Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ጎበዝ ነገሩ እንዴት ነው? ሁላችንም የአንበሳን ልደት የምናከብር መሰልን እኮ፡፡ አዲስ አበባ ዙሪያ ገባዋ እንዲህ በጥሬ ሥጋ ይጥለቅለቅ እንዴ? ሃያ ሁለት ይቆረጣል፣ ዶሮ ማነቂያ ይቆረጣል፣ ካዛንቺስ ይቆረጣል፣ ቦሌ ይቆረጣል፡፡ የጎመን ምንቸት ውጣ የሥጋ ምንቸት ግባ የተባለው ምርቃት ዘንድሮ ደረሰ እንዴ? የሐበሻ ልጆች ከሥጋ ጋር የነበራቸው ፍቅር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል፡፡ ሁሉም ቦታ ሥጋ እንደ ጉድ ይበላል፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ብዙኃን የሸማቾችን በራፍ ሲያጨናንቁ፣ የደላቸው ደግሞ ኪሎውን በ500 ብር እየሸመቱ ያወራርዱታል፡፡ ለብዙኃን ታላቅ፣ ታናሽ፣ ሽንጥ፣ ዳቢት፣ ሳልገኝ፣ ምናምን እያሉ መምረጥ ተረት ሲሆን፣ ቅንጡዎች ደግሞ ቲፕ እየሰጡ ይምነሸነሻሉ፡፡ በፋሲካ ማግሥት ይህንን ጉድ ስታዘብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ መንግሥት ሲያቀብጠው የዋጋ ጣሪያ አውጆ የተፈጠረው ትርምስ ይታወሳል፡፡ ያኔ ሥጋ ኪሎው በ52 ብር እንዲሸጥ ተወሰነ፡፡ የባለልኳንዳዎች ኩርፊያ ግን አይጣል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ምኑ ከምኑ የማይለይ ሥጋ እየቀረበ ስንት ጉድ ታይቶ ነበር፡፡

ቀደም ሲል ደንበኞቻቸውን 32 ጥርሶቻቸውን እያሳዩ እንደ ጠዋት ፀሐይ በደመቀ ፈገግታ ይቀበሉ የነበሩ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ሥጋ ቆራጮች፣ አክሽን ፊልም ውስጥ የሚተውኑ ኮስታራ አክተሮችን መስለዋል፡፡ ግንባራቸውን ከስክሰው አንዴ ከላይ አንዴ ከታች የሚቆራርጡት ሥጋ ለመብል የተዘጋጀ ሳይሆን፣ ለውሻ የሚጣል እያስመሰሉት ነበር፡፡ ከሞራው፣ ከአጥንቱ፣ ከማይታኘከውና ሥራ ሥርና ከመሳሰለው እየመረጡ ሚዛኑ ላይ ሲያስቀምጡት ለምግብነት የሚውል ሳይሆን ገንዳ ውስጥ የሚጣል ይመስላል፡፡ አንዳንዶቹማ ቢላዋዎቻቸውን እያፏጩ አፍጥጠው ሲያዩን ለምን መጣችሁ እያሉ የሚያስፈራሩን ይመስሉ ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ የተገኘውን የሥጋ ዘር ሳንመርጥ በግዴታ እያጣጣምን ሰነበትን፡፡ ከሥጋ ጋር ተለያይቶ የከረመው ደግሞ ይህንን ማን አየበት እያለ የሰጡትን ቢመገብ ማንን ሊገርም ይገባ ነበር? ‹የቤቴ መቃጠል ለትኃኑ በጀው› እንዲሉ ማለት ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ድባብ በነበረበት ሁኔታ ውስጥ የከተማው ልኳንዳ ቤቶች በሰዎች ቢሞሉ አይገርምም፡፡ እኔንም በወቅቱ የገጠመኝ ይኼው ነው፡፡ እንዳሁኑ የበዓል ሰሞን ያኔ ከአሜሪካ ከመጣች ጓደኛዬ ጋር ሃያ ሁለት አካባቢ የሚገኝ አንድ ልኳንዳ ቤት፣ የናፈቀችውን የሥጋ ጥብስ ለመብላት እንሄዳለን፡፡ የሥጋ መሸጫው ሥፍራና ግቢው በሥጋ በላተኛ ተጣቧል፡፡ እንደ ምንም ብለን አዘዝንና ከአንዱ ጥግ ተቀመጥን፡፡ ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ ያዘዝነው ጥብስ ቀዝቅዞ ደረሰ፡፡ የጥብስ ማባያ አዋዜ ስላልቀረበ መጠበቅ ጀመርን፡፡ አንድም ብቅ ያለ የመስተንግዶ ሠራተኛ ባለመኖሩ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ቢያንስ አራት ለሚሆኑት አስተናጋጆች ነገርኳቸው፡፡ አንዳቸውም ግን ሊታዘዙ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ቢቸግረኝ እንደገና ለእነዚሁ ሠራተኞች ተናገርኩ ‹‹እሺ›› ከማለት ይልቅ ማንም አዋዜውን ለማምጣት አልፈለገም ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የእኔን ወጣ ገባ ማለት በተደጋጋሚ የተመለከተ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ችግሬን ሲረዳ በጣም ተናዶ አዋዜው ከሚታደልበት ሥጋ ቤት በስንት መከራ ተጋፍቶ አመጣልኝ፡፡ ለካ አካባቢውን በሚገባ አላየሁም እንጂ ጥሬ ሥጋ ያስቆረጡ ሰዎች ራሳቸው ሥጋውንና አዋዜውን እየተሸከሙ ሲያስተናግዱ፣ ሠራተኞቹ በደንታ ቢስነት ይመለከቷቸው ነበር፡፡ ከዚህችው ጓደኛዬ ጋር የቀዘቀዘውን ጥብስ ባልደረባዬ ተጋፍቶ ባመጣልን አዋዜ እንደምንም በላን፡፡ ከዚያም በሁኔታው እየተገረምን ሹልክ ብለን ወደ መውጪያው በራፍ ማምራት ጀመርን፡፡ የሥጋ መሸጫው ኪዮስክ ላይ የሥጋ ሻጩ ረዳትና አንድ ተስተናጋጅ ይጨቃጨቃሉ፡፡

የሥጋ ቆራጩ ረዳት በደንታ ቢስነት ሥጋ የሚቆረጥበትን ቢላ እያወዛወዘ፣ ‹‹አጋጣሚ የፈጠረልህን ዝም ብለህ ብላ፤›› ይላል፡፡ ተስተናጋጁም፣ ‹‹አጋጣሚ ሳይሆን በመንግሥት የተረጋገጠልኝ ሕጋዊ መብቴ ነው፤›› በማለት ይመልሳል፡፡ ረዳቱ እየሳቀ፣ ‹‹ለምን ነጠላ ዜማ አታወጣውም ታዲያ?›› እያለ ሲያሾፍ፣ ሰውዬው በንዴት ዓይኖቹ እየተንቀለቀሉ ‹‹የማትረባ!›› በማለት ይሰድበዋል፡፡ የሥጋ ቆራጩ ረዳት በበኩሉ፣ ‹‹አላርፍም ካልክ ይኼ ይከተላል›› በማለት ቢላዋውን ሲያሳየው፣ አንድ ወጣት መሀላቸው ይገባል፡፡ የሥጋ ቆራጩን ረዳት አፍጥጦ እያየው፣ ‹‹ሕግ መኖሩን አታውቅም እንዴ?›› ሲለው፣ የሥጋ ቆራጩ ረዳት፣ ‹‹ምን ሕግ አለና?›› ማለት፡፡ ይኼኔ ወጣቱ እየሳቀ፣ ‹‹እንደናንተ ዓይነቶችን ሕግ ሳይሆን ኃይል እንደሚገዛችሁ አየን እኮ፣ ሕግ የማይገዛውን ኃይል ይገዛዋል፤›› ብሎ መንግሥት ስላወጣው የዋጋ ተመን ሲነግረው ጥርሱን ነክሶ ፊቱን አዞረ፡፡ ምንም ጥቅም በሌለው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያ ሁሉ ትርምስ ተፈጥሮ መመርያው ከወራት በኃላ ተሻረ፡፡ አሁን ደግሞ ነጋዴ ባሻው ዋጋ እየሸጠ የመደብ ልዩነቱን ቢለጥጠውም እንደ አቅሚቲ ሥጋ ቤት መሄዳችን ይቀጥላል፡፡ ጥሬ ሥጋ ዓይቶ ማን ያልፋል የተባለ ይመስል ቀጠሮአችን ሁሉ ከካፌ ወደዚያው ከተሸጋገረ በጣም ቆየ፡፡ በፋሲካ ሰሞን ምን ይወራ ታዲያ?

(ናትናኤል ባህሩ፣ ከኦሊምፒያ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...