Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየወመዘክር የአልማዝ ኢዮቤልዩ

የወመዘክር የአልማዝ ኢዮቤልዩ

ቀን:

በአንድ ወቅት በዚህ ታላቅ ቤተ መጻሕፍት ቀኑን ሙሉ ሲያነብ ውሎ 12 ሰዓት ላይ የቤተ መጻሕፍቱን መዘጋት የሚነግረው ደውል ይደወላል፡፡ ሌሎች አንባቢዎች እንደ ቤተ መጻሕፍት የንባብ ሥርዓት ወደ የቤታቸው ሲሄዱ፣ አንድ ንባብን እጅግ የሚወድ ሰው ግን ይኼንን ጥሪ መቀበል አዳጋች ይሆንበታል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎቹን ያናግራል፡፡ ‹‹ቤተ መጻሕፍቱ ጧት 2 ሰዓት ላይ ይከፈታል?›› በማለት ጠየቀ፡፡ ባለሙያዎቹ አዎንታቸውን ገለጹለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔን እዚሁ ዘግታችሁብኝ ሂዱ፣ ጧት ስትመጡ ታገኙኛላችሁ አለ፡፡››

የዚህ ታሪክ ባለቤት የሆነው ታዋቂው ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ይመኘው የነበረው ነገር ዕውን ሆኖ ዛሬ ቤተ መጻሕፍቱ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት በቅቷል፡፡ በቤተ መዛግብቱና ቤተ መጻሕፍቱ ታዋቂውና በጥበብ ሥራዎቻቸው ዓለምን ያስደመሙት የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በዚህ ቤተ መጻሕፍት ላይ ቢሮ እንደነበራቸው፣ ሥራዎቻቸው ተፀንሰው የተወለዱት እዚህ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚህም ባለፈ በቤተ መዛግብቱና ቤተ መጻሕፍት ታሪካዊና ታላላቅ ጸሐፍያን የጻፏቸው ይገኙበታል፡፡

 ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ መስፈርትን አሟልተው በሒደት ላይ የሚገኙ አራት ድርሳናት አሉት፡፡ እነሱም ክታብ አልፍራይድ፣ ክታብ አልሙሳጠል፣ መጽሐፈ ድጓ፣ ባሕረ ሐሳብ ናቸው፡፡

‹‹ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር›› በሚል መጠሪያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት የተመሠረተው ሚያዝያ 27 ቀን 1936 ዓ.ም. ነው፡፡ የወመዘክር 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን ‹‹ቃል ያዛልቃል›› በሚል መሪ ቃል ከሚያዝያ 23 እስከ ሚያዝያ 27 በተለያዩ ፕሮግራሞች ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ  ክርስቲያናዊና እስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከብራና መጻሕፍት አዘገጃጀት ጋር የተጎበኙበት ዐውደ ርዕይ፣ ያሬዳዊ ዜማና መንዙማም የተሰሙበት መድረክታላላቅ ኢትዮጵያውያንን  ስላፈራው ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ታሪክም የቀረበበት ሰገነት፣ ደራስያንና ተርጓሚያን ስለ ሥራዎቻቸው ያወጉበት፣ ከዚህ ባለፈምለሕፃናት መጻሕፍትና ልዩ ልዩ የንባብ ፕሮግራሞች ቀርበውበታል፡፡

ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ላይ ድል የተቀዳጀችበት የሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ድል ተንተርሶም ‹‹አርበኝነትና ኢትዮጵያዊነት ከትናንት እስከ ዛሬ›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን፣ ባከባበሩም ላይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላትም ተገኝተዋል፡፡

በቅጥር ግቢው በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹የቤተ መጻሕፍት ታሪክ የደግነት ታሪክ ነው፡፡ ደጋግ ጸሐፍት በብዙ ትጋት ለአንክሮ፣ ለተዘክሮና ለአስተምህሮ የከተቡትን ክርታስ ሌሎች ደጋጎች በበኩላቸው ቤት ሠርተው፣ መንበር አበጅተው፣ ማቶት አብርተው ትውልዱ እንዲታደምላቸው ‹እንካችሁ ይኽችን መጽሐፍ ብሉ› ማለታቸው የኅብረተሰብ መሠረቱ ደግነት መኾኑን ያበስረናል፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ ‹‹የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን 75ኛ ዓመት ስንዘክር ከዚያ በፊት ለበርካታ ዘመናት ብራና ፍቀው፣ ቀለም ጨምቀው፣ ጽፈው፣ ተርጉመው፣ ኢትዮጵያን ‹ሃገረ መጻሕፍት› ያሰኟትን ጠቢባንና ሊቃውንት ውለታ፤ እሳት ስንወራወር መጻሕፍቱ እንዳይቃጠሉ በቃል አጥንተው፣ ዋሻ ተከተው ትውፊታችንን ያቆዩልንን ዐቃቢያነ ታሪክ ወሮታ አብረን መዘከራችን እንዳይዘነጋ አደራ፤›› በማለት ያስተጋቡት ምስጋናና አክብሮትን በማከል ነው፡፡

‹‹ከጥንት ለመጡት ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ለሚመጡት መጻሕፍትን መኖሪያና መነበቢያ ያበጁትን ታላቅ መሪ የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አባታዊ ስጦታ ከምስጋና ጋር እናስባለን፡፡ በመጻሕፍት ብርሃን እንድናይ ለሚተጉ ኹሉ የዛሬው ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ የአክብሮት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡››

የቤተ መጻሕፍት/ ቤተ መዛግብት አጀማመር

ወመዘክር የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ ባዘጋጀው መጽሔቱ፣ የቤተ መጻሕፍት አጀማመር እንዴት እንደሆነ ሳይገልጽ አላለፈም እንዲህም አለ፡፡ ‹‹ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ መጻሕፍትን በአንድ ቦታ ለማሰባሰብ የተለያዩ ጥረቶች ተጀምረው ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥንታዊ ጽሑፎችን በነገሥታት ቁጥጥር ሥር በአንድ ቦታ አሰባስቦና አደራጅቶ ለአገልግሎት ያቀረበው አፄ ገላውዴዎስ (1540-1555 ዓ.ም.) ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጻድቁ ዮሐንስ (1664-1675) እንደዚሁ በጎንደር ቤተ መንግሥታቸው የብራና መጻሕፍትን በማሰባሰብ በአንድ ከፍል ያከማቹ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒልክም የብራና መጻሕፍትን በቤት መንግሥታቸው በማሰባሰብ ያስጠኑ እንደነበር በጽሑፍ ከሚገኙ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡

በ20ኛው ምዕት ዓመት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ የመጀመሪያው ሦስት አሠርት ውስጥ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡-

‹‹…ይህ ቤት ጥንታዊ ታሪካችንን ለመጠበቅ ባላደራ ከመሆኑ በቀር ለመጪው ታሪካችን ሁሉ በቀጥታ ረዳታችን መሆን አለበት፡፡ አንድ የመጻሕፍት ቤት የሚፈለግበትን ሁሉ ፈጻሚ ለመሆን የዓለም ዕውቀት ለሁሉ የሚገኝበትና የሚታደልበት አማካይ መሣሪያ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም ከሕዝባችን ውስጥ እጅግ የተማሩ ሰዎች ተሰብስበውበት በትምህርት ለንጉሠ ነገሥት ግዛታችን የበለጠ የዕውቀት ብልጽግና  የሚያስገኙበት ቦታ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ያንድ መጻሕፍት ቤት ጠቃሚነት የሚገመተው በሚሠሩበት ሰዎች ቅንነትና ዋጋ ባለው አሳብ ነው እንጂ፤…

‹‹…ማንበብ ወይም ምልክት ማድረግ ብቻ የበቃ አይደለም፣ የቅን ትምህርት ዋናው ምልክቱ የተነበበውን ከአዕምሮ ጋር ማዋሃድ ነው፡፡ ላይ ላዩን ከማንበብ የሚገኝ ዕውቀትና ከአንድ መጽሐፍ ውስጥ አንዳንድ ገጽ በመመልከት ብቻ ተገኝቶ የሚጠቀስ ቃል ሁሉ ለእውነተኛ የዕውቀት መሻሻል እጅግ የሚያሰጋና መሰናክል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ መጻሕፍት ቤት ከሚገኘው የዕውቀት ምንጭ ለመቅዳት የሚመጡት ሁሉ መሠረት ከሌላው አፍአዊ ዕውቀት እንዲርቁ በጥብቅ እናስጠነቅቃችኋለን፡፡ …የምናስበው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻችንም ይሁን፡፡››

በሔለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...