Thursday, July 25, 2024

ንፁኃንን መግደል አገርን ከመግደል አይተናነስም!

መንግሥት ከዚህ ቀደምም ሆነ በቅርቡ በሰጣቸው መግለጫዎች፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች በደረሱ ጉዳቶችና አለመረጋጋቶች ዋናው ተጠያቂ ራሱ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የገዛ ራሱን የአፈጻጸም ክፍተቶች በምክንያትነት መደርደርም እንደሚያዋጣ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን አሁንም አሳዛኝና አሰቃቂ የንፁኃን ግድያዎች ቀጥለዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችን የደኅንነት ሥጋት በአጭር ጊዜና በዘላቂነት ለማስተካከል ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ መሆኑን ቢናገርም፣ ከቀናት በፊት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በግለሰቦች መካከል የተቀሰቀሰ ፀብ ተስፋፍቶ፣ ንፁኃን ወገኖች በቀስትና በጦር ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ በርካታ ንፁኃን ተገድለዋል፡፡ የፖለቲካ ቁማርተኞች በተለያዩ ጊዜያት በሚጭሩት እሳት ምክንያት ንፁኃን ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ፣ የአገር ህልውናም ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡ በየትም ሥፍራ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን በተባበረ ድምፅ ማውገዝ አለብን፡፡ በንፁኃን ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች አገርን ከመግደል አይተናነሱምና፡፡

ለዘመናት አብረው ክፉና ደግ እያዩ አብረው የኖሩ ኢትዮጵያውያንን በብሔር በመከፋፈል ለማፋጀት ከመሞከር ባለፈ፣ ግድያዎችን በብሔር እየለዩ ማውገዝም ሆነ ማወደስ የሰብዓዊነት ተፃራሪ የጭካኔ ድርጊት ነው፡፡ በማንም ላይ የተፈጸመ ነውረኛ ድርጊት በአንድነት መወገዝ አለበት፡፡ በንፁኃን ደምና ሕይወት የሚቆምሩ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ደግሞ በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ የንፁኃን ሕይወት በከንቱ እያለፈ ዝም ማለት፣ የአገር ጥፋት መቃረቢያ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ሰብዓዊ ፍጡርን እንደ አውሬ አድኖ ከመግደል ጀምሮ በዘር ለይቶ መጨፍጨፍ ነውረኛ አረመኔያዊ ወንጀል ስለሆነም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን፣ ነፍሰ ጡሮችን፣ እመጫቶችን፣ አቅመ ደካሞችንና ለፍቶ አዳሪዎችን ያለ ጥፋታቸው በጭካኔ ደማቸውን እያፈሰሱ የሚገድሉትን ያለ ምንም ማመንታት ሕግ ፊት መገተር ይገባል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው እንደ ባዕድ እንዲሳደዱ የሚያደርጉም ሆነ፣ ድርጊቱን በዝምታ የሚያዩ ሹማምንትና የሕግ አስከባሪዎች ጭምር በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ የዜጎች ደኅንነት ተናግቶ አገር ሰላም አትሆንም፡፡

መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ካልቻለ አገር የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ትሆናለች፡፡ ንፁኃን እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየወደመ መቀጠል አይቻልም፡፡ መንግሥት ታች ድረስ ያለውን መዋቅሩን ይፈትሽ፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎቹን ሥምሪት ይቆጣጠር፡፡ ውስጡ የመሸጉ የፖለቲካ ቁማርተኞችን ሥርዓት ያስይዝ፡፡ የግጭት ነጋዴዎች የሚደበቁት ኅብረተሰቡ ውስጥ ስለሆነ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ምሁራንን ጭምር በማሳተፍ መፍትሔ ይፈልግ፡፡ ንፁኃን በየዕለቱ በተለያዩ ሥፍራዎች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ምን ያህል ርቀት መጓዝ ይቻላል? የሕግ የበላይነት መኖሩን ማሳየት ካልተቻለ የጥፋት እጆች ሕዝብ ማባላታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ሕግ ማስከበር ማለት፣ ማንኛውም ሰው ከሕግ በላይ እንዳልሆነ ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ሕግ ይከበር ሲባል ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይ አይሁን ማለት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ መንግሥት ከመጠን ያለፈ ኃይል እየተጠቀመ በተለመደው መንገድ አገር ያተራምስ ማለት ሳይሆን፣ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ለማድረግ የሚዳዳቸው ኃይሎች በሕግ አማካይነት ልካቸውን ይወቁ ማለት ነው፡፡ በንፁኃን ሕይወትና በአገር ቀልድ ስለሌለ፡፡

ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ የሚቀንሰው ሕግ ለማስከበር ዳተኛ ሲሆን ነው፡፡ ዳተኝነት የሚታየው ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከግለሰብ መብት ተሟጋቾች ነን ባዮች በሚመጣ ተፅዕኖ እንደሆነ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አገር በሕግ የበላይነት መተዳደር ካልጀመረች የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ነው የምትሆነው፡፡ መንግሥት ከማንም በላይ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ የታጠቀ ሠራዊትም ሆነ ፀጥታ አስከባሪ የሚያሰማራው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንዲሉ፣ ክፍተቶችን እየተጠቀሙ በማንነት ስም ትርምስ መፍጠር እየተለመደ ነው፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ትግል ከማድረግ ውጪ ታጣቂ ማሰማራት እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ስብስብ ታጥቆ መሰማራት አይችልም፡፡ የታጠቁ ሰዎችም ቢሆኑ ሕጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው ይዞታቸውን ከመጠበቅ ባለፈ፣ ራቅ ብለው መንቀሳቀስና ሥምሪት ውስጥ መግባት አይኖርባቸውም፡፡ መንግሥት አላስፈላጊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሹማምንቱንም ሆነ ተከታዮቻቸውን አደብ ማስገዛት አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት ከተቻለ የንፁኃን ሕይወት ከአደጋ ይጠበቃል፡፡ የአገር ህልውናም ሥጋት አይገባውም፡፡

የአንዳንድ ወገኖች ድርጊት በጣም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ለውጡን መሠረት አስይዞ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ  ጎዳና ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ሲገባቸው፣ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላምና ነፃነት አደጋ ውስጥ ለመክተት ይባዝናሉ፡፡ ነፃነትን በኃላፊነት ከማጣጣም ይልቅ፣ በድል አጥቢያ አርበኝነት ስሜት ለአምባገነንነት የሚያመቻች ጎዳና እየቀየሱ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከብሔር፣ ከቋንቋ፣ ከእምነት፣ ከባህልና ከመሳሰሉ ጋር ብቻ እያቆራኙ፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ማየት ተስኗቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው፡፡ ይህንን ማሳካት ከተቻለ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት በጋራ የሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አያዳግትም፡፡ ከዚህ ውጪ ንፁኃንን እየገደሉ፣ እያፈናቀሉና አገርን እያተራመሱ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊነት መናገር አይቻልም፡፡ ‹‹በመጀመርያ የመቀመጫዬን›› እንዳለችው እንስሳ ስለአገር ህልውና በቅጡ ማሰብ ይገባል፡፡ ስህተትን በስህተት እያረሙ ትርምስ ውስጥ መግባት ለፀፀት ይዳርጋል፡፡ ንፁኃንን መግደል ማለት አገርንም መግደል መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...