ዘመን ባንክ በቅርቡ ከኃላፊነታቸው በለቀቁት ምክትል ፕሬዚዳንት ምትክ ተጠባባቂ መሰየሙን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከኃላፊነታቸው በለቀቁ አራት ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላትን በአዲስ ለመተካት እየተዘጋጀ መሆኑ ታወቀ፡፡
ምንጮች እንደሚገልጹት አዳዲስ የቦርድ አባላት ከተመረጡ ወዲህ፣ በባንኩ ውስጥ እየተደረገ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ አምስት ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ሥራቸውን ለቀዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ የባንኩ የኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አንዱ ናቸው፡፡ በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቃቸው በእሳቸው ምትክ የኮርፖሬት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ካሳሁን አያሌው፣ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መሰየማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ በወራት ልዩነት ከባንኩ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባልነታቸው የለቀቁት የፋይናንስ፣ የሕግ፣ የፐርሶኔል፣ የቢዝነስ ባንኪንግና የፕሮሞሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሮች ናቸው፡፡
የማኔጅመንት አባላቱ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በባንኩ ቦርድ ተፅዕኖ ነው የሚል አስተያየት የሚሰነዘር ቢሆንም፣ ከባንኩ አካባቢ የተገኘው መረጃ ግን የባንኩን አሠራር ከመለወጥና አዲስ አሠራር ለመዘርጋት እየተከናወነ ካለው ሥራ ጋር በተያያዘ ነው እንጂ በተፅዕኖ አለመሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡
እንዲያውም አዲሱ ማኔጅመንትና የቦርድ አባላት ባደረጉት ለውጥ ባንኩ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት፣ ከ70 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በለቀቁት ኃላፊነት ምትክ አዳዲስ ምደባዎች እየተደረጉ መሆኑን ምደባ ባልተደረገባቸው ደግሞ በቅርቡ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡