Thursday, February 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥትን ትኩረት የሚሹ ዘይቶችና የታሸጉ ምግቦች

በተስፋ ሚካኤል አወቀ

የሰው ልጅ ለምግብነት ከሚጠቀማቸው ዓይነቶች ዘይት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ የሚዘጋጅ፣ ደሃውም ሆነ ሀብታሙ ለምግብነት የሚጠቀመውም ነው፡፡ ከምግብነት ባለፈም በኢንዱስትሪዎች፣ ለመዋቢያ ቅባቶች፣ ለመድኃኒት ለቀለሞችና ለሌሎችም የኢንዱስትሪ ምርቶች በግብአትነት ይውላል፡፡ ይህ በስፋት በሰው ልጆች የለት ተዕለት ምግብ ውስጥም ጥቅም ላይ የሚውለው ዘይት፣ እንደየአገሮች የዕድገት ደረጃና የጤና ፖሊሲ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው፡፡

የሚፈቀድ የአመራረት፣ የጥራትና በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች መጠን ምን መሆን እንዳለበት መስፈርት የሚቀመጥለትም ነው፡፡ ከዚህ መስፈርት አፈትልኮ የወጣ ዘይት አመራረቱ እንዲስተካከል፣ ካልሆነ እንዲወድ ብሎም የጥራት ደረጃውን ጠብቆ የማያመርት ኩባንያን እስከማሸግ የሚደረስበት ጊዜ አለ፡፡ የሕዝቡን ጤና የሚጎዳ ምግብም ሆነ የምግብ ግብአት ለሸማቹ ቀርቦ አይደለም ሳይቀርብ እንኳን የጥራት ችግር እንዳለበት መረጃ አፈትልኮ ቢወጣ የመንግሥት ፖሊሲ አስፈጻሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የሸማቾች ማኅበራት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሆ ብለው በመውጣት ኩባንያዎችን ፍርድ ቤት ከመገተር እስከ ማዘጋት ይደርሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለማንኛውም አገር መሠረታዊና የሕዝቡን ጤና መጠበቂየ ቁልፍ ነው፡፡  

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በአገር ውስጥ የሚመረቱትን ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ ዘይቶችና የታሸጉ ምግቦች ላይ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ የምግብነቱን ይዘትና የመጠቀሚያ ጊዜ ከማሳወቅ አንጻር ችግር እንዳለ ቢነገርም፣ በየገበያው የይዘታቸው ምንነት በግልጽ ያልተቀመጠና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምግቦችን ማየቱ የተለመደ ነው፡፡

የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣንም ደረጃዎች ኤጀንሲ ባስቀመጠለት መስፈርት መሠረት ችግር ያለባቸው ምርቶች አንዳንዴ ሲያጋጥሙት ከገበያው እንዲወገዱ ማድረጉን ሲነግርና ሕዝቡም ባለሥልጣኑ ስም ጠቅሶ የሚያስቀምጣቸውን ምግቦች እንዳይጠቀም ሲወተውት ቢሰማም፣ ችግሮችን ግን መቅረፍ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ዘይትንም ሆነ ሌሎች ለተላላፊ በሽታዎች ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችን ከገበያው ማውጣት አልተቻለም፡፡

አቅራቢውም ከሥነ ምግባር ጉድለትም ይሁን ከዕውቀት ማነስ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርበው ምግብ ላይ የሚያደርገው ጥንቃቄ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን በተለያዩ መድረኮች ሲነገር ከርሟል፡፡ ሆኖም ባለሥልጣናት ጭምር እጃቸውን ያስገቡበታል በሚባለው ንግድ ውስጥ ችግር አለ ብሎ መናገርን ከመፍራት ይሁን ከማን አለብኝነት ማናቸውም አካል በቂ እና የማያዳግም ዕርምጃ ሲወስዱ አይስተዋልም፡፡

በተለይ መንግሥት የሚደጉመውና ከኢትዮጵያውያን የአኗኗር ዘይቤ አንጻር ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እንደ አንድ ምክንያት የሚነሳው የሚረጋው የፓልም ዘይት ከዓመታት በፊት ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች የጤና እክል ያስከትላል ቢሉም የሚሰማቸው አልነበረም፡፡

ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት የፓልም ዘይትና በአገር ውስጥ የሚመረቱት ላይ የተደረገ ጥናት ከጥራትም ከጤናም አንጻር ችግር እንደሚያስከትል ቢያሳይም፣ ጤና ሚኒስቴር ከውጭ የሚገባው የፓልም ዘይት የጤና ችግር ስለሚያስከትል በሌላ ፈሳሽ ዘይት እንዲተካ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የጠየቀው ዘንድሮ መጀመርያ ነው፡፡ ይህም እስካሁን ተፈጻሚ ስላለመሆኑ በየሸማቾች መደብር ቢጫውን ጀሪካን ማየቱ በቂ ነው፡፡    

እንደ አጠቃላይ ሲታይ የምግብን ጥራት መጠበቅ ወሳኝ ቢሆንም በዘይት ላይ አተኩሬ ከጥናት ያገኘኋቸውን በማጣቀስ እንደሚቀጥለው ላቀርብ እወዳለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት አቶ ክፍሌ ሀብቴ እ.ኤ.አ. በ2016 በነበረ የሥነ ምግብ ጥናቶች ኮንፈረንስ በዘይቶች ላይ የተደረገ ጥናትን አቅርበው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የሚመረቱ ሰባት የዘይት ዓይነቶችን ጨምሮ በ16 የዘይት ምርቶች ላይ የተደረገው ጥናት ያሳየው ሁሉም ዘይቶች ተገቢው የምርት ዓይነትና ይዘት መግለጫ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡

ከውጭ ከሚገቡት ዘጠኝ ዓይነት ዘይቶች አምስቱ የምርት መግለጫ (labeling) ሲያሟሉ አራቱ የማያሟሉ ነበሩ፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙ የዘይት ዓይነቶች አምስቱ በቅጡ ያልተጣሩ በመሆናቸው ቀለማቸው ጥቁር ቢጫ፣ ቢጫማ ቡናማ ወይም ደማቅ ቢጫ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሦስት የዘይት ዓይነቶች ደግሞ ዝቃጭ ያለባቸው ነበሩ፡፡

በ2013 የተሠራው የኢትዮጵያ ናሽናል ፉድ ኮንሰምሽን ዳሰሳም፣ በአዲስ አበባ የምግብ ዘይት አጠቃቀም 27.8 ግራም በቀን እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በመንግሥት ድጎማ በመላ አሪቱ የሚሠራጨው የሚረጋ የፓልም ዘይት ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀመው ሲሆን ሽፋኑም ከ90 በመቶ እስከ 95 በመቶ ነው፡፡

ይህ ዘይት በተለያዩ ጊዜያት ለጤና ጠንቅ፣ በተለይም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አንድ መንስኤ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢነገርም መንግሥት ደሃው እንዲጠቀም በሚል ሰበብ ከገበያው ሊያስወጣው አልቻለም፡፡

በ100 ግራም ውስጥ ከአራት ግራም የበለጠ ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድና ትራንስ ፋት አሲድ አንድ ላይ ሲወሰዱ ለጤና ጎጂ ናቸው፡፡ በቀን ሊወሰድ የሚገባው ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ ደግሞ አጠቃላይ ከሚወሰደው 2000 የካሎሪ መጠን 2.8 ግራም (ሰባት በመቶ) ብቻ መሆን አለበት፡፡

ሆኖም ጠጣር ወይም ሃይድሮጅኔትድ የፓልም ዘይት ላይ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት በ100 ግራም ፓልም ዘይት ውስጥ 47.2 ግራም ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ መኖሩን ነው፡፡

ይህም በቀን 13.12 ግራም ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ እንደሚወሰድ ማለትም የአሜሪካ የልብ ማኅበር ካስቀመጠው የሚመከር የሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ መጠን በ4.7 እጥፍ የበለጠ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረቱት ዘይቶች ዝቅተኛ ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድና ትራንስ ፋቲ አሲድ ያላቸው ቢሆንም፣ በፋብሪካ ውስጥ የማጣራት ሒደት ይቀራቸዋል፡፡ ለሆድ ሕመምና ለቃር ወይም (የሆድ ማቃጠል) ምክንያት የሆነው አሲድ ይዘታቸው ከፍተኛ ስለሆነም ይህንን ማጥራት ተገቢ ነው፡፡

ማጣራትና ጎጂ ቅንጣቶችን ማስወገድ አገር ውስጥ ከሚጨመቁ ዘይቶች የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሁሉም በሚባል ሁኔታ የማያሟሉትን ሌብሊንግ (የይዘት መግለጫ) ማሟላትም ተገቢ ነው፡፡

ከፈሳሽ ዘይቶች ጋር ሲነጻጸር በአገሪቱ አብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀመው ፓልም ዘይት ለጤና ጎጂ የሆኑትን ትራንስ፣ ሳቹሬትድና ሞኖ አንሳቹሬትድ እንዲሁም ኦሜጋ 9 ፋቲ አሲድ በከፍተኛ መጠን አለው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ተፈላጊ የሆነው የኦሜጋ 3፣ የኦሜጋ 6 እና የሲስ ፋቲ አሲድ ይዘታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

በመሆኑም የሚረጋውን የፓልም ዘይት በፈሳሽ ዘይቶች መቀየር ለጤና ተመራጭ ነው፡፡  መንግስት ከውጭ የሚገባውን ከሚደጉምም  በገሪቱ የሚገኙትን ዘይት አምራቾች ምርታቸው ጥራቱን ጠብቆ እንዲዘጋጅ ማገዝና ተገቢውን መስፈርት አስቀምጦ በዚህ እንዲያልፉ ማድረግ ይገባዋል፡፡

የፓልም ዘይት ጉዳት አሳሳቢነት ተገልጾ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መሠረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለንግድ ሚኒስቴር ገበያውን አጣርቶና በፈሳሽ የሚተካበትን መንገድ አጥንቶ እንዲያቀርብ ከወራት በፊት መመርያ ቢሰጥም እስካሁን መፍትሄ አልተሰጠም፡፡ እዚህ ላይ ጤና ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ መግፋት እንዳለበትም ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

በሌላ በኩል ታሽገው የሚቀርቡ ምግቦች ከውጭ የሚመጡትም ሆነ አገር ውስጥ የሚመረቱት ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በሠለጠነው ዓለም ለጤና ጎጂ ናቸው፣ ለካንሰር፣ ለልብ፣ ለደምና ደምስር በሽታዎች፣ ለስትሮክና ለሌሎችም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚባሉ ምግቦች በኢትዮጵያ የገበያ ሥፍራዎች ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ከልክ ላለፈ ውፍረትና ከዚሁ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ በሽታዎች ምክንያት የሚሆኑ ምግቦችን ያለምንም ግንዛቤ መፍጠር ገበያው ላይ እንዲገቡ ማድረግም ሌላው ችግር ነው፡፡ ሥራ አጦችን ሥራ ለማስያዝ የሚፈጠረው ሥራ በተለይ ከምግብ ጋር የተያያዘ ከሆነ ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግበት፣ የሥነ ምግባርና የጥራት ደረጃ ሊቀመጥበት ይገባል፡፡

ለካርዲዮቫስኩላር (ለደምስር ሕመሞች) ምክንያት የሚሆኑ ማርጋሬን፣ ቺዝ፣ የረጉ ዘይቶች፣ ስብና ሌሎችንም በተመለከተ በአመጋገብ ሥርዓት ላይ ግንዛቤ መፍጠር ግድ ይላል፡፡ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከሚከሰት ሞት 50 በመቶ ያህሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጫናም ተላላፊ ከሆኑት እየተገዳደረ ነው፡፡ ሆኖም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ በቂ መሰረተ ልማቶች የሉም፡፡ የመድኃኒት አቅርቦትም ቢሆን ሲያሻው የሚገኝ ሲያሻው የሚጠፋ ነው፡፡ የአኗኗር ዘይቤን ስለማዘመን ሆነ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሕመሞችን ቀድሞ ግንዛቤ መፍጠሩም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በመሆኑም ለአንድ አገር ዕድገት ቀዳሚ የሆነውን የሰው ልጅ ጤና ለመጠበቅ መንግሥት፣ በዘርፉ የተሰማሩና ዕውቀቱ ያላቸው እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles