Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየሙስና ወንጀልን መታገል ለምን ያቅታል?

የሙስና ወንጀልን መታገል ለምን ያቅታል?

ቀን:

በተስፋዬ ነ.

የመንግሥት አገልግሎት ለዜጎች በገንዘብ ወይም በነፃ የሚሰጥ ነው፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡት ደግሞ ለእዚሁ ሥራ ተብለው የተሾሙና የተቀጠሩ አመራርና ሠራተኞች ናቸው፡፡ ሹመት በፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት የሚሰጥ ኃላፊነት ነው፡፡ አገልግሎት የሚሰጡት ሹመኞች፣ አመራርና ሠራተኞች በሚሰጡት አገልግሎት ዓይነት ላይ የትምህርት ዝግጅትና የልምድ ክህሎት ያላቸው ናቸው ተብሎ ይጠበቃል፡፡  ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት ከዜጎች ጉቦ የሚጠይቁት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በተለይም አገልግሎቱን የሚፈልገው ሰው ቁጥር በርከት ሲል አጋጣሚውን በመጠቀም አገልግሎትን በቅድሚያ ወይም በፍጥነት መስጠት ጉቦ ይጠየቃሉ፡፡ የሚሰጠው አገልግሎት ቅድመ መሥፈርት ማሟላትን የሚጠይቅ ከሆነ ባልተሟላ ሰነድ አገልግሎቱን ለመስጠት ጉቦ ይጠየቃሉ፡፡ አገልግሎት ፈላጊውም ያልተሟላ ወይም ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብ የሚፈልገውን አገልግሎት ጉቦ በመስጠት ያገኛል፡፡ በዚህ ሒደት ላይ ደላላው ድርሻውን ያገኛል፡፡ በሒደቱ በአብዛኛው ጊዜ የአገልግሎት ፈላጊው ሰው ከፍተኛ ተጠቃሚ ሲሆን፣ አገልግሎት ሰጪው ደግሞ በነፃ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

በዚህ ሒደት አገልግሎቱን በትክክል ማግኘት የነበረበት ሰው ላያገኝ ይችላል፡፡ ካልሆነም የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት በተደጋጋሚ ለመመላለስ ይገደዳል፣ ነገር ግን ሰሚ ላያገኝ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዜጋው ለሚፈልገው አገልግሎት ትክክለኛና የተሟላ መረጃ እያለውም የአገልግሎት ሰጪው ከአገልግሎት መስጫ ቦታ ላይ እየተደበቀ ወይም ፋይል እየደበቀ ወይም ምክንያት እየፈለገ እንደማይሰጥ ሲነገረው ተገልጋዩ ዜጋ ተገዶ ጉቦ ለመስጠት እንዲገደድ ይደረጋል፡፡ እዚህም የደላሎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለው በጉቦ ፍለጋ የተጨማለቀ አገልግሎት ዜጎች መንግሥት ላይ እንዲማረሩ፣ ያለው መንግሥት ሙሰኛ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ፣ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እየሆነ ያለው ሀቅ ይህ ነው፡፡ የመብራት ኃይል ሰዎች በሚፈጥሩት ከፍተኛ ሻጥር በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት ክፍያ ለመክፈል በአንድ ክፍያ ጣቢያ ሁለት ገንዘብ ተቀባይ ብቻ በመመደብ እየፈጠሩ ያሉት ከፍተኛ ሥቃይ፣ ሠልፍና የጊዜ ማባከን ጉዳይ፣ እንዲሁም ለዘመናት በፖልና ፊውዝ ችግር እያሉ ሕዝብን እያታለሉ የመብራት ማቆራረጥና ለቀናት ማጥፋት በሌላ በኩል ደግሞ ጉቦ አምጡ ማለት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡

- Advertisement -

በመንግሥት ተቋማት ውስጥ አብዛኛው ሙስና ወንጀል የሚፈጸመው በዕቃና አገልግሎት ግዥ ላይ ነው፡፡ ይህ ሙስና የሚሠራው ከመነሻው የበጀት ዕቅድ ሲታቀድ ነው፡፡ ዕቃው ወይም አገልግሎት እያለ የግዥ በጀት ዕቅድ ይያዛሉ፡፡ ይህ አንድ ነገር ሲሆን፣ ትክክለኛ የግዥ በጀት ተይዞም በግዥ ሒደት ላይ ሙስና ወንጀል የሚፈጸምበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡ ለአንድ አቅራቢ የሚመች ዝርዝር መግለጫና መሥፈርት በማዘጋጀት ጉቦ የከፈለ ወይም ቃል የገበ አቅራቢ እንዲያሸንፍ ያደርጋሉ፡፡ መንግሥትንና ሕዝብን ይመዘብራሉ፡፡ ለራሳቸው የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራሉ፡፡ የዘረፉትን ገንዘብ ቤተሰቦቻቸው ስም ከፍተው ያስቀምጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ዛሬ ለመንግሥት ኃላፊ በጥሬ ገንዘብ ጉቦ አይሰጥም፡፡ በቪዛ ኤቲም በውጭ አገር የባንክ ሒሳብ በመክፈት ነው፡፡ በዚህ ግዥ ላይ የሚሠማሩት በተቋም ውስጥ የፋይናንስና የግዥ ሠራተኞች፣ የፕሮጀክት ሠራተኞች፣ የምህንድስና ክፍል ሠራተኞች፣ የግዥ ኮሚቴና ተቋም የበላይ ኃላፊ ናቸው፡፡ በቅርቡ በሙስና ተጠርጣሪ የሆኑ ሰዎች ጉዳይም ይህን የሚያሳይ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ሁሉም ሠራተኞችና አመራር በአንድ ላይ የሙስና ወንጀል ባይፈጽሙም፣ ጠንሳሽ የሆኑት ብቻ ተለይተው የሙስና ወንጀል በመፈጸም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ይህ ሙስና በቀጥታ ከዜጎች ዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር ባይያያዝም ውሎ አድሮ ልማት ያደናቅፋል፡፡ እየቆየ የኑሮ ውድነትንም ያባብሳል፡፡

በመንግሥት አገልግሎት ሙስና ወንጀል ለመከላከል በተቋማት ውስጥ የውስጥ ኦዲተርና የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች አሉ፡፡ የውጭ ኦዲተር የተቋሙን ሒሳብ ይመረምራል፡፡ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲም የግዥ አፈጻጸም ላይ ኦዲት ያደርጋል፡፡ የቅሬታና አቤቱታ የሚቀበሉ ሰዎች በእየ ተቋሙ ቢሮአቸውን ከፍተው ቅሬታና አቤቱታ ለመቀበል ይጠብቃሉ፡፡ የፌዴራል ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል በመመርመር ይከሰሱ፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን ከመከላከል በተጨማሪ፣ በሥነ ምግባር የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የተቋማትን ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተቋማት ለምን ግን ሙስና መቆጣጠር አልቻሉም የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት ለእነዚህ ቁጥጥርና ክትትል ለሚያደርጉ ተቋማት ሰዎች ከፍተኛ በጀት ይመድባል፡፡ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮም ብዛት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችና ደላሎች እስር ቤት ገብተዋል፡፡ በቅርቡ 59 ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እስር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ለምን ይሆን እነዚህ ሁሉ ተቆጣጣሪ አካላት እያሉ ይህ ሁሉ ሙስና ወንጀል የሚፈጸመው? የተጠቀሱት ተቋማት ሙስና የበለጠ እንዳይባባስ ይከላከላሉ እንጂ ማስወገድ በፍፁም ዓይችሉም፡፡ የሰዎች የእኔነት እምነትና ስሜት መቀየር አለበት፡፡ ምክንያቱ ሙስና ውስብስብና በተማሩ ሰዎች የሚፈጸም ስለሆነ በቀላሉ ሊጠፋ አይችልም፡፡ የሰዎች ስግብግብነት እየጨመረ ሲሄድ የሙስና ወንጀል ክርስቲያን ሙስሊም አይልም፣ በሁሉም ዘንድ የሙስና ወንጀል ይፈጸማል፡፡ ይልቅ አገሪቱ ወደ ባሰ መቀመቅ ውስጥ እንዳትገባ የተጠቀሱት ተቋማት በርትተው ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ መንግሥትም ለሙስና ወንጀል መከላከልና መዋጋት ሥራ የእውነት ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡

የሙስና ችግር እየተባባሰ በሄደ ቁጥር በሒደት በመንግሥት አገልግሎት ላይ የተማረረው ዜጋ አጋጣሚውን ሲያገኝ፣ ቀድሞ የሚያጋየውና የሚያወድመው የመንግሥት ተቋምና ንብረት ነው፡፡ ለምን ዜጎች የመንግሥት ተቋማት ጠላት ይሆናሉ? ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት ተቋማት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ዜጎችን ያንገላታሉ፣ ከወንድማቸው ጉቦ ይጠይቃሉ፣ ለዘመዶቻቸው ያዳላሉ፣ ዘመዶቻቸውን ይቀጥራሉ፣ ዘመድ የሌለው በመንግሥት ተቋም ሊቀጠር አይችልም፣ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ ሊሆኑ እንሠራለን ይላሉ፣ የራሳቸውን ዘመድ ግን በመንግሥት ተቋም ቀጥረው ያሠራሉ፡፡

ዜጋው ራሱ ተቀጥሮ የሚሠራበት መሥሪያ ቤት ላይ ጥቃት ሲያደርስ ምክንያት አለው፡፡ የደረጃ ዕድገት የሚያገኘው፣ ጥቅም የሚገኝበት ቦታ ላይ እንዲሠራ የሚደረገው ዘመድ ያለው ሠራተኛ ነው፡፡ ዘመድ ካለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለበቂ ዕውቀትና ክህሎት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ይመደባል፣ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ሳይኖረው ዘመድ ካለው ብቻ ሚኒስቴር፣ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ይሾማል፡፡ ጮማ ዘመድ የሌለው የፈለገውን ያህል ዕውቀትና ክህሎት ቢኖረው ዞር ብሎ የሚያየው አካል የለውም፡፡ ‘ላለው ይጨመርለታል፣ ከሌለው ይወሰድበታል’ ነው ነገሩ፡፡ ዘመድ ለሌለው ያለው ዕውቀትና ክህሎት የትም አያደርሰውም፡፡ ዘመድ የሌለው ከፍተኛ ተግዳሮቶች ያለበት ቦታ ይሠራል፣ ለብዙ ዓመታት ዕድገት አያገኝም፡፡ ይህ ድርጊት በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ ያለና የሚኖር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የለውጥ አመራር በተባለውም አይብዛ እንጂ ይህን ሲሠራ ይታያል፡፡

የሚያሳዝነው በዘመድ የተቀመጡት አመራሮች ሙስናን ለመከላከል ያላቸው የዝግጁነት ችግር ነው፡፡ በእርግጥ ሥልጣን ላይ የሚመደበው ለፅድቅ እንዳይደለ ማንም ዜጋ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ዝና ለማግኘት፣ ዘመናዊ መኪና ለመንዳት፣ ቤት ለማግኘት፣ ባሉት ሚዲያዎች ለመታየት፣ ለመዝናናት፣ ወዘተ. እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ዜጎቼ ደሃዎች ናቸው ብሎ ማሰብ የለም፡፡ ነገ ባልታወቀ ቀን ከሥልጣን ሊወርድ ስለሚችል መጠቀም አለብኝ የሚባል ብሂል እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ በአደጉት አገሮች ውስጥ ግን ሰዎች በቂ ገንዘብ ስላላቸው ሥልጣንን የሚፈልጉት ታዋቂነት ለማግኘት ነው፡፡ ስለዚህ ለሥርቆት ብዙም አይነሳሱም፡፡ እንደ እኛ ባሉ አገሮች ግን እነዚህ ሰዎች ሙስና መታገልን አይደለም ልታገል የሚለውን ሰው ማገዝ ቀርቶ እንኳን ማየት አይፈልጉም፡፡ በአፍ ግን ሙስናን ከበቂ በላይ ይረግሙታል፡፡

ለምሳሌ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል በተለምዶ ሥነ ምግባር መኮንን የሚባሉ አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሁል ጊዜ በተቋም አመራር ስሞታ ያቀርባሉ፣ አያግዙንም፣ አይሰሙንም፣ አይበቃንም  የሚሉ ስሞታዎችን በተደጋጋሚ ያሰማሉ፣ ከቦታችን ዝቅ ተደርገናል፣ ዕቅዳችንን ይሰርዝብናል፣ አያቀርብልንም ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በለውጥ ተኮር አመራር በተሾሙ ሰዎች ላይም ይህ ስሞታ በስፋት ይሰማል፡፡ ለምን ይመስላል ይህ ክፍል የተቋም አመራር ሊያገኝ ለሚገባው ጥቅም መንገድ ዘጊና እንቅፋት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እዚህ ላይ ሥነ ምግባር መኮንኖችን የሚያበቁና በትክክል የሚደግፉ ትክክለኛ ዜጋ የሆኑ ሹመኛ አመራሮች እንዳሉ ሳንዘነጋ፡፡ ለእነሱ ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተቋማት ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን እንዲሻሻሉ እየሠራው ነኝ ይላል፣ ሰሚ እያገኘ አይደለም፡፡ የጥናት ሥራ አልሳካ ሲለው ደግሞ ለምን ተቋማት በራሳቸው ሙስናን ለመከላከል አይንቀሳቀሱም ብሏል፣ አንዳንዶች ተቋማት እየሠራን እያሉ የእውነት ይሁን የውሸት የአፈጻጸም ሪፖርት ይልኩለታል፣ ነገር ግን የተቋሞቻቸው አገልግሎት አሰጣጥ ግን ዜጎችን እያረካ አይደለም፡፡ ለሦስት ዓመት በሙሉ ለዕቅድ ትግበራ እየተዘጋጀን ነው እያሉ ያሉት ተቋማት ቁጥር ደግሞ በጣም ይበዛል፡፡

ኃያላን ተቋማት ደግም አንተ ማነህ ያሉት ይመስላል፡፡ ለሦስት ዓመታት ስትራቴጂውን ለመሥራት ፈቃደኞች አይደለም፡፡ ኮሚሽኑ ለሥነ ምግባር ሥልጠና ጥሪ ሲያቀርብ በተደጋጋሚ አንድ ሰው ብቻ ይልካሉ፣ ወይም ለተቋሙ ምንም አይፈይድም የሚሉት ሰው መርጠው ይልካሉ፡፡ አመራሩን ላሠልጥን ካለም በጣም ሥራ ስለሚበዛብን የሚል ሰበብ እያቀረቡ ሊገኙ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ሀብታቸውን አስመዝግቡ ሲላቸው ላለማስመዝገብ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም፡፡ ምክንያት እየፈጠሩ ጊዜውን ያራዝሙታል፡፡ አሁን አሁን ኮሚሽኑ ወደ ተቋማቸው አይድረስብን የሚሉ ተቋማት ብቅ ብቅ ማለት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የተቋሙ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል እንዳይረብሸን በሚል ዕሳቤ ከተቋሙ በራቀ ቦታ ላይ ቢሮ ተከራይተው አስቀምጠው፣ አገሪቱን ለብጥብጥ የሚያነሳሱ ሪፖርቶችን በምክር ቤትና በሚዲያ ሲያስተላልፉ ይስተዋላሉ፡፡ ዋና መሪው በዓመት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አግኝተናል ሲል፣ ይህን የሚያስተባብረው የተቋም ኃላፊ ደግሞ ምክር ቤት ቀርቦ ያለን ዶላር ለመድኃኒትነትና ለነዳጅ ግዥ ብቻ ነው ይላል፡፡ መቼም የማይሰማ የለም፡፡ ጉድ ነው፡፡

በመንግሥት ተቋማት የዕቅድ አፈጻጸም የሚገመግመው የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲት ሪፖርትንም ይገመግማል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ የኦዲት ግኝት በማምጣት ረገድ ያለው ክፍተት እንደጠበቀ ሆኖ፣ በአንድ ተቋም ላይ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የአሠራር ብልሹነትን የሚያሳይ የኦዲት ሪፖርት ያቀርባል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም በተመሳሳይ በአንድ ተቋም ውስጥ የአሠራር ብልሹነት መኖሩን በተደጋጋሚ ይሰማል፣ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ተገቢ ዕርምጃ ሲያስወስድ ግን አይታይም፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአንድ ተቋም ውስጥ የአሠራር ብልሹነት የፈጠረው ከፍተኛ አመራር በሌላ ተቋም ውስጥ ሌላ አመራር ሆኖ ይመደባል፡፡ ካልተመደበ የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ይሆናል፡፡ ቆይቶ ደግሞ አንድ አገር አምባሳደር ሆኖ ይሄዳል፡፡ መታደል ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጮማ ዘመድ አለው፡፡ ጮማ ዘመድ እያለው ለምን ይወድቃል?

ይኼን በምሳሌ ላንሳ፡፡ አንድ ሚኒስትር የነበረ የአገሪቱን ወርቅ ሲያዛርፍ ስለነበር ከቦታው ተነስቶ ብዙ ፕሮጀክቶች ወዳለበት ሌላ ተቋም ሚኒስቴር ሆኖ ተመደበ፡፡ በዚህም አፋር ክልል ተንዳሆ ፕሮጀክትን ጨምሮ ብዙ ፕሮጀክቶችን ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ቆይቶ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ሆነ፡፡ ቀጥሎም የውጭ አገር አምባሳደር ሆነ ተመድቦ ሄደ፡፡ ይህ ሰው በአመራር ዘመን በመራቸው ዘመናት ራሱ ተጠቅሞ ሌሎችንም ጠቅሟል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ወደ መቀመቅ ውስጥ እንድትገባ አድርጓል፡፡ ማንም ጠያቂ አልሆነም፡፡ ጮማ ዘመድ ስላለው ብቻ ኃላፊነትን እንደ እንቁራሪት እየዘለለ እየተጠቀመ ኖሯል፡፡ ሰውዬው ፀረ ሙስና ኮሚሽንን እንደ ጠላቱ ነበር የሚያይ የነበረው፡፡ እሱ ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሲያይ የነበረው ዕይታ አሜሪካ እንኳ ቢላደንን እንደ እሱ አይታየውም፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲፈርስ ተመሳሳይ ጀሌዎች ጭምር አስተባብሮ የሚፈልገውን አድርጓል፡፡ ሥራውን ከሚሠራበት ሕንፃ አስወጥቷል፡፡ ተሳክቶለታል፡፡

በእርግጥ ከጉምሩክና ከፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራና ክስ ሥራ እንዲወጣ ሲደረግ፣ የአገሪቱ አንዳንድ ሀብታሞች ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በቅርቡ አንድ ባለሀብት ነኝ ባይ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባዘጋጀው መድረክ ላይ፣ አትድረሱብን እንኑርበት ሲል በመስማቴ ግርምትን ፈጥሮብኛል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ኮንቬሽን ፈራሚ ስለሆነች በግሉ ዘርፍ ላይ ያለውን ሙስና መከላከልና መዋጋት ግዴታ አለባት፡፡ የምርመራና ክስ ሥራ ከተቋማቱ የማስወጣቱ ሥራ የሠራው ሰው ደግሞ በነበረበት ክልልና አዲስ አበባ ውስጥ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ ሲሆን፣ በትዕዛዝ እንዳይከሰስ ታግዶ እያለ አሁን ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ነው፡፡

ቀጥሎ የፀረ ሙስና ትግል ላይ የፐብሊክ ሠራተኞች ሚና እንየው፡፡ ከፐብሊክ ሠራተኞች ውስጥ አንዱ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል አንዱ ነው፡፡ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ደግሞ አዲስ አበባ አስተዳደር የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል ላይ ያለውን አቋም ለጊዜው በቂ ማስረጃ ስላልተገኘ ወደ ፊት በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ ይህን ክፍል እንዳይጠናከር በአንዳንድ ተቋማት አመራሮች የሚደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የሚመደበው ሰው ኃላፊነትን ለመወጣት ያለው ብቃትና ክህሎት በጣም ውስን መሆን፣ በተቋማት ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲበራከት እያደረገ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ተቋሙን ከሙስና ጥቃት የማይከላከሉ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች አሉ፡፡ ሌላው የፐብሊክ ሠራተኛ በቤት ኪራይ ችግር የሚሰቃይ፣ የትራንስፖርት ችግር የሚያንገላታው (ለመንግሥት ሠራተኛ ብቻ በነፃ የሚሰጠው ትራንስፖርት ንጋት ላይ መውጣትን የሚጠይቅ ስለሆነ ምሬቱ ያው ነው)፣ የዕቃ ዋጋ በእየቀኑ ወደ ላይ እያሸቀበ የሚያሰቃይ፣ ቢሮ መጥቶም ምሳውን ሳይበላ የሚውል እንደ ትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም የሚያስፈልገው ከመሆኑም በላይ፣ በፌስቡክ በሚተላለፍ የመርዘኛ መልዕክቶች አዕምሮን አሳብጦ ማታ ወደ ቤቱ የሚሄድ ነው፡፡

በተቋማት ውስጥ ግንባር ቀደም የሆኑ አመራሮችና ሠራተኞች የሚፈልጉትን ለመሥራት እንዲያመቻቸው ለሠራተኞች ፈጣን ብሮድባንድ ኢንተርኔት ያስገቡላቸዋል፡፡ በየኮሪደሩ ፈጣን ዋይፋይ ይገባላቸዋል፡፡ ሞኙ አብዛኛው የፐብሊክ ሠራተኛ ፌስቡክና ዩትዩብ ላይ ተጠምዶ ይውላል፡፡ ዋናዎቹ በግዥ አፈጻጸም ላይ ከ100 ብር እስከ ሚሊዮኖች ብር ድረስ ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ ይዘርፋሉ፡፡ በዚሁ ጉዳይ መንግሥት በራሱ መረጃ ደኅንነት በመከታተል እየወሰደ ያለው ዕርምጃ በጣም የሚያስመሰግን ነው፡፡ ለዚህ መንስዔ የሚሆነው በኢትዮጵያ አመራር ላይ ከሚመደቡት ሰዎች አንዳንዶቹ ባለ ራዕይ ሆነው ተቋምና አገርን ለማሳደግ ሳይሆን፣ በቅድሚያ ከመንግሥት ዘመናዊ ቤትና መኪና ካገኙ በኋላ በሌብነት ሀብት ለማካበት አቅደው ስለሚንቀሳቀሱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሙስናና ወንጀል ይፈጽማሉ፡፡ ለዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት ተቋሙን ከማሳደግ ይልቅ፣ የራሳቸውን ኑሮ ለማመቻቸት ተግተው ይሠራሉ፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች ደግሞ እንዲህ በከፍተኛ አመራር ሁኔታ ላይ የሚፈጸሙ ሙስና ወንጀሎችን በቅርበት በመከታተል ከመታገል ይልቅ፣ እነሱም በአቅማቸው ለራሳቸው እንዲመቻቸው በተቋሙ በሚያጋጥመው የአቅርቦት ችግሮች፣ የተሽከርካሪ፣ የኮምፒዩተርና የመዝናኛ ክበብ እጥረት፣ የውኃና የመብራት መጥፋትን እያነሱ በተደጋጋሚ ያላዝናሉ፡፡ የመደበኛ የሥራ ሰዓትን አርፍደው ይገባሉ፣ ቀድመው ከቢሮ ይወጣሉ፡፡ ማዳመጫ ጆሮአቸው ላይ አድርገው ዩቲዩብ ሙዝቃ ይሰማሉ፣ በፌስቡክ ላይ የሚለቀቁ መርዘኛ መልዕክቶችን ሲያነቡ ይውላሉ፡፡ ጋዜጦች ላይ የክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎች አንብበው የመሥሪያ ቤቶችን አድራሻ ሲፈላልጉ ይውላሉ፡፡ ሲቪ አዘጋጅተውና ከተቋሙ የድጋፍ ደብዳቤ አጽፈው የመንግሥት ተሽከርካሪ ተጠቅመው በተቋማት ይበትናሉ፡፡ የውድድር ፈተና ተፈትነው ካለፉ ይለቃሉ፡፡ ዕድሜአቸውን ከተቋም ተቋም እንደ ፌንጣ እየዘለሉ ይጨርሳሉ፡፡ በገቡበት ተቋም ሁሉ መንግሥት ለምን ደመወዝ አይጨምርም እያሉ ሲቆዝሙ ይውላሉ እንጂ፣ ተቋሙ ውጤታማ ሆነ አልሆነ ጉዳያቸውም አይደለም፡፡ እንዲህ ሲባል ባለራዕይ ሆነው የተቋምን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት ሌት ተቀን የሚጥሩ አመራሮችና ሠራተኞች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አሉ ነገር ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡

ከተቋም ተቋም የሚዘሉ ሠራተኞች ተቋሙ ውስጥ ያሉትን የለውጥ መሣሪያዎችለ፣ ዕውቀትና ክህሎትም መያዝ አይፈልጉም፡፡ በሥራው ላይ ዕውቀትና ክህሎትን ማሳደግ አይፈልጉም፡፡ መንግሥትንና የተቋሙን አመራር ሲቦጭቁ መዋል ልማዳቸው ነው፡፡ ደግሞም ለሐሜት በጣም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ዜጎች በተቋማት የሚሠሩ የሙስና ወንጀል ለማወቅ በጣም ሩቅ ናቸው፡፡ የተቋሙን ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሙ ተብለው እንኳ ሲጠሩ፣ የተቋሙን አመራር አሞግሰውና በራሳቸው ላይ የደረሰ እንግልት ካለ ብቻ አውርተው ምሳቸውን በልተው፣ የሚሰጣቸውን የትራንስፖርት አባል ይዘው ሹልክ ይላሉ፡፡ ተመልሰው አያስቡም፡፡ ይህም ለተቋም በጀት ብክነት እንጂ የሚያለማ አይደለም፡፡ የሚያቀርቧቸው የሙስና ወንጀሎችም ቢሆኑ በአብዛኛው ጥቃቅን ናቸው፡፡ አገልግሎት ፈልጌ ሄጄ ጉቦ ተጠየኩ፣ የእኔ መሬትና ቤት ለእከሌ በሕገወጥ መንገድ ተሰጠ፣ እከሌ የሚባል ሠራተኛ ተቋሙንና አመራሩን ተጠቅሞ እንደ ልቡ ይኖራል፣ እከሊት የተቀጠረችው በዘመድ ነው፣ ለከፍተኛ አመራር ወይም ለሰው ሀብት ሥራ አመራር ዘመዱ ነች፣ እከሌ የአክሲዮን ገንዘብን ዘረፈ፣ እነዚህና የመሳሰሉት ጥቃቅን የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን ከማቅረብ ውጪ አገርን የሚጎዳ የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ፣ ለማወቅ የሚችሉበት መንገድም ስለሌላ ጥቆማ ለማቅረብ አይችሉም፡፡ በአብዛኛው የሚቀርበው ሙስና ወንጀል ከራስ ጥቅም የተያያዘ ስለሆነ ፋይዳው እምብዛም አይሆንም፡፡ መርማሪዎችም የቀረበውን ጥቆማ በሙሉ በትክክል በመመርመር ለውጤት ሲያበቁ አይታይም፡፡ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ደግሞ የመንግሥት ተቋማት መረጃ ለሚዲያና ለዜጎች ዝግ በመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋም መረጃ በጓጉንቸር ቁልፍ የተቆለፈ ስለሆነ ዜጋው መረጃ ማግኘት አይችልም፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ጉዳይ ነው፡፡ በአገራችን ማኅበረሰብ አቀፍ ሚዲያን ሳይጨምር ከ21 በላይ የቲቪና ከ15 በላይ የሬዲዮ ሚዲያዎች አሉ፡፡ ብዛት ያላቸው ጋዜጦችና መጽሔቶችም አሉ፡፡ ሚዲያዎች ብዙውን ጊዜ የሚለፉት ለአገር ሳይሆን፣ የሚነውጥ ዘገባ ላይ ትኩረት አድርገው ስለሚሠሩ በአገር ልማት ግንባታ ላይ ያላቸው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በእርግጥ በጣም ጥቂት የሆኑ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያዎች ገንቢ የሆኑ የልማት ዘገባዎች እንደሚሠሩ ይታወቃል፡፡ በተለይም በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ እስር ቤት ገባ ከተባለ ተቀባብለው ይዘግባሉ፡፡ ከዚሁ ውጪ የዜጎችን መልካም ሥነ ምግባር ለማሳደግ በሚያግዙ ሥራዎች ላይ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ ሌቦች ጋዜጠኞችም አሉ፡፡ ይህንን እንድዘግብ ከፈለግክ ገንዘብ ክፈለኝ የሚሉም እንዳሉ ጸሐፊው በመረጃ ጭምር ያውቃል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች የሙያ ሥነ ምግባር ያልተላበሱና ከፍተኛ ሙስና ወንጀል ከሚፈጽሙ የመንግሥት ኃላፊዎች ለይተን የማናያቸው ናቸው፡፡፡ ሚዲያዎች አራተኛው መንግሥት የሚባሉ ስለሆኑ በእየ ተቋሙ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ፈልፍለው በማውጣት ለዜጎች ማቅረብ ቢችሉ፣ እንደ ስፖርቱ ሁሉ የመንግሥት ተቋማት ለዜጎች መስጠት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እየሰጡ ነው የሚለውን ርዕስ ይዘው በትክክል መሥራት ቢችሉ ኖሮ፣ ሌባ የመንግሥት ኃላፊዎች ቢያንስ እጃቸው ያጥር ነበር፡፡

የፌስቡክ አክትቪስቶችም ዘር፣ ሃይማኖትንና ፖለቲካ መነሻ በማድረግ ዜጎችን እርስ በርስ የሚያጋጩ ተልካሻ ዘገባዎችን፣ በተለይም የግለሰቦችን ሰብዕና የሚነኩ ነገሮችን ከመጻፍ ይልቅ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ምን እንደሚመስል፣ ተቋማት መስጠት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለዜጎች በቅልጥፍናና ውጤታማ በሆነ መንገድ እየሰጡ ስለመሆናቸው፣ የትኛው ተቋም የመንግሥት ኃላፊዎች የሙስና ወንጀል እየፈጸሙ ሀብት እያካበቱ ስለመሆናቸው፣ የየተቋሙን ሠራተኞችንም ሆነ ተገልጋዮችን በመጠቀም ማጋለጥ ቢጀምሩ ኖሮ የመንግሥት ሌቦች እጃቸው በከፍተኛ ሁኔታ ያጥር ነበር፡፡ በተለይም በቂ የገቢ ምንጭ ሳይኖር በከፍተኛ ወጪ የሚዝናናውን፣ ገቢ ሳይኖር ቤት የሚገዛውን፣ መሬት የሚዘርፈውን፣ በማስፋፋት በትዳር ላይ የሚማግጠውን፣ በመንግሥት ንብረት የሚነግደውን ሌባ ማጋለጥ ቢችሉ ኖሮ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ የዜግነት ኃላፊነት ተወጥተዋል ለማለት ያስችላል፡፡ ስለዚህ የሲቪል ማኅበራት በመንግሥት ሴክተሮች ስለሚፈጸመው ሙስና በቂ ግንዛቤ በመያዝ ዜጎች በፅናት እንዲታገሉ ግንዛቤ መፍጠር፣ ተቆጣጣሪ ተቋማት የሙስና መከላከልና መዋጋት ሥራ በተበታተነ ሁኔታ ሳይሆን፣ ተቀናጅተው በትጋት መሥራት፣ አገሪቱን የሚመራው የለውጥ መንግሥትም በሙስና ወንጀል ላይ ያለውን አቋም በግልጽ በማስቀመጥ የሚመራቸው ተቋማት ውስጥ ሹመኞች ሙስናን ከልብ ስለመጠየፋቸው አመላካች የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ግምገማ በማካሄድ ወቅታዊ መፍትሔ መስጠት፣ ሚዲያዎች ሙስናን ከልብ በፅናት መታገል፣ ዜጎች በአገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የሚሰጡትን የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ሥልጠና መነሻነት በቂ ግንዛቤ በመያዝ፣ ሙስናን በንቃትና በትጋት መታገልና ማጋለጥ ቢችሉ በአገራችን እየተባባሰ ያለው የሙስና ወንጀል ሊቀንስ ይችላል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

ፈጠሪ ኢትዮጵያን ይበርካት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ