Sunday, February 5, 2023

አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በፈተናዎች የተተበተበው የፖለቲካ ምኅዳር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከደርግ መገርሰስ በኋላ በመሠረተው መንግሥት አማካይነት፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚደግፉ የሕግ ማዕቀፎችን ሲያዘጋጅና የተወሰኑ የተግባር ዕርምጃዎችን ሲወስድ ተስተውሏል፡፡ ይሁንና ይኼ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ፖለቲካውን በማላቅ ረገድ ሊኖረው የሚችለውን ሚና ባገናዘበ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገ ባለመሆኑና የገዥው ፓርቲም ሙሉ ቁርጠኝነት ስላልነበረ፣ በሚጠበቀው ደረጃ በአገሪቱ ሊመጣ አልቻለም ተብሎ በበርካታ ምሁራንና ፖለቲከኞች ይተቻል፡፡

ኢሕአዴግ ፖለቲካውን በበላይነት በመቆጣጠር በተቃዋሚ ጎራ ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እምብዛም ፋይዳ እንዳይኖራቸው አድርጓል ተብሎ የሚተች ሲሆን፣ ፓርቲ መሥርተውም ትግል እናደርጋለን የሚሉ ቡድኖችም ቢሆኑ የገዥው ፓርቲ ምርኮኞች እንጂ በራሳቸው ፕሮግራምና ዓላማ የሚመሩ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ሆኖም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር የትየለሌ ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲወጡ የነበሩ ቁጥሮች እንደሚያመለክቱት፣ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበውና ዕውቅና ተሰጥቷቸው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች ቁጥራቸው ከ70 አያንስም ነበር፡፡ ለአብነት ያህልም በ2007 ዓ.ም. በነበረው ጠቅላላ ምርጫ ለፓርላማ መቀመጫ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 52 ነበር፡፡ በክልል ምክር ቤቶች በተደረገው ምርጫ በአሥራዎቹ የሚቆጠሩ ፓርቲዎች ተወዳድረው ነበር፡፡ ነገር ግን ቁጥሮቹ ምንም ታሪክ የማይናገሩ ባዶ አኃዞች ናቸው እንጂ፣ ለትንታኔ የሚመች መልዕክት የላቸውም የሚሉ ትችቶች በተደጋጋሚ ይሰነዘራሉ፡፡

ይኼ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ለፖለቲካ ሥርዓቱ ራሱን የቻለ አሉታዊ ተፅዕናዎች እንደሚኖሩት ሲነገር የቆየ በመሆኑ፣ በተለይ መራጩን የማወዛገብና ግራ የማጋባት ሚናቸው የጎላ እንደሚሆን ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲዎች እምብዛም ልዩነት ሳይኖራቸው የተለያዩ ቡድኖችን በተናጠል የመመሥረትና የመምራት ባህልን እንዳዳበሩና በዚህም ምክንያት ወደ ላቀ የፖለቲካ ተሳትፎ መግባት እንዳልተቻላቸው ይነገራል፡፡

አሁን በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ110 በላይ የደረሱ ሲሆን፣ አዳዲስ ፓርቲዎች በመመሥረት ላይም ይገኛሉ፡፡ ይኼ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛትና በየጊዜው መጨመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ፓርቲያቸውን ሳይቀር ያሳስባቸው ይመስላል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በመንቀሳቀስ የሚገኙ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈራረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ፓርቲዎች ሰብሰብ እንዲሉ ጥሪ በማቅረብ፣ ይኼንን ማድረግ ከተቻለ እሳቸውም ጭምር በግል ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚሹ ገልጸው ነበር፡፡ ይኼንን ሐሳብ ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ከ80 በላይ ከሆኑ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም ያንፀባረቁ ሲሆን፣ ፓርቲዎቹ ሦስትና አራት ቢሆኑ ለድጋፍ እንደሚያመቻቸው ተናግረዋል፡፡

ይኼንን ተከትሎ አብሮ ለመሥራት ያስችለናል ካሉት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ውይይት የጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ ተግባራዊ የሆነ ውህደት አልታየም፡፡ የተወሰነ ተጨባጭ ዕርምጃ የታየው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓና አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ስድስት ፓርቲዎች ያደረጉት ራስን የማክሰምና የመዋሀድ ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን ይኼም አልተጠናቀቀም፡፡

ይህ ቢሆንም ቅሉ በአገሪቱ የተለየዩ አካባቢዎች አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተመሠረቱ ሲሆን፣ እነዚህ ፓርቲዎች ለመመሥረት በቂ ምክንያት አለን ይላሉ፡፡ ከእነዚህ አዳዲስ ፓርቲዎች አንደኛው የሆነው የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሲሆን፣ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ሚካኤል ለማ ለፓርቲው መመሥረት ዋነኛ ምክንያት የሆነው በወላይታ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ኢፍትሐዊነት በብቃት የሚታገል የፖለቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡

መሥራች ጉባዔውን ሚያዝያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በወላይታ ሶዶ ከተማ አድርጎ አሁን ከ1,000 በላይ የተመዘገቡ አባላት እንዳሉት የገለጹት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር፣ የአጭር ጊዜ ዕቅዳቸው በፀደቀው ሕገ ደንብና መመሥረቻ ጽሑፍ አማካይነት ሕጋዊነትን ማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በረዥም ጊዜም በምርጫ መሳተፍና አደረጃጀትን ማጠናከር ዕቅዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ንቅናቄ እንደ መሆናችን መጠን ዋነኛ ትኩረታችን ንቅናቄ ነው፡፡ የፖለቲካዊ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ንቅናቄ ለማምጣት እንተጋለን፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ሚካኤል፣ በፖለቲካ ረገድ የወላይታ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል የክልልነት ጥያቄውን በጉልህ እንደሚያራምዱ በመግለጽ፣ ‹‹የወላይታ ሕዝብ ለረዥም ዓመታት የነገሥታት አመራር የነበረውና ከ52 በላይ ነገሥታት ያስተዳደረው ወላይታ ሕጋዊ፣ ትክክለኛና ራሱን የቻለ አስተዳደር ያስፈልገዋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ የወላይታ ሕዝብ የሥራ ዕድሉ እንዲሰፋና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲደረግለት እንደሚታገሉ፣ ብሎም በማኅበራዊ ዘርፍ ሚሊዮኖች የሚናገሩት የወላይታ ቋንቋ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እንደሚሠሩ፣ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ኃይለ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡

ስለዚህ የወላይታን ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅና ለእነዚህ ዓላማዎች የቆመ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ ፓርቲውን መመሥረታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም በመጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም ላይ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት የቀድሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) እና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር)፣ ፓርቲያቸው በደቡብ ክልል ከሚመሠረቱ ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሮና ተመርጦ መምራት እንደሚፈልግ ገልጸው፣ በክልሉ ለሚነሱ የተለያዩ የክልልነት ጥያቄዎች የሚደረገው ጥናት ደኢሕዴን የሚመራቸውን ክልሎች ለመመሥረት እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

እንደ አቶ ኃይለ ሚካኤል አቋም ግን ይኼ በፍጹም ሊደረግ እንደማይቻልና ደኢሕዴን የወላይታን ሕዝብ እንደማይወክል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ደኢሕዴን የወላይታን ሕዝብ ህልውናና ጥቅም አያስጠብቅም፡፡ የወላይታ ሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ የወደቀው በደኢሕዴን ምክንያት ነው፤›› ሲሉም አምርረው አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ይኼንን አቋምና እምነት በመያዝም በትብብር አብረው መሥራት ከሚችሏቸው ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የዳሰሳ ጥናት እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በትግራይ ክልልም በቅርቡ የተመሠረቱ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) እና ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ናቸው፡፡

የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ የሚል ትርጓሜ የያዘው የባይቶና ፓርቲ መሥራች ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ኪዳኔ አመነ ለፓርቲው መመሥረት ዋነኛ ምክንያት የሆናቸው፣ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ እንደሆነና የችግሩ ፈጣሪ የሆነው ኢሕአዴግ የችግሩ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል በማመን እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ይኼንን ችግር ብቻውን መፍታት ስለማይችልም የመፍትሔ አካል ለመሆን እንደሚሹና ዋነኛ መንቀሳቀሻቸውንም በትግራይ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በአገራችን በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ይኼ የሆነው በዋናነት በኢሕአዴግ ካድሬዎች ተሳትፎ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ምንጩ የኢሕአዴግ መዋቅር ነው፡፡ በፓርቲው ውስጥ ፖለቲካውና የመንግሥት ሥራ ባለመለየቱ እኛ የምንሻው ሀቀኛ ዴሞክራሲ ሊመጣ አይችልም፡፡ መንግሥትና ፓርቲ የማይለይበት አሠራር በመኖሩ ይኼንን ለማስተካከል እንጥራለን፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት ባለሥልጣናትና ለመንግሥት ቅርበት ባላቸው ሰዎች ቁጥጥር ሥር የገባው ኢኮኖሚም ቀውስ ውስጥ እንዳለ በመግለጽ፣ ‹‹ማዕቀብ የተጣለበት አገር ይመስል ለመድኃኒት ብቻ ነው የውጭ ምንዛሪ ያለኝ የምትል ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምንኖረው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ተቋም ገለጻ አራት ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖሩ የሚችሉ ሲሆን፣ ተቋማዊ የሆኑ ብሔራዊ የፕሮግራም ፓርቲዎች የሚለው ክፋይ እነዚህ ሁለቱን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ፓርቲዎችን የሚገልጻቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፓርቲዎች የአንድ ብሔር ድጋፍ ሊኖራቸው እንደሚችል፣ ከጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ ሊመነጩ እንደሚችሉም ያትታል፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፕሮግራም ሊኖራቸው ቢችልም፣ ያላቸው የሰፋ ግንኙነት የፖሊሲ ወጥነት እንዳይኖራቸው ሊያደርግም ይችላል ሲል ያመለክታል፡፡

ለመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2014 ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ሰለሞን ገብረ ዮሐንስ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔርን መሠረት አድርገው ከተቋቋሙ ፕሮግራም ለመከተል አያስችላቸውም ይላሉ፡፡ ይኼም የሚሆነው ምርጫዎች የሚያደርጉት በፖሊሲ ክርክሮች ላይ ተመሥርተው አይሆንምና ነው ሲሉም ይደመድማሉ፡፡

አጥኚው ይኼንን ይበሉ እንጂ የዎብን ምክትል ሊቀመንበር ፓርቲያቸው የሚከተለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተራማጅ ዴሞክራሲ (Progressive Democracy) እንደሆነ በመግለጽ፣ ይኼም ምናልባትም በየትኛውም ፓርቲ ያልታሰበና የተለየ የፓርቲ ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹እያንዳንዱን ጉዳይ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እናያለን፡፡ ቀኖናዊ የሆነ ምንም አካሄድ የለም፤›› የሚሉት አቶ ኃይለ ሚካኤል፣ ለአብነትም የቡድን መብትና የግለሰብ መብት እኩል መከበር አለባቸው እንጂ አንዱ ሲከበር ሌላኛውን ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ይከበራል ይባላል እንጂ፣ ዜጎች ያሉባት አገርም አትመስልም፤›› ሲሉም ይተቻሉ፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነትና የግሉን ዘርፍ ሚና በእኩል ማስኬድን እንደሚደግፉ፣ ብሎም መንግሥት ያለውን ውስን ሀብት በማከፋፈል ላይ ብቻ ሳይሆን ሀብት ፈጠራ ላይም መሳተፍ እንዳለበት እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡

በተመሳሳይ የባይቶና አንዱ መሥራች አቶ ኪዳኔ የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም የመሥራች ጉባዔ ሲደረግ ይፋ የሚሆን እንደሆነ በመግለጽ፣ በብዛት ግን ወደ ሶሻል ሊበራሊዝም እንደሚያዘነብሉ አስታውቀዋል፡፡ ለቡድንና ለግለሰብ መብቶች የሚያታግል ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ በመናገር፣ በበለጠ መገለጫዎቹን ግን ከመሥራች ጉባዔው በኋላ እንደሚያስታውቁ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም እንኳን ይኼንን ርዕዮት እንከተላለን፣ ለዚህ ዓላማና ለዚህ ሕዝብ ጥቅም ተደራጀን ቢሉም የጥያቄና የመሠረታዊ አቋም ልዩነት የላቸውም የሚሉ ትችቶች በተደጋጋሚ ሲሰነዘሩባቸው ይደመጣሉ፡፡

ይኼንን ዕውነታ የዎብን ምክትል ሊቀመንበር እንደሚያምኑበት ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ በርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች አሉ፡፡ የእነዚህ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የራስን ቋንቋና ባህል የማሳደግና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች አንድ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ኃይለ ሚካኤል፣ የወላይታ ጥያቄ ከሲዳማና ከካፋ ጥያቄዎች እንደማይለይ ነገር ግን የኢፍትሐዊነቶቹ መጠን ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ እየበራከቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለፖለቲካ ሥርዓቱ ማጠናከሪያና ለመራጩ ምርጫ ከመሆን ይልቅ አወዛጋቢና ግራ አጋቢ ሊሆኑ ይችላሉ ከሚሉ ትችቶች በዘለለ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው በበርካታ ፈተናዎች የተተበተቡ መሆናቸውን ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡

ለጉተንበርግ ዩኒቨርሲቲ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን መዋቅር በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2014 ጥናት ያደጉት አቶ ጉደታ ከበደና አቶ ዓለሙ ካሳ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፈተናዎች የገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ፣ ሕዝቡ ለፖለቲካ ተሳትፎ ያለው ፍርኃትና ራስን ማራቅ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያሉ አለመግባባቶች፣ አናሳ መዋቅራዊ ጥንካሬ፣ እንወክለዋለን ከሚሉት ሕዝብ ጋር ያላቸው የላላ ግንኙነትና በጥቂት ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዙሪያ መሰባሰባቸው፣ የግንዛቤ እጥረት፣ ሰፊ የአባላት መሠረት አለመኖር፣ ከተሳትፎ መገለልና የውስጥ ዴሞክራሲን ማጣት ናቸው ሲሉ ያሰገነዝባሉ፡፡

ሆኖም አሁን በወጣቱ ዘንድ የተፈጠረው የፖለቲካ መነቃቃት የተወሰኑትን ፈተናዎች ሊቀርፍ የሚችል ዕድል እንደሚያመጣ በጉዳዩ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -