Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአተት በሽታ ምልክት በመታየቱ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቢያ ተሰጠ

የአተት በሽታ ምልክት በመታየቱ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

ወቅቱ የፀደይ (በልግ) እንደመሆኑ መጠን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ዝናብ እየጣለና ጎርፍም እያስከተለ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ምልክቶች በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ በመሆኑና በየትኞቹም የአገሪቱ ክፍሎች ሊደርስ እንደሚችል በመጠርጠሩ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ ለሁሉም ክልሎች የማንቂያና የማስጠንቀቂያ ጥሪ በደብዳቤ ተላልፏል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በማንቂያ ጥሪው መሠረት ሁሉም ክልሎች ቅድመ ዝግጅቶች እንዲያደርጉ፣ ራሳቸውን እየፈተሹ፣ ዝግጅቶቻቸውንም እያመዛዘኑና እየለዩ ክፍተት ባለባቸው የግብዓት ጥሪ እንዲያቀርቡ ተነግሯል፡፡ ኢንስቲትዩቱም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በየማከማቻ መጋዘኖች ቀርበው እንዲከማቹ ያደርጋል፡፡

ከዚሁ አኳያ በአማራና በትግራይ ክልሎች በሚገኙና አተት በተጠረጠሩባቸው ቦታዎችና አጎራባች በሆኑ ወረዳዎች ላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲደረጉ መድኃኒቶችና ለአተት ሕክምና የሚያገለግሉ የመመርመሪያና የሕክምና ግብዓቶች ወደ ቦታው እንዲደርሱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ሳምንት ትኩረት የሚሹ ሦስት ዓብይ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የአተት በሽታ ምልክት ነው፡፡ በሽታው ባይረጋገጥም ምልክቶቹ ግን በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ወረርሽኞቹ ሊከሰቱ እንደሚችሉ በማሰብ ትኩረትና ከፍተኛ ጥንቃቄ ይስፈልገዋል፡፡ ኅብተሰቡም ውኃን አፍልቶ፣ በተለያዩ ኬሚካል አክሞ መጠቀም፣ የግልና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣ የመመገቢያና የማብሰያ ዕቃዎችን ማጠብና በደንብ መያዝ ይገባዋል፡፡

ጎርፍ የሚከሰትባቸውና ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሁሉ ለአተትና ለሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ዶ/ር በየነ ጠቁመው፣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከሚታይባቸው ቦታዎች መካከል አንደኛው የፀበል ቦታዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የፀበል ቦታዎቹ የበሽታው ምንጭ ማለት ሳይሆን፣ ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ፍሳሾች የፀበል ቦታዎችንና ፀበሉን ሊበክሉ ስለሚችሉና በዚህም ወረርሽኙ ሊከሰት እንደሚችል መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ምልክት አለማሳየታቸው ሌላው ችግር ሲሆን፣ ሰዎቹ ለተለያዩ ጉዳዮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሊቀንቀሳቀሱ እንደሚችሉ፣ በዚህም ምልክት የማያሳየውን በሽታ በምግብና ውኃ በሌሎችም ነገሮች ላይ ሊያስተላልፉና በዚህም ወረርሽን ሊቀሰቀስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ 16 የፀበል ቦታዎችን ለይቶና ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ከሚያከናውናቸው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች መካከልም የፀበል ቦታዎች በጎርፍ እንዳይበከሉ ለማድረግ የመከለለል ሥራ እንደሚገኝበት ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ለፀበል ተጠቃሚዎች የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የእጅ መታጠቢያ እንዲመቻችላቸው፣ እንዲሁም የንፅህና መስጫ ወይም መፀዳጃ ቤት እንዲኖራቸው መደረጉ ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የአተት በሽታ ምልክቶች በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ታይቷል የሚል ጥርጣሬ እንዳሳደረ፣ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ አተት አለመሆኑን እንደተረጋገጠ፣ በበሽታውም አዲስ የተጠረጠሩ ሰዎች እንደሌሉና የታመሙትም ታክመው እንደዳኑም አክለዋል፡፡

ከሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን በአበርጌሌ ወረዳ 56 ሰዎች ተጠርጥረው ሁለት፣ በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ 63 ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው ሁለት በአጠቃላይ አራት ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በበየዳ ወረዳ ሦስት፣ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን መሀል ሳይንት ወረዳ ስምንት፣ በድምሩ 11 ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው ሕክምና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመሀል ሳይንት በሽታውን በላብራቶሪ የማረጋገጥ ሥራ ተከናውኖ ውጤቱ ኮሌራ እንዳልሆነ ተረጋግጧል፡፡ በሌሎች ወረዳዎች ግን በላብራቶሪ የማረጋገጥ ሥራው በቀጣይ የሚከናወን ይሆናል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት በአንዳንድ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች አገልግሎት መቋረጡና በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶችና አዳዲስ ተፈናቃዮች መኖራቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ በዚህም በተለያዩ ክልሎች በግጭት ምክንያት ከፈረሱት የጤና ተቋማት መካከል 50 ከመቶ ያህሉ ተገንብተው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ግንባታውን የሚያከናውኑት ክልሎች ሲሆኑ፣ ለግንባታ የሚውለውን በጀት የሚሸፍነው ደግሞ ጤና ሚኒስቴር መሆኑን ዶ/ር በየነ ጠቅሰው፣ ክልሎቹም ግንባታውን ለማስጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለተፈናቃይ ወገኖች የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በተመለከተ፣ በተለያዩ ክፍሎች በሚገኙ 65 ወረዳዎች ከሚያዝያ 9 ቀን እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለ10,898 ሰዎች ሕክምና ተሰጥቷል፡፡ ከእናቶችና ሕፃናት ጋር በተያያዘ 16,361 እናቶች የእርግዝና ክትትል አድርገዋል፡፡ 734 የወሊድ አገልግሎት ሲያገኙ፣ 648 እናቶች ከወሊድ በኋላ ክትትል አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም 11,926 ሴቶች የእርግዝና መቆጣጠሪያ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡  

ከሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት የባለሙያዎች ቡድን ለመላክ የቅድመ ዝግጅትና የዳሰሳ ጥናት በስድስት ወረዳዎች ውስጥ እየተከናወነ እንደሚገኝ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ለተጎዱ ወገኖች ሕክምና የሚጡ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ተልኮ የሕክምና አገልግሎት መስጠቱም ታውቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል 60,000 ተፈናቃይ ወገኖችን ማከም የሚያስችል መሠረታዊ የሕክምና መድኃኒቶችና ግብዓቶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ከፌዴራል ሆስፒታሎች፣ ከኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ተንቀሳቃሽ የኮሌራ ሕክምና መስጫ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...