Wednesday, February 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኤሌክትሪክ የሚሠራ ባለሦስት እግር መኪና በኢትዮጵያ ሊገጣጠም ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ትራንስፖርት ሚኒስትሯ የመሬት መንሸራተትን ለመከላከል የጃፓንን ድጋፍ ጠየቁ

ሚትሱይና ኩባንያው የተሰኘው የጃፓን ድርጅት በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ የመክፈት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

ኩባንያው በኤሌክትሪክ የሚሠራ በተለምዶ ባጃጅ እየተባሉ የሚጠሩትን (በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ “ቱክ-ቱክ” ይሏቸዋል) ተሽከርካሪ ለመገጣጠም እንዳቀደ ይፋ ያደረገው፣ በዕለተ ስቅለት ሚያዝያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ግቢ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ነበር።

የሚትሱይና ኩባንያው የንግድ ልማትና የመኪና መለዋወጫ ንግድ እንዲሁም የብረታ ብረት ንግድ ዘርፍ ኃላፊ ሚስተር ሐጂሚ ሚያኪ በኢትዮጵያ ሊገጣጠም የታሰበውን ዓይነት ሥሪተ መኪና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ለሆኑት ዳዮሱኪ ማትሱናጋ እንዲሁም ለትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጻ አቅርበዋል። በገለጻው ወቅትም ሚኒስትሯ በርካታ ጥያቄዎችን በማቅረብ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ሊገጣጠም መታቀዱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ የባለሦስት እግሩ መኪና ለኢትዮጵያ አየር ጠባይ ስላለው ተስማሚነት፣ በገጠሪቱ ክፍል በተለይም የጥርጊያ መንገዶች በብዛት ባሉባቸው ገጠራማ አካባቢዎች መኪናው አገልግሎት ይሰጥ እንደሆነ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

አሽከርካሪውን ጨምሮ ስድስት ተሳፋሪዎችን ማጓጓዝ እንደሚችል የተነገረለትና “ኢ-ትራይክ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ባለሦስት እግር የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌት መሰል ተሽከርካሪ፣ ለየትኛውም የአየር ጠባይ ሁኔታ እንዲስማማ ተድርጎ መፈብረኩን ሚስተር ሚያኪ አብራርተዋል። በከተማም ሆነ በገጠር መንገዶች ላይ ያለ ችግር መጓዝ እንደሚችል፣ ለዚህም በሦስቱም እግሮቹ ሥር የተገጠሙለት ስፕሪንጎች በእነዚህ መንገዶች ላይ ያለ ችግር እንዲጓዝ እንደሚያስችሉት ለሚኒስትር ዳግማዊት ተገልጾላቸዋል።

እስከ ሰባት ሰዓት በሚደርስ ጊዜ በመደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ቻርጅ ተደርጎ 80 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል የተባለው ይህ ተሽከርካሪ፣ አምስት ቻርጅ የሚደረጉ ባትሪዎችም ተገጥመውለታል። የኤሌክትሪክ ፍጆታውን በተመለከተ ሚያኪ እንዳሉት 7.3 ኪሎዋት አወር ሊደርስ ይችላል።

ስለመኪናው ተስማሚነት አምባሳደር ማትሱናጋ ሲያስረዱ፣ ድምፅ አልባ መሆኑና ነዳጅ የማይጠቀም መሆኑ ለአካባቢ ብክለት ብሎም ለውጭ ምንዛሪ ወጪ መቀነስ አስተዋጽኦው እንደሚጎላ አክለውበታል። ምናልባትም በአምባሳደሩ ግምት እስከ 30 በመቶ የነዳጅ ፍጆታን ሊቀንስ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ይጠበቃል።

ምንም እንኳ የአንዱ መኪና ዋጋ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ወደፊት የሚታወቅ ነው ቢባልም፣ በአሁኑ ወቅት ባጃጅ ከሚሸጥበት ዋጋ ባነሰ ሒሳብ እንደሚቀርብ ተጠቅሷል።

ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር በሚጠይቅ ካፒታል መገጣጠሚያ ፋብሪካው እንደሚቋቋም ሲገለጽ፣ የመኪናውን አንዳንድ ክፍሎችም ከአገር ውስጥ ምንጮች የመጠቅም ሐሳብ መኖሩ ታውቋል።

ይህም ይባል እንጂ መኪናውን በመገጣጠሙ ጉዳይ ላይ ከወዲሁ ሁለት ሥጋቶች ተደቅነዋል። አንደኛው ለመኪናው ተስማሚና በቀላሉ ቻርጅ ሊደረጉ የሚችሉ ባትሪዎችን እንደ ልብ የማግኘቱ ጉዳይ ነው። ሁለተኛው ለገቢ ሸቀጦች በተለይም መኪና ነክ ለሆኑ ዕቃዎች የሚጠየቀው ቀረጥ ነው። በመሆኑም ኃይል ቆጣቢና ለአካባቢ ተስማሚ ለሆኑ ምርቶች በሚሰጠው የቀረጥና ታክስ ድጋፍ በመጠቀም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ባትሪዎችን የማስመጣት አማራጭ እንደሚኖርም ተገልጿል።

የመኪናው ቀለም ለሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ከተለመደው ይልቅ ቀይና ብርማ ሲሆን፣ ይህ ቀለሙ ተቀባይነት አግኝቶ በኢትዮጵያ መሥራት ቢችል ምኞታቸው እንደሆነ አምባሳደር ማትሱናጋ ሳይገልጹ አላለፉም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጃፓን ካላት የቴክኖሎጂ ብቃትና አቅም አኳያ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን ለመከላከል ጃፓን ድጋፍ እንድትሰጥ ወ/ሮ ዳግማዊት ለጃፓኑ አምባሳደር ጥያቄ አቅርበዋል።

በመንገድ ሥራዎች ሒደት የመሬት መንሸራተት ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች መሠረት ያደረገ ግንባታ ለማካሄድ ኢትዮጵያ በዚህ መስክ ዕውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎች ዕጥረት እንዳለባት በመጥቀስ ጃፓን ድጋፋን እንድትሰጥ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ማትሱናጋ በበኩላቸው አገራቸው ያላት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከ70 በመቶው በላይ ተራራማ በመሆኑ ለመሬት መንሸራተትና ናዳ ተጋላጭ ያደርጋታል። በመሆኑም እንዲህ ያለውን ፈታኝ የተፈጥሮ አቀማመጥ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተቋቋመችው እንደምትገኝ አብራርተው፣ ለኢትዮጵያም ልምዷንና ቴክኖሎጂዎቿን እንደምታካፍል፣ ኢትዮጵያውያንም በመስኩ እንዲሰለጥኑ በማገዝ እንደምትረዳ ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ፈታኝና ተደጋጋሚ መንሸራተት ከሚያጋጥማቸው አካባቢዎሽ መካከል የዓባይ ሸለቆ ይጠቀሳል። ከሰሜን መዘጋጃ እስከ ደብረ ማርቆስ የሚዘረጋውን መንገድ የጃፓን መንግሥት በዕርዳታ እንደገነባው ይታወቃል። የህዳሴው ድልድል ተብሎ የተሰየመውን ዘመናዊ ድልድይ በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ነባሩ ድልድይ ከጫና እንዲያርፍ ቢደረግም፣ በተደጋጋሚ በአቅራቢያው በሚከሰተው የመሬት መንሸራተት ሳቢያ ሥጋት ማሳደሩ አልቀረም። ከድልድዩ ያልቅ በተደጋጋሚ የመሰንጠቅ አደጋ እያጋጠመው የሚገኘው የዓባይ በረሃ መንገድ ግን የጃፓንን ዕውቅ ባለሙያዎች ጭምር ፈተና ላይ የጣለ ሆኗል። በተደጋጋሚ ቢታደስና በጃፓን ምሁራንም ጥናት ቢደረግበትም፣ የዓባይ በረሃ መንገድ ግን ከመሰንጠቅ የሚገታው አልተገኘም።

በሌላ ዜና የጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ በመጪው ሳምንት ኢትዮጵያን እንደሚጎኙ ታውቋል። ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ስለሚጠበቁት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጉብኝት የጃፓን ኤምባሲ ቢያስታውቅም፣ ስለጉብኝታቸው ጉዳይ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች