የሥራ ፈጠራ ዕድሎችን የሚያስተባብር ኮሚሽን ማቋቋሙን አስታወቀ
ስንዴ ገብስና ዘይት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ይደረጋል ብሏል
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኞ ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ ኢኮኖሚው ከዚህ ቀደም ሲል ከነበረውም እየተቀዛቀዘ መምጣቱን እንደ ገመገመ አስታወቀ፡፡
ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያካሄደውን ስብሰባ በማስመልከት በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በኩል በቀረበው የዜና መግለጫ መረዳት እንደተቻለው፣ ከ2003 እስከ 2010 ዓ.ም. በአገሪቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንደተገመገመና በእነዚህ ዓመታትም አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት በአማካይ 9.6 እንደነበር ጠቅሶ፣ ሆኖም ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት የኢኮኖሚው ዕድገት ከነበረበት 10.1 በመቶ ወደ 8.6 በመቶ ዝቅ እንዳለ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትም እየተቀዛቀዘ መምጣቱ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተገምግሟል።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ያሳየው መዋቅራዊ ለውጥም አዝጋሚ እንደሆነ ገምግሟል። መዋቅራዊ ለውጡ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ በዓመታዊ የኢኮኖሚው ዕድገት ውስጥ የግብርናው ዘርፍ የ5.7 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የ19.1 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ 10.3 በመቶ፣ ዕድገት ማስመዝገባቸውን አመልክቷል።
ይሁን እንጂ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በመፍጠር የዋጋ ንረትንም ከአሥር በመቶ በታች የማድረግ ዕቅድ ተቀምጦ ላለፉት ሰባት ዓመታት ይኸው ግብ ተግባራዊ ሲደረግ ቢቆይም፣ ‹‹ከ2003 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት የተሳካ እንዳልነበረ የገመገመው ኮሚቴው፣ በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ በአገሪቱ ባለው አለመረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ ቅነሳ የዋጋ ንረቱ 13.1 በመቶ መድረሱን›› እንደተመለከተም በመግለጫው አስፍሯል። በአገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳም የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት መቀዛቀዙን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡
እስካሁን ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ‹‹የልማት ፋይናንስ ሞዴል በብድር ላይ የተመሠረተ መሆኑንና የፋይናንስ አቅርቦት የተመደበላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ብቃት ማነስ›› ኢኮኖሚውን ችግር ውስጥ እንደከተተው ተገምግሟል ተብሏል። በመሆኑም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚወሰዱና አጭር የመክፈያና የችሮታ ጊዜ ያላቸው ብድሮች የአገሪቱን የውጭ ብድር ጫና ከፍተኛ እንዲሆን በማድረጋቸው፣ እንዲህ ያሉ የአጭር ጊዜ ብድሮች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ መደረጋቸውን ኮሚቴው አስታውሷል፡፡ ይህ ውሳኔ ከተላለፈ ቆየት ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ኮሚቴው የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ያለፉትን ዓመታት የኢኮኖሚ አፈጻጸሞች ገምግሞ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞችና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን እንዳጠናቀቀ ተገልጿል፡፡ የመንግሥትን ወጪ ውጤታማና ከገቢው ጋር የተቀራረበ ብሎም የተገደበ ማድረግ፣ የታክስ ገቢን ማሳደግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ብድር አቅርቦትን ላለመሻማት ለበጀት ጉድለት ማሟያ መንግሥት ከባንክ የሚበደረው የገንዘብ መጠን ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ከሦስት በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ እንደተጣለበትም ተጠቅሷል፡፡
‹‹የታክስ አሰባሰብን ማዘመን፣ የግብር ግዴታቸውን በማይወጡ ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ከምንጩ ማድረቅ፣ የዕዳ ጫናቸው ከፍተኛ የሆኑ ብድሮችን ማገድ፣ ቀድሞ የተወሰዱ ብድሮችን የዕዳ ክፍያ ጊዜ ማሸጋሸግ›› ወደፊት ትኩረት የሚደረግባቸው ተግባራት እንደሆኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አስታውቋል። የወጪ ንግድን በዓይነት በብዛትና በጥራት ማሳደግም የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ተጠቅሷል።
የግብርናው ዘርፍም ትኩረትና ርብርብ የሚደረግበት መስክ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ አነስተኛና ሰፋፊ የመስኖ ልማት፣ የግብርና ግብዓት ፋይናንስ አቅርቦት፣ የእንስሳት ዕርባታ ምርታማነት፣ የግብርና አመራረት ዘዴን ማሻሻል፣ የድኅረ ምርት ብክነት መቀነስ፣ የምግብ ዋስትና ሥርዓትን በተጠና መንገድ ተግባራዊ ማድረግ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ሥራዎች ትኩረት እንደሚደረግባቸው ተጠቅሷል፡፡ በእነዚህ ማሻሻያዎች መነሻነትም ‹‹በአጭር ጊዜ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ የምግብ ዘይትና ጥሬ ዕቃዎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ይገባል፤›› ብሏል። የማዕድን ምርት፣ ማኑፋክቸሪንግና ቱሪዝም ትኩረት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ዓመት ከ1.5 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ስንዴ ከውጭ በግዥ እንደሚገባ ሲገመት፣ በግብርና ግብዓቶች ግዥ በተለይም ለማዳበሪያ ግዥ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ፣ የግብርናና ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የስምንት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት አግባብ ላይ የተለየ ዲሲፕሊን መከተል፣ ሁሉንም የኢኮኖሚ ተዋናዮች በእኩል የሚያሳትፍ፣ ፍትሐዊ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የውድደር ሜዳን መዘርጋት በቀጣይ ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች ውስጥ መሆናቸውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አስቀምጧል።
ሥራ አስፈጻሚው በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የፊሲካል ፖሊሲና የወጪ ንግድ ቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎች መሆናቸውን አስታውቋል። የኢኮኖሚ ዕድገቱ ከጥራት አኳያ ያሉበትን ጉድለቶች በዝርዝር አጥንቶ፣ የሪፎርም ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የአገር ውስጥ የሥራ ፈጠራንም ሆነ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት መሠረተ ልማትን፣ በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መሠረት ያደረጉ የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያስታወቀው ሥራ አስፈጻሚው፣ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለማሻሻል የንግድና የሥራ ፈጠራን ለማሳለጥ የማሻሻያ ፕሮግራም ተነድፎ የሥራ እንቅስቃሴ እንደተጀመረም አስረድቷል። የሥራ ዕድል በሁሉም የልማት ዘርፍና በሁሉም የልማት ተዋናዮች የሚፈጠር ቢሆንም፣ ሥራውን በባለቤትነት የሚመራና የሁሉንም ተዋናዮች ሚና የሚያስተባብር ኮሚሽን መቋቋሙን ጠቁሟል።
ከኢኮኖሚው ባሻገር ሰላም የማስፈን፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት መከበር ለአገሪቱ ሕዝቦች ሁለንታናዊ እንቅስቃሴ መሠረት እንደሆኑ ያወሳው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ የኢትዮጵያን ሕዝብ ‹‹ለቅሬታ የዳረጉ በርካታ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው፣ ሕዝቡ ወደ ልማት በመመለስ በተሻለ የለውጥ መንፈስ ለመሥራት የሚያግዝ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን›› አመልክቷል።
ኢትዮጵያ በዓለም ብሎም በአኅጉር ደረጃ ተቀባይነት ማግኘቷ ያጋጠሟትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ያለው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም በልማት መስክ እንዲሳተፉ እየተደረገ በመሆኑና ሕዝቡም በፖለቲካና በልማት እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ እየተጠናከረ በመምጣቱ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለማለፍ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩ ናቸው ብሏል ተብሏል፡፡
የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች በአገሪቱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በተደራጀ መንገድ ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻች መደረጉንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጠቅሷል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚያነቃቁ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ባሻገር፣ ብክነትና የአመራር ዝርክርክነት የሚታይባቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ማስተካከል ባለፉት በአንድ ዓመት ውስጥ ከተወሰዱት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መካከል እንደሚጠቀሱም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አስታውሷል፡፡