Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክለው ሕግ ተሻሽሎ ፓርላማ እንዲያፀድቀው ተላከ 

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትውልደ ኢትጵያውያንን አግልሎ የቆየውን የአገሪቱን ሕግ በይፋ ይቀይራል የተባለው ረቂቅ የባንክ አሠራር አዋጅ ማሻሻያ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ ወደ ፓርላማ ተላከ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን በማስመልከት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ የአገሪቱን የባንክ ሥራ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ ዋነኛ ዓላማ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የውጭ ዜጎች በባንክ ዘርፍ መሳተፍ እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡

ማሻሻያው በተጨማሪ ባንኮች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እንዲውል በማድረግ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚያስችሉ አንቀጾች እንዳሉት ተጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተወያየና ማስተካከያ ካደረገ በኋላ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚጠቁሙት፣ ረቂቁ የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

የባንክ መቋቋሚያ አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ እንዳይገቡ መከልከለ አግባብ አይደለም ተብሎ ክርክር ሲቀርብት የቆየው በሥራ ላይ ያለው አዋጅ እንዲሻሻል መደረጉ፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን አቅም በመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ የሚሳተፉበት ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል፡፡ የረቂቅ አዋጁ ዝርዝር  ባይገለጽም ውሳኔው በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያጡትን ዕድል እንዲያገኙ የሚያደርግ  መሆኑ ታውቋል፡፡ አዋጁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን አሳታፊ ማድረጉ ባንኮች አክሲዮኖቻቸውን በውጭ ምንዛሪ ለመሸጥ የሚስችላቸውን ዕድል ይሰጣቸዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ይህም የባንኮችን አቅም ለማጎልበት ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትም የሚኖው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ፣ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ገልጸዋል፡፡   

ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ እንደተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ ከሆነ፣ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ረቂቁ ትውልደ ኢትጵያውያን ተሳታፊ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች የፋይናንስ ዘርፎች ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሞጋች የነበሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ቀድሞም ቢሆን የፋይናንስ ዘርፉ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን መከልከል አልነበረበትም ይላሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ትውልደ ኢትዮጵያውን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የነበራቸውን የአክሲዮን ድርሻ ተገደው ሸጠው እንዲወጡ መደረጉ አግባብ አልነበረም ይላሉ፡፡ ‹‹ከአሥር ዓመታት በላይ ስሟገትበት የነበረን ጉዳይ ዛሬ ሰሚ ተገኝቶ መፈጸሙ እጅግ ደስ ብሎኛል፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ዕርምጃው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹በእኔ እምነት የባንኮችን አቅም ከማሳደግ ባሻገር የባንክ ኢንዱስትሪ በተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችም እዚህ መጥተው እንዲሠሩ ዕድል የሚሰጥ ነው፤›› ሲሉም የአዋጁ መሻሻል ዘርፈ ብዙ ተቀሜታ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀድም ሲል ባወጣው መመርያ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው የውጭ ዜግነት የነበራቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮናቸውን ሸጠው እንዲወጡ እያደረገ ሲሆን፣ ይህ መመርያ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለሌሎች ባለአክሲዮኖች ተላልፈዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች