የመጀመርያው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሆነው ለስድስት ዓመታት ያገለገሉት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ሥርዓተ ቀብር፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጉለሌ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸው ከእኩለ ቀን በኋላ ከመፈጸሙ በፊት በሚሌኒየም አዳራሽ በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት፣ ጸሎትና ዝማሬ ከመከናወኑ ባሻገር ባለቤታቸውና ልጆቻቸው፣ ባልንጀሮቻቸውና የትግል አጋሮቻቸው ንግግር አድርገዋል፡፡
‹‹ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለእምነትና ለህሊና የኖሩ ታላቅ የሕዝብ ልጅ ናቸው፤›› ይህን ኃይለ ቃል ያስተጋቡት በሥርዓተ ቀብራቸው የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቷ በዕለቱ ባሰሙት ዲስኩር፣ ዶ/ር ነጋሶ አገርን ማገልገል ምን እንደሚመስል በተግባር ያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ ትሁትና ቅን፣ ሰውን የማይለዩና የሰውን ሐሳብ ማዳመጥ የማይሰለቹ መልካም ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ዶ/ር ነጋሶ የግል ጥቅምና ሀብት ምንም እንዳልሆኑ፣ በእምነትና በጽናት እንዴት መኖር እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ፣ አገራችን አንድ ቀን አድጋና በልጽጋ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እውን ሆኖባት የምትታይ አገር እንደምትሆን ያላቸውን ተስፋ በሙሉ ልብ የሚናገሩ ነበሩ፤” ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
21 ጊዜ መድፍ በተተኰሰበት ሥርዓተ ቀብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኰንንን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ ሹማምንት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ተገኝተዋል።
ዶ/ር ነጋሶ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገበት 1983 ዓ.ም. እስከ ሽግግር መንግሥት ፍፃሜ 1987 ዓ.ም. ድረስ፣ በተከታታይ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይና የማስታወቂያ ሚኒስቴሮች በሚኒስትርነት፣ ከነሐሴ 1987 እስከ መስከረም 1994 ዓ.ም. ድረስ ለአንድ ዙር፣ ለስድስት ዓመት የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ከገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር በአቋም ከተለዩ በኋላ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ በግል ተወዳድረው ለአንድ ዙር የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ የተቃዋሚው የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበር፣ በይቀጥላልም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አመራርም ሆነውም ሠርተዋል።
ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጀው ብሔራዊ የሐዘን ቀን በቀብራቸው ማግስት ተፈጽሟል፡፡ የልብ ሕመምን ጨምሮ በገጠማቸው የጤና ዕክል ሳቢያ በ76 ዓመታቸው ያረፉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።
ዶቼ ቬሌ እንደዘገበው፣ በዛክዘን ሃውሰን ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያሉ ያረፉት ዶ/ር ነጋሶ አስከሬን፣ ከፍራንክፈርት ወደ አዲስ አበባ ከመሸኘቱ በፊት እዚያው በሚገኘው የካቶሊክ የሱስ ክርሽየ ቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ጀርመን በነበሩበት ዘመን ያከናወኗቸውን ተግባራት ተዘክረዋል፡፡
በ35 ዓመታት የትዳር ቆይታቸው አንዲት ሴት ልጅ ያፈሩት ጀርመናዊቷ አዋላጅ ነርስ ሬጂና አልበል፣ ዶ/ር ነጋሶ ሲመሰክሩም “ለኢትዮጵያውያን የሐሳብና የዴሞክራሲ መብት መከበር በጽናት የታገሉ ታላቅ ሰው ነበሩ” ሲሉም ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል::
ሚስስ አልበል በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ በሚባለው አካባቢ በመሠረቱትና “ሬይጂና የቤተሰብ የጤናና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል” በተሰኘው ተቋማቸው አማካይነትም ወላጅ አልባ ለሆኑ እንዲሁም ለችግረኛ ሕፃናትና ሴቶች የጤናና የምክር ግብረሰናይ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ተዘግቧል::
ከአባታቸው ቄስ ጊዳዳ ሶለን ከእናታቸው ከወ/ሮ ዲንሴ ሾሊ ጳጉሜን 3 ቀን 1935 ዓ.ም. ከቾ በሚባል የደምቢዶሎ መሀል ከተማ የተወለዱት ነጋሶ (ዶ/ር)፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ አግኝተዋል፡፡
የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በጀርመን፣ ፍሮቤኒዩስ የኢትኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ትምህርታቸውን (ሜጀር) ኢትኖሎጂ፣ በንዑስ (ማይነር) ደግሞ ሶሻል ሳይኮሎጂ በማድረግ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በታሪክ አግኝተዋል፡፡ ጥናታዊ ድርሳናቸውም (ቴሲስ) ‹‹የምዕራብ ኢትዮጵያ የቄለም አውራጃ ታሪክ›› በሚል ርዕስ መሥራታቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም በ1977 ዓ.ም. ያገኙት በታሪክ ሲሆን የመመረቂያ ድርሳናቸው ‹‹The history of Seyyoo Oromo of South Western Wallega Ethiopia from 1730 to 1886›› የሚል ነበር፡፡
ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበሩት ነጋሶ (ዶ/ር)፣ በጀርመን በሕክምና ላይ ሳሉ ድንገት ያረፉት ቅዳሜ ሚያዝያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡