በተመስገን ተጋፋው
ኢትዮጵያ ፋሺስት ጣሊያንን ድል ያደረገችበት 78ኛው የድል በዓል በአዲስ አበባ ሚያዝያ 27 አደባባይ በሚገኘው የድል ሐውልት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ተከብሯል፡፡
በአርበኞች ሠልፍና በወጣቶች ትርዒት በታጀበውና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ሥነ በዓል ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ድሉ የፋሺስቶችን የቂምና የበቀል ዕርምጃ ያፈረሰ፣ የኢትዮጵያውያንን ፅናት፣ አይበገሬነትና አንድነት ዳግም ያረጋገጠ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ባደረጉትም ንግግር፣ ኢትዮጵያ በጀግኖቿ አማካይነት በወራሪው ጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው ድል የሰው ልጅ ሁሉ በእኩልነት እንዲታይ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የበላይ ጠባቂ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ መሆናቸውን ያስታወሱት ልጅ ዳንኤል ፕሬዚዳንቷ የአርበኛ ልጅ በመሆናቸው በተተኪ አርበኛነት መመዝገባቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በተያያዘ ዜና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዘንድሮውን የድል በዓል ምክንያት በማድረግ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ‹‹እኔ ለአገሬ›› በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ በዋዜማው አዘጋጅቶ ነበር፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. የነበረውን የጣሊያን ወረራና የኢትዮጵያ የአርበኞች ተጋድሎ የሚዳስስ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በዳሰሳቸውም በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻው አካባቢ ጀምሮ በርካታ የውጭ አገሮች የኢትዮጵያን ግዛትን ለመንጠቅና ሉዓላዊነቷን ለመፈታተን ሙከራዎችን ማድረጋቸውን በምሳሌነት ቱርክን፣ ግብፅን፣ ጣሊያንንና የሱዳን ማህዲስቶችን በማንሳት ጠቅሰዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያን አንድነት በብርቱ የፈተነው የጣሊያን ወራሪ ኃይል እንደሆነ የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ መንግሥትንም ሆነ ሕዝብን አላስቀምጥ አላስተኛ ያለው ትልቅ ፈተናም ሆኖ ነበር፡፡ ጣሊያን ዶጋሊ ላይ በራስ አሉላ አዝማችነት ቢደመሰስም፣ ዓድዋ ላይ ድል ቢደረግም ቅኝ ግዛት የመያዝ ህልሙን ግን ጭራሽኑ አልተወም፡፡
በ1916 ዓ.ም. በጣሊያን የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በቤኔቶ ሙሶሎኒ የሚመራው የፋሺስት ፓርቲ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረም ኢትዮጵያን ለመውረር የሚያደርገውን ሒደት እንደ አዲስ ጀመረ፡፡
የወረራውም ዋና ዓላማ የጣሊያን ክብር ከፍ ለማድረግና በአውሮፓ ገናና አገር እንድትሆን በኢንዱስትሪም የበለፀገች፣ እንደሌሎች ሁሉ የአውሮፓ አገሮች ቅኝ ግዛት ያላትና የተከበረች እንድትሆን በማሰብ ነበር ሲሉ አቶ አበባው አስታውሰዋል፡፡ አክለውም ኢትዮጵያን ለመውረር ያነሳሳትም ሁለት ነገሮች መካከል የዓድዋ ድልን ለመመለስና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማሳደግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከአምስት ዓመት ተጋድሎ በኋላ የፋሺስት ጣሊያን ጦር ተደምስሶ ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ወጥቷል፡፡
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዕለቱ ባሰሙት ንግግር፣ ሚያዝያ 27 የድል በዓል እንጂ የነፃነት ቀን አለመሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ ታላቅ ድል ያበቁ የኢትዮጵያ ጀግኖች አባቶችን አደራ ለማስቀጠል አሁን ያለው ትውልድ አንድነቱን አስጠብቆ ለኢትዮጵያ ዕድገት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ፋሺስት ጣሊያን አዲስ አበባን በያዘበት ሚያዝያ 27 ቀን (1928 ዓ.ም.) በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድልን ቀን ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መበሰሩ ይታወቃል፡፡