Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥት ኃላፊዎችን ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአንድ ጣሪያ ያገናኘው ዓውደ ርዕይ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፈርኒቸር ቤተ ውበትና ግንባታ አጨራረስ በአገራችን በኢትዮጵያ ብዙ መሥራት እየተቻለ ያልተሠራበት ዘርፍ መሆኑን ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በመንግሥት ደረጃም ከአገር በቀል አምራቾች ከመግዛት ይልቅ ከውጭ አገሮች በማስመጣት ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2018 የአሥር ቢሊዮን ብር የፈርኒቸር ግዥ የፈጸመ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች የገዛው 20 በመቶ ያህሉን ነው፡፡ ከሚያዝያ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የቆየው የመጀመርያው የፈርኒቸር ቤተ ውበትና ግንባታ አጨራረስ ዓውደ ርዕይም ይኼንን ታሳቢ በማድረግ የአገር በቀል ድርጅቶች አቅማቸውን እንዲሁም አማራጮችን ለመንግሥት የሚያሳዩበትን መድረክ ማመቻቸታቸውን አቶ አክሊለ በለጠ የሻክረክስ ንግድና ኢቨንት ማኔጅመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

ዓርብ ሚያዝያ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ የተካሄደው የፓናል ውይይት ላይም አቶ ሳሙኤል ሃላላ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ናትናኤል አሰፋ በመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ፣ አቶ ዓለማየሁ ገብረየስ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ፣ ወ/ሮ ቤዛዊት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ተወክለው የመጡ ሲሆን፣ በፈርኒቸር፣ በቤተ ውበትና ግንባታ አጨራረስ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ባለሙያዎችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይም በሙያው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ለመንግሥት ተወካዮች ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ፣ በ2009 ዓ.ም. ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች አምራቾችን በአንድ መድረክ እንዲገናኙና እንዲሠሩ ለማስቻል በሚደረገው ሒደት ውስጥ ይህን ዓውደ ርዕይ ማዘጋጀታቸውን አውስተው፣ በወቅቱ ግሩም ሊባል የሚችል ሥራ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ይህንኑ ለመድገም ዕቅድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል ሃላላ እንደ ትልቅ ችግር ያነሱት የአማካሪዎችንና የኮንትራክተሮች አለመግባባት ነው፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ ያነሱት ባለቤቶችን ቀጥታ ማገናኘት ነው፡፡

‹‹የመንግሥት ግዥዎች በየትኛውም ሁኔታ በሕዝብ በጀት ላይ መሠረት የሚያደርጉት በአገር ውስጥ የሚመረቱትን ምርቶች መግዛት ነው፡፡ ነገር ግን እንዳይገዙ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች እንዳይኖሩ እንደ ተቋም ከደረጃ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ደረጃዎችን እያወጣን እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ሳሙኤል አክለዋል፡፡

በአገራችን ግዥ ላይ ልዩ አስተያየት አለ ያሉት ደግሞ በመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳዳር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ የሆኑት አቶ ናትናኤል አሰፋ ናቸው፡፡ ‹‹ከውጭ አገር ተጫራቾች ጋር የአገር ውስጥ ተጫራቾች በሚጫረቱበት ወቅት እኩል ነጥብ ቢያመጡ ቅድሚያ የሚሰጠው ለአገር ውስጥ ምርት ነው፡፡ ሌላው በጨረታ ግምገማ ወቅት ለአገር ውስጥ ምርቶች የ15 በመቶ ልዩ አስተያየት ይሰጣል፤›› በማለት አቶ ናትናኤል መንግሥት ለአገር ውስጥ አምራቾች የሰጠውን ዕድል አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ መድረኩ የመንግሥት ተወካዮች የአገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ፍላጎት ያሳዩበት ነው፡፡ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ባለሀብቶች ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲያዩም ያመላከተ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች