Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአንዳንድ የክልል አመራሮች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን አስገድደው ለማስፈጸም ተፈናቃዮችን በካምፖች እስከ ማገት መድረሳቸው...

አንዳንድ የክልል አመራሮች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን አስገድደው ለማስፈጸም ተፈናቃዮችን በካምፖች እስከ ማገት መድረሳቸው ተገለጸ

ቀን:

‹‹እንደ ዜጋም እንደ አመራርም ግራ የሚያጋቡኝ ሁኔታዎች አሉ››

 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

 ‹‹ጨከን ማለትና መከፈል ያለበት ተከፍሎ የዜጎችን ሥቃይ ለማስቆም ወስነናል››

 / ሙፈሪያት ካሚል

አንዳንድ የክልል አመራሮች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው እንዲፈጸምላቸው ጫና ለመፍጠርና ለማስገደድ ተፈናቃዮችን በካምፖች እስከ ማገት የደረሰ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስትሯ / ሙፈሪያት ካሚል ለፓርላማ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ በአካል ተገኝቶ እንዲገመግም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁሉም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የተወጣጡ አባላትን በማካተት ያዋቀረው የሱፐርቪዥን ቡድን፣ የምልከታ ሪፖርቱን ዓርብ ሚያዚያ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ባቀረበበት ወቅት ነው።

በአጠቃላይ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ጉዳይና ፓርላማው ያሰማራው የሱፐርቪዥን ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ ማብራሪያ ለመስጠት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትሯ / ሙፈሪያት ካሚል የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ (/) እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸውመፈናቀል አደጋ በዜጎች ላይ እንዳጋጠመ የሱፐርቪዥን ቡድኑ ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል፡፡ ቡድኑ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት በትግራይ ክልል 111,465 በደቡብ ክልል 873,272 በኦሮሚያ ክልል 1.4 ሚሊዮን በላይ፣ እንዲሁም በአማራ 107 ሺሕ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች በመጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ አስረድቷል።

ለተፈናቃዮቹ የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች የማድረግና መልሶ የማቋቋም ሥራ በተወሰነ ደረጃ የተሠራ ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነና ተፈናቃዮቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ቡድኑ በሪፖርቱ አመላክቷል።

የቀረበውን ሪፖርት ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ የተቀበሉት / ሙፈሪያት፣ በግጭቶች ምክንያት ነዋሪዎችን ከቀዬአቸው የማፈናቀል የወንጀል 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰና ያልተቀረፈ ችግር እንጂ፣ ዘንድሮ የመጣ እንዳልሆነ ግንዛቤ እንዲወሰድ አሳስበዋል።

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ አመራሮች የችግሮቹ ጠንሳሽና አቀጣጣይ፣ እንዲሁም እንዳይፈታ እክል በመፍጠር በዋነኝነት ተሳታፊ በመሆናቸው ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታትም ሆነ ማስቆም እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

‹‹አንዳንድ አካባቢ የፖለቲካ አመራሩ ራሱ ገዳይ ወይም አስገዳይ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ የመብት ተቆርቋሪ ሆኖ ይቀርባል፤›› ያሉት ሚኒስትሯእነዚህን ኃይሎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋል ካልተቻለ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደማይቻል ጠቁመዋል።

 ‹‹በአንዳንድ ክልሎች ያሉ አመራሮች ተፈናቃዮችንሆስቴጅ” (ማገት) የማድረግ ተግባር እየተፈጸመ ነው። ይህ ካልተሟላልኝ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አላደርግም የሚል አመራር አለ። የወሰን ጥያቄዬ ካልተመለሰ ተፈናቃዮችን አልመልስም የሚል አመራር አለ፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ ክልሎች ነዋሪዎችን በማፈናቀል ድርሻ የነበራቸው ተጠርጣሪዎችን፣ በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ የመንግሥት መዋቅሩ ከለላ እንደሚያደርግና አሳልፎ አለመስጠት መኖሩንም ገልጸዋል።

ለአብነትም በጉጂናጌዴኦ አካባቢዎች ሕግ የማስከበር ሥራ ገና አልተነካም ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዚህ አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭትና ዜጎችን የማፈናቀል ወንጀል ተጠርጥረው ከሚፈለጉት ውስጥ ዘጠኙ ብቻ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከሚፈለጉት 183 ተጠርጣሪዎች መካከል፣ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉት ስድስት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‹‹ከዛሬ ነገ ይሻላል ይሆናል ብለን ነገሮችን ስናስታምም ቆይተናል። በዚህም ዘግየተናል። አሁን ግን መቆም አለበት። ጥርሳችንን ነክሰን ጨከን ማለት አለብን፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ‹‹መከፈል ያለበት ዋጋ ተከፍሎ የዜጎችን ሥቃይ ማስቆም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።

 ተቋማቸው የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲያከናውን መወሰኑን፣ በዚህም መሠረት የክልል የፀጥታ አካላትን ያካተተ የፀጥታ አካላት ሥምሪት መጀመሩን ገልጸዋል። ‹‹የወንጀል ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት ጉዳይ ስለሆነ ከዚህ በኃላ አናስታምም፤›› ብለዋል።

በተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ‹‹መፈናቀልንና ሞትን እንደ ዋዛ እየተለማመድን ነው፣ ደንገጥ ማለት አለብን፤›› ብለዋል።

‹‹እንደ ዜጋም እንደ አመራርም ግራ የሚያጋቡኝ ሁኔታዎች አሉ፤›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በአንድ በኩል አገሪቱ ዓለምን ያስደመመና የሚያኮራ የለውጥ ጉዞ ላይ ሆና፣ በሌላ በኩል አንገት የሚያስደፋ የዜጎች ሥቃይ ውስጥ መሆናችን ምን ጎድሎን ነው?›› እንደሚያሰኛቸው ተናግረዋል።

‹‹ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ ይሞታሉ፣ አመራሮች ግን አይሞቱም፣ አይፈናቀሉም፤›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹ነገሩ በደሃ ኢትዮጵያውያን ላይ ጨዋታ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ በብሔር ጉያ ውስጥ መደበቅ በየትኛውም ሚዛን አመራር እንደማያሰኝም ገልጸዋል። ‹‹ስለዚህ ወደ ሰንኮፉ መጠጋትና መንቀል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክትትል ቡድኑ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ በማየት ያቀረበውን ሪፖርት አድምጦ የሕግ፣ፍትሕናዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አፅድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...