Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሔ

ራሔል ጌታቸው የማኅበረሰብ ጤና ነርስ ናት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን በአፍሪካ የወጣቶች የአመራር ክህሎትን ለማዳበር በተመሠረተው ኢንሺዬቲቭ በኢትዮጵያ የያሊ አሉሚኒ ቻፕተር የኢንጌጅመንት ኮሚቴ ሰብሳቢ ናት፡፡ ወጣቶችን ለመርዳት በያሊ ውስጥ ያላትን ተሞክሮና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሳሙኤል ጌታቸው አነጋግሯታል፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶችን ለማሠልጠን በየቦታው ተዘዋውረሻል፡፡ እንዴት አገኘሽው?

ራሔል፡- ወጣቶች ጎበዞች፣ የመፍጠር ችሎታ ያላቸውና አዲስ ነገር ለመማር የሚጓጉ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ስፖንሰር እንዲያገኙ፣ አዳዲስ ነገሮችን እንዲያውቁ፣ እንዲታወቁ፣ እንዲሠለጥኑ፣ ጥበቃ እንዲያገኙ ክህሎታቸውንና በኢንተርፕሩነርሺፕ ላይ ያላቸውን አመለካከት በመልካም እንዲቀረጹ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀላቅለው ሲሠሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ አዳዲስ ጉዳዮች ሲመጡ ክህሎታቸውንና ሙያዊ ብቃታቸውን ተጠቅመው የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ ፕሮግራሙ ከ18 እስከ 28 ዓመት ያሉ ወጣቶችን የሚያግዝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወጣቶች ጋር ካለሽ መስተጋብር ከምታነሷቸው የተለያዩ ጉዳዮች ላንቺ ዋነኛው የቱ ነው?

ራሔል፡- ይህ አገር በችሎታ የተሞላ ዕውቀት ያለበት ነው፡፡ የጋራ ከሆኑ ችግሮች መፍትሔ ለመፈለግም ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚደፍሩ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በቂ ያልሆነ ወይም የለም በሚባል ደረጃ ላይ ለሚገኘው የገንዘብ ድጋፍም ሆነ እዚህ ግባ የሚያባል የገበያ ትስስር ዕድል በሌለበት ሁኔታ መንግሥት ላይ ትልቅ ጫና ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም ከገንዘብ ተቋማትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች አነስተኛ ንግድ ውስጥ ለተሰማሩ የገንዘብም ሆነ ጥሬ ዕቃ ማግኘት በሚቻልበት ላይ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የትምህርት ተቋማትና አትራፊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወጣቶች የኤክስፐርት ምክር፣ የመሥሪያ ቦታ፣ መመራመሪያ የሚያገኙበትንና ከሌሎች ከወጣቶቹ ጋር ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠሩና ፍላጎቱ ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩበትን ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ይህ ጥረት ተደምሮ ቀስ በቀስ ጥራቱን የጠበቀና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኢንተርፕሩነርሺፕ እንዲፈጠር ይረዳናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ዘመን የያሊ አባል ነበርሽ፡፡ ምን ዓይነት ልምድ አገኘሽ?

ራሔል፡- አንዱና ዋነኛው ልምድ የተለያዩ ባህሎችንና ብዝኃነትን ማወቁ ነው፡፡ በያሊ የምሥራቅ አፍሪካ ሊደርሺፕ ማዕከል ከ100 በላይ ከምሥራቅና ከመካከለኛው አፍሪካ የመጡ ወጣቶች ጋር ለመሰብሰብ ችያለሁ፡፡ ከተለያዩ አመለካከቶች፣ እምነቶችና ባህሎች የመጡ ናቸው፡፡ የአፍሪካን ችግር በተመለከተ አፍሪካዊ የሆነ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚጥሩም ናቸው፡፡ የነበረኝ ቆይታ መቻቻል፣ ከተለያዩ ዘውግ የመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አመለካከት እንዴት ማክበር እንዳለብኝ ልምድ ቀስሜበታለሁ፡፡ ይህንን ሳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አፍሪካን የተሻለች የመኖሪያ ሥፍራ ማድረግ እንደምንችልም ይሰማኛል፡፡ በሰዎች ላይ ማዕከል ስላደረገ ሥርዓትም ተምሬያለሁ፣ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ ሐሳቦችና ተግባሮች ላይ ዕውቀት አግኝቻለሁ፡፡ በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ሰባት ልምዶች ላይ በታዋቂው አስተማሪና ንግግር አዋቂ ስቴፈን ኮቬይ ሠልጥኛለሁ፡፡ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቀድመው ከመከሰታቸው በፊት እንዴት አድርጌ መወጣት እንደምችል ግንዛቤ ያገኘሁበትና ጥንካሬን የተላበስኩበት ነው፡፡ አብሮ መሥራትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል፣ በጋራ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር መቻልንም አውቄበታለሁ፡፡ ፕሮግራሙን በግል ደረጃ ለመክፈል ውድ ቢሆንም የያሊ ተካፋይ በመሆን ሁላችንም ሕይወታችንን የሚለውጥ ዕድል አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የያሊ ፊሎውሽፕ ላንቺ ምን ጠቀመሽ?

ራሔል፡- ፊሎውሽፕ ጨርሼ ስመለስ በግልም ሆነ በጋራ በመሆን ለውጥ ማምጣት የምችልባቸውን ሁኔታዎች ነበር የተመለከትኩት፡፡ ወጣቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያለን ችግር ለመፍታት መፍትሔ መሆን ይችላሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ወጣቶች ውሳኔ ለመስጠት አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህንን ግብ ለመምታት እኔና የያሊ አባላት የነበረንን ልምድና ከፕሮግራሙ ያገኘናቸውን ዕውቀቶች በመጠቀም ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በግሌ እንደ ማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ የተለመዱ የጤናው ችግር የሆኑትን ለመፍታት በተለያዩ ጉዳዮች አስገብቼ እየሠራሁ ነው፡፡ በያሊ የኢትዮጵያ ቻፕተር ተሳታፊዎችን ለመምራት ተመርጬ ተሳታፊዎች ለተለያዩ ችግሮች ችግር ፈቺ በሚሆኑበት ላይ ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣት ኢንተርፕሩነርስ ህልማቸውን ወደ ተግባር ሲቀየሩ የራሳቸውን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡንም ይቀይራሉ ትያለሽ፤ ስለዚህ ብታብራሪልን፡፡  

ራሔል፡- በፕሮግራሙ ተሳታፊ ሆኜ በተዘዋወርኩባቸው ቦታዎች ያገኘኋቸው ወጣት ኢንተርፕሩነርስ አስገራሚ የሆነ ምልከታ አላቸው፡፡ ከሕዝባቸው ብዙ ተምረዋል፡፡፡ ስለ አካባቢያቸው፣ ፖለቲካ፣ ችግሮችና ሌሎችንም ከቀያቸው አውቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የለውን ችግር የመፍቻ አካል ሊሆን የሚችል አቅም እንዲለውጥ ይህንን ማስቀጠል እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኙ ሀብቶችን ተፈጥሮአዊ፣ ማኅበራዊና ቴክኖሎጂያዊ ዕውቀቶችን በመጠቀምና ፈጣሪ በመሆን በሌሎች ዕርዳታ ሰጪዎች ላይ ሳይመረኮዙ ገቢ ማግኘት ጀምረዋል፡፡ በዚህም ለራሳቸውና ለማኅበረሰባቸው የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ለችግሮቻቸው የዘየዱት መፍትሔ ማኅበረሰቡ ላይ ብቻ ለውጥ በማምጣት የተገደበ ሳይሆን በአካባቢ የተጀመረውን ለውጥና ዕድገት ወደ ሌሎች ማኅበረሰቦች በማስተላለፍ ለችግር ፈቺ እየሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶች ውጤታማ ኢንተርፕሩነር እንዲሆኑ ምን ዓይነት ዘዴ ያስፈልጋቸዋል ትያለሽ?

ራሔል፡- ውጤታማ የሆኑ ወጣት ኢንተርፕሩነሮችን ለማፍራት የሰዎች ችግሮችን መፍታት ላይ ያተኮሩ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ወጣቶች ስለማኅበረሰባቸው እንዲያስቡ፣ ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሔዎች ላይ እንዲያተኩሩ፣ በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ይረዳል፡፡ ከዚህ ባለፈም ወጣቶች የማኅበረሰቡን ፍላጎት፣ ባህልና እሴት በጠበቀ መልኩ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ይዘው እንዲመጡ ያስችላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...