Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርጆሮ ሊሰጠው የሚገባ የአንድነት ድምፅ

ጆሮ ሊሰጠው የሚገባ የአንድነት ድምፅ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው    

የኢትዮጵያን አንድነት (ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት)ን ጮክ ባለ ድምፅ  ለመናገር አንዱ  መሰናክል የሚሆነው፣ ለስያሜውም ሆነ ለድርጊቱ ሲሰጠው የቆየው ዳራ  ነው፡፡ ይኼም ጭፍለቃና ዕመቃ ብሎም አናሳውን ሕዝብ በብዙኃን የመደፍጠጥ  ስሜት ያነገበ መሆኑ ነው፡፡ ያለ ምንም ማመንታት እንግለጸው ከተባለም ቀደም ሲል የነበሩት ፊውዳላዊና ወታደራዊ መንግሥታት የኢትዮጵያን አንድነት መፈክር አንስተው፣ በአፈጻጸም አፈናና ጭቆናን ብሎም የአገሪቱ የቋንቋ፣ የማንነትና የሃይማኖት ብዝኃነትን በሚጫን መንገድ ሊተገብሩ በመሞከራቸው አሁን ያለው ሥጋት ሊንሰራፋ ችሏል፡፡ አክራሪ ብሔርተኛውም ለራሱ ፖለቲካዊ ትርፍ ሲል ነግዶበታል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢሕአዴግ መራሹ የ1960ዎቹ  የፖለቲካ ትግል በአገሪቱ የተዘረጋውን ‹‹የብሔር ጭቆና›› ለመቀልበስ የታገለ እንደ መሆኑ፣ የጦርነቱን  ዓውድማ የአንድነትን አስተሳሰብ  በማፈራረስ ላይ በማነጣጣሩ ነው፡፡ በዚህ መዘዝ ያኔም ሆነ ዛሬ ዴሞክራሲያዊና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያራምዱ ሰዎችና የፖለቲካ ኃይሎች ሳይቀሩ ድምፃቸው ታፍኗል፡፡ ቢናገሩ የማይሰሙ፣ ቢደራጁም በነፃነት የማይላወሱ ሆነውም ቆይተዋል፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለአገር ህልውናም ሆነ ለሕዝቦች አብሮነት ዋስትና እንደሆነ ቢታወቅም፣ ድምፁ የሰለለን ማንም ደፍሮ አይጠጋውምና ክፍተቱ ዛሬም ወለል ብሎ እየታየ ነው፡፡

ይሁንና አሁን ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ምንም ያህል በአገራዊ አንድነት ግንባታ ረገድ ተዋናዩ ድምፁ ቢኮስስና የተደራጀው ወገን ቢዳከምም፣ አገር ወዳድ ኃይሎችና የአንድነት አራማጆች ሊሰባሰቡ የሚገባበት ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ በዜግነት ፖለቲካ፣ በሕገ መንግሥት ማሻሻያም ይባል የፌደራል ሥርዓቱን አንዳንድ ክፍተቶች በመሙላት፣ አገራዊ ፖለቲካውን ከብሔርና ከማንነት ማታገያ ሥልት ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ማድረስ ታሪክ በዚህ ትውልድ ላይ የጣለው ኃላፊነት ነው፡፡ ደግሞም ሊሳካ የሚችል የውዴታ ግዴታ ልንለው እንችላለን፡፡

  እርግጥ እዚህ ላይ አንድ ወዳጄ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲመጣ መመኘት ብቻ ሳይሆን መታገል መልካም ቢሆንም፣ የጎሳ ብሔርተኝነቱ ክንፍ አውጥቶ በመብረር ሰማዩን ስለሞላው ፈተናው ቀላል አይሆንም ያለኝ ሥጋት የሚናቅና የሚዘነጋ አለመሆኑን እገነዘባለሁ፡፡

 ሥጋቱን ተጨባጭ የሚያደርገው ነባራዊ ሀቅ ደግሞ በተለይ ባለፉት 28 ዓመታት ኢትዮጵያዊያን የከረረ የብሔርና የጎሳ ብሔርተኝነትን ከሚገባው በላይ እየተላበስን የመጣን በመሆናችን ነው፡፡ በእኩልነት መተሳሰብና በማንነት መኩራት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ሁሉም ብሔርና ዘሩን ፈላጊ ብቻ እየሆነ በመሄዱ የዜግነት ፖለቲካም ሆነ የኢትዮጵያ አንድነትና የሕዝቦች አብሮነት በግላጭ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡  ይህ አካሄድም የጋራ ቤታችንና በታሪከ ‹‹የእኛ›› ስንላት የኖርናትን አገር ለልጆቻችን ስለማስተላላፋችን ዋስትና የሚያሳጣ እየሆነ ነው፡፡

በእርግጥ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ለዚህ ሁኔታ መባባስ መንግሥት ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ከመደብ ይልቅ፣ በብሔር የመብት ጥያቄ ላይ የሚነታረክ ትውልድ ማብዛቱ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ ጉዞም በልዩነት መዘውርና በነጣጣይ ፖለቲካ ተረግዞ የወለደልን አክራሪ ዘውጊያዊነትን፣ የፖለቲካ ጥላቻና መገፋፋትን መሆኑ ነው አስከፊነቱ፡፡ አሁን የምንከተለው የፌደራል ሥርዓት በልማት፣ በብሔረሰብ መብትና ታሪክን  በማስተዋወቅ ረገድ ያመጣው ለውጥ እንዳለ ባይካድም፣ በአብዛኛው የሕዝቡንና የአገርን አብሮነትና መስተጋብር በተቃርኖ ፖለቲካ በማናጋት፣ የአገረ መንግሥቱን አንድነት ክፉኛ ስለማዳከሙ ራሱ ገዥው ፓርቲም በግምገማው በስፋት አንስቶት ነበር፡፡

እንግዲህ ምንም ሆነ ምን በነበረው ነጣጣይ የፖለቲካ ሥርዓት በማላዘን ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይልቁንም የከረረ የዘውጌ ፖለቲከኛውና ብሔርተኛው ኃይልም ሥጋትና መጠራጠር ሳይገባው፣ የአገር ህልውናም አደጋ ላይ ሳይወድቅ መፍትሔ ማምጣት ላይ ማተኮር ነው የሚበጀው፡፡ በዚህ ላይ የሚኖር ልዩነት ግን ውኃ የማይቋጥር ብቻ ሳይሆን፣ በኋላ ቀር አስተሳሳብ አገርን ገፍትሮ የሚጥል መሆኑ ሊጤን ይገባዋል፡፡

አሁን ማን ይሙት የዘውጌ ፖለቲካም ሆነ  የብሔር ፌደራሊዝም  አዋጭና ዘላቂ  የአገር አንድነት የሚያስከብርና የኖረውን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ጥያቄ የሚፈታ ቢሆን ‹‹ተለወጥን!›› እያልን ይህን ያህል አገራዊ ትርምስ ይታይ ነበር? እስኪ በጥሞና እናጢነው፣ እንመርምረው፡፡  የዘር ፖለቲካስ በዚሁ እንዲቀጥል ይበልጥ በር ካሰፋንለት አንድነታችንን መሸርሸር ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ ህልውናን አያዳክምም? ጉዳቱን  በወጉ መፈተሸ ግድ ይላል፡፡

እንዲያውም የዚህ ዕሳቤ ዋነኛ አራማጆች አዛውንቶቹ ኦነግና ሕወሓትን የመሳሰሉት ኃይሎች ካለመክሰማቸው ባሻገር፣ አዳዲስ አክራሪ  የዘውጌ  ኃይሎችም በአሁኑ ትውልድ በፈረጠመ ድጋፍ ተወልደዋል፡፡ ይህ እውነታም እየተባባሰ እንጂ እየተቀዛቀዘ ባለመሄዱ፣ አክራሪ ብሔርተኛ  አካሄዱን በሕግ ለመግታት ጥረት መጀመር እንዳለበት ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ አንድነት ሥጋት መባባስ ሌላው ምልክት በአገሪቱ በሕጋዊነት ከተመዘገቡት ከ100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች 85 በመቶው የሚሆኑት በብሔር የተዘጋጁ የመሆናቸው አንድምታ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ባለፉት ዓመታት በግልጽ እንደታየው አገራዊ ራዕይና ግብ የሰነቁና የተዋሀዱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያደከመና ያጠፋ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ዴሞክራሲውም እንዳይጠናከር አንዱ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በቀጣይ ለትውልዱ ይህን ሳንካ ማሸጋገር ደግሞ ተጨማሪ ታሪካዊ ስሀተት እንደመፈጸም  የሚቆጠር ነው፡፡

በዚያ ላይ አሁን አሰፍስፈው በብሔር ክልልና ልዩ ዞን የመመሥረት ጥያቄና ግፊት የሚያሳድሩ የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎት ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ አካሄዱ በእርግጠኝነት በዘውጌ ዕሳቤ ተጠራርቶ ሥልጣንና ሀብትን ይዞ በራስ አጥር ለመከለልና ሌላውን ‹‹አትድረስብን›› ለማለት ሲሆን፣  አለፍ ሲልም አንቀጽ 39ን  ወደ መተግበር ለመንደርደር ነው፡፡  ለአብሮነትና ለጋራ አገር ግንባታ ቢታለምማ መነሳት ያለበት የልማት፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የመልካም አስተዳዳርና የጋራ ብልፅግና አጀንዳ መሆን ነበረበት፡፡

ለዚህ ደግሞ አሁን ያሉትም ክልሎች ቢሆኑ በዋናነት በብሔር ንፍቀ ክበብ  ታጥረው አላላውስ ወደ ማለት መሄዳቸው ዋነኛ ምልክት ነው፡፡ እስካሳለፍነው ሳምንት  የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የዜጎች እልቂት ድረስ፣ በምንም ይነሳ በምን በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት (የዜጎች መፈናቀል፣ መቁሰልና መሞት) እየበረታ ነው፡፡ ይኼንንም እየለኮሰና እያባባሰው ያለው ራሱ የመንግሥት መዋቅሩና ለዘረፋ ያሰፈሰፈው ኃይል መሆናቸው እየታየ ነው፡፡

በዚህ ላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በድፍረት ክልሎች ሚዲያ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይል የመሳሳሉትን በአቅማቸው ልክ ብቻ ሳይሆን እንዳሻቸው በመፍጠራቸውና በራሳቸው ወሰን በማዘዛቸው አጉል ፉክክር እየተጀመረ ነው፡፡  ብሎም የፌደራሉ መንግሥትንም አቅምና ውሳኔ የመገዳደር ፍላጎት እየተንፀባረቀ መሆኑ ሲታይ ሥጋቱን የሚያንር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለም የአገር አንድነትና ህልውናን በሚያናጋ ደረጃ፣ ክልልን ከክልል ጋርም ሆነ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ማፋጠጡ አይቀርም፡፡

ይህን የአገር አንድነትና የሕዝቦች አብሮነት የሚጎዳ፣ ብሎም የዜግነት ፖለቲካን ቀፍድዶ የሚይዝ አካሄድን ለማረም የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት በግልጽ የሚያረጋጋጥ መፍትሔ ማሰስ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ይሉኝታም የአንድነት ኃይሎችን ድምፅ እንደ አማራጭ ወደ ውይይት በማምጣት ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ትግሉ መጠናከር ማዋል  ግድ የሚል ነው፡፡

እውነት ለመናገር  ‹‹የአገራችን  ሕዝቦች  በማንነታቸው የተጋመዱ፣  ጨዋ፣ አንድነትና መከባበር የሚያውቁ፣ ለዘመናት በመቻቻልና በመደማመጥ የዘለቁ፣ አንዳንዱ ሕዝብም በባህላዊ ትውፊቶቹ ዴሞክራሲያዊነትንና  ዕርቅን  የተለማማደ …››  እያልን ምንም ያህል ብንዘምር፣ ከአክራሪ ብሔርተኝነት ፖለቲካ  ትርምስ  ካልተወጣ፣ ሁሉም ወደ ራሱ መሰባሰቡ አይቀሬ ነው ፡፡ ይህም ኅብረ ብሔራዊ  የሆነውን  ሕዝብ እየገፋ፣ ያለ ጥርጥር ጠባብነትነና ዘረኝነትን እያፋፋ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ሁሉም ነገር  ‹‹የእኔ ነው፣ የእኔ ነው››  የማለቱ ስግብግብነትም ይባባስ እንደሆነ እንጂ፣ ሊቀንስ የሚችል አይደለም፡፡

በእርግጥ ከቀውስ የምንወጣበት ተስፋም አለን፡፡  የጥላቻ ፖለቲካ ምንም ያህል ቢነበነብ፣ የቀድሞዎቹ ሥርዓቶችም ቢሆኑ በማወቅም ሆነ ባለመዋቅ  በአገራዊ አንድነት ፍልስፍና  ስም የዘረጉት  ጭቆናም  ቢበረታ፣ ከዚህ መውጣት የሚቻልበት ዕድል አለ ፡፡ ይኸውም  የአገራችን ሕዝቦች ታሪክ  ከተመረመረ ለአንድነትና ለአብሮነት መሠረት የሚሆን እርሾ ያለው በመሆኑ ነው፡፡  ሕዝቡም ለዘመናት የተዋለደና የተወሀደ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ነብር ቆዳ ተዥጎርጎሮ የተጋመደ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ አባባል አንድ ጥናታዊ አብነትን ብቻ በመጥቀስ ሐሳቡን ማጠናከር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ኃይሌ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) የተባሉ ምሁር ‹‹አብሮነት በኢትዮጵያ›› (1994 ዓ.ም.) የሚል አነስ ያለ ታሪካዊ ጥናት ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀደምት ታሪክ፣ አብሮነትና አኩሪ እሴቶች ጠቃሚ ሐሳቦችን የሚያነሳ ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ የሚረዳኝን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪካዊ  ውህደትና መስተጋብር ብቻ ልጥቀስ፡፡

ይህ ሐሳብም ቢያንስ ከዚህ በኋላ እውነታውን መርምረን ከተረዳን፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም የአገራችን የጎሳና የብሔር ፖለቲከኞች መንገድ ቆም ተብሎ መታየት እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡ ሕዝቡ በነፃነትና በዴሞክራሲያዊነት ከተወያየበትም የዘር ፖለቲካ የብዙኃኑን ተቀባይነት የማያገኝ፣ ፉርሽ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እስካሁንም በአገሪቱ ሕዝብ ለሕዝብ ባልተጨቋቆነበት ሁኔታ፣ በፖለቲከኞች ሴራ እየተመረዙ  እንጂ  ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና ውህደት ለመጪው ትውልድም ሊሻገር የሚችል ነው፡፡  በተጨባጭ መስተጋብሩ ኢትዮጵያዊያን ለአፍታም የማይለያዩና የተሳሳሩ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያንፀባርቃል፡፡

እንዲህ ይላል፣ ‹‹ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች መስተጋብር ስንጠቅስ ጥንት የአክሱም መንግሥት በዮዲትና በቤጃዎች ሲደመሰስ፣ አክሱማውያን ወደ ሰሜንና ወደ መሀል አገር ፈልሰው ኑሮ መመሥረታቸው በቅድሚያ ይወሳል፡፡ የዛጉየ መንግሥትም ሮሃ ላይ ከተመሠረተ በኋላ የአክሱማውያንን ዕደ ጥበበኞችና ሌሎች ሠራተኞች  ስቧል፡፡

‹‹የሸዋ መንግሥት በጀመረው የመስፋፋት ጉዞ ደግሞ ቋሚ የጦር ሠፈሮችና የአካባቢ ጋሻ ጃግሬዎች በሐረር፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በደዋሮ፣ በባሌ፣ በሐዲያ፣ በከምባታ፣ በወላይታ፣ በጋሞ ጎፋ፣ በሸዋ፣ በቢዛሞ፣ በዳሞት፣ በእናርያ፣ በጉራጌ ወዘተ… እንደነበሩትና በዚህም ሰፊ መስተጋብር እንደተፈጠረ ይታወቃል፡፡

‹‹ዛሬ ድረስ ወላይታ ውስጥ ትግሮ (ትግሬ)፣ ቡልጎ (ቡልጋ)፣ መንዞ (መንዝ)፣ ቄሶ (ቄስ)፣ መራቤቶ (መረሃቤቴ) ወዘተ የሚባሉ ጎሳዎች አሉ፡፡… ከምባታ ውስጥ ኦያ የሚባለው ጎሳ ከጎንደር ከመጣ ሐመልማል ሠራዊት የሚመነጭ መሆኑ ሲታወቅ፣ ሐድያ ውስጥም ጋስ አማራ (የጥንት አማራ) የሚባል ጎሳ እንደነበር ተመዝግቧል፡፡

‹‹የጉራጌም ሕዝብ በአመዘኙ፣ የእናርያ፣ የሲዳማ፣ የሐረር፣ የአሮሞና የሐዲያ ሕዝቦች መስተጋብር ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል በ16ኛው ምዕተ ዓመት መጀመርያ ሩብ አጋማሽ ግራኝ መሐመድ ከሐረር ተነስቶ ከብዙ ሕዝቦች የተውጣጣ ሠራዊት መሥርቶ ኢትዮጵያን እንዳጥለቀለቀ ይታወሳል፡፡

‹‹ከግራኝ ሽንፈት በኋላ የግራኝ ሠራዊት እንደሟሸሸ  ቢታወቅም፣ ጦርነቱ የፈጠረው መስተጋብር የኦሮሞ ሎባዎችን ወደ ባሌ፣ ደዋሮ (አርሲ)፣ ሐረር፣ ሸዋ፣ ቤተ አማራ (ወሎ)፣ ጎንደር፣ ከፋና ጎጃም አሰባስቧል፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሮሞዎች ከነባር የየአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር ተወራርሰዋል፡፡ ተዋህደዋል፡፡

‹‹እዚህ ላይ የባሌ፣ የደዋሮ፣  የዳሞት፣ የቤዛም፣ የእናርያ፣ የሐዲያ (በከፊል)፣ የጉራጌ (በከፊል) ሕዝቦች ማንነታቸውን ትተው ኦሮሞዎች ሲሆኑ፣ በተለዋጩ ወደ ቤተ አማራ፣ ጎንደር፣ ትግሬና ጎጃም የዘለቁ ኦሮሞዎች ደግሞ ማንነታቸውን ትተው አማራዎችና ትግሬዎች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል የማዕከላዊ መንግሥት ግዛት አካል የነበረው ባህረ ነጋሽ (የዛሬው ትግራይና ኤርትራ) ብዙ የጎንደር፣ የጎጃምና የቤተ አማራ ሕዝቦችን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስቧል፡፡ ስለሆነም በኤርትራ ውስጥ ሐማሴን የሚባለው ሕዝብ በአመዛኙ ከጎንደር የፈለሰ መሆኑ ታውቋል፡፡ …›› (ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ገጽ 60 ከተጠቀሰው ይኼው ይበቃል)

እንግዲህ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት በጠንካራ አገረ መንግሥትም ይሁን በየአካባቢው መሳፍንቱ እየተነሳ፣ ሕዝቡ ሲዋሀድና ሲዋለድ የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ይህን አብሮነት የመሠረተውን ማኅበረሰብ በዘር ፖለቲካ ለመነጣጣል መጣደፍ ይሻለል? ወይስ ዴሞክራሲንና ፍትሕን እያረጋጋጡ አንድነቱን ማጠናከር? መልሱን ለአንባቢዎች እተዋለሁ፡፡ እዚህ ላይ ከሰሞኑ እዚሁ ሪፖርተር ጋዜጣ ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም.  ዕትም ላይ ‹‹የታሪክ ሥፍራችንና የጋራ  ወደፊታችን›› በሚል ርዕስ በጥልቀት የቀረበውን የአቶ አንዳርጋቸው አሰግድን ጽሑፍም በመፈተሸ ዳራውን ማጤን ይቻል ይመስለኛል፡፡

ምንም ተባለ ምንም ውሳኔው የሕዝቡ ሆኖ እየተጠናከሩ መምጣት ያለባቸው ግን የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች፣ የኅብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት አቀንቃኞች ሊሆኑ ይገባል፡፡ የእነዚህ ወገኖች ድምፅ ይበልጥ ሊደመጥና ለውይይት ሊቀርብ እንዲችልም፣ ከሕዝቡ ድጋፍ ባሻገር የመንግሥት የሕግና የፖሊሲ ድጋፍም ሊታከልበት ይገባል፡፡ በተለይ ባለፉት ዓመታት እንደታየው በአንድነት ኃይሉ (ኢትዮጵያዊው ብሔርተኛ) ላይ የተጫኑ የማሸማቀቂያና የማስፈራሪያ ታፔላዎች  ሊነሱለት ግድ ይላል፡፡  በዚህም  እንደ አንድ ታሪካዊት አገር ሕዝቦች አማራጭ አልባ ከመሰለውና  ከተጠመደልን የዘረኞችና  የጠባቦች የከሰረ መንገድ መላቀቅ ይኖርብናል፡፡

ጽሑፉ ሲቋጭም መምህር ታየ ቦጋለ የተባሉ የታሪክ ምሁር ተናግረውት በቅርቡ በማኅበራዊ ድረ ገጽ (በተለይም ፌስቡክ ላይ) ብዙ ድጋፍ ያገኘውን አጭር ሐሳብ ላስቀምጥ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለእኔ ከነፍስና ሥጋዬ ጋር የተሸመነች ማንነቴ ናት፡፡ ይህች አገር አባቶቻቻን ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ  ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ከአንድ ፅዋ ውኃ ተቋድሰው፣ ጥርኝ ቆሎ ከአንድ ማዕድ ተጎራርሰው፣ በአንድ የቀበሮ ጉድጓድ  ውስጥ ወድቀው ደማቸው በየቦታው ፈሶ፣ ጅረት ሠርቶ ኢትዮጵያ የሚል ስም የፈጠረች አገር መሆኗን ለአፍታም ያህል መዘንጋት ውርደትን ያስከትላል፡፡›› ስለዚህ ፖለቲካችን በምንም መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አንድነት የሚያውክ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ፣  የአንድነት ኃይሎች ድምፅም ይደመጥ ነው መልዕክቴ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...