Wednesday, October 4, 2023

በብሔር ተኮር ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሚሊዮኖች ላይ የደረሱ በደሎች ሪፖርት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች በተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ ብሔር ተኮር ግጭቶች ያሉበትን ሁኔታ በአካል በመገኘት እንዲገመግም ተልዕኮ ተሰጥቶት የተዋቀረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሱፐርቪዥን (ምልከታ) ቡድን፣ ተልዕኮውን ጨርሶ ዓርብ ሚያዝያ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የሪፖርቱ የተጨመቀ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የሱፐርቪዥን ቡድኑ በተገኘባቸው መጠለያ ጣቢያዎችና ምልከታ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን መረጃ ከአራት ክልሎች አመራሮች አሰባስቧል፡፡ በዚህም መሠረት በትግራይ ክልል 111,465፣ በደቡብ ክልል 873,272፣ በኦሮሚያ ክልል 1,477,720 እና በአማራ ክልል 107,097 ነዋሪዎች ለረዥም ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው ቀዬአቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች በተለያዩ ቦታዎች ተበትነው እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎችን ከሚያስተዳድሩ አመራሮች ስለተፈናቃዮቹ መረጃ ሰብስቧል፡፡ ምልከታው በተደረገባቸው በተወሰኑ አካባቢዎች በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የተፈናቀሉ ወገኖችን መረጃ በተቻለ መጠን በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሥራ መስክና የሴቶችንና ሕፃናትን የጤና ሁኔታን በመለየት በመያዝ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት እየተረገ መሆኑ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የተከናወኑና በግጭቶቹም መንስዔ ተደርገው የሚነሱት ችግሮች የተለያየ ገጽታ ያላቸው መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች መፍትሔ ሳይሰጥ በየጊዜው ሰፊ አካባቢ የሸፈነ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ መፈናቀሉንና ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን፣ አብዛኞቹ አመራሮች መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ተፈናቅለው የመጡበትን አካባቢ በሚመለከት በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች አብዛኞቹ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎችና ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ከሁሉም ክልሎች መሆናቸውን፣ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ወሰን አካባቢ፣ በደቡብ ክልል የሚገኙት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፣ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ከሶማሌ ክልልና ከሌሎች አጎራባች ክልሎች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ከጂቡቲ፣ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ወረዳዎችና ከቤኒሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ መሆናቸውን ከየአካባቢው አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይት ለማወቅ እንደተቻለ ቡድኑ ያመለክታል፡፡

ተፈናቃዮቹ በተለያየ ሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ይሠሩ የነበሩ የከተማ ነዋሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ትልልቅ የንግድ ሥራ ያከናውኑ የነበሩ የንግድ ድርጅት ባለቤቶች፣ አነስተኛ የንግድ ሥራና የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ዜጎች፣ በተለያየ የመንግሥት ሥራ ላይ ተቀጥረው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የተለያዩ የሙያ ባለቤቶች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

የተፈናቃዮች አጠቃላይ ስሜትና የአካባቢዎቹ የፀጥታ ሁኔታ

ከሁሉም ምልከታ በተደረገባቸው ክልሎች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ‹‹ዘግናኝ የሆነ ጉዳትና እንግልት አድርሰው እንድንፈናቀል ያደረጉንና በወገኖቻችን ላይ በደል የፈጸሙብን አንዳንድ የየክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ የየአካባቢው ፖሊስና ሚሊሺያዎች በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ናቸው፤›› ሲል ቡድኑ ያቀረበው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በማከልም፣ ‹‹በየአካባቢው ያለው ሕዝብ አብረነው በሰላም ስንኖር የነበረ፣ እርስ በርስ የተጋባን፣ የተዋለድንና በደም የተሳሰርን ሕዝቦች በመሆናችን አሁንም ሕዝብ ለሕዝብ ችግር የለብንም፤›› በማለት የሚገልጹ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህንን ሕገወጥና ፀረ ሕገ መንግሥት ተግባር የፈጸሙትን የፀጥታ አካላትንና ከፌዴራል ጀምሮ ያሉ የየአካባቢው አስተዳደር አካላትን በስም ጭምር በመጥራት የነበረውን ሁኔታ ለቡድኑ መግለጻቸውን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሁሉም ምልከታ በተደረገባቸው ክልሎች በዝርዝር የደረሰውን ጉዳት አስመልክተው ሲገልጹ፣ ‹‹ባልጠበቅነውና ባላሰብነው ጊዜ በብሔራችንና የማንነት ጥያቄ በማንሳታችን ብቻ እየተለየን አሰቃቂ የሆነ የአካል ጉዳትና በዚህ ዘመን ሊፈጸም የማይገባ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶብናል፡፡ በሴት እህቶቻችን ላይ ለመግለጽ በሚቸግር ሁኔታ የፆታ ጥቃት፣ አካል ማጉደልና ግድያ ተፈጽሞብናል፤›› በማለት መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በተለይም ይህ የተፈጸመው በጉራጌ ዞን በመስቃን ወረዳ (ኢንሴኖ) እና በምዕራብ ጉጂ/ቃርጫ ወረዳ ሲሆን፣ ለዚህም ተለይቶ የተጠየቀ አካል እንደሌለ በምሬት እንዳነሱ ተጠቁሟል፡፡

በሁሉም ምልከታ በተደረገባቸው አካባቢዎች ያሉ ተፈናቃዮች፣ ‹‹በነበርንበት ቀዬ ለበርካታ ዓመታት ያፈራነውን ሀብት ንብረት ወይም ምንም ነገር ሳንይዝ ባዶ እጃችንን ወጥተናል፤›› በማለት የተዘረፉትን ንብረት ይዘረዝራሉ፡፡ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት ቁሳቁስ፣ ጥሬ ገንዘብና እንስሳት፣ እህል፣ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች፣ የቡና መፈልፈያ ማሽኖችና የቤት ቁሳቁስ ጥለው እንደወጡና ለእንግልት እንደተዳረጉ መረዳቱን ቡድኑ ገልጿል፡፡ የተዘረፈባቸውን ንብረት በየአካባቢያቸው ላሉ ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ቢያሳውቁም፣ መረጃ ቢኖራቸውም፣ እስካሁን ምንም ምላሽ ያላገኙ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የወደመባቸው ሀብትና ንብረታቸው መልሶ እንዲተካላቸው፣ የመጠቀምም ሆነ የመሸጥ፣ የመለወጥ መብታቸው እንዲረጋገጥላቸው በአጽንኦት እንደሚጠይቁ ያመለክታል፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁን ካሉበት አካባቢ አኳያ ትልቁ ያገኙት ጥቅም በሰላም ወጥቶ መግባትንና የሰላም ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን በስፋት የሚያነሱት ቢሆንም፣ ተፈናቃዮች በደረሰባቸው በደልና አሁንም እየተደረገላቸው ባለው ያልተሟላ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ እንዲሁም በቀጣይ በዘላቂነት ያለ መቋቋም ሥጋት ተስፋቸው እየተሟጠጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከባንክ ብድር ወስደው እየሠሩ የነበረ ቢሆንም አሁን የወሰዱትን ብድር መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመሆናቸው፣ ለክልሉ መንግሥትም ሆነ ለፌዴራል አስቀድመው ቢያሳውቁም ቤትና ንብረታችን በሐራጅ ለመሸጥ ባንኮች ዝግጀት እያደረጉ መሆኑን፣ አንዳንድ ግለሰቦችም ባልሆነ መንገድ ለመግዛት እንቅስቃሴና ፍላጎት ያላቸው ስለሆነ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ቡድኑ በሪፖርቱ አቅርቧል፡፡

በአብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞች በመንግሥት ክፍት የሥራ ቦታዎች የተመደቡ ቢሆንም፣ ሲመደቡ መረጃቸው ታይቶ ሳይሆን እነሱ በሰጡት ሐሳብ እንደሆነና መረጃቸውን ከነበሩበት ክልል በማምጣት ቢሞክሩም ማግኘት ባለመቻላቸው ለማሟላት ችግር የገጠማቸው መሆኑን፣ ባል ወይም ሚስት ከልጆች እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ የመጥፋትና የመለያየት ችግር ቢኖርም ለመገናኘት ያላቸው ተስፋ የተሟጠጠ መሆኑንና ምንም ዓይነት የማገናኘት ዕገዛ በማንኛውም የመንግሥት አካል አለመደረጉንም ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ለህዳሴ ግድብ ማሠሪያ የገዛነውን የቦንድ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት አልቻልም፣ ቦንዱን ከገዛችሁበት አካባቢ ውሰዱ እየተባልን ስለሆነ አሠራር ተዘርግቶልን ገንዘባችንን ለችግራችን ለማዋል እንድንችል ቢደረግልን?›› የሚል ጥያቄ እንደሚያነሱ፣ እንዲሁም የሚዲያ አካላት በዋናነት የፌዴራል ሚዲያ ችግራቸውን ለኅብረተሰቡ በማሳወቅና በማስገንዘብ በኩል ባለመሥራቱ በቅሬታ እንደሚያነሱ ያመለክታል፡፡ ‹‹በመንግሥት ደረጃም ዕውቅና አልተሰጠንም፣ ምንም ዓይነት ትኩረት አላገኘንም፣ የፌዴራል መንግሥት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው እየሠራ ያለው፣ ሚዲያዎች ብሔርን ከብሔር፣ ሕዝብን ከሕዝብ በሚያቃቅር መንገድ ሲሠሩ ፓርላማውና መንግሥት ሊቆጣጠራቸው አልቻለም፤›› በማለት ወቀሳ መሰንዘራቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ ‹‹ከተጠለልንበት ወደ ቀድሞ ቀዬአችን ስንመለስ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቃርጫ ወረዳ ሄደን ቤት ንብረታችንን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ድንኳን ውስጥ እንድንቀመጥ ተደርገናል፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ አልተደረገልንም፡፡ የሚመጣውን ሰብዓዊ ድጋፍ ድርሻችሁን ከደቡብ ስለወሰዳችሁ አትወስዱም እንባላለን፡፡ በአካባቢው ወጣቶችና ታጣቂዎች መሬታችሁን ለጠበቅንበት እየተባለ ክፍያ እንድንከፍል ተደርገናል፡፡ በተቃጠለው ቤታችን ላይ የቃርጫ ከተማ ማዘጋጃ መንገድ አውጥቶበታል፡፡ የቀረውም ለጉጂ ተወላጆች ተሸንሽኖ እየሰጠብን ነው፡፡ ንብረታችን እንዲዘረፍ ይደረጋል፡፡ ለአካባቢው የአስተዳደር አካላት አቤቱታ ስናቀርብ መልሰው ወደ ዘረፉን አካላት ይልኩናል፤›› ማለታቸውን ቡድኑ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በቅርቡ በቃርጫ ወረዳ ጭጋ ቀበሌ በ20 አርሶ አደሮች የቡና ማሳ ላይ እሳት እንደተለቀቀባቸው፣ እርሻቸውን እየተቀሙና ለስታዲየም ተብሎ በእርሻቸው ላይ የሚገኙ አትክልቶች እየተመነጠሩ መሆኑን፣ ያመረቱትን ምርት ዋጋ በማውጣት ቡና በሁለትና በሦስት ብር እንዲሸጡ የሚገደዱበት ሁኔታ መኖሩን፣ ቤታቸው ያልፈረሰባቸው ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ለቤቱ ዋጋ በማውጣት እንዲከፍሉ መደረጉን ሥራውን በቅርበት የሚከታተሉ አመራሮች ዕለቱን ማስረዳታቸውን ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም በምዕራብ ጉጂ፣ በመስቃን፣ በማረቆ፣ በመሎ ኮዛና በባስኬቶ እስካሁን በአካባቢው ተኩስ፣ ዘረፋ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ዜጎች የሚገደሉበት ሁኔታ መኖሩንና አስከሬናቸውን ለማንሳት ባለመቻሉ እስከ አምስት ቀናት ቆይተው በመከላከያ መነሳቱን፣ በጉጂ ዞን የታጠቁ ኃይሎች መኖራቸውንና ችግሩን ለመፍታት በመከላከያ የሚከናወን ኦፕሬሽን ቢኖርም የመንግሥት መዋቅሩ ስለሚደብቃቸው ችግሩን ለመፍታት አለመቻሉና በወቅቱ ዜጎችን ሲያፈናቅሉ የነበሩ የአስተዳደር አካላት፣ አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች አሁንም በኃላፊነታቸውና በሥራቸው ላይ በመሆናቸው ለመመለስ ሥጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

በአካባቢው በሰባት ካምፖች ኦነግ ለተመላሽ ሠራዊቶችና ለሌሎች አካላት የሚሊሻ ሥልጠና እየሰጠ እንደሆነ በፌዴራል መንግሥት ሪፖርት ቢደረግም የተወሰደ ዕርምጃ አለመኖሩን፣ በቃርጫ ወረዳ በተጠለሉ ተፈናቃዮች ላይ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ድብደባ የተፈጸመባቸው መሆኑንና የአካባቢው አመራሮችም ችግሩን ለመፍታት ተባባሪ አለመሆናቸውን ከተፈናቃዮች መረዳቱን ቡድኑ ገልጿል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕርዳታ ለእኛም ሊሰጠን ይገባል በማለት ዕርዳታ ጭነው የሚያልፉ መኪኖችን የመከልከል አዝማሚያ መኖሩን፣ በሁለቱ ክልሎች ችግሩን ለይቶ ከመፍታት ይልቅ መሳሳብ በመኖሩ፣ ጉዳዩን እየገመገሙና እያረሙ ባለመሄዳቸው ችግሮች እየሰፉ መምጣታቸውን ከተፈናቃዮች እንደተገነዘበ ገልጿል፡፡

በመስቃንና በማረቆ በግጭቱ በሁለቱም ወገን ለሞቱ ዜጎችና ለወደመ ንብረት መንስዔ የሆኑና ግጭቱ እንዲከሰት ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት ማለትም ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አንዳንድ አመራሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶችና የፀጥታ ኃይሎች በሕግ ተጠያቂ ባለመደረጋቸው አሁንም ግድያ፣ ቤት ማቃጠልና ዘረፋ እንዳለና በስምም ጭምር የሚገለጽ መሆኑ፣ እንዲሁም መስከረም 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በተፈጠረው ግጭት ችግሩን የፈጠሩ አካላትን በሕግ ተጠያቂ እንዲደረጉ ክስ ከተመሠረተ በኋላ የክልሉ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ክሱ እንዲቋረጥና ጉዳዩ በሽምግልና እንዲፈታ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ክስ ተቋርጦ ለ29 ጊዜ ሽምግልና ቢቀመጡም፣ ችግሩ ሊፈታ አለመቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ እኛ ክስ ስናቋርጥ ማረቆዎች እንዲከሱን ተደርጓል በሚል ከኅብረተሰቡ ሰፊ ቅሬት መነሳቱ፣ እንዲሁም በመስቃን ወረዳ በዞኑና በወረዳ አመራሩም ሆነ በኅብረተሰቡ ‹‹ያስገደለን ደኢሕዴን ነው፣ የክልሉ መንግሥት እንድንፈናቀል አድርጎናል፣ በእኩል ዓይን አያየንም፣ በክልል የፍትሕ አካላት ገለልተኛና ፍትሐዊ አገልግሎት እያገኘን አይደለም፣ ክስ የመሠረትንበትንና ያስመሰክርንበትን ሰነድ ጠፋ እንባላለን›› ማለታቸውንና አሁንም ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች እየተለዩ የሚመቱበትና የሚታሰሩበት ሁኔት መኖሩን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ተፈናቃዮቹ ከዞን እስከ ፌዴራል ያሉ የጉራጌ ዞን ተወላጅ አመራሮች ተፅዕኖ እያደረጉባቸው እንደሆነ በስምም ጭምር እንደሚጠቅሱ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ ‹‹በሁለቱም ወረዳዎች የክልሉ ልዩ ኃይል ጫና እያደረሰብን ነው፡፡ ልዩ ኃይሉ እያለ ነው የተገደልነው፡፡ ቤታችን ሲቃጠልም እያየ ዝም ይላል፤›› የሚል ቅሬታ መኖሩ፣ በሁለቱም ወገን አንዱ ወደ ሌላው ወሰን ገብቶ ግብይት መፈጸም የሚቻልበትም ሆነ ነፃ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉ የሚነገር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ከአመራሩም ሆነ ከኅብረተሰቡ በመናገራችን እንመታለን፣ እንታሰራለን፣ ዕርምጃ ይወሰድብናል በማለት የሚነሱ ሐሳቦች መኖራቸውን፣ ቡድኑ በሚያነጋግርበት ወቅት ሐሳባቸውን በነፃነት ለመግለጽ ሥጋት እንዳላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሁለቱም ወገን በማንኛውም ሰዓት መልሶ ወደ ግጭት ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን፣ ከአመራሩ ጀምሮ በክልሉ መንግሥት፣ በድርጅቱና በፀጥታ መዋቅሩ ላይ እምነት እንደሌላቸው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ከክልሉ ጋር በተደረገው የመውጫ ውይይትም ችግሩ እንዲፈታ ለዞኑ ኃላፊነት እንደተሰጠ ቢገለጽም፣ የሱፐርቪዥን ቡድኑ ዞኑ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት እንደሌለው አመልክቷል፡፡

በከንባታ ጠንባሮ ዞን በአንጋጫ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ ‹‹በ1996 ዓ.ም. በምግብ ዋስትና ፕሮግራም በሰፈራ ወደ ቦታው እንድንሄድ ስንደረግ ለካፋ ዞን ነዋሪዎች እንድንከላከልና አጥር እንድንሆን ተደርገናል፡፡ በጊዜው ግጭቶች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ለክልሉ እያመለከትን ምላሽ ባለመሰጠቱ ግጭቱ የከፋ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል፤›› በማለት እንደሚገልጹ፣ ችግሩ በተከሰተበት አካባቢው ያሉ የካፋ ዞን የቀበሌ አመራሮች ‹‹ለራሳችን መጠበቂያ ትጥቅ ስጡን ብለን ስንጠይቅ በማን መሣሪያ ማንን ልትገድሉ ነው በሚል ተከልክለናል፤›› ሲሉ እንደሚከሱ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ስለግጭቱ ሲገልጹ፣ ‹‹የሕዝብ ግጭት የለም፣ ግጭቱን እየፈጠረ ያለያየን አመራሩ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት የለፋንበት ንብረታችን ወድሟል፡፡ በማሳ ላይ የሚገኙ ሰብላችን ተቃጥሏል፡፡ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካታ በደሎች ደርሰውብናል፡፡ እኩል ፍትሕ አላገኘንም፡፡ የመሄድ ፍላጎት ቢኖረንም ችግሮቹ ባልተቀረፉበትና ሰላም ባልተረጋገጠበት አሁንም ተመለሱ እንባላለን፣ ዋስትናችን ምንድነው?›› በማለት እንደጠየቁ ያስረዳል፡፡ ‹‹ግጭቱን የፈጠሩና የሚያባብሱ ጥቂት አጥፊዎች የማይጠየቁበት ሁኔታ በመኖሩ ለጥቃት ተዳርገናል፡፡ አካባቢውም ከሥጋት ነፃ ሊሆንልንና አብሮ የመኖር ባህላችንንና እሴቶቻችንን አጠናክረን እንድንቀጥል የመከላከያ ሠራዊቱና የአካባቢው አመራር ከጎናችን እንዲቆም ሊደረግልን ይገባል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ መንግሥት ሊያመጣልንና ሊያረጋግጥልን ይገባል፤›› ማለታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ ‹‹ወደ አካባቢያችን ብንመለስም የምንመገበው፣ የምንጠለልበትና የምንለብሰው የለንም፡፡ እኛ አንመለስም እዚሁ በዘላቂነት የምንቋቋምበት ሁኔት ይመቻችልን፡፡ በአካባቢውም ዘላቂ የሆነ ሰላም አልተረጋገጠልንም፡፡ አሁንም ፍርኃት አለን፡፡ የተለያዩ የመንግሥት አካላት በየጊዜው እየመጡ ያዩናል እንጂ ላነሳናቸው ጥያቄዎች መልስ አይሰጡንም፤›› በማለት እንደ ከሰሱም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ በተጨማሪም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሁንም አልፎ አልፎ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለጹ የፀጥታ ችግሮች፣ ማለትም የሰው ሕይወት መጥፋትና ተኩስ በመኖሩ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ሥጋት እንዳላቸው እንደሚገልጹ ተጠቅሷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቃዮች በደረሰባቸው አሰቃቂ የቤተሰብ ሞትና እንግልት እጅግ የሚያዝኑና የሞራል ውድቀት የደረሰባቸው መሆኑን እንደሚናገሩ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ላደረጉላቸው ዕርዳታና በጊዜ በመድረሳቸው የሚያመሰግኑ ቢሆንም፣ እነዚህ ተፈናቃዮች ለረዥም ዓመታት በአካባቢው የኖሩ በመሆናቸው ብዙ ሀብትና ንብረት አፍርተው ሌላውን ሲረዱ የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ተረጂ በመሆናቸው ከፍተኛ የሞራል ውድቀት እንደደረሰባቸውና ወደመጡበት ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም ከፍተኛ ሥጋት እንዳለባቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ብዙ ቤቶች በመቃጠላቸው መኖሪያ እንደ ሌላቸውና የቀሩትን ቤትና ንብረታቸውን ደግሞ የአካባቢው ሰዎች ሰፍረውበት እንደሚገኙ በማውሳት፣ መንግሥት መፍትሔ ሊፈልግላቸው እንደሚባ ይጠይቃሉ፡፡ ከፀጥታ አንፃርም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን ውስጥ ባለው ሰላምና ፀጥታ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው፣ ‹‹በወቅቱ የነበረው የዞን አመራርና የፀጥታ ኃይሉ ሲያስገድለን፣ ሲያሳርደንና ሲያዘርፈን የነበረ በመሆኑና አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥልጣን ላይ እያሉና አንዳንዶቹም እስከ ክልል ዕድገት ባገኙበት እንዴት መተማመን ይቻላል? አሁንም ድረስ በጽጌ ወረዳ በዘጠኝ ቀበሌዎች ውስጥ ወጣቶችን በመመልመል በድብቅ እያሠለጠኑ ናቸው፤›› በማለት ሥጋታቸውን እንደገለጹ የቡድኑ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በሁሉም ምልከታ በተደረገባቸው ክልሎች የደረሰውን በደል ከላይ በተገለጸው መንገድ ከገለጹ በኋላ፣ የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን ተከታትሎ በአጭር ጊዜ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ ተስፋ በቆረጠ ስሜት በፓርላማ በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚውና በመከላከያ ኃይሉ ላይ የሚከተለውን አስተያየት እንደሰጡ ቡድኑ አመልክቷል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደረሰብንን ችግር እያወቅችሁና እየሰማችሁ አልጠየቃችሁንም፡፡ የሕዝብ ተወካይ በመሆናችሁ አስፈጻሚውን የምትከታተሉ፣ የምትቆጣጠሩና ሕግ የምታወጡ ሆናችሁ ሕገ መንግሥቱን በመፃረር በደልና ግፍ ሲፈጸምብን ድምፃችሁን አላሰማችሁልንም፡፡ ይህንን የማታደርጉ ከሆነ ሕዝብ በሰጣችሁ ወንበር ላይ መቀመጥ ለምን ያስፈልጋል?›› በማለት ፓርላማው ባለመሥራቱ የተሰማቸውን ስሜት በምሬት እንደገለጹ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

‹‹መንግሥት በሰላም በምንኖር ሕዝቦች ላይ ዓይተነው የማናውቅ ግፍ ሲፈጸምብን ፈጥኖ ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው ዝም ብሎ ተመልክቶናል፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ያለንበትን ሁኔታ የተመለከቱ አመራሮች መፍትሔ አልሰጡንም፡፡ ይህ በመሆኑ በፌዴራል መንግሥት በእጅጉ አዝነናል፣ ተስፋም ቆርጠናል፡፡ የሕዝቦች መፈናቀል፣ ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉድለት፣ የሀብትና ንብረት ውድመትና ዝርፊያ መንስዔውን መንግሥት አጥንቶ በዘላቂነት መፍታት ባለመቻሉ፣ አሁንም ችግሩ እየቀጠለ በመሆኑ አገሪቱ ወደ ማትመለስበት የውድቀት አዙሪት ውስጥ እንደምትገባ ሥጋት አለን፤›› ማለታቸውንም ጠቁሟል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ ሕገ መንግሥቱ የሚከበርበት፣ ለዜጎች ጥበቃ የሚደረግበትና ያለ ሥጋት ተዘዋውሮ የሚኖርበት ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት፣ መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች ይህን ሁሉ በደል የፈጸሙትን፣ በግፍና በዘግናኝ ሁኔታ ሕይወት ያጠፉና የንብረት ውድመት ያደረሱትን፣ በሁሉም አካባቢዎች ለችግሩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትንና በመፈናቀሉ ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸውን አመራሮችን፣ የፀጥታ አካላትን፣ የታጠቁ ኃይሎችንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ ዕርምጃ ባለመውሰዱና ሕግ ባለማስከበሩ አጥፊዎቹ የባሰ ጥፋት እንዲያደርሱ ዕድል ሰጥቷቸዋል፣ መንግሥት የመንግሥትነት ሚናውን አልተወጣም በማለት በምሬት እንደሚገልጹ የቡድኑ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት አካላት የሚሰጡ መግለጫዎችም ሚዛናቸውን ያልጠበቁ፣ ሞራላቸውን የሚነኩና በእውነታ ላይ ያልተመሠረቱ ናቸው በማለት በመንግሥት ያላቸውን ቅሬታ እንደሚገልጹ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን በተመለከተ በአብዛኞቹ አካባቢዎች የመከላከያ ኃይል በአካባቢያቸው ከገባ በኋላ አንፃራዊ ሰላም ማግኘታቸውን ሆኖም አሁንም መከላከያ እያለ ጭምር በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እየደረሰባቸው ስለሆነ፣ ከሁሉም ክልሎች ጋር በመቀናጀት ዘላቂ ሰላም የሚያገኙበትን አግባብ ሊፈጥርላቸው እንደሚገባ መጠየቃቸውን ቡድኑ ገልጿል፡፡

የሱፐርቪዥን ቡድኑ ሪፖርቱን ካቀረበ በኋላ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ከውሳኔዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላት በቅንጅት በመሥራት በሁሉም ክልሎች ለተፈጠሩ ግጭቶች ሚና የነበራቸውን አንዳንድ የፀጥታ አካላት (ፖሊሶች፣ ሚሊሺዎችና ልዩ ኃይሎች) በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመለየት ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ቅድሚያ ሰጥተው በትኩረት መሥራት አለባቸው ሲል ወስኗል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ዜጎች ደኅንነቴን ይጠብቅልኛል የሚሉት፣ አመኔታ ያለውና ገለልተኛ የሆነ የፀጥታ ተቋም የመኖር፣ የአባላቱን አቅም የመገንባት ሥራና በሁሉም አካባቢ የሚስተዋሉ ግጭቶችን የማስቆም፣ ለግጭት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ መፍታትና ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ መከናወን እንዳለበት ቡድኑ አሳስቧል፡፡

በየመጠለያ ጣቢያዎችና በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚገኙ ተፈናቃዮች በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ ድረስ የፌዴራል መንግሥትና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ዜጎች በምግብ ምክንያት እንዳይሞቱ ለማድረግ፣ ንፁህና በቂ የመጠጥ ውኃ ማግኘት እንዲችሉ በትኩረት መሥራትና የተለየ ትኩረት የሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች በልዩ ሁኔታ ሊስተናገዱ የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

የሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ለተፈናቃዮች አገልግሎት የሚውሉ ግዥዎች በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱበትን አግባብ መፍጠር፣ በተለይ የውኃ አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ለተቋሙ ተጨማሪ ረቂቅ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንዲፀድቅ መደረግ እንዳለበት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት በመፈናቀሉ ምክንያት ከሥራ ውጪ የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ ሥራ እስከሚጀምሩ ድረስ እንደ ሌሎች ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መረጃቸው ተጣርቶ እስካሁን ያልተከፈላቸውን ደመወዝ ማግኘት እንዲችሉ መሠራት አለበት ብሏል፡፡

የዜጎችን የመኖሪያ ቤት በሚመለከት ከመጪው የክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ በተለይ የጌዴኦ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም፣ በሁሉም አካባቢዎች መጠለያ ያላገኙትን፣ በዘመድ ቤትና በኪራይ ቤት ያሉ ዜጎችን ችግር ለመፍታት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መሥራትና በየመጠለያ ጣቢያው ያሉ ተፈናቃዮች የተለያዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸት አለበት ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላትና የፍትሕ ተቋማት የዜጎችን ሰላም የማረጋገጥ፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ለማስከበር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሱ፣ ሕይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉና ንብረት ያወደሙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ ቡድኖችንና ግለሰቦችን በመለየት በአፋጣኝ ባጠፉት ጥፋት ልክ አስተማሪ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወሰድበትን፣ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎች በአስቸኳይ ፍትሕ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ፈጣን የምርመራና የችሎት አገልግሎት ሥርዓት በመዘርጋት፣ በልዩ ሁኔታና በልዩ ትኩረት ተግባራዊ ማድረግና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ዜጎች በየቀዬአቸው ያለ ሥጋት እንዲኖሩ ማድረግ አለባቸው ብሏል፡፡

እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ከተሰጠባቸው ተግባርና ኃላፊነት በመነሳትና ችግሮችን በቅደም ተከተል በመለየት፣ በአስቸኳይ ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል የተለየና የተቀናጀ ዕቅድ ይዘው ለምክር ቤቱ መላክ እንዳለባቸው፣ በምክር ቤት የተላለፈውን የውሳኔ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ በየጊዜው የተከናወኑ ሥራዎችን በጽሑፍና በአካል ተገኝተው ሪፖርት ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -