Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከሥጋት የማላቀቅ ፈተናዎች

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከሥጋት የማላቀቅ ፈተናዎች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ላይ ተከብሯል፡፡ ፕሬሱ በየአገሮቹ ስላሉበት ሁኔታም ደረጃ ወጥቷል፡፡ የየአገሮቹ መንግሥታትም ያጣበቧቸውን፣ የገደቧቸውንና የጣሷቸውን መብቶች ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህ አካሄድ ምናልባት ገበናቸውን ሌሎች ሲያውቁባቸው ኃፍረት ተሰምቷቸው እንዲያሻሽሉ የተሻሉ አገሮችና አካላትም ጫና እንዲያደርጉባቸውም ይረዳል፡፡

በዚሁ ዓመትም በኢትዮጵያም ይህንኑ ዕለት በማሰብ አዲስ አበባ ላይ ብዙ ሽር ጉድ ተብሏል፡፡ የሽር ጉዱም መነሻው በዋናነት የኢትዮጵያ ደረጃ ከወትሮው በተለየ አኳኋን ከሦስት ደርዘን በላይ አገሮችን ዘልላ 110ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ በእመርታዊ ለውጥ መታየቱ ይመስላል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የፕሬስ ነፃነት ባለፈው ዓመት ስለነበረው ሁኔታ ደረጃ ካወጡላቸው ከ180 አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ 150ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧት ነበር፡፡ ካቻምናው ተመሳሳይ ደረጃ ነው የነበራት፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ 110ኛ ሆናለች፡፡ ፕሬሱ ለዴሞክራሲ ካለው አስተዋጽኦም ይሁን ከሌሎች ግቦችና አድራጎት አንፃር በዓለም አቀፍ ተቋማትም ይሁን በአገሮች ሪፖርት ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን በሚመለከት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ አከራካሪ አይደለም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ በአንድ ዓመት አርባ አገሮችን እንድትዘል ያደረጋት የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ ያጠፋቸውን ጥፋቶች በማስተካከሉ ነው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁን፣ የሚዲያ ሕግጋቱን ለማሻሻል እየተጋ በመሆኑ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች በመልቀቁ፣ የዘጋቸውን ብሎጎች በመክፈቱና ኢትዮጵያ ውስጥ በአካል በመግባት አገልግሎት እንዳይሰጡ የተከለከሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲገቡ በመፍቀዱ እንዲሁም ተጨማሪ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሥራ በመጀመራቸውም የይዘት ነፃነትም ላይ ጣልቃ የሚገባበት ረዥም እጁን ስለሰበሰበ ነው፡፡

ደረጃውን ከሰጠው ተቋም ሪፖርት በመነሳት ኢትዮጵያ ያሻሻለችው ነገር በዋናነት መንግሥት እንዳያደርግ የሚጠበቅበትን አሻፈረኝ ብሎ ሲደርግ የነበረውን አሁን ላይ በማክበሩ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብትን በጥቅሉ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ደግሞ በተለይም በሚመለከት መንግሥት የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታዎች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ የማክበር ግዴታ፣ መንግሥት ጣልቃ ባለመግባት፣ እጁን በመሰብሰብና አርፎ በመቀመጥ ነው ግዴታውን ተወጣ የሚባለው፡፡ የማስከበር ደግሞ መብት እንዳይጣስ የመጠበቅ፣ የመከላከልና ዕርምጃ የመውሰድ ወዘተ. ተግባራትን በመፈጸም ግዴታውን እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ አልፎም መተግበር፣ መፈጸም፣ ማድረግ፣ ማሟላት፣ ማመቻቸትና ማቅረብ የመሳሰሉት ኃላፊነትም የሚኖርበት ሁኔታ ስላለ የማሟላት ግዴታም አለበት ማለት ነው፡፡ ብሎጐችን መዝጋት፣ አሳሪና ቀፍዳጅ ሕግ ማውጣት የማክበር ግዴታን አለመወጣት ነው፡፡ የሌሎች መብቶች ሲጣሱ ዝም ማለትን ከማስከበር ግዴታው መውደቅ ይሆናል፡፡ መረጃ አለመስጠት፣ የኢንተርኔት አገልግሎትን አለማቅረብና ማቋረጥ፣ ለሚዲያ ተፈላጊ የሆኑ ሥልጠናና ትምህርት የሚሰጥባቸውን ተቋማት አለመክፈትን ብንወስድ ደግሞ የማሟላት ግዴታን አለመፈጸም ይሆናሉ፡፡

ከላይ የቀረቡትን ሦስቱን የመንግሥት ኃላፊነቶች ወደ ሁለት ምድብ ውስጥም የሚከቷቸው መኖራቸው ይታወቃል፡፡ መነሻቸው ነፃነት ሁለት ፈርጆች አሉት ከሚል ነው፡፡ አንዱ ነፃነት የሚኖረው ከሌሎች ነፃ መሆንን ስለሚጠይቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ፈርጅ፣ ሌሎች አካላት ለምሳሌ መንግሥት ሲያደርግና ሲፈጽም እንጂ በዝምታው ባለማድረጉ የተነሳ ነፃነት ስለማይኖር ነው፡፡  መንግሥት ማድረግ ያለበትን ካላደረገ ነፃነቱ አይገኝም፡፡ የዘርፉ ምሁራንም፣ ፈላስፋዎችም ጭምር የመጀመርያው የአሉታ ነፃነት (Negative Freedom) ሁለተኛውን የአወንታ ነፃነት (Positive Freedom) በማለት ይጠሯቸዋል፡፡

የፕሬስ ነፃነት ሲከበር ኢትዮጵያ እመርታዊ ለውጥ ያመጣችበት የአሉታ ነፃነት በሚለው ጎራ ሥር ያሉትን ግዴታዎች መወጣቷ ነው፡፡ በአዎንታ ነፃነት ላይ ያሉት ብዙም የተስተዋለ ለውጥ የለም፡፡ ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ ካባ በመሸፈን ወይም በማሳበብ የሌሎች ሰዎች መብት መጣስን በምሳሌነት ብናነሳ የጥላቻ ንግግርን የግለሰቦችን ግላዊነትና መልካም ስምና ክብር ለማስጠበቅ የሄደበት የአጭር ርቀት ሩጫ ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከቀድሞው የተንሸራተተባቸውም ይኖራሉ፡፡ መረጃ የማግኘት መብትን በሚጥስ አኳኋን፣ ሐሰተኛ ዜናና መረጃ ማስተላለፍም እየጨመረ ነው ማለት ይቻላል፡፡   የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ሙሉ በሙሉ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ ጋር የሚያያዙ መብቶችንና ግዴታዎችን የሚገልጽ ነው፡፡ በመጀመርያው ንዑስ አንቀጹ ላይም ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት የመያዝ መብት ያለው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ለማስጠበቅ በመንደርደሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡

ከዚያ ውጭ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብና አመለካከት የመያዝ ወይም የመጣል መብትን በተመለከተ ጥበቃ ቢደረገለትም ባይደረግለትም ብዙም ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የመሰለውን፣ ያመነበትንና የፈለገውን ወዘተ. አመለካከት ቢይዝና ሌላውን ቢተው ሌላ አካል በግዳጅ በተቃራኒው የሆነን ሐሳብና አመለካከት እንዲይዝ ወይም እንዲጥል ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ ነው፡፡ በዋናነትም ውስጣዊ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መገደብ የሌለበት መብት ነው፡፡ በዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም በአስቸኳይ ጊዜም ቢሆን እንኳን ዕገዳ የለበትም፡፡ ከገደብም ከዕገዳም ነፃ የሆነ ነው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚታገዱት ውጭ አልሆነም፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት ከመያዝ ቀጥሎ የሚመጣው የማካፈሉና የመቀበሉ  የመግለጹ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ተጨባጭ ዋስትና መስጠት የሚቻለውና ጥበቃ የሚያስፈልገውም ይኸው መብት ነው፡፡ ይህ መብት ለዴሞክራሲ እምብርት ነው፡፡ ሕዝብ ራሱን በራሱን ለማስተዳደርና አማናዊ የምርጫ ሥርዓት ይተገበር ዘንድ መራጩ ስለሚመርጠው ሐሳብም ወኪልም መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ የፈለገውንና የሚበቃውን ዕውቀት ለማገኘት ደግሞ የትኛውም ዓይነት ሐሳብ ያለገደብ የሚሠራጭበት ሥርዓትን ይጠይቃል፡፡

በሥልጣን ላይ ያሉ ወይም የማድረግ አቅም ያላቸው የማይፈልጉትን ሐሳብ እየነጠሉ የሚያስቀሩ መሆን የለባቸውም፡፡ እንዲህ ከሆነ የሐሳብ ፍሰት ይገደባል፡፡ በበቂ ሁኔታ የማይታወቅን ለመምረጥም ሆነ ሳያውቁ ለመጥላትና ላለመምረጥም ያጋልጣል፡፡ ዴሞክራሲም ይኮሰምናል ወይም ጭራሹኑ አይኖርም ማለት ነው፡፡ የሚመረጥ ከሌለ ደግሞ ዴሞክራሲ አይኖርምና፡፡ የሐሳብ ፍሰትንና ሥርጭትን መጠምዘዝ የዴሞክራሲ ተቃራኒ ነው፡፡ እየፋፋ ሲሄድም የተረጋጋ ነገር ግን ቀጣይነትና ተያያዥነት ያለው ለውጥንም ያመጣል፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነትና መግባባትንም ይፈጥራል፡፡ ካልሆነ አለመረጋጋት ይከሰታል፡፡ በአንድነት ሊኖሩ የሚችሉ ጤናማ የሆኑ ልዩነቶች አይኖሩም፡፡ አገራዊ መግባባትም ይነጥፋል፡፡ የዚህ ውጤቱም ከለውጥ ይልቅ አብዮት ይሆናል፡፡

የንግግር ነፃነት ወይም ሐሳብን የመግለጽ መብት ሲባል የራስን አመለካከትንና ሐሳብን፣ ያለመንግሥታዊ ብቀላና ዕቀባ እንዲሁም ያለማኅበረሰባዊ ክልከላ፣ የማንጠርና   የማስተላለፍን መብትን ይመለከታል፡፡ ይህንን ለማከናወን ደግሞ ሐሳብንና መረጃን በነፃነት የመሰብሰብ (seek)፣ የመቀበል (Receive) እና የማሠራጨት (Impart) ድርጊቶችን ማስጠበቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሲባል እነዚህ ሦስት ፈርጆችን ይይዛል ማለት ነው፡፡ በሕገ መንገሥቱ በአንቀጽ 29(2) ላይ የተገለጹ ናቸው፡፡ ሐሳብን የመሰብሰብ ወይም የመሻት ነፃነት የሚመለከተው መረጃ መሰብሰብን፣ መፈልግንና ማግኘትን ነው፡፡ ከየትም ቦታ የሚተላለፍን የሚዲያ ሥርጭቶችን መከታተልንና መረጃ ማግኘትንም ማረጋገጫና ዋስትና ነው፡፡ ሐሳብን መቀበል ደግሞ በዋናነት ሚዲያ ከመከታተል ጋር ይያያዛል፡፡ የመረጃ ምንጭ ላይ ገደብ መጣል ወይም እንዳይደርስ ማድረግን ይከለክላል፡፡ እንዲሁም ዜጎችን ከሆነ የመረጃ ምንጭ ሐሳብ እንዳያገኙ አለማስፈራራትን (ከፍርኃት ነፃ) መሆንን ይመለከታል፡፡

በሌላ በኩል ሐሳብን ማሠራጨት ለፖለቲካዊ መብቶች መከበርና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋና መሠረት ነው፡፡ ትርጉም ያለው ምርጫ ከዚህ የሚቀዳ ነው፡፡ መንግሥት ላይ የሚኖር ቅሬታና ትችት ለመግለጽና ለሕዝቡ በማሳወቅ ደጋፊዎችን ማፍራት የሚቻለው ሐሳብን በማጋራት ነው፡፡ ሐሳብን ማሠራጨትና መቀበል የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም ማለት ነው፡፡ የሚያሠራጭ ነገር ካለ የሚቀበል አለ ማለት ነው፡፡ ሐሳብ ወይም አመለካከት ደግሞ በተለያዩ ዘዴዎችና ምንጮች ሊገኝ ይችላል፡፡ ከኅትመት ውጤቶች፣ ከሰዎች፣ ከሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ ምንጫቸውም ከአገር ውስጥ ወይም ውጭም መሆኑ ለውጥ የለውም፡፡ የሚተላለፍበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን፣ ከየትም አገር ይሠራጭ ጥበቃው ተመሳሳይ ነው፡፡ በየትኛውም ዘዴና ከየትም አገር ከሚሠራቸው ሚዲያ ማንም ሰው ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት መብቱ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ለግለሰቦች ሐሳብን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨትን መብትን በንዑስ ቁጥር 2 ላይ ጥበቃ ከዳረገ በኋላ እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ ወይም ለማንሸራሸሪያነት ወሳኝ የሆኑትን የፕሬስና የመገናኛ ብዙኃንንና የሥነ ጥበብ የፈጠራ ነፃነት እንደተቋም በንዑስ ቁጥር 3 ላይ ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው በእነዚህ ተቋማት በመረጠውና በመሰለው ዘርፍ ውስጥ በመሰማራት ሐሳቡንና አመለካከቱን በነፃነት መግለጽ ወይም ማንሸራሸር ይችላል ማለት ነው፡፡ በፕሬስ አማካይነት ሰው ሐሳቡን መግለጽ ሲፈልግ በማናቸውም መልኩ ከራሱ ከሐሳቡ ባለቤት ፈቃድ ውጭ አስቀድሞ ሳንሱር አይደረግበትም፡፡ የአርትኦትም ሥራ አይደረግበትም፡፡ በወንጀል የሚያስጠይቅ ቢሆን እንኳን ከኅትመት በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ከመሠራጨቱ በፊት የሚታገድ ወይም የሚያዝም ከሆነ ዞሮ ዞሮ ያው ክልከላ ነው፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ ይህንን ሲያጸናና ሲያስረግጥ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት መሠረት በማድረግ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ ገደብ እንዳይጣል ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡ 

ሚዲያ በዋናነት የሐሳብን ነፃነትን ለማስከበር የሚያገለግል ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው ለመገደብም ሊውል ይችላል፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ብቻ የሚጠቀሙበት ከሆነም ለአፈናም ሊውል ይችላል፡፡ ጥበቃ የሚፈለገው ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ጭምር ነው፡፡ ለፕሬስም ይሁን ለማንኛውም ዓይነት መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነፃነት መኖር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29(3) ሥር ዋስትና የሰጠው ‹‹የሕዝብን ጥቅም›› የሚመለከት መረጃን ብቻ ነው፡፡ ለዚሁም ቢሆን መረጃ የማግኘት ዕድል እንዲኖር እንጂ በመብትነት የተቀመጠ አይደለም፡፡ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት ካልሆነ መረጃን መንፈግ ይቻላል ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከትና የማይመለከት የሚለውን መለየት  አስቸጋሪና ለባለሥልጣናትና መረጃውን ለያዘው ሠራተኛ መልካም ፈቃድ ላይ እንዲንጠለጠል ሊያደርግ ይችላል፡፡ ካልሆነም የሕዝብን ጥቅም የሚመለከቱና የማይመለከቱ ብሎ በሕግ ለመዘርዘር ሰፊ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት ካልሆነ ፕሬሱ ከመብት አንፃር ሊጠይቅ የሚችልበት መነሻም የለውም ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ‹‹የማግኘት ዕድል›› የሚለው መረጃውን ለሚፈልጉት በመብትነት ባለመቀመጡ መረጃውን የያዘውን የመንግሥት ባለሥልጣን በፍርድ ቤት ማስገደድም የሚቻል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም መብት ስላልሆነ፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(4) ላይ  ፕሬስ በተቋምነቱ ጥበቃ እንደተደረገለት ይገልጻል፡፡ ለጥበቃው ምክንያቱ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ እዚሁ ንዑስ አንቀጽ ላይ ተገልጿል፡፡ ፕሬስ በተቋምነቱ አሠራሩ ነፃነት እንዲኖረው በሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ይህ የግልም ይሁን የመንግሥት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ቢሆኑ ልዩነት የለውም፡፡ ሁሉም ላይ ተፈጻሚ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥት የሚተዳደረው ላይ ተጨማሪ ግዴታ እንዲኖር ንዑስ አንቀጽ አምስት ይደነግጋል፡፡ በመንግሥት ሀብት የሚተዳደር መገናኛ ብዙኃን ሲሆን የሐሳብ ብዝኃነትን ለማስተናገድ በሚያስችል መንገድ መተዳደር እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ መንግሥት ከመገደብ ወደ ኋላ ሊል እንደማይችል ቀድሞ በማሰብ የተቀመጠ መከላከያ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን መከልከል አይቻልም፡፡ ወንጀል ማድረግማ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ በሕግ የሚገደብባቸው ‹የወጣቶችን ደኅንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን  የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ› ብቻ ናቸው፡፡  የብዙዎቹ መለኪያዎች በሕግ መደንገግና ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ መሆን ሲሆኑ፣ የሁለተኛውን መሥፈርት አስፈላጊነቱን የመወሰን በአብዛኛው የተተወው ለሚመለከታቸው አገሮች ነው፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች እንደፈለጉ ለመፈንጠዝ የተመቹ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው  ሕገ መንግሥቱ የመረጣቸው ደግሞ ጥብቅ እንዲሁም ለመለካት የማያስቸግሩ መሥፈርቶችን ነው፡፡

የኢትዮጵያን የሚዲያ ነፃነት ይዞታና አቋም ዋዣቂ ስለሆነ ቁም ነገሩ ያለው በወጥነት እየተሻሻለ መሄዱ ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈበት የሚዲያ ነፃነት ጉዞ ወቅታዊነት ያጠቃው እንደነበርም የታወቀ ነው፡፡ የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር ብንተወው እንኳን በተመሳሳይ ሕገ መንግሥት፣ በተመሳሳይ ገዥ ፓርቲ አስተዳደር ወጥነት የጎደለው የሚዲያ አስተዳደር ዘመንን አሳልፏል፡፡ በዚህ ዓመትም ያስመዘገበችው ለውጥ ሕገ መንግሥቱ ተመሳሳይ ገዥው ፓርቲም ያው የቀድሞው የፓርቲው መሪዎች ግን ሌላ ስለሆኑ ነው ውጤቱ የተለየው፡፡ የአመራሩ መለወጥም የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታም መለወጥ በድምሩ የሚዲያውንም ነፃነት ከወትሮው እንዲለይ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽም ይሁን የሚዲያ ሁኔታ እንደተቋም ወጥነትና ዘላቂነት አሁንም ከፈተና መውጣቱን መናገር አይቻልም፡፡ በተለይ የዲጂታል ሚዲያው አስተዳደርን በሚመለከት ብዙ ፈተናዎች የተደቀኑበት ስለሆነ በተለይም የጥላቻ ንግግርም የተሳሳተና የሐሰት መረጃ ዕለት ዕለት በመጠንም በአቅርቦትም እየበዛ በመሄዱና ሁሉም ሰው እንደ ጋዜጠኛ የመሥራት አዝማሚያው እየጨመረ መሄዱ ለኢትዮጵያም ጭምር ፈተናዋን ማብዛቱ አይቀርም፡፡ በምሳሌነትም በቅርቡ፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ የተለቀቀው የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨትን ለመከላከል የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ረቂቁ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቀረበበት ሁኔታ ቢፀድቅና ሥራ ላይ ቢውል ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የሚኖራት ደረጃ ከመሻሻል ይልቅ ወደ ኋላ ሊያፈገፍግም ሊያሽቆለቁልም ይችላል፡፡

 አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...