በተያዘው ወር የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ከተመዘገበው ግሽበት ጋር ሲነፃፀር በ12.9 ከመቶ ከፍ ማለቱን፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አደረገ፡፡ ካለፈው ወር አኳም በሚያዝያ ወር የ1.8 በመቶ ጭማሪ ተመዝግቧል፡፡
በኤጀንሲው የሚያዝያ ወር የዋጋ ግሽበት ሪፖርት መሠረት ከተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ውስጥ፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አኳያ በ14.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በሚያዝያ ወር በሁሉም የእህል ዓይነቶች (በተለይም ጤፍ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና በቆሎ)፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ፣ ለምግብ ዋጋ ግሽበት መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል ያለው ሪፖርቱ፣ በተጨማሪም ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የሥጋ፣ የቅቤ፣ የወተት፣ የአይብና የእንቁላል ዋጋ ላይም ጭማሪ መታየቱን አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ከዋጋ ግሽበት ጠቋሚ መመዘኛ ክፍሎች ውስጥ የምግብ መመዘኛ ወይም ኢንዴክስ በሚያዝያ ወር ፈጣን ዕድገት በማሳየቱ፣ ለአጠቃላዩ ዋጋ ግሽበት መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀርም የ11 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ያመላክታሉ፡፡
ምግብ ነክ ካልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ ናርኮቲክስና አነቃቂዎች (በተለይ ጫት)፣ ልብስና መጫሚያ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ሕክምናና ትራንስፖርት (በተለይ የቤት መኪና) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡
በሌላ በኩል በሚያዝያ ወር የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ12.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የሚያዝያ ወር የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የምግብ የዋጋ ግሽበትም በ11.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበትም በ13.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበት ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን የሚያሳይ መመዘኛ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የ2011 ዓ.ም. የሚያዝያ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በ1.8 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ወርኃዊ የዋጋ ግሽበት ምጣኔው በመጨረሻዎቹ ሁለት ተከታታይ ወራት መካከል ያለውን የዋጋ ለውጥ ለመለካት ያገለግላል፡፡