Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹የብሔርና የመሬት ለአራሹ ጥያቄ›› ከ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አንፃር

‹‹የብሔርና የመሬት ለአራሹ ጥያቄ›› ከ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አንፃር

ቀን:

በክንፈ ኪሩቤል ተስፋ ሚካኤል

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄና ተቃውሞዎች እየጨመረ የመጣው እነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ በ1953 ዓ.ም. ዘውዳዊውን መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ለማስወገድ ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ሲሆን፣ በአውሮፓና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበራትን እየተመሠረቱ የመጡበትም ወቅት ነበር፡፡ እነዚሁ ድርጅቶች ዋነኛው የንቅናቄያቸው ማዕከል በነበረው በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኒቨርሲቲ አባሎቻቸውን በመመልመልና ኮሙዩኒስታዊ አስተሳሰብን በማስረፅ ጥቂት በነበሩት ኮሌጆች፣ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ አደረጉ፡፡ ይህ የባዕዳኑ አስተሳሰብ ለዘውዳዊው አገዛዝ አሥጊ እየሆነ ከመምጣቱም ባሻገር በ1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ፈንታ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ማንም አልቻለም፡፡ እናም አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደረሰች፡፡ በአጠቃይ ከ1953 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. የዘውዳዊው ሥርዓት ቀስ በቀስ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ መስኮች ቀውሶች እየተባባሱበት መጡ፡፡

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በዋነኛነት የሚታወቅበት ‹‹የመሬት ለአራሹ›› ጥያቄ ነበር፡፡ አብዛኛው ተማሪ መሠረቱ ከአርሶ አደሩ ስለነበር ተቀባይነትንና ተደማጭነትን ከአርሶ አደሩ እያገኘ ቢመጣም፣ የመሬት ባለቤትነትን ከዘውዳዊ አገዛዝ የገዥ መደብ ወደ አራሹ ገበሬ እንዴት እንደሚያዛውር የታለመ ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን ሲይዝ መሬትን ለገበሬው በግል ንብረትነት ከማስተላለፍ ይልቅ፣ ከኢሕአፓና ከመኢሶን የተቀበለውን ሶሻሊስታዊ ሐሳብ ፎቶ ኮፒ በማድረግ የመሬትን ባለቤትነት የመንግሥት አደረገ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስለሶሺያሊስትና ኮሙዩኒስት ርዕዮት ዓለም ትንሽ እንበል፡፡ ሐሳቡ በጀርመናውያኑ ማርክስና ኤንግልስ ተረቆ እ.ኤ.አ. በ1948 ‹‹የኮሙዩኒስት ማኒፌስቶ›› በመባል ከተሠራጨ በኋላ የሩሲያው ሌኒን የተወሰነውን ሐሳብ ተቀብሎ በማሻሻል፣ ከከፊል ካፒታሊስትና ከፊውዳል ኅብረተሰብ ወደ ሶሻሊስት ሥርዓት ለመሸጋገር ዘገምተኛ የለውጥ ሒደት ሳይከተል የተገዥውን/ተጨቋኙን መደብ በማደራጀት፣ በአብዮት ማለትም በኃይልና በአመፅ አማካይነት የገዥውን መደብ አስወግዶ የሶሻሊዝምን ሥርዓት መመሥረት ይቻላል ብሎ አስተማረ፡፡ በዚህም የቦልሼቪክን (የብዙኃን) ፓርቲ አቋቁሞ የሩሲያውን ዘውዳዊ የዛር መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1917 በአመፅ አስወገደ፡፡ ብሎም የወዝ አደሩን አምባገነናዊ መንግሥት በመመሥረት መሬት ወደ መንግሥት ተዛወረ፡፡ ደቀ መዝሙሩ ከመምህሩ እንደሚማር ሁሉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች የሌኒንን አስተምህሮ የተቀበሉ ስለነበሩ፣ ይህንን ርዕዮተ ዓለም ወደ ተግባር ለመለወጥ ትግል አድርገዋል፡፡

ከ1967 ዓ.ም. በኋላ ብቅ ያለውና ኮሙኒስታዊ  አስተሳሰብን  ያራምድ  የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)  የመሬት ለአራሹን  ጥያቄ  ተቀብሎ ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም››  በሚለው መፈክር ሥር የታገለ ቢሆንም፣ ከተከተለው የተሳሳተ የከተማ ትጥቅ የትግል መስመር የተነሳ እንደ ጠዋት ጤዛ ታይቶ ጠፋ፡፡ ኢሕአፓ እንደታገለው ተሳክቶለት ሥልጣን ቢይዝ ግን መሬትን ወደ ግል ንብረትነት ለማዛወሩ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ምክንያቱም ኮሙዩኒስታዊ ድርጅት ስለነበረ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የአገራቸውንና የዓለም አቀፉን ተጨባጭ ሁኔታ በጥንቃቄ ተመልክተው አገራዊ መፍትሔ ማዘጋጀት ባለመቻላቸው፣ በተለይ የአውሮፓና የአሜሪካ የተማሪዎች ማኅበራት ከጀርባቸውም በነበረው የውጭ እጆች ሴራ ትግሉ ፍሬ ሳያፈራ ቀረ፡፡ (በዶ/ር አያሌው መርጊያው ጉበና የኢሕአፓ አባል የነበረ ‹‹እናት አገር!››  የኢሕአፓ እንቆቅልሸና የባዕዳን ኃይሎች … አገር በቀል ወኪሎቻቸው ጋር ያቀነባበሩት ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ! … ከማውቀው፣ … ከተካፈልኩት፣ …ካየሁት፣ …ከሰማሁትና … ከተወራው! ሁለተ ዕትም የሚል ታሪካዊ መረጃ ያለው መጽሐፍ በአማዞን ኩባንያ በመሸጥ ያለ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ጸሐፊው ፈቃድ የውጭ ሽፋኑ ተቀይሮ በሕገወጥ መንገድ የሚሸጥ ያለ፣ ሊነበብ የሚገባ መጽሐፍ!

በሌላ ወገን የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) የተባለውም ድርጅት እንዲሁ ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብን የሚከተል ስለነበር፣ ከሶቪየት ኅብረት ወይም ከቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲዎች በተለየ መሬትን ወደ ግል ንብረትነት እንዲዛወር  እንደማይፈልግ ግልጽ ነው፡፡ ኢሕአፓም ሆነ መኢሶን ደርግ መሬትን ወደ መንግሥት ባለቤትነት ማዛወሩን አልተቃወሙም፡፡ ምክንያቱም የኮሙዩኒስታዊ  ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ተራማጅና አብዮታዊ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያን ዘውዳዊውን መንግሥት በማስወገድ ለሥርዓተ ለውጥ መፍትሔ ያመጣል ብለው አምነው ተቀብለው ነበርና፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ያነበቡትን የባዕዳን አስተሳሰብ እንደ ወረደ በመቀበል፣ ከአገራቸው ነባራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታ ጋር ሳያገናዝቡ የሶቪየት ኅብረትን ኮሙዩኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም በመቀበል አገራቸውን ለአስከፊ የደርግ ኮሙዩኒስታዊ አገዛዝ አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ምክንያቱም ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፕሮግራም፣ እንዲሁም አገር ለመምራት ልምድ ያልነበረውን ደርግ በተባለው የበታች መኮንኖች ስብስብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደር፣ ወደ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሶሺያሊስታዊ ርዕዮት እንዲቀበል አድርገዋልና፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ቢያንስ አንድ ወጥነት ያለው የፖለቲካ አቅጣጫ ባለመያዛቸው ብሎም አገር ውስጥ ገብተው ጎራ ለይተው መፋለም በመጀመራቸው፣ ይኼንን ክፍተት በመጠቀም ወታደራዊው ደርግ ለሥልጣን ማጠናከሪያው ሲል ከእነርሱ የወሰደው ኮሙዩኒስታዊ ሐሳብ ፎቶ ኮፒ በማድረግ ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን ለማወጅ በቅቷል፡፡ መሬት ለአራሹ እያለ ያስተጋባውን የተማሪዎች መፈክር ለራሱ ሥልጣን ማራዘሚያ ሲል ደርግ የመሬትን ባለቤትነት አብዮታዊ በሚለው ዕርምጃ ወደ መንግሥት ባለቤትነት ከማዛወሩም ባሻገር፣ የሶቪየት ኅብረትን የአርሶ አደሮች አደረጃጀት በመከተል የጋራ እርሻ ማኅበራት እንዲቋቋሙ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህም ማለት አርሶ አደሩ በንጉሣዊው አገዛዝ ዘመን ያርሰው የነበረውን መሬት ለግሉ ሳይጠቀም፣ ከሌሎች አርሶ አደሮች መሬት ጋር ተደምሮ በማኅበር እንዲያርስ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከኖረበት ቀዬው በግዳጅ ተፈናቅሎ ያለ ምንም ዝግጅት በመንደር እንዲሰባሰብ በመታዘዙ በዚህም የተነሳ የመሬት ባለቤትነቱ ተስፋ ጨለመበት፣ የመሥራት ፍላጎቱ ቀዘቀዘ፣ በካድሬነት የተመለመሉ አርሶ አደሮች የቀድሞውን የባላባቶቹን ቦታ ተኩ፡፡ አሳዛኝ ዘመን ሆነ!

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ልብ ያላሉት ጉዳይ ምንም ዓይነት ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በሌሉባት አገር፣ ሕዝብን ለመምራት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲና የድርጅት ባህል በሌላት አገር፣ በመካከለኛው ዓረብ አገሮች ዓይነ ቁራኛ ሥር የነበረችን አገር ወደ ተሻለ ሥርዓት ለመቀየር ጥበብና ማስተዋል ጥንቃቄም ያሻቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የወጣትነት ባህርይ እንደ ንፋስና እሳትነት ባህርይ ስላለው ይህንን በአግባቡ የሚመራ አካል ስላልነበረው፣ የተከተሉት የባዕዳን አስተሳሰብ አገሪቱን እስከ ዛሬ ለጥፋት ዳረጋት፡፡ ጥበብና ማስተዋል ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ተሠውራ ስለነበር አባቶቻችን በጥበብ ያቆዩልን አገር እንደ ዋዛ አሳልፈው ለባዕዳን አስተሳሰብ ስለሰጡ፣ ከዚህ አዙሪት እስካሁን ድረስ አልወጣንም፡፡

‹‹ፊደል ያድናል፣ ፊደል ይገድላል›› ይላሉ አባቶቻችን፡፡ ያለ ጥንቃቄና ማስተዋል የምንጠቀመው ሐሳብ በእርግጥም ያጠፋናል፡፡ በማስተዋልና በጥበብ ሐሳቡን መርምረን ጎጂ ከሆነ መተው፣ መልካም ከሆነ መጠቀም ይገባል፡፡ የእኛ 1960ዎቹ የፖለቲካ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች ያልመረመሩት ፊደል ገደላቸው፣ አገራችንንም ገደለ፡፡ ሌላው አሳዛኝ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች ጥፋት አሁንም አገሪቱን ለከፋ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት እየዳረጋት ያለውና በፍፁም በተሳሳተ መንገድ የተተረጎመው የብሔር ጥያቄ አስተምህሮ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አባላት እንዴት ይህንን የስታሊንና የሌኒን አስተምህሮ እንዳልተረዱትና እንደተረጎሙት እንመልከት፡፡

በሩሲያ የዛር መንግሥት አገዛዝ ወደ 150 ሚሊዮን ይጠጋ ከነበረው ሕዝብ ወደ 43 በመቶ ሩሲያውያን ሲሆኑ፣ 57 በመቶ የሌሎች አገሮች ዜጎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፖላንድ፣ ዩክራይንና ጆርጂያ በዛሩ አገዛዝ በኃይል ተይዘው ቋንቋቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ወዘተ እንዳይጠቀሙ ተከለከሉ፡፡ ስታሊን የጆርጂያ ሰው ነበር፡፡ ሌኒን በመሠረተው የቦልሼቪክ ፓርቲ አባል የነበረ ሲሆን፣ ከሩሲያ ቅኝ አገዛዝ ሥር አገሩ ጆርጂያ ነፃ እንድትወጣ መፈለግ ብቻ ሳይሆን ስለብሔር ጥያቄ እ.ኤ.አ. በ1913 ጽፎ ነበር፡፡ ዛሬ በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 39 ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚለው አንቀጽ ማለት ‹‹ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ የሥነ ልቦና ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ›› የሚለው ዓረፍተ ነገር ከስታሊን ጽሑፍ የተቀዳ ነው፡፡ ሌኒን በታመመበት እ.ኤ.አ. በ1921፣ ስታሊንም ‹‹የብሔረሰቦች ኮሚሳሪያት›› በነበረበት ወቅት ይህንን ትንታኔውን አስደግፎ የጆርጂያን ቦልሼቪኮችን በማደራጀት በኃይል የገዥውን የሜንሼቪክ ፓርቲ በማስወገድ ጆርጂያን ነፃ አገር ከማድረግ ይልቅ፣ ሶቪየት ኅብረትን እንድትቀላቀል አድርጓል፡፡ የራሱን ሐሳብ በተግባር ካደው፡፡

ሌኒን የቦልሼቪክ ፓርቲውን በመምራት በአብዮት የዛሩን መንግሥት ካስወገደ በኋላ ያራመደው ፖሊሲ፣ በሩሲያ ቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ አገሮች በፈቃዳቸው የሶቪየት ኅብረትን ፌዴሬሽን በእኩልነት ደረጃ እንዲቀላቀሉ ነበር ያደረገው፡፡ በተጨማሪ ሌኒን ያራመደው ሐሳብ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ሌኒን ይህንን ሐሳብ ሲያራምድ የየአገሮቹ የቡርዣ መደብ ከሩሲያ ቅኝ አገዛዝ ጭቆናን በመቃወም ለብሔራዊ ነፃነት እንዲታገሉ እንጂ፣ መልሰው የአገራቸውን ሕዝብ እንዲጨቁኑ አልነበረም፡፡ በዚህም አቋሙ የተነሳ ድጋፍ አግኝቶበታል፡፡ ሌኒን ብሔሮች የራሳቸውን ዕድልን በራስ እንዳይወስኑ መከልከልና ብሔርተኝነትን መዋጋት ተመሳሳይ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ምክንያቱም ከጨቋኝ ቅኝ አገዛዝ ለመውጣት የሚታገልን ሕዝብ በኃይልና በግድ በብሔራዊ አንድነት ስም እንዲያዝ ስለማያምን፡፡ አንባቢያን አስተውሉ፡፡ የሌኒን ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ መሠረቱ የየብሔሮች ወዝ አደሮች አንድነትን በመፍጠር፣ የየአገራቸውን ቡርዣ (የካፒታሊስት ሥርዓት አራማጁን መደብ) በመታገልና በማስወገድ የሶሺያሊስት ሥርዓት እንዲመሠረቱ ነበር፡፡ የብሔር ጉዳይ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ሌኒን አበክሮ አስጠንቅቋል፡፡ ምክንያቱም ይኼንን ጥያቄ የተለያዩ ወገኖች ለራሳቸው ጥቅም እንደሚጠቀሙበት ተረድቶ ነበርና፡፡ ለማጠቃለል በሌኒንም ሆነ በስታሊን ጽሑፍ የብሔር ጥያቄ ከቅኝ አገዛዝ ጉዳይ ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው፡፡

ሌኒን እ.ኤ.አ. በ1916  በጻፈው ስድስተኛ ጽሑፍ “The Socialist Revolution and the Right of Nations to Self Determination”  የሚለው ርዕስ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ሌኒን የብሔር ጥያቄን ወዝ አደሩ ለሶሻሊስት ሥርዓት ከሚያደርገው ትግል ፈጽሞ ነጥሎ ዓይቶትም፣ አቅርቦትም አያውቅም፡፡ አንባቢው በጎግል (JOHN G. Wright, Lenin on the Problem of Nationalities (January 1943) From Fourth International, Vol 4, NO.1, PP 15 – 18 https://marxist.org.>wright>selfdet) ፈልጎ እውነቱን ይረዳ፡፡ ሌኒን በትንታኔው ስለብሔር ጥያቄ በጻፈው ጽሑፉ ያነሳቸው አገሮች በምሥራቅ አውሮፓ እንደ ኦስትሪያ፣ ባልካንና በተለይ በሩሲያ ቅኝ ግዛት ሥር ይተዳደሩ ስለነበሩት ሕዝቦች፣ እንዲሁም  በቅኝና በከፊል ቅኝ አገዛዝ ሥር ለነበሩት ቻይና፣ ፐርሺያ፣ ቱርክና ህንድን ለመሳሰሉት አገሮች ነበር፡፡

ሌኒን በኢምፔሪያሊስትና ቅኝ ገዥዎች ሥር የነበሩ እነዚህ ሕዝቦች ብሔራዊ መብታቸውና ክብራቸውን ለማስመለስና ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት፣ እንደ አንድ ሉዓላዊ ብሔር (አገር) ተደራጅተው መታገል ይገባቸዋል የሚለውን ሐሳብ ነው ያራመደው፡፡ ሌኒን ይህንን ያለው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች የዓለም ወዝ አደር ጠላቶች ስለሆኑ በማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምና በሶቪየት ኅብረት ኃይል ድጋፍ ጭምር፣ ከኢምፔሪያሊዝምና ከፊውዳሊዝም (ዘውዳዊና ባላባታዊ ሥርዓት) በትግል በቀጥታ ወደ የሶሺያሊስት ሥርዓትን በአብዮት መሸጋገር ይችላሉ በማለት ነበር ያስተማረው፡፡

በሌኒን ትንታኔ መሠረት በካፒታሊስት ኅብረተሰብ ወይም በፊውዳል ሥርዓት ውስጥ ያሉትን የገዥ መደቦችን ጨቋኝ ብሎ በአንድ መደብ፣ በሌላ ወገን የወዝ አደርና የአርሶ አደርን ክፍል ተጨቋኝ በማለት እንደ አንድ መደብ መድቦ ትንታኔ ሰጠ፡፡ በወዝ አደሩ የበላይነት የሚመራ ሶሻሊታዊ መንግሥትም እንዲመሠረት አስተማረ እንጂ፣ አንዳችም ቦታ በጽሑፉ ብሔርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ትንታኔ አልሰጠም፡፡ ሌኒን እንደ ቻይና የመሰሉ በከፊል ቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ፣ እንደ ህንድ፣ ፐርሺያ፣ ቱርክና በሩሲያ ዛር መንግሥት ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ ሁሉ ለብሔራዊ ነፃነታቸው እንዲታገሉና  የሶሻሊስት ሥርዓትን እንዲቀላቀሉ፣ የካፒታሊስቱ ዓለም ወዝ አደር እንዲደግፋቸው ጭምር ነበር ጥሪ ያደረገው፡፡ የዓለማችን ቅኝ ገዥዎች ነጮች እንጂ ጥቁር ሕዝቦች አልነበሩም፡፡ ስለሆነም በሌኒን አስተምህሮ ቆዳው ‹‹ቢጫም›› ሆነ ‹‹ቀይ››፣ ‹‹ጥቁር››  ሕዝብ ብሔራቸውን (ሉዓላዊ አገራቸውን) መሠረት አድርገው ከኢምፔሪያሊስቶችና ከምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎችና ጭቆና ሥር የነበሩ ሕዝቦች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ አስተምሯል፡፡

የሌኒን ጽሑፍ በግልጽ የብሔር ጥያቄን ያነሳው በኢምፔሪያሊስቶችና በምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች ሥር ለነበሩ ከላይ ለተጠቀሱት አገሮች እንጂ፣ በቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ የአፍሪቃ አገሮችን በስም አላካተተም፡፡ ያም ቢሆን ሌኒን ሥልጣን ከመያዙ 21 ዓመታት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ቅኝ ገዥዎችን ተዋግታ ድል ነሳች፡፡ እንዲሁም ለብሔር ነፃነቷ ታገለችና ለጥቁር ሕዝቦች አርዓያ ሆነች፡፡ በዚህም የተነሳ ሌኒን ለኢትዮጵያ አክብሮት እንደነበረው ማሰብ የማይችል ሌኒኒስት ካለ ‹‹ሐሳዊ ሌኒኒስት› ነው ማለት እንችላለን፡፡ አንባቢው ያስተውል፣ ሌኒን በመራው እ.ኤ.አ. የ1917 የቦልሼቪክ ፓርቲ አብዮት አማካይነት የተመሠረተችው ታላቋ ሶቪየት ኅብረት ወደ 15 የሚጠጉ አገሮችን የያዘች የኅብረት ፌዴራል መንግሥት እንጂ፣ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ሥርዓት አልነበረም፣ ቻይናም እንዲሁ፡፡ ምክንያቱም የርዕዮተ ዓለም መርሆ የሶሻሊዝም ብሎም የኮሙዩኒዝም ሥርዓት ለመመሥረት እንጂ፣ በቋንቋ ተከፋፍሎ ለሚናቆር ሥርዓት አልነበረም፡፡ ስለሆነም ሕወሓት ካራመደው የተውገረገረ ሐሳብ ይልቅ የሌኒን ሐሳብ ልዕልናው ከፍተኛ ነው፡፡ የሚገርመው ማርክሲስት ሌኒኒስቱ ሕወሓትና የደገፉት ልሂቃን፣ አብዮታዊ ተብሎ የሚሞገሰው ሌኒን በብሔር ጥያቄ ስም ፈጽሞ ያላስተማረውን በብሔር ስም ሕዝብን በቋንቋ የሚከፋፍል የፌዴራልዝም አስተምህሮን ከየትኛው መጽሐፍ አገኙት? 

ከሌኒን አስተምህሮ በተቃርኖ በቅኝና በከፊል ቅኝ አገዛዝ ሥር ስለነበሩት አገሮች የጻፈውን የብሔሮች ጥያቄ ጉዳይ ሕወሓት በተሳሳተ አረዳድ ይሁን በተንኮል፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጥቁር ቅኝ ገዥዎች ሥር እንደነበሩ በማድረግ የዓለምን ሕዝብ በቅኝ ግዛትነት ረግጠው ከገዙት፣ ሀብቱንና ጉልበቱን ከመዘበሩት የነጭ ወራሪዎች ከእነ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ስፓኝ፣ ፖርቹጋል፣ ቤልጂየም፣ ጀርመን፣ ሆላንድ ጣሊያን፣  ወዘተ ጎራ የኢትዮጵያን ነገሥታትን መድቦ የትግራይን ሕዝብ ከቅኝ አገዛዝ  ለማውጣት ታገለ፡፡ እጅግ የሚገርመው ሕወሓት ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሥልጣን ይዞ በቆየባቸው ዘመናት ከማን ነፃ እንደሚወጣ ባይታወቅም፣ ‹‹ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ›› የሚለውን ስሙን ያለ መቀየሩ በእርግጥም መሪዎቹ የዕውቀትና የንድፈ ሐሳብ መረዳት ታላቅ ችግር እንደነበረባቸውና እንዳለባቸው ያሳያል፡፡ እናም በዓለም የታሪክ መዝገብ ሠፍሮ የማይታወቅ የጥቁር ቅኝ ገዥዎችን ታሪክ በመፍጠር፣ ‹‹የብሔር ጥያቄን›› መፍታት አለብኝ በሚል መርህ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም አዋቀረ፡፡ የጣሊያን ፋሺስት የሞሶሎኒ መንግሥት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ቢይዝ ኖሮ ቋንቋን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ዘይቤ ለኢትዮጵያ ነድፎ እንደ ነበር በቂ መረጃዎች አሉ፡፡

ወደ ጉዳያችን ስንመለስ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ክልል ሕወሓት ሲያቋቁም፣ በደርግ ጦርነት የተሰላቸው ሕዝብ በጉዳዩ ሳይመክርበት እንደፀደቀ የሚካድ አይደለም፡፡ በተቀረፀው ሕገ መንግሥት ውስጥ ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ›› የሚሉት ቃላት ዋነኛውን ይዘት የያዙ ሆነው ሳለ ለቃላቱ ትርጓሜ ለመስጠት ያልተቻለበት ዋነኛ ምክንያት፣ ጓድ ስታሊን ባቀረበው የብሔር ጥያቄ ጽሑፉ ‹‹ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑና ሥነ ልቦና ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ›› የሚሉትን ሐረጎች ከቅኝ አገዛዝ ለመውጣት ለሚታገሉ አገሮች ሕዝቦች ለብሔር ጥያቄያቸው እንደ ማሟያ መሥፈርቶች አስቀምጦ ስለተወው ነው፡፡

የእኛ ሕገ መንግሥት አርቃቂዎች ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ›› ለሚለው ትርጓሜ ለመስጠት ስላልቻሉ ሥልጣን ፈላጊ ቡድኖች ከላይ የተጠቀሱትን መሥፈርቶች በፈለጉት መንገድ እያራገቡ፣ በብሔር ጥያቄ ስም ሕዝብን ግራ እያጋቡት ይኖራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ የአገራችን ፌዴራሊዝም ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ቋንቋን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ ሁለተኛ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ፣ ሦስተኛ በፈቃደኝነት ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ፣ አራተኛ ሕዝቦች ተከባብረው የጠበቁዋቸውን ቀድሞ የነበሩ ወሰኖችን በአንድ ገዥ ፓርቲ ፍላጎት በማፍረስና በማካለል የተዋቀረ በመሆኑ ለዛሬ ቀውስ በቅተናል፡፡

ጓድ ሌኒን ከሞተና የጓድ ስታሊን አምባገነናዊ አገዛዝ ከተጠናከረ በኋላ የሶቪየት ኅብረቱ ፌዴሬሽን የገጠመው ችግር ብዙ ነው፡፡ ጓድ ሌኒን በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የመሠረተው የሶቪየት ኅብረቱ ፌዴሬሽን ቀስ በቀስ በሩሲያ የበላይነት ሥር በመግባቱና የሌኒን የእኩልነት ፌዴሬሽን መርሆች ባለመጠበቃቸው፣ ብሎም የኮሙዩኒስት ፖሊት ቢሮው አመራር ፈላጭ ቆራጭ እየሆነ በመሄዱ፣ ከዓለም አቀፋዊው ተጨባጫ ሁኔታ ጋር ሁኔታዎችን ገምግሞ ባለመራመዱ የተነሳ በ1980ዎቹ መጨረሻ በፖላንድ፣ በቼኮዝሎቫኪያ፣ ቀጥሎም በዮጎዝላቪያ፣ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በዩክሬን በቤላሩስ ብሔራዊ ንቅናቄዎች እያየሉና እየተስፋፉ ሄደው የሶቪየት ኅብረቱ ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. በ1991 ፈረሰ፡፡ እናም ከሶቪየት ኅብረት ፌዴሬሽን መፍረስ በኋላ ዛሬ በምዕራብና በምሥራቁ የአውሮፓ ምድር የኅብረቱ አገሮች የነበሩ ወደ ቀድሞው ስማቸው ተመልሰዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የሆነው የምዕራባውያኑ ፌዴራሊዝም ግን እነሆ በሰላም ቀጥሏል፡፡

የአገራችን ሕዝቦች በተለያዩ መልክዓ ምድር ሠፍረው፣ በድንበር ዘለል ጋብቻ ተሳስረው፣ አንፃራዊ አንድነት ፈጥረው፣ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ አዳብረው፣ በጋብቻ፣ በዝምድናና በጉርብትና ሐረግ ተቆላልፈው ከነገዶች ወደ ጎሳዎች ውህደት የፈጠሩት መስተጋብር የሚታይባት አገር ናት፡፡ የአገራችን ሕዝቦች ለየብቻቸው ያዳበሩት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ባይኖራቸውም፣ በነበራቸው ማዕከላዊ መንግሥት አገዛዝ ሥር እንደ አንድ አገር የብሔራዊ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ፈጥረው ተከብረው ኖረዋል፡፡ ሕዝቦቻችን በጋብቻና በዝምድና፣ በንግድ ግንኙነት የፈጠሩትን ትስስር፣ በሰላምና በጦርነት ዘመናት የፈጠሩትን አንድነትና ኅብረት፣ በደስታና ሐዘን ወቅቶች የተጋሩትን የሥነ ልቦና ስሜት በአንቀጽ 39 የማለያየት ዓላማ በቋንቋ አመካኝተን እንድንለያይ ለምንድነው የተፈለገው?  

የፌዴራሊዝም አስተዳደርና አወቃቀር የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት ተቀብለው የተገበሩ ጥቂት የአፍሪካና የእስያ አገሮች አሉ፡፡ መልካም የአስተዳደር ዘይቤ ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት በጥንቃቄ አጥንቶ ሕዝቦችን ለሰላም፣ ለዕድገትና ለብልፅግና የሚያደራጅ አድርጎ ማዋቀር ሲገባ ያለ ማስተዋልና ያለ ዕውቀት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር እንዲያጋጭ አድርጎ ክልል ብሎ ማዋቀር ትክክለኛው መንገድ አልነበረም፡፡

ስለሆነም የሕወሓት ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ወይ ከመምህሩ ከሌኒን አስተምህሮ አይደሉ፣ ወይ ከምዕራባውያኑ ፌዴራሊስቶች፣ ወይ ከኢትዮጵያ አባ ገዳዎች፣ ወይ ከአፄ ዮሐንስ አይደሉ፣ ታዲያ ከየት እንመድባቸው?? ደቀ መዝሙሩ ከመምህሩ  አይበልጥም የሚለውን ብሂል ዘንግተውታል ወይም አያውቁትምና የሌኒንን የብሔር ጥያቄ አስተምህሮ ስለበረዙበት ጊዜው ሲደርስ፣ የሌኒን አስከሬን ከመቃብሩ ተነስቶ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ሳይፈርድባቸው ይቀር ይሆን? ኢትዮጵያ ግን በፈጣሪዋ ጥበቃ ትቀጥላለች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...