ከላይ የሚወርደው ሐሩር ራቁቱን ለሚድኸው ሕፃን የተለመደ ይመስላል፡፡ ሕፃኑ ከየስደተኞቹ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾችን ይዞ በሚያልፈውና ከሲሚንቶ በተሠራው ክፍት ትቦ ውስጥ መቀመጫውን ዞር አድርጎ እግሩን በማስቀደም ሲገባ በአካባቢው የነበሩ ጋዜጠኞች የካሜራቸውን ሌንስ ወደ ሕፃኑ አዞሩ፡፡ ሕፃኑ አጠር ካለው ቱቦ ውስጥ ሆኖ ከትከሻው በላይ ቢታይም፣ በራሱ አቅም ከውስጥ መውጣት የሚችል ግን አይመስልም ነበር፡፡ የድረሱልኝ ዓይነት ቢያለቅስም በአካባቢው ፀጉረ ልውጦችን ያዩት የሮሃኒንጋ ስደተኞች ቤቶችን የሚከፍሉትን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ይዘው ችምችም ብለው ከማየት ውጪ የእኔ ልጅ ብሎ ወዲያው ያነሳው አልነበረም፡፡
እንግዳ በመጣ ቁጥር በመሰባሰብ ብሶታቸውን፣ ሥጋታቸውንና ችግራቸውን ለመግለጽ ከየቤታቸው መውጣት ልማዳቸው ከሆኑት ስደተኞች አንዱም እንኳን ለሕፃኑ ትኩረት አልሰጠም፡፡ ሕፃኑ ታትሮ ከትቦው ውስጥ ወጥቶ መዳኹን ቀጠለ፡፡
ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከሚልቀው የአካባቢው ሙቀት ጋር ከየቱቦዎቹም ሆነ ከየነዋሪው የሚወጣው ፍሳሽ የሚጣራበት የመፀዳጃ ገንዳ የሚለቀው ሽታ አካባቢውን ተንፍጎታል፡፡ ‹‹በእንዲህ ዓይነት ሽታ ውስጥ መኖር ይከብደናል፤›› ብሎ መጠየቅ ምናልባት ለስደተኞቹ የቅንጦት ይሆናል፡፡
ከ26 ስኴዌር ኪሎ ሜትር በሚልቅ ሥፍራ ላይ ከቀርከሃና ከፕላስቲክ ረድፋቸውን ጠብቀው በብሎክ በብሎክ የተሠሩት ካምፖች ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሮሃኒንጋ ስደተኞችን አስጠልለዋል፡፡
ዳገትና ቁልቁለት በሚበዛበት፣ ውስጥ ለውስጥ የሚፈሱ ወንዞች የሚታዩበት የኩቱፖሎንግ ስደተኞች ካምፕ፣ ከዓመታት በፊት ጥቅጥቅ ያለ ደንና የአራዊት መናኸሪያ እንደነበር ይነገራል፡፡ የቱሪስት መስህብ እንደነበር በሚነገርለትና ከዓለም ረዥሙ የባህር ዳርቻ ከሚገኝበት ከቴክናፍ ኮክስ ባዛር ከፍተኛ ቦታዎች ትይዩ በሆነውና በባንግላዴሽና ማይናማር ድንበር በሚገኘው ናፍ ወንዝ አካባቢ ለሠፈሩት የማይናማር ስደተኞች፣ አካባቢው በቀዬአቸው ከተፈጸመባቸው ጭፍጨፋ ሲነፃፀር ሰላም ቢመስልም፣ ኑሮው ግን ፍፁም የተለየ ነው፡፡
ተራራ በሚበዛበትና ለመሬት መንሸራተት በተጋለጠው አካባቢ የተጠለሉት የሮሃኒንጋ ስደተኞች ዛሬ ላይ እንደቀድሞ አርሰው መብላት አይችሉም፡፡ ሠርተው የሚያድሩ እጆች በልመና ተገኝቶ ለሚሰፈር ቀለብ ተዘርግተዋል፡፡ ዙሪያውን ከታጠረውና ከሁለት ሺሕ በሚልቁ ወታደሮች ከሚጠበቀው ካምፕ ደጃፍ ስንዝር እንኳን መውጣት አይችሉም፡፡ ቀን ተቆጥሮ የሚሰፈርላቸውን ሩዝና ምስር ይዘው ወደ ካምፓቸው መመለስ ግዴታቸው ነው፡፡ ለስደኞቹ በዓለም አቀፍ መንግሥታት ትብብር የጤናና የትምህርት አገልግሎት ቢሰጥም፣ ኩፍኝና በባክቴሪያ የሚመጡ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሥፍራው ፈታኝ ችግሮች ናቸው፡፡
ሮሃኒንጋ ከትውልድ ቀዬአቸው ማይናማር እንዴት ተሰደዱ?
ከአምስት ክፍለ አኅጉር የተውጣጡና ከ26 አገሮች የመጡ ከ40 በላይ ጋዜጠኞች በሮሃኒንጋ ስደተኞች ካምፕ መገኘት፣ ጭር ብሎ የነበረውን የስደተኞች መንደር በሕፃናትና በአዋቂ እንዲሞላ ያደረገው ጋዜጠኞቹ ካምፑ ገብተው አፍታም ሳይቆዩ ነበር፡፡ የሚድኹትን ጨምሮ በርካታ ወንድ ሕፃናት መለመላቸውን፣ አዋቂ ወንዶች ሽርጣቸውን ገልደም አድርገውና ከወገብ በላይ ራቁታቸውን ሆነው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ሕፃናቱ፣ ወጣቱና አዛውንቱ ቀስ በቀስ በረድፍ የተሠሩት መጠለያዎችን የሚያካፍሉ የእግረኛ መንገዶችን ሞሏቸው፡፡ ሁሉም በሚባል ሁኔታ የተጎሳቆሉና በሐሩሩ ፊታቸው የወየበ ነው፡፡
ከእነዚህ የ80 ዓመቷ ዲልባ አንዷ ነበሩ፡፡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች አንድ ላይ ግር ብለው የሚሆነውን በርቀት ሲመለከቱ፣ ሚርስ ዲልባ ግን የመኖሪያቸውን ጠርዝ ደገፍ ብለው ብቻቸውን ነበር አሻግረው የሚያዩት፡፡ በአስተርጓሚ በመታገዝ ልናናግራቸው ስንቀርብ በአካባቢው ከሚገኙ ዕፀዋቶች ባህላዊ ነው የተባልነውን አረንጓዴና ቀይ ቅጠል እያኘኩ ነበር፡፡ ሁለት እጃቸውን ሰዎች ፈጣሪያቸውን ሲለማመኑ እንደሚዘረጉት በመዘርጋት በትውልድ ቀዬአቸው ማይናማር የገጠማቸውን ነገሩን፡፡
የአንድ ልጅ እናት እንደሆኑ የገለጹት ዲልባ፣ ከእነ ልጃቸው የማይናማርን ድንበር አቋርጠው ባንግላዴሽ ስደተኞች ካምፕ የተጠለሉ ወደው አልነበረም፡፡ በማይናማር አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የሮሃኒንጋ ሙስሊሞች እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ ጀምሮ በደልና ግድያ ሲፈጸምባቸው ኖሯል፡፡ ጎሳንና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ በየጊዜው እንደሚጨፋጨፉ የሚነገርላቸው ሮሃኒንጋ፣ ስደታቸውን ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያና ፊሊፒንስን ጨምሮ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ካደረጉትም አሠርት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2012 ወዲህ ሮሃኒንጋ በወታደሮች ጭምር መጨፍጨፋቸውና ቤት ንብረታቸው መቃጠሉ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከቀዬአቸው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሕፃናትን ጨምሮ ወንድ፣ ሴት፣ አዛውንት፣ ወጣት፣ ሳይል በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሮሃኒንጋ እዚያው ቆዬአቸው በእሳት ተበልተዋል፣ በጥይት ረግፈዋል፡፡ የማይናማር መንግሥት ከደሙ ንፁህ ነኝ ቢልም፣ በካምፑ ውስጥ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ስደተኞች ግን መለስ ብለው በማስታወስ የሚናገሩት ይህንኑ ሰቆቃ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የነበረው ጭፍጨፋ ደግሞ የዓለም አቀፍ መንግሥታትንም ሆነ የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡
በወቅቱ የ78 ዓመት አዛውንት የነበሩት ሚርስ ዲልባም፣ በዚህ ወቅት ነበር ከአንድ ልጃቸው ጋር የባንግላዲሽን ድንበር አቋርጠው በስደተኞች መጠለያ ካምፕ የገቡት፡፡
አርሶ አደር እንደነበሩ የሚገልጹት ሚርስ ዲልባ፣ ዛሬ ላይ የሚሰፈርላቸውን ተቀባይ ሆነዋል፡፡ የራሴ የሚሉት ቤትም ሆነ መሬት የላቸውም፡፡ እንዲህ ፀጉረ ልውጥ አካባቢውን ሊጎበኝ ሲመጣ ወጣ ብለው ለማየት ካልሆነ፣ ከቀርክሃና ከላስቲክ በተሠራው ቤታቸው ውስጥ ተሰብስቦ መቀመጥ የዕለት ተዕለት ውሏቸው ነው፡፡
ሚርስ ዲልባ በዕድሜያቸውም መግፋት በቤታቸው ይታጠሩ እንጂ ወጣቶች የተጨፈጨፈውን ደን በጥቂቱም ቢሆን መልሶ በማልማት፣ አትክልት በመትከልና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ይተባበራሉ፡፡ ተነፃፃሪ ሰላም ያገኙበት በባንግላዲሽ የሚገኘው ካምፕም በሌሎች አገሮች ከሚገኙ የሮሃኒንጋ ስደተኞች ካምፖች ትልቁና ብዙዎቹም የሚገኙበት ነው፡፡
የሮሃኒንጋ ወደቀዬአቸው መመለስ
ሮሃኒንጋን ወደቀዬአቸው ለመመለስ በማይናማርና በባንግላዴሽ መንግሥታት መካከል ከ2017 ማብቂያ ጀምሮ ጥረት ቢደረግም፣ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ይህም በተለይ የመሬት ስፋቷ ከአማራ ክልል ያነሰ ሆኖ 160 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት ባንግላዲሽ ራስ ምታት ነው፡፡ ሮሃኒንጋ የሠፈሩበት የቀደመ ደን ተራቁቷል፡፡ የቱሪስት መስህብ የነበረው ኮክስ ባዛር እየነጠፈ ነው፡፡ ስደተኞቹ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስደተኞች ኮሚሽንና በዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ትብብር ድጋፍ ቢያገኙም፣ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችና የመሬት መንሸራተት ከፍተኛ ሥጋት ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም ስደኞች ወደ ባንግላዲሽ ሲጎርፉ ነዋሪዎች ያሏቸውን አብልተው፣ መጠለያ አጋርተው የተቀበሏቸው ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ይህንን ማድረግ አይቻልም፡፡ ሆኖም ስደተኞች አሁንም ወደ መጠለያው ይመጣሉ፡፡
ሮሃኒንጋ ወደ መጡበት ማይናማር መመለስ እንደሚፈልጉ የስደተኞች ተወካይ ይናገራሉ፡፡ ሲመለሱ ግን የማይናማር መንግሥት ጥበቃ እንዳያደርግላቸው ዓለም አቀፍ መንግሥታት ጫና እንዲፈጥሩ በመጠየቅ ነው፡፡ ወደ ማይናማር መመለስ ፍላጎታቸው ስለሆነ ቻይናና አሜሪካ ማይናማር ላይ ጫና እንዲፈጥሩ የስደተኞች ተወካይ ይጠይቃሉ፡፡ ተወካዩ ይህን ይበሉ እንጂ ከዚህ ቀደም ሐሳቡ ሲነሳ በካምፑ የሚኖሩ ወጣቶች ለሕይወታቸው ዋስትና ስለሌላቸው ሐሳቡን ተቃውመውት ነበር፡፡ በዳካ የሚገኙ አንዳንድ ዜጎችን ስንጠይቅም፣ ሮሃኒንጋ ከስደተኞች ካምፕ ወጥተው ማይናማር ዳግም ይኖራሉ የሚለው ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ ከአገራቸው ቢወጡላቸውም ይወዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ሮሃኒንጋ አካባቢያቸው እየተቃጠለ፣ ዘመድ ወዳጅ፣ ልጅ፣ አባት፣ ሴት፣ ወንድ፣ አዛውንት፣ ወጣት ሳይለይ የደረሰባቸውን በደል ሸሽተው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከወጡበት ቀዬ ለመመለስ ድፍረት አግኝተው ለመመለስ ያገኛሉ ወይ? የሚለው ለባንግላዲሻውያኑም ጥያቄ ነው፡፡
ሆኖም ሥራ አጥነትና የመሬት ስፋት ችግር በሆነባት ባንግላዲሽ የሮሃኒንጋ ስደተኞች መጉረፍ ሊያበቃ እንዲሚገባ ያክላሉ፡፡
በካምፑ የዕርዳታና ስደተኞችን የመመለስ ኮሚሽነር ሚዛኑር ራህማን (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ ወሳኝ ቢሆንም፣ ከማይናማር ጋር የተደረገው ስምምነት ተስፋው እየጨለመ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም፣ ‹‹የሮሃኒንጋ ስደተኞችን መቀበል አልችልም፣ ከአቅም በላይ ነው፤›› ብላ ባንግላዲሽ ብታሳውቅም፣ ስደተኞች አሁንም ከመምጣት አልተቆጠቡም፡፡
የመጡትን በቀዬአቸው መልሶ ማቋቋሙ ግን የተስፋ ዳቦ ሆኗል፡፡ በሥፍራው በነበረን የሦስት ሰዓታት ያህል ቆይታ አንዳንድ ወጣቶችን ለማነጋገር ሞክረን ነበር፡፡ አንዳንዶቹ እንደነገሩን፣ በቀዬአቸው ሰቆቃን አሳልፈዋል፡፡ ቤቶች ሲቃጠሉ፣ ሰዎች ሲገደሉ ሴቶች ሲደፈሩ ዓይተዋል፡፡ የነበረው ሁኔታ ከአዕምሯቸው ተቀብሮ ሰላም የነሳቸው በስደተኞች ካምፕ ሆነው፣ ለአዕምሮ ሕመም ተዳርገዋል፡፡ በካምፑ ከሚገኙ 158 መሠረታዊ ጤና ጣቢያዎችም የተወሰኑት የአዕምሮ ሕመም ሕክምና መስጠት ጀምረዋል፡፡
የሴቶች መደፈርና ጥቃት ሌላው አሳሳቢ አጀንዳ ነው፡፡ በስደተኛ ካምፑ ከተጠለሉት 67 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ በርካቶቹም ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ናቸው፡፡ እርጉዝና በቅርቡ የወለዱ በርካታ መኖራቸውም ይነገራል፡፡
ከባንግላዴሽ መንግሥት ጎን ቱርክ፣ አሜሪካና ሌሎች አገሮች ተደምረው ለስደተኞቹ የሕክምና፣ የምግብና ሌሎች አቅርቦቶችን ለማሟላት ቢረባረቡም፣ ስደተኞቹን ወደ ማይናማር ለመመለስ የተገቡ ስምምነቶች ተፈጻሚ አለመሆናቸው ባንግላዲሻውያኑን ሐሳብ ውስጥ ከቷል፡፡ በመሆኑም የሮሃኒንጋ ስደተኞች ወደ ማይናማር እንዲመለሱ ዓለም አቀፉ መንግሥታት ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም ማይናማር በሮሃኒንጋ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሳቢያ የመሣሪያና የሌሎች ቁሳቁሶች ዕገዳን እስከ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ማራዘሙን በተያዘው ሳምንት አሳውቋል፡፡
በምሕረት ሞገስ፡ ኮክስ ባዛር፣ ባንግላዴሽ