Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የገንዘብ ሚኒስቴር የተቀናሽ ወጪዎች መመርያ ሲቃኝ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስለተቀናሽ ወጪዎች የሚደነግገው አዲሱ የገንዘብ ሚኒስቴር መመርያ፣ የንግድ ተቋማት የወለድ ወጪዎቻቸው እንደ ተቀናሽ ወጪ ሊያዝላቸው የሚችለው በብድሩ የተገኘው ገንዘብ ለንግድ ሥራ እንቅስቃሴ መዋሉ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ መመርያው ተቀናሽ ወጪዎችን በተመለከተ በተበታተነ ሁኔታ ሲሠራባቸው የነበሩትን መመርያዎች ማሻሻያዎችን በማከልና አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካቶ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደረገበትም ነው፡፡ በቅርቡ በገንዘብ ሚኒስቴር ፀድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ሰባት መመርያዎች ውስጥ አንዱ በሆነው በዚህ ስለተቀናሽ ወጪዎችን የሚመለከተው መመርያ ቁጥር 5/2011፣ በውስጡ 21 አንቀጾችን ያካተተና አጠቃላይ ወጪዎች ስለሚቀነሱበት ሁኔታና ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎች የትኞቹ እንደሆነ በዝርዝር ያስቀመጠ ነው፡፡

በዚህ መመርያ ውስጥ ቀደም ብሎ ከነበረው አሠራር ማሻሻያ ተደርጎበት ከቀረቡት ውስጥ የወለድ መጠንን የሚመለከተው አንዱ ሲሆን፣ የወለድ ወጪ ሊፈቀድ የሚችለው በብድሩ የተገኘው ገንዘብ ለንግድ ሥራ እንቅስቃሴ መዋሉ ሲረጋገጥ እነደሆነ ያመለክታል፡፡ ሆኖም የፋይናንስ ተቋማትን ሳይጨምር አንድ ግብር ከፋይ ለተወሰነ የሥራ እንቅስቃሴ የወሰደውን ብድር ለሌላ ዓላማ የሚያውል ወይም ይህንኑ ብድር ለሌላ ተግባር በብድር የሰጠ ከሆነ፣ የሚፈቀድለት ተቀናሽ የወለድ ወጪ ለሌላ ያበደረው ብድር መጠን ብቻ ስለመሆኑ በአዲሱ መመርያ ውስጥ ተመልክቷል፡፡

አንድ ግብር ከፋይ በዱቤ ለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ዋጋውን እስኪከፍል ድረስ ወለድ እንደሚከፈልበት ውል የገባ እንደሆነ፣ ለከፈለው የወለድ መጠን በአዋጁና በደንቡ መሠረት የወጪ ተቀናሽ የሚፈቀድ መሆኑንም የወለድ መጠንን በተመለከተው የመመርያው ክፍል ውስጥ ተካቷል፡፡

ከዚህም ሌላ ግብር ከፋይ ሕንፃ ለመገንባት ብድር የወሰደ እንደሆነ ሕንፃው እስኪጠናቀቅ ድረስ የተከፈለው ወለድ በእርጅና ተቀናሽ የሚካተት ሆኖ ሕንፃው ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የተከፈለው ወለድ በወጪ ተቀናሽ የሚፈቀድ ይሆናል፡፡

የተቀናሽ ወጪን በተመለከተ የወጣው ይህ መመርያ በዋናነት ተቀናሽ ወጪዎች የትኞቹ እንደሆኑም በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህንንም ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎች ማንኛውም በግብር ከፋዩ ግቢ ውስጥ የተካተቱትን ገቢዎች ለማስገኘት ለሥራው ዋስትናና ሥራውን ለማስቀጠል በግብር ዓመቱ ውስጥ የተደረገ አስፈላጊ የሆነ ወጪ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ እንደ ወጪ እንደሚያዝ ያመለክታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አስፈላጊ ወጪዎች ተብለው በተጨማሪነት ያካተታቸው ደግሞ በነፃ የሚጠቀምበት ወይም በተረከበው ሕንፃ ሥራውን ሲያከናውን ቤቱን በሰጠው ወይም በአከራዩ ስም በሚታወቀው የመብራት፣ የውኃ ወይም የስልክ ቆጣሪ የተጠቀመ እንደሆነ ተቀናሽ ወጪው እንዴት የሚሰላ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ እነዚህ እንደ መብራትና ውኃ ያሉ ክፍያዎች በግብር ከፋዩ እንደሚከፈሉ በግልጽ በውል ውስጥ የተካተተ ስለመሆኑ ከተረጋገጠና ወጪው የተከፈለበትን ደረሰኝ ኦርጂናል ካቀረቡ እንደ ወጪ የሚያዙ መሆኑን ነው፡፡ በተያያዘም ለማዘጋጃ ቤት አገልግሎት የተከፈለ ክፍያ፣ የተመዘገበ ተርን ኦቨር ታክስና ኤክሳይዝ ታክስ እንዲሁም ተመላሽ ያልተደረገ ወይም በጊዜው ባለመቅረቡ ተመላሽ የማይደረግ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተበላሸ ዕቃ ዋጋ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውና የተወገዱ ዕቃዎች ዋጋ ለማስወገድ የወጣ ወጪም በተመሳሳይ በወጪ እንደሚይዝ አመልክቷል፡፡

ሆኖም ግብር ከፋዩ ለንግድ ድርጅትና መኖሪያ ቤት በአንድ የመብራት፣ የስልክ ወይም የውኃ ቆጣሪ የሚጠቀም ከወጪው 75 በመቶ ብቻ እንደሆነ የሚያመለክተው በመመርያው እንደ ወጪ ከሚያዙ ካስቀመጣቸው ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ወጪዎች ከሚያስገኙት ገቢ ለሥራው ከሚሰጡት ዋስትናና ቀጣይነት ጋር ሲነፃፀር ያልተጋነኑና ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ወጪዎቹ የተጋነኑ በሚሆኑበት ጊዜ ባለሥልጣኑ በዚህ መመርያ መሠረት ገቢዎች ሚኒስቴርን በተገቢው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ማስተካከያ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቅሳል፡፡

አንድ ግብር ከፋይ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴው በተቋረጠበት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ወይም ሥራ ባላገኘበት ጊዜ ያወጣው ወጪ የማይቀየር ወጪ ሆኖ ከተገኘ፣ ገቢ ያላስገኘ ወጪ ቢሆንም በወጪ ተቀናሽ ሊፈቀድለት እንደሚችል በዚሁ መመርያ ተካቷል፡፡

ግለሰብ የንግድ ሥራ ባለሀብት ከመደበኛ የሥራ ቦታው ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ በመሄድ የንግድ ሥራውን ለማከናወን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሚያወጣቸው ወጪዎችን በተመለከተም በመመርያው ተካቷል፡፡ በዚሁ መሠረት ለምግብና ለመኝታ ለአንድ ቀን እስከ 1,000 ብር፣ ለትራንስፖርት ያወጣው ወጪ በሥራ ላይ ባለው የአየር፣ የውኃና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋጋ መሠረት በማስረጃ ተረጋግጦ የወጪ ተቀናሽ የሚፈቀድለት ሆኖ ከዚህ መጠን በላይ የሚያወጣው ወጪ በተቀናሽ ወጪ የማይያዝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው በቋሚነት ለሚሠራ ድርጅቱ ይቅም ያደረገውን ትክክለኛ ወጪ ለመተካት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በቋሚነት የሚሠራ ድርጅት የሚፈጽመው ክፍያ ተቀናሽ የሚደረገው ወጪው የንግድ ሥራ ገቢ ለማግኘት ለንግዱ ሥራ ዋስትና ለመስጠት ወይም የንግድ ሥራውን ለማስቀጠል የተደረገና በቋሚነት በሚሠራው ድርጅት ሊሠራ የማይችል ከሆነ ብቻ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

የጥቃቅንና አንስተኛ ድርጅት በሥራ ላይ ላሰማራው አባሉ የሚከፍለው ደመወዝ እንደ ወጪ ተቀናሽ የሚፈቀድለት ስለመሆኑ እንዲሁም በዲዛይን ለውጥ ምክንያት ሕንፃ ፈርሶ ላሰማራው አባሉ የሚከፍለው ደመወዝ እንደ ወጪ ተቀናሽ ይያዛል የሚል ተቀምጧል፡፡ የተሽከርካሪ ጎማ የሚሰጠው አገልግሎት ከአንድ ዓመት ያነሰ እንደሆነ እንደ አላቂ ዕቃ ተቆጥሮ በተቀናሽ ወጪ የሚያዝ መሆኑንም መመርያው ያመለክታል፡፡

መመርያው የማስታወቂያ ወጪዎችን በተመለከተም የንግድ ሥራ ለማስተዋወቅ በወጪነት የሚያዘው ግብር ከፋይ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ለሚደረግ የማስተዋወቅ ሥራ በገንዘብ ወይም በምርት ወይም በአገልግሎት የሚፈጸመው ክፍያ ወጪ ተቀናሽ የሚያዘው ከጠቅላላ ገቢ ሦስት ከመቶ ባልበለጠ መጠን ብቻ እንደሆነ ነው፡፡  

ግብር ከፋይ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ ለመገናኛ ብዙኃን ወይም ለማስታወቂያ ድርጅት የሚከፍለው ክፍያ ሙሉ በሙሉ በወጪው ተቀናሽነት የሚያዝለት ሲሆን፣ ምንም የማስተዋወቅ ሥራ ሳይሠራበት የሚሰጥ ገንዘብ ምርት ወይም አገልግሎት ክፍያ በማስታወቂያ ወጪ ተቀናሽ ሆኖ እንደሚያዝም ያመለክታል፡፡

በዚህ የገንዘብ ሚኒስቴር አዲሱ መመርያ ውስጥ ለበጎ አድራጎት ሥራ የሚደረጉ ሥራዎች ተቀናሽ ወጪን በተመለከተ የሰፈረ ድንጋጌው ደግሞ  በአዋጁ አንቀጽ 24/2/ በጎ አድራጎት የሚደረጉ ሥጦታዎች በወጪ ተቀናሽነት የሚያዙት የዚህ ዓይነት ወጪ ከግብር ከፋዩ ግብር የሚከፈልበት የግብር ዓመቱ ገቢ ከአሥር በመቶ ካልበለጠ ብቻ ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡ ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም ግብር የሚከፈልበት የግብር ዓመቱ ገቢ ማለት ለበጎ አድራጎት ሥራ የተደረጉ ሥራዎች ሳይቀንሱ በሒሳብ መዝገብ የታየው ግብር የሚከፈልበት ገቢ ነው፡፡

ይህ መመርያ የእርጅና ተቀናሽ ሒሳቦችን እንዴት እንደሚያስተናግድ የሚያመለክቱ አንቀጾችንም የያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ ለንግድ ሥራ በጥቅም ላይ የዋለው የሕንፃ ክፍልን የተመለከተው አንዱ ነው፡፡ በግብር ከፋዩ የተገነባ ሕንፃ የእርጅና ቅናሽ መታሰብ የሚጀምረው ሀብቱ የንግድ ሥራ ገቢውን ለማስገኘት ለአገልግሎት ዝግጁ ከሆነበትና አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ቀን አንስቶ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ተቆጣጣሪው ለባለሥልጣን ለግብር ከፋዩ የሕንፃ ግንባታው ስለመጠናቀቁ የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ከሰጠበት ጊዜ በፊት ሊሆን እንደማይችል በመመርያው ተካቷል፡፡፡ ለእርጅና ተቀናሽ አያያዝ ከጠቅላላ የሕንፃ ስፋትና ዋጋ ለንግድ ሥራው ጥቅም ላይ የዋለው የሕንፃው መጠን ዋጋ ተለይቶ ካልቀረበ፣ በወለሉ ስፋት መቶኛ በማስላት ዋጋው ተለይቶ መቅረብ እንደሚኖርበትም ያሳያል፡፡

ግብር ከፋዩ በዚህ መሠረት ለይቶ ካላቀረበ ከጠቅላላ የሕንፃው ዋጋ ለንግድ ሥራው የዋለው የሕንፃው ስፋት መጠን በማስላት ባለሥልጣኑ በራሱ ወስኖ ተቀናሽ ያደርጋል፡፡ ጥቅም ላይ የዋለ የሕንፃ ክፍል ማለት የሕንፃው ለሌላ ዓላማ እስካልዋለ ድረስ ግብር ከፋዩ ሕንፃውን ለኪራይ አገልግሎት ዝግጁ ያደረገ ከሆነ ሕንፃው ባይከራይም ለኪራይ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተቆጥሮ ከቤት ኪራይ በተገኘ ገቢ ላይ ግብር በሚሰላበት ጊዜ እንደ ወጪ ተቀናሽ ሊያዝለት ይገባል ይላል፡፡ ለኪራይ ገቢ ግብርም በተመሳሳይ ተፈጻሚ ይሆናሉ የሚሉ አንቀጾችን ይዟል፡፡

ለእርጅና ቅናሽ መሠረት የሆነ ዋጋ ካልቀረበ በገበያ ዋጋ ስለመወሰን ደግሞ  የአንድ ዋጋው የሚቀንስ ሀብት የእርጅና ቅናሽ ለማስላት መሠረት የሆነው የተሠራበት ወይም የተገዛበት ዋጋ የሚገልጽ ሰነድ ታክስ ከፋዩ ማቅረብ ያልቻለ እንደሆነ ባለሥልጣኑ በታክስ አስተዳደሩ አዋጅ መሠረት በሚወሰነው የተሠራበት ወይም የተገዛበት የገበያ ዋጋ 70 በመቶ የእርጅና ተቀናሽ ይፈቀድለታል ይላል፡፡ ድንጋጌ ቢኖርም ሀብቱ የተገዛበት ወይም የተሠራበት ዋጋ የተጨማሪ እሴት ታክስ የግብዓት ታክስ የተካካሰለት ከሆነ የተካካሰው መጠን በሚፈቀድለት የእርጅና ተቀናሽ ዋጋ ውስጥ አይካተትም፡፡

የእርጅና ቅናሽ የሚፈቀድበት ሁኔታ በተመለከተ መመርያው ስለእርጅና የሚደረገውን ቅናሽ ለመወሰን ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባቸዋል ያላቸውን የእርጅና ቅናሽ ጊዜያቸውን ያልጨረሱ ንብረቶች ሽያጭ የተከናወነው ግንኙነት ባላቸው ሰዎች መካከል ከሆነና የተላለፈበት ዋጋ ከተጣራ የመዝገብ ዋጋው የሚበልጥ ከሆነ የእርጅና ቅናሽ ለማስላት መሠረት የሚሆነው የተጣራ የመዝገብ ዋጋው ስለመሆኑም አመልክቷል፡፡

ዋጋው እየቀነሰ የሚሄድ የእርጅና መጠን የሚሰላው በግብር ዓመቱ መጀመርያ በነበረው የተጣራ የመዝገብ ዋጋ ላይ የእርጅና ተቀናሽ ምጣኔውን በማስላት ይሆናል፡፡ በግብር ዓመቱ መጀመርያ የነበረው የተጣራ የመዝገብ ዋጋ ማለት ከመጀመርያው የመዝገብ ዋጋ በየጊዜው የተቀነሱ የእርጅና ተቀናሾች ከተቀነሱ በኋላ የሚገኝ ዋጋ ነው፡፡

ሀብትን ማስተላለፍና ባለቤትነትን መያዝ ጋር በተያያዘም በዚህ መመርያ  ለእርጅና ቅናሽና የካፒታል ሀብት በማስተላለፍ በሚገኝ ጥቅም ላይ ለሚከፈል ግብር ዓላማ ምዝገባ የሚፈጸምበት ሀብት በሽያጭ፣ በልውውጥ ወይም በሥጦታ ሲተላለፍ አስተላላፊው ሀብቱን እንዳስተላለፈ የሚቆጠረውና የተላለፈለት ሰው ሀብቱን በባለቤትነት እንደያዘ የሚቆጠረው የሽያጭ የልውውጥ ወይም የሥጦታ ውል ለመዋዋል ሥልጣን በተሰጠው አካል ዘንድ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ሆኖ የእርጅና ተቀናሽ ሊጠየቅ የሚችለው ሀብቱ የተመዘገበ መሆን ሲረጋገጥ ነው፡፡

በዚህ ስለተቀናሽ ወጪዎች መመርያ በምርት ዝግጅት አቅርቦት ሒደት የሚያጋጥምን ብክነት እንደ ወጪ መያዝ እንዲቻል የተካተተው አንቀጽ ደግሞ በምርት ዝግጅትና አቅርቦት ሒደት (በብጣሪ፣ በትነት፣ በሽርፍራፊና በቆይታ ጊዜ ወዘተ.) የሚባክን  ምርት የዕቃ መጠን በሚመለከተው የመንግሥት አካል በቀረበ ጥናት መሠረት እንደ ወጪ ሊያዝ እንደሚችል ያመለክታል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት የተሟላ ጥናት ማግኘት ካልተቻለ ባለሥልጣኑ ከግል ተቋም፣ ከግብር ከፋዮች፣ አግባብነት ያለው አካል ወይም ባለሥልጣኑ በሚያደርገው ጥናት መሠረት ወጪ የሚያዝበት መጠን ሊወሰን እንደሚችል ታውቋል፡፡

ተቀናሽ የሚደረግ የመዝናኛ ወጪ እንዴት መያዝ እንዳለበት የሚያሳየው ሌላው የመመርያው ክፍል የማዕድን ማውጣትና ፍለጋ፣ የማኑፋክቸሪንግና የግብርናና ሆርቲ ካልቸር ሥራ ላይ የተሰማራ ቀጣሪ ለተቀጣሪ በነፃ የሚያቀርበው ምግብና መጠጥ ዋጋ በዚህ መሥሪያ መሠረት በወጪ የሚያዘው በአንድ ወር የሚያወጣው ወጪ በወሩ ለተቀጣሪዎቹ ካወጣው አጠቃላይ የደመወዝ ወጪ ከ30 በመቶ ባልበለጠ መጠን ብቻ ነው ይላል፡፡

አያይዞም በሆቴሎች፣ በሬስቶራንቶች ወይም በሌሎች የምግብ አገልግሎት በሚያቀርቡ ተቋማት ውስጥ ለተሰማሩ ሠራተኞች ቀጣሪዎች የሚያቀርቡት የምግብና መጠጥ ወጪ ተቀናሽ የሚደረገው በአንድ ወር የወጣው ወጪ በወሩ ለተቀጣሪዎቹ ከወጣው አጠቃላይ የደመወዝ ወጪ 20 በመቶ ባልበለጠ መጠን ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡  

የምግብ አገልግሎት የሚያቀርቡት በራሳቸው አዘጋጅተው ከሆነ ከምግብ ዝግጅት ጋር በተያያዘ የተደረጉት የግብዓት ወጪዎች በወጪ ተቀባይነት አግኝተው ግብር ከሚከፍልበት ገቢ ላይ ተቀናሽ ሊደረግ የሚችለው ከድርጅቱ በሚቀርብ ሕጋዊ ደረሰኝ/የግዥ ማስረጃ መሠረት እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች