ ‹ለምን ይዋሻል?› ያሉት ወደው አልነበረም? ስለኢትዮጵያዊነት ይዋሻል፡፡ ያልተደረገ ነገር ተደረገ ተብሎ ይዋሻል፡፡ ዳያስፖራ ተብዬው ይዋሻል፡፡ ፖለቲከኛ ተብዬዎች ይዋሻሉ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይዋሻሉ፡፡ የብሔር ተጠሪ ነኝ ባይ ደላሎች ይዋሻሉ፡፡ ውሸት በውሸት ሆን እኮ ‘ለምን ይዋሻል?’›› ብላን ተለየችን፡፡ አሁን ነው ‹ለምን ይዋሻል?› መባል ያለበት እያሰብኩ ሳለ፣ የውሸት ዘመን ወጎች የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ በቅርቡ ገበያ ላይ የሚውል መሰለኝ፡፡ በውሸት ዘመን በህልማችን ሳይቀር የበላነው ምግብ በእውናችን ጭምር የሚያጠግብ ይመስለኝ ጀመር፡፡ ይኼኔ ነበር አንድ ወፈፍ ያደረገው ጎልማሳ፣ ‹‹ስማኝ ወገኔ! ለብቻህ እውነትን ይዘህ አትንገታገት፣ ዓለም የተሞላችው በሞላጮች ነው. . .›› ሲል፣ ብዙዎች አንገታቸውን በይሁንታ እየነቀነቁ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት