Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የሠለጠነና የዘመነ ማኅበረሰብ እንዲኖረን የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልገናል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

‹‹የሠለጠነና የዘመነ ማኅበረሰብ እንዲኖረን የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልገናል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሲከበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የመናገር ነፃነት መንግሥት፣ ፓርቲ ወይም አንድ ሌላ አካል ለፈለገው የሚሰጠው ወይም ላልፈለገው የሚነፍገው እርጥባን አይደለም አሉ፡፡ ‹‹ተፈጥሮ ያጎናፀፈችን መተኪያ የሌለው ታላቁ ስጦታችን፣ ሰው በመሆናችን ብቻ የምናገኘው ፀጋ ቢኖር ያሰብነውን በነፃነት መናገር ነው፡፡ ሰው የፈለገውን ሐሳብ በፈለገው መንገድ ለፈለገው ሰው የማቅረብ መብት አለው፤›› በማለት፣ የሠለጠነና የዘመነ ማኅበረሰብ እንዲኖር የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለት ፈርጣማ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች የሚረቱበት እንጂ፣ ፈርጣማ ጡንቻ ስላላቸው ሌላው እንዳይናገር በማፈን ስንኩል ሐሳባቸው እንዲያሸንፍ የሚያደርጉበት ሜዳ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲያብብ ብቻ ሳይሆን አሽቶና ጎምርቶ ፍሬውን እንድንበላ ከተፈለገ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከወረቀት ባለፈ በተጨባጭ መሬት ላይ ሳይሸራረፍ ሲተገበር ማየት አለብን፤›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ መከበሩ ብቻ ሳይሆን በዚህ ወቅት መከበሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹የፕሬስ ነፃነትን አታከብርም ተብላ ስትወቀስ በቆየች አገር ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን እንዲከበር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የተለወጠና የተሻሻለ ነገር መኖሩን ዓለም መረዳት ጀምሯል ማለት ነው፡፡ መንገዳችን ፈታኝ ቢሆም ልንደርስበት ያሰብነውን ግብ ዓለም ተገንዝቦታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ከመላው ዓለም ተሰባስባችሁ በአዲስ አበባ የተገኛችሁትን የፕሬስ ተዋንያን፣ የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኞችና የፕሬስ ነፃነት ተከራካሪዎች ሁሉ በዚህች አገር እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በቅርበት ለመረዳት፣ ተረድታችሁም ለማገዝ እንደ መጣችሁ እናምናለን፡፡ እናንተ እዚህ በተሰባሰባችሁበት ጊዜ ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ ለሰው ልጅ ኑሮ ምቹ አገር እንድትሆን ለማስቻል እየተረባረብን ነው፡፡ ለዚህም መሠረት የሆነውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ቅድሚያ በመስጠት ባለፈው አንድ ዓመት አያሌ የለውጥርምጃዎችን ወስደናል፤›› በማለት ባለፈው አንድ ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አስረድተዋል፡፡

ዕድሜ ልክና ሞት የተፈረደባቸው የመንግሥት ተቃዋሚዎች ከእሥር መፈታታቸውን፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞች አሁን የሚገኙት ከእሥር ቤት ውጭ መሆኑን፣ ተዘግተው የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደገና ወደ ኅትመት ብርሃን መምጣታቸውን፣ ከአገር ውጭ ሆነው የቆዩ ሚዲያዎች በነፃነት ወደ አገር ቤት መግባታቸውን፣ 260 በላይ ተዘግተው የነበሩ ብሎጎችና ድረ ገጾች እንደተከፈቱ በአገር ውስጥነፃነት መታገል ያልቻሉና በመሣሪያ ጭምር ከአገር ውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ከአሥር በላይ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ቤት መግባታቸውን፣ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ፍረጃው ተነስቶላቸው በፖለቲካው ሜዳ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉን፣ የብዙዎችን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብት በመጫን የሚታወቀው የፀረ ሽብር ሕግ እየተሻሻለ መሆኑን፣ የምርጫ ቦርድንና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ለማሻሻልና ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በሚረዳ መንገድ ለማዋቀር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩበትን የሥነ ምግባር ሕግ ማፅደቃቸውን፣ እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የመዋቅርና የሕግ ማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ዘርዝረዋል፡፡

‹‹እናንተ ወደ አዲስ አበባ የመጣችሁበት ወቅት አገራችንን ወደፊት ለማስኬድና ወደኋላ ለማስቅረት ትግል በሚደረግበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ የምትሰሟቸው ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ ውጥረቶችና እንካ ሰላንትያዎች ወደኋላ ለመቅረት ወይም ባሉበት ለመቸከል በሚፈልጉ ሐሳቦችና ኃይሎች የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች የለውጡን ጉዞ ፈታኝ፣ ከባድና መራራ ያደርጉት ይሆናል እንጂ አያስቀሩትም፡፡ ያለፈውን አንድ ዓመት እንደተጓዝን ሁሉ ቀጣዮቹን ሺሕ ዓመታትም እንጓዛለን፡፡ እናንተም የዚህ ታሪክ ምስክሮች ትሆናላችሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የፕሬስ ነፃነት ማለት የጋዜጠኞች ነፃነት ማለት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነፃነት ጭምር ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ፕሬስ የሁላችንም ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ማሳለጫ መንገድ ነው፡፡ ለፕሬስ ነፃነት የምናደርገው ትግል ለጋዜጠኞች መብት ስንል የምናደርገው ሳይሆን፣ ለራሳችን መብት ስንል የምናደርገው ትግል ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነትም የራሳችን ነፃነት ነው፡፡ ባለፉት ወራት በዋጋ ጭማሪ ምክንያት የጋዜጣ ወረቀት ከ70 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ መንግሥት ግን ይኼ ጭማሪ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ እንዲጨመር አልፈቀደም፡፡ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ጭማሪ ራሱ መንግሥት ድጎማ አደርጎ ተሸክሞታል፡፡ ይህንን ያደረግነው የፕሬስ መብት የኛም መብት ስለሆነ ነው፡፡ የሠለጠነና የዘመነ ማኅበረሰብ እንዲኖረን የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ስንልም መብቱን የሚያስከብር፣ ኃላፊነቱንም የሚወጣ ማለታችን ነው፡፡ መብት የሌለው ኃላፊነት ባርነት ነው፣ ኃላፊነት የሌለው መብትም ልቅነት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ባርነትንም ሆነ ልቅነትን አንፈልጋቸውም፤›› ሲል አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የፕሬስ ነፃነት መብት በሚገባ እንዲከበር ብዙ ሥራዎች ቢሠራም ሌሎች ብዙ ሥራዎች ደግሞ ይቀሩታል ካሉ በኃላ የሚዲያዎችን አቅም ለማሳደግ፣ የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ዕድሎችን ለማመቻቸት፣ የተሻለ ሥራ የሚሠሩትን የሚያበረታታበት መንገድ ለመፍጠር፣ ለሚዲያ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን የቀረጥ ዋጋ ለመቀነስ፣ መረጃ ለማግኘት ያለውን ፈተና ለመቀነስ፣ የሚዲያ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ ሚዲያዎችን አካባቢያዊ ወይም ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ቁመና እንዲኖራቸው ለማድረግ ብዙ መሠራት እንዳለበት መንግሥታቸው መረዳቱን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ማኅበራዊ ሚዲያው ሚናውን በተገቢው መንገድ ለመወጣት የሚችልበትን ሕግና አሠራር መዘርጋት እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ እነዚህን ለማከናወን የሚያስችል የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎችን እያደረግን ነው፡፡ አንዳንዶቹም በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናሉ፡›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በዚሁ ተነፃሪ ፕሬሶች መብትና ኃላፊነትን አጣምረው እንዲጓዙ እንደሚፈለግ ጠቁመዋል፡፡ 

አራተኛው መንግሥት (ሚዲያው) ኃላፊነት ያለበት መሆኑንና ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም መሆኑን በመጠቆም፣ በተለይ ደግሞ በሽግግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብን ለማገዝና ለማሻገር የሚያስችል የሚዲያ ከባቢያዊ ሁኔታ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ‹‹ከግጭት ቀስቃሽነት፣ ከጠብ ጫሪነት፣ ከአሉታ አነፍናፊነትና ከስሜታዊነት የወጣ ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ ሙያዊ ብቃቱን የጠበቀ፣ የሞራል ልዕልና ያለው፣ የሚሠራው ሥራ የሚያስከትለውን ውጤት ቀድሞ ለመገመት የሚችል ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ በተለይም በቀጣዩ ዓመት ከሚኖረን ምርጫ ጋር ተያይዞ በእውነት፣ በዕውቀትና በሚዛናዊነት የሚሠራ ፕሬስ ያስፈልገናል፤›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የዩኔስኮ የፊሊክስ ሁፋዌ ቦኚ የ2019 የሰላም ሽልማት የተበረከተላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለሽልማት ምሥጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ሽልማቱን ያገኙት በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣትና ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የፕሬስ ነፃነት እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋፅኦ መሆኑ ተነግሯል።

የዓለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር፣ ከመላው ዓለም በርካታ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዘንድሮ አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት አገር ተብላ የተሞካሸች ሲሆን፣ በቅርቡ የፈረንሣይ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት 40 ደረጃዎችን እንዳሻሻለች ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ጋዜጠኞች የሚታሰሩባት፣ የሚሰደዱባትና ለፕሬስ ነፃነት ያልተመቸች አገር ተብላ በየዓመቱ ሪፖርት ይወጣባት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...